Saturday, 26 March 2016 11:45

ፍልስፍና በጠና ተይዛለች

Written by  በደረጀ ይመር
Rate this item
(3 votes)

  ፍልስፍናዊ ግብር
ታላቁ የግሪክ ፈላስፋ አፍላጦን ግዑዝ አካል የነፍስ መቃብር ነው ሲለን ያለነገር አልነበረም። በእርግጥም የነፍስ መለቀቅ በግዑዝ አካል ማክተም እውን እንደሚሆን ምልከታውን እያኖረልን ነው። ነፍስ እንደ መቃብር ድንጋይ የተጫናትን የሥጋ ቁልል ገሽሽ አድርጋ ትንሳኤዋን ለማብሰር የኃይል ቋትን በጽኑ ትሻለች፡፡ የተሰወረችበትን ደመነፍሳዊ ዓለም አሳብራ ለማማተር ፍልስፍናን ክንድ ድጋፍ ታደርጋለች፡፡ ፍልስፍና ነፍስ በሥጋ መቃብር የተጣባትን ምርጊት እያራገፈች ሕያው የምትሆንበት የጽድቅ መንገድ ነች፡፡ በጽድቁ መንገድ የሚመላለሱት ግን እፍኝ አይሞሉም፡፡ ከብዙኅኑ ዘለግ ብለው ለዓይን የሚበረክቱት ልዕለ ሰብ ጥቂቶች ናቸው። እነዚህ “ጥቂቶች” የሰው ልጅ ካሸለበበት ጥልቅ ድብታ እንዲነቃ በየዘመኑ ፊት ለፊት ሲሰለፉ ኖረዋል፡፡
የፍልስፍናን ውሃ የቀመሰ ብጽሑ ሰብዕና ከሸፍጥ ዓለም ጋር ዓይን እና ናጫ ይሆናል፡፡ በሃቅ ግዛት ላይ በሰፊው እንደተንጣለለ፣ በፍቅርና በሰላም ዙሪያውን እንደባረከ ዘመናትን ይሻገራል፡፡” “እኔ ኖሬ ሃቅ ከምትዳፈን፣ እኔ ከመቃብር ወርጄ ሃቅ ዝንተ ዓለም እንደወበራች ትናኝ” የሚለው የሶቅራጦስ ቀኖና በሁሉም የፍልስፍናዊ ዜጋ ልቦና ላይ ያድራል።
ፍልስፍና በግብ ዓልባ መርሕ የምትሾር እንዝርት ናት፡፡ ማቅኛዋ እንጂ ፍጻሜዋ አያስደምም። በማቅኛው መንገድ ላይ የሚቃረሙትን መልካም ፍሬዎች እየዘሩ ሽምጥ መጋለብ የፍልስፍና ወግም ልማድም ነው። በማቅኛው ጎዳና ላይ ከዓይን የሚገባ መቆሚያ አጥር አይኖርም፡፡ ዙሪያ ገባው አድማስ ነው፡፡
በፍልስፍና ጉዞ የእኔነት ግምብ ይፈራርሳል፡፡ ዴካርት ማሰቡን ሲያውቅ፣ ሶቅራጠስ አለማወቁን አወቀ። ለሁለቱም ልዕለ ሰብ ምስጢሩ ይገለጥላቸው ዘንድ የብቻ፣ የምናኔ ጉዞ ማድረግ ግድ አላቸው። በአጥር አልባ የፍልስፍና አውድ ውስጥ በብርቱ በመዋተት በዘመን አይሽሬ እሳቤያቸው የሰው ዘርን ወደ ንቃት ከፍታ ላይ ለመስቀል የድርሻቸውን አበረከቱ፡፡ ጥልቅ እሳቤያቸው እኔነትን ጥሎ፣ ነፍስን ሸክፎ በተደረገ የማውጠንጠን ሒደቱ ውስጥ የተገኘ ሲሳይ ነው፡፡
ታላቁ ጀርመናዊ ፈላስፋ ፍሬዴሪክ ኒቼ፤ ዛራስቱስራን ለሰው ዘር በሙሉ የወንጌል ያህል ለመስበክ የተውተረተረው የፍልስፍናን ማቅኛ መንገድ ለማመልከት በማሰብ ነበር፡፡” “Nitzche is alive,God is dead” በውስጡ ወለፈንዴ ቁምነገር ታቅፏል፡፡ ሕያውን አምላክ ለማግኘት ሐሳዊውን አምላክ  እንግደል እንደማለት ነው። የውሃ ጠብታ ከውቂያኖስ ውሃ ጋር ስትሳሳም ደብዛዋ እንደምትጠፋ ሁሉ ሐሳዊውን አምላክ የሞት ጽዋ ስናስጎነጨው ከጊዜና ከቦታ ማዕቀፍ ነፃ ከሆነ ሕያውነት ጋር ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እንወዳጃለን፤ ይለናል ጠቢቡ፡፡
በጠቢባን ምልከታ ፍልስፍና ትሽኮረመማለች። ምልከታውን አሳብሮ ከጥልቅ እሳቤያቸው ጋር መወዳጀት የማውጠንጠኑ ዋንኛ አላማ ነው፡፡ በምናብ የተራቀቁበትን ጥልቅ ቁምነገር በቃላት አብሎ መቀመጥ ግን ይቅር የማይሉት ሸፍጥ ይሆናል የጠቢባን አባባልን ልክ እንደ ደብተራ በቃል እያነበነቡ ጥበብን ለመከወን መሞከር  በፍልስፍና ፊት የዋህ የሚያስብል ምግባር ነው፡፡ ቃላትና ንቃት ኩታገጠም ሰብዕና ሊሆኑ አይችሉም፡፡ የቃላት ሚና ጥቆማ እንጂ ጥልቅ እሳቤውን ማቀበል አይደለም፡፡
ከልቦናቸው ይልቅ አንደበታቸው ለአምላክ ቅርብ የሆኑትን ፊደላዊያን ደቀመዛሙርቶችን ለማንቃት የዜን መምህሩ አንድ ምሳሌ አሰናዳ፡-
ዘወትር ከሥሩ ከማይጠፋው ታማኝ ውሻው አናት ላይ በትሩን ከፍ አድርጎ ወደ ጨረቃዋ እየጠቆመ፡-
“ጨረቃዋን አውርድልኝ! ጨረቃዋን አውርድልኝ ”ብሎ ልሳን አልባ ውሻውን በስላቅ ጠየቀው፡፡   በሁኔታው ግር የተሰኙት ደቀመዛሙርቱ የምሳሌውን መቋጫ ለማወቅ ቋመጡ፡-
“አያችሁ! ውሻዬ የሚመለከተው በትሩን እንጂ ጨረቃዋን አይደለም፡፡ የእናንተም ምግባር ከእዚህ ውሻ አይለይም፡፡ ከጨረቃዋ ይልቅ በትሩን መመልከት ይቀናችኋል፡፡ የእኛ የዜን ቡዲሂዝም  ምልከታ፣ምሳሌ እንደዚህ በትር ነው፡፡ ምልከታው በራሱ ሕይወት አይኖረውም፡፡ ከበትሩ በላይ አሳብሮ መሄድ የማይችል ምዕመን በጨረቃዋ ጥልቅ ውበት ሊደመም አይችልም። ቃላት ከመጠቆም ውጪ ከእውነታው ዓለም ጋር የሚያወዳጁበት አቅምን አልተቸሩም፡፡” መምህሩ ደቀመዛሙርቱ የሰሙት በልቦናቸው እንዲያድር ተመስጦ ውስጥ ገባ፡፡ የጠቢባንን ቅንጭብ ጩኸት መልሶ መላልሶ እንደገደል ማሚቱ እያስተጋቡ ለመጠበብ መሞከር ጨረቃዋን በበትሩ እንደመለወጥ ይቆጠራል። የበትር ልኅቃን  ከፍልስፍና ጋር ሆድና ጀርባ ናቸው፡፡ በቃላት ዳንኪራ ስሉጥነት እንጂ የጥበብ ከራማ ሊወርድ አይችልም፡፡ ፈላስፋ አባካኝ ነው። በተቀየሰለት ጎዳና አያዘግምም፡፡ የብዙኃኑን ሐዲድ ስቶ በራሱ ይከንፋል። ስንዝር በሄደ ቁጥር ምስጢራትን እየፈለቀቀ ለአውደ ርዕይ ያቀርባል። ከበትሩና ከጨረቃዋ ጋር የሚወዳጀው እንዲህ ሃሞት በሚጠይቅ በተናጥል ጉዞ ነው፡፡
የዘመኑ ፍልስፍና
ታላላቅ የግሪክና የመካከለኛው ዘመንን ያፈራው የፍልስፍና ዘይቤ አሁን አፈር ለብሷል፡፡ በምትኩ የጸጉር ስንጠቃ ትንታኔ የሚከተለው የፍልስፍና ዘውግ /Analytic Philosophy/ በክሎታል፡፡ ፍልስፍና ልክ አንደ ተርኪስ ባቡር ተገትራ ቆማለች። ሳይንስ ከጊዜ ወደ ጊዜ እንደ ቀስት እየሾለ፣ ወደፊት ሲስፈናጠር ፍልስፍና ግን በማይታዩ ረብ-የለሽ ረቂቅ ፅንሰ ሐሳቦችን እያነሳች፣ በቪሺየስ ሰርክል አውድ ውስጥ በብርቱ ትሾራለች፤ ይላሉ ሎጂካል ፖዘተቪስቶች፡፡
እነዚህ የሃያኛው ክፍል ዘመን ንድፈ-ሃሳባዊያን ፍልስፍናን በሳይንስ ወርድና ቁመት መትረው አበጃጅተውታል፡፡ ዲበአካለዊ የሆኑ ዕውነታዎች ሳይቀሩ በአመክንዮ ሚዛን እየተሰፈሩ ጽንሰሐሳባዊ ትንታኔዎችን ያቀርባሉ፡፡ ሁሉንም ሕልውና ወደ ታዋቂነት ደረጃ ያወርዱታል፡፡ ፍልስፍና እንደጥንቱ የነፍስ ጥም ማርኪያ መሆኗ ቀርቶ በሕግ እና በስርዓት ለተቀነበበ ስርዓት እጅ ሰጠታለች፡፡ ዊሊያም ባሬት “ኢራሽናል ማን” በሚለው መጽሐፍ ላይ የዘመኑን ፍልስፍና እንዲህ አድርጎ ይሸነቁጠዋል፡
“The profession of philosophy did not always have the narrow and specialized meaning it now has. In ancient Greece it had the very opposite: instead of a specialized theoretical discipline philosophy there was a concrete way of life, a total vision of man and the cosmos in the light of which the individual’s whole life was to be lived.”                                                                    
ፍልስፍናን ከንግስና ዙፋኗ ወርዳ ተራና አልባሌ ሆናለች፡፡ በማዕረጋቸው ደረታቸውን በሚነፉ ግብዝ ፊደላዊያን በሚርመሰመሱበት የአስኳላ ወህኒ ቅጥር ግቢ ውስጥ እንደአልባሌ ሆና  ተከርችማለች፡፡
ፍልስፍናን የአልጋ ቁራኛ ያደረገው አስኳላ ሥፍር ቁጥር የሌላቸው የአመክንዮ ልኂቃንን በመፈብረኩ ረገድ የተካነ ቢሆንም እንደ ሶቅራጠስ፣ አፍላጦን፣ አሪስጣጣሊስ፣ ዴካርት፣ ካንት፣ኒቼ ያሉትን እፍኝ የማይሞሉ ጥበበኞችን ለዓይነ ሥጋ ማብቃት እንደተሳነው፣ የበይ ተመልካች እንደሆነ ዘመናትን ሊያስቆጥር ችሏል፡፡

Read 2803 times