Saturday, 26 March 2016 12:05

ዙማ ስልጣን ለመልቀቅ መጠየቃቸውን ፓርቲያቸው አስተባበለ

Written by 
Rate this item
(2 votes)

   ተቃውሞ የበረታባቸው የደቡብ አፍሪካው ፕሬዚዳንት ጃኮብ ዙማ፤ በገዛ ፈቃዳቸው ስልጣናቸውን ለመልቀቅ ጥያቄ አቅርበዋል በሚል ሰሞኑን በስፋት ሲሰራጭ የሰነበተውን መረጃ ፓርቲያቸው አፍሪካን ናሽናል ኮንግረስ ማስተባበሉን ሮይተርስ ዘገበ፡፡
የአገሪቱን ኢኮኖሚ በቅጡ መምራት አቅቷቸዋል፣ ከባለሃብቶች ጋር በመመሳጠር የአገር ሃብት ይመዘብራሉ በሚል ተቃውሞ ያየለባቸው ፕሬዚዳንት ዙማ፣ ሰሞኑን በተካሄደው የፓርቲው የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ስብሰባ ላይ ስልጣናቸውን ለመልቀቅ ጥያቄ አቅርበዋል በሚል የተለያዩ ጋዜጦችና ድረገጾች መዘገባቸውን ያስታወሰው ሮይተርስ፤ የፓርቲው ቃል አቀባይ ግን፣ መረጃው ሃሰተኛ ነው ሲሉ ማስተባበላቸውን ጠቁሟል፡፡
“ይህ ፍጹም መሰረተ ቢስና ሃሰተኛ መረጃ ነው!... እንዲህ አይነት ነገር አልተደረገም!” ብለዋል የአፍሪካን ናሽናል ኮንግረስ ፓርቲ ቃል አቀባይ ዚዚ ኮድዋ፣ ጋዜጦቹና ድረገጾቹ ያሰራጩትን ዘገባ ሲያስተባብሉ፡፡
የፕሬዚዳንቱ ፓርቲ በአገሪቱ ፖለቲካ ላይ አለመተማመን እንዲሰፍን አድርጓል፣ ኢኮኖሚውንም አደጋ ውስጥ ከትቶታል በሚል ከፖለቲከኞች ትችት እየተሰነዘረበት እንደሚገኝ ያስታወሰው ዘገባው፣ የአገሪቱ የጸረ ሙስና ኮሚሽንም ፕሬዚዳንቱ የተጠረጠሩበትን ድርጊት እንደሚመረምር ባለፈው ማክሰኞ ማስታወቁን አክሎ ገልጧል፡፡

Read 1800 times