Monday, 04 April 2016 07:26

“በወልቃይት ጉዳይ ጥያቄ በማንሳታችን በደል ተፈፀመብን” - አቤቱታ አቅራቢ “ጥያቄ አቅርበዋል የተባሉት የወረዳው ሰዎች አይደሉም” - የወልቃይት አስተዳደር

Written by 
Rate this item
(5 votes)

የወልቃይት ወረዳ በአማራ ክልል ውስጥ መሆን አለበት የሚል ጥያቄ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ያስገቡ አቤቱታ አቅራቢዎች፤ ምላሽ እንዳልተሰጣቸው የተናገሩ ሲሆን ፌዴሬሽን ም/ቤት በበኩሉ፤ በመጀመሪያ ጥያቄው መታየት ያለበት በክልል ምክር ቤት ነው የሚል ምላሽ ሰጥቻለሁ አለ፡፡
ጥያቄ በማንሳታችን በደል እየተፈፀምብን ነው በማለት አቤቱታ አቅራቢዎቹ ገልፀዋል፡፡ የወረዳው አስተዳደር ግን አስተባብሏል - የወረዳው ነዋሪዎች አይደሉም በማለት፡፡
ጥያቄያችንን ለፌዴሬሽን ምክር ቤትና ለተለያዩ የመንግስት አካላት በተደጋጋሚ አሰምተናል ያሉት አቤቱታ አቅራቢዎች፤ የወረዳው ባለስልጣናት እንግልትና በደል እየፈፀሙብን ነው ብለዋል፡፡
ህግን ተከትለን የወልቃይት ጠገዴ ወረዳ በአማራ ክልል ስር እንዲሆን ጥያቄ ማንሳት የጀመርነው በ1983 ዓ.ም ነው በማለት የተናገሩት አቤቱታ አቅራቢዎች፤ “ጥያቄያችን ምንም የፖለቲካ ፍላጎት ባይኖረውም አላግባብ ተፈርጀን እንግልት እየደረሰብን ነው ብለዋል፡፡
የወልቃይት ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ጀጃው ደሞዝ በበኩላቸው፤ “ጥያቄ ማንሳት ያለበት የወረዳው ህዝብ እንጂ በሌላ አካባቢ የሚኖር ግለሰብ አይደለም፤ ህዝቡ እንዲህ አይነት ጥያቄ አላነሳም” ብለዋል፡፡
ጥያቄ አቅርበዋል የሚባሉት ሰዎች የወረዳው ነዋሪዎች አይደሉም ያሉት አቶ ጀጃው፣ የወረዳው ማህበረሰብ በመልካም አስተዳደርና በልማት ስራዎች ላይ እየተረባረበ ነው ብለዋል፡፡

Read 2241 times