Monday, 04 April 2016 07:24

በኩዌት ኢትዮጵያውያን ሴቶችን የሚሸጥ ቡድን በቁጥጥር ስር ዋለ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

- ቡድኑ 5 ኢትዮጵያውያን አባላት አሉት ተብሏል
- በስደተኞች ጀልባ አደጋ ከሞቱት መካከል አንደኛው ኢትዮጵያዊ ነው ተባለ

   በኩዌት በቤት ሰራተኝነት ተቀጥረው የሚሰሩ ኢትዮጵያውያን ሴቶችን ከቀጣሪዎቻቸው ቤት በማስኮብለል ህጋዊ ባልሆነ መንገድ ሌላ ቦታ በማስቀጠርና ገንዘብ በመሰብሰብ ህገወጥ ስራ ላይ ተሰማርቷል የተባለ ቡድን ከትናንት በስቲያ በፖሊስ ቁጥጥር ስር መዋሉን ገልፍ ዲጂታል ኒውስ ድረገጽ ዘገበ፡፡
አምስት ኢትዮጵያውያንን በአባልነት የያዘውና ህጋዊ ፍቃድ ሳያወጣ በተጭበረበረ ሰነድ የሚንቀሳቀሰው ይህ ቡድን፣ በአገሪቱ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን የቤት ሰራተኞችን ከፍ ባለ ደመወዝ እናስቀጥራችኋለን እያለ ከተቀጠሩበት ቤት በማስኮብለል በድብቅ ቦታ እያቆዩ ለሌሎች ቀጣሪዎች ይሸጣል መባሉን ዘገባው ገልጧል፡፡
ከቡድኑ ጋር ይሰራሉ የተባሉ ኢትዮጵያውያንና የሌሎች የአፍሪካ አገራት ዜግነት ያላቸው 17 ወንዶችና 13 ሴቶችም በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውለዋል ያለው ዘገባው፣ የቡድኑ አባላትና ተባባሪዎቻቸው ለፍርድ ቀርበው ህጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድባቸው አስታውቋል፡፡በተያያዘ ዜና የተለያዩ የአፍሪካ አገራት ስደተኞችን ጭና በሜዲትራኒያን ባህር ላይ ስትቀዝፍ በነበረች ጀልባ ላይ ከትናንት በስቲያ በደረሰ የመስጠም አደጋ ለህልፈተ ህይወት ከተዳረጉትና አስከሬናቸው ከተገኘ 9 ሰዎች መካከል አንደኛው ኢትዮጵያዊ እንደሆነ መረጋገጡ ተዘግቧል፡፡
የግብጹ ዴይሊ ኒውስ ድረገጽ ያወጣው ዘገባ፣ በአደጋው ለህልፈተ ህይወት የተዳረገው ኢትዮጵያዊ የ43 አመት ጎልማሳ መሆኑ መረጋገጡን ከመግለፅ በስተቀር፣ ስለ ሟቹ ማንነት ዝርዝር መረጃ አልሰጠም፡፡





Read 4033 times