Monday, 04 April 2016 07:57

ከጌታሁን ሄራሞ ጋር የማልስማማባቸው ነጥቦች

Written by  ተመስገን ካሳዬ፣ ከአርባምንጭ ዩኒቨርስቲ)
Rate this item
(0 votes)

ክፍል-2
ባለፈው ሳምንት ጽሑፌ ከጌታሁን ግምገማ አላሳመኑኝም ያልኳቸውን ነጥቦች አንስቼ ነበር፡፡ በዚህች ጽሑፌ የጌታሁን ሒስ ከርዕሰ-ነገሩ ይልቅ በሰዎች ላይ ማተኮር የሚበዛበት (Ad Hominem)፣ ከእርሱ ሀሳብ የተለየውን ሰው የመከራከር መብት የሚነፍግ (denying right to be skeptic) ሳይንሳዊነት የሚጎድለው እና ብዙም ባይሆን አንድ ቃል አንድ ትርጉም ብቻ ያለው የሚያስመስል (semantic trap) መሆኑን በማሳየት አጠናቅቃለሁ፡፡
ከጉዳዩ ጋር የማይገናኙ ነገሮችን እየጨማመረ አንባቢን ከርዕሰ-ጉዳዩ ይልቅ ወደ ሰዎቹ ግለ-ሰብዕና ለመምራት መሞከሩ አልተዋጠልኝም፡፡
እንዲህ የምለው የጨማመራቸው ከጉዳዩ ጋር የማይገናኙ አስረጂዎች ብዙዎች ‹‹ፍየል ወዲያ ቅዝምዝም ወዲህ›› የሚያሰኙ፣ ፍልስፍና Logical Falacies የሚላቸው ዓይነት ሆነው ስላገኘኋቸው ነው። ስለ ‹‹ከአሜን ባሻገር›› ጭብጦች ከማውራት ይልቅ ስለ በዕውቀቱ ኮሜዲያንነት፣ ኢ-አማኒነት፣ ደራሲነት፣ ወዘተ፣ በፍሮይድ መጽሐፍ ላይ ከማተኮር ይልቅ ስለ ፍሮይድና በአስተዳደጉ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ስለነበረው ግንኙነት፣ ሌሎች ሰዎች ስለ ፍሮይድ ስለጻፉት፣ ስለ ኮኬይን ተጠቃሚነቱ፣ ወዘተ አብዝቶ መጻፉ አንባቢም ‹‹እውነትም በዕውቀቱ የተሸወደው ፍሮይድ በኮኬይን ተገፋፍቶ የጻፈውን Illusion አንብቦ ነው›› እንዲልለት የመፈለግ ይመስላል፡፡ ይህም በሲግመንድ ፍሮይድ የተጻፈውን መጽሐፍ ማንበብ አያስፈልግም የሚል መልዕክት የያዘ (Genetic Fallacy) ነው፡፡ ጌታሁን ሙግቱን የሚያጠናክርለት ወይም የተቃወመውን ሀሳብ የሚያፈርስለት ከመሰለው የሚያነሳው ነገር ከጉዳዩ ጋር ባይገናኝምና አንባቢ ባያሳምንም ዝም ብሎ የማይገናኝ ነገር ይጨማምራል፡፡
‹‹የአይሁድ ዝርያ ያለው ፍሮይድ፤በልጅነት ዕድሜው ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ጥብቅ ግንኙነት እንደነበረው እርሱ ራሱ ተናግሯል፡፡ አሳዳጊው ክርስቲያን ነበረችና ፍሮይድ ለክርስትና ቅርብ ነበር፡፡ ፍሮይድ ኮኬይን ተጠቃሚ ነበር፡፡ በዕውቀቱ ኃይማኖታዊ እሴትና ባህል በናኘበት ማህበረሰብ መካከል ተወልዶ ነው ያደገውና ከሙሉ በሙሉ ኢ-አማኒነት አውጥቼ ኃይማኖታዊ ኢ-አማኒ ውስጥ እመድበዋለሁ›› የመሳሰሉ ማጠቃለያዎቹ ከPsychoanalysis ጋር የሚገናኝ ዕውነታ ቢኖራቸውም በጌታሁን አጠቃቀም በርዕሰ-ጉዳዮቹ ሳይሆን በሰዎቹ ላይ የተቃጡ ማጣጣያዎች ሆነዋል፡፡ ፍሮይድ ለእጮኛው የጻፈው ደብዳቤ፣ የፍሮይድ ጓደኛ የጻፈው መከራከሪያና የፍሮይድ መጽሐፉን ለማሳተም መጨነቅም የጌታሁንን የንባብ ስፋት ከማሳየት አልፈው እየገመገምኩት ነው ለሚለው ‹‹ከአሜን ባሻገር›› የአስረጂነት ሚና የላቸውም፡፡
በዕውቀቱ ‹‹መጣጥፎቼ የልግጫና የእንጉርጉሮ ናቸው›› ማለቱን ከአደጋ መከላከልና ዝግጁነት ኮሚሽን ተልዕኮ ጋር ማመሳሰሉ የአንባቢን ትኩረት ለማዞር ጠቅሞት ካልሆነ ለሒሱ የሚጠቅም ነገር አላስገኘለትም። ‹‹ቀልደኛን ማሄስ በጣም ከባድ ነው›› ካለ በኋላ በዕውቀቱ ያደረገውን የጸሐፊ ጥንቃቄ ‹‹በፖለቲካ ቀመስ መጣጥፎቹ ላይ ጠንከር ያለ ሂስ ለመሰንዘር የሚያኮበክቡ ሐያሲያንን እዚያው መሬት ላይ አጣብቃ የምታስቀር›› አድርጎ ወስዷል፡፡ ለጌታሁን መጣጥፎቹ በሙሉ በ”ቀመስ” ጀምረው በ”ቀመስ” ከመጠናቀቃቸውም ሌላ እንዲህ መሆናቸው ስነ-ልቦናዊ ጨዋታን ስለሰነቁ ይሆናል ብሎ ተጠራጥሯል፡፡ በምርምር የተደገፈና ጥናታዊ እንደሆነ የተነገረው ጽሑፍ ወደ “ቀመስነት” ደረጃ የወረደበት አግባብም ሊገባው አልቻለም፡፡ ጠንካራ የርዕዮተ-ዐለም ትንታኔ እንዳይሰጥበት እንደ አደጋ ዝግጁነት ኮሚሽን ተጠንቅቋል ብሎት ሲያበቃ፤ ‹‹የተለመደውን አተያይ ለማፍረስ በእጅጉ ከሚተጉት ደራሲያን ተርታ›› መድቦታል፡፡ ‹‹ሊገጥመው የሚችለውን ተቃውሞ ከቁብ ሳይቆጥር በጥረቱ መቀጠሉን››ም አድንቆለታል። ኢ-አማኒ በመሆንህ የአማኞችን ዕምነት መቀለጃ አደረከው የሚል ዓይነት ይዘት ያለው ሒስ ካቀረበለት በኋላ፣ ኢ-አማኒያንን በሳይንሳዊ መንገድ መድቦ ‹‹…በዕውቀቱ ሙልጭ ያለ ኢ-አማኒ አይደለም፡፡ ከጠንካራ ኢ-አማኒነት ለሃይማኖተኛ ኢ-አማኒነት ይቀርባል›› ሲል ኢ-አማኒነቱን አስተካክሎለታል፡፡ ይኼን ሁሉ ብሎ ግን መጽሐፉ ላይ ከወጡት ጭብጦች ጋር አሰናስሎ ለሒስ የሚጠቅመው አንዳች ነገር አላወጣም፤ ምክንያቱ ደግሞ የመጽሐፉን ጭብጦች በመሔስ ላይ ባለማተኮሩ ነው። ሐያሲው እንዲህ ዓይነት የሒስ ውጣ ውረድ ውስጥ የገባው መጽሐፉን “ከአሜን ባሻገር”ን ትቶ ጸሐፊውን በዕውቀቱን በመሔሱ ነው፡፡ (በነገራችን ላይ በሚቀጥለው በዕውቀቱን ‹‹የከሸፍኩ ሠዓሊ ነኝ ያልከው ስታስመስል ነው›› የሚል ሌላ ሐያሲ ቢመጣ ለመከራከር ዝግጁ አይደለሁም)፡፡
ጌታሁን ‹‹የእንጉርጉሮና የልግጫ ድብልቅ ናቸው›› ከተባሉት መጣጥፎች ውስጥ የትኞቹ በየትኛው ጠጣር ርዕዮተ-ዓለም ቢገመገሙ ምን ፍሬ ነገር እንደሚጎድላቸው ለማሳየት አልደከመም እንጂ ቢሞክር ኖሮ ብርቱ አሳብያንና ፈላስፎች ከሕዝብ ልግጫና ዕንጉርጉሮ ብርቱ ብርቱ ንድፈሃሳቦችን ማፍለቃቸውን ይረዳ ነበር፡፡ በዕውቀቱ በትሁትነቱ ይሁን በኮሜዲያንነቱ ‹‹የልግጫና የዕንጉርጉሮ›› ያላቸው ምልከታዎቹ፣የእኛን መሰረተ-አኗኗር የሚፈቱ ንድፈ-ሃሳቦችን ሊወልዱ እንደሚችሉ ማሰብ ይችል ነበር፡፡ ከ1960ዎቹ የአሜሪካውያን የፈንጠዝያና የመደነጋገር ሕይወት፣ የሰውን ልጅ መስተጋብርና ማኅበራዊ ግንኙነት የሚገልጹ ንድፈ-ሃሳቦች ተቀምረዋል፡፡ ሲግመንድ ፍሮይድም የሚታወቅበትን Psychoanalysis Theory የፈጠረው  እንደ በዕውቀቱ በንቁ ታዛቢነቱና በባለሙያነቱ በየዕለት ከሚያያቸው ገጠመኞቹ ነው፡፡ እናም የበዕውቀቱን ‹‹ልግጫዎችና ዕንጉርጉሮዎች›› በሚታወቅ ጠንካራ ርዕዮተ-ዐለም መገምገም የግድ ሳይሆን ከእነዚህ ‹‹ቀመሶች›› ወፍራም ወፍራም የንድፈ-ሃሳብ ሸማዎች ሊሸመኑ እንደሚችሉ መረዳት ነበረበት፡፡ ጌታሁን እንደሚለው፤ የበዕውቀቱ አድናቂ ከሆነ በደፈናው ‹‹እንዳይተች ፈርቶ ጽሑፎቹን የልግጫ ናቸው አለ›› ከሚለው ይልቅ በዕውቄም እንደ ፍሮይድ ኢትዮጵያዊ ንድፈሃሳብ እንዲቀምር በምልከታዎቹ ዙሪያ ጠጣር የርዕዮተ-ዓለም ጥያቄ እያነሳ ቢፈታተነው ይሻል ነበር፡፡
‹‹በምርምር የተደገፈና ጥናታዊ እንደሆነ የተነገረን ጽሁፍ ወደ ቀመስነት የወረደበት አግባብ ሊገባኝ አልቻለም›› የሚለው ምርምርን እንዴት ባለ መንገድ ተረድቶት እንደሆነ ግልጽ አልሆነልኝም፡፡ ለእኔ ግን እነኝህ ‹‹ቀመሶች›› ሁሉም ባይሆኑ እንኳ ቢያንስ የተወሰኑት በይዘታቸው ሆነ በአቀራረባቸው በአካዳሚክ ጆርናሎች ቢወጡ አቅም የማያንሳቸው፣ የዘመኑን ቴክኖሎጂ የሚመጥኑ ይመስሉኛል፡፡ እንደ ስጦታ ዕቃ እጥር ምጥን ያሉ ረዝመዋል ተብለው ማሳጠር የማያስፈልጋቸው፣ አጥረዋል ተብለው ማርዘም የማይሹ ዘመኑ የሚፈልጋቸው የምሁራን መጣጥፎች፤ አከራካሪ ከሆኑም አከራካሪነት የአካዳሚክ አርቲክሎች ዋና ባህሪ ነው፡፡ ጌታሁን ምርምርን የቤተ-ሙከራ ውሎ ብቻ አድርጎ ካልወሰደው በቀር (የድሮ ሳይንቲስቶች እንደሚሉት) ከግላዊ ማስተዋል እንደሚጀምር የሚያግባባን ይመስለኛል፡፡ ጌታሁን የበዕውቀቱን ምርምር ከማጣጣል ባለፈ ስለ ምርምር ዘርዘር አድርጎ ስላልተናገረ እኔም ‹‹ሊገባኝ አልቻለም›› ባለው በዚህ ነገር ላይ ከዚህ የበለጠ አልልም፡፡
ስለ ፍሮይድ የጠቃቀሰውም አንባቢው ከመጽሐፉ ይልቅ በፍሮይድ ሰብዕና ላይ ትኩረቱ እንዲሰረቅ የሚያደርግ ተመሳሳይ አካሔድ አለው፡፡ እዚህ ጋ በፍሮይድ መጽሐፍ ይዘትና አቀራረብ ላይ ጌታሁን ባጣመመው ልክ የመሟገት ሀሳብ የለኝም፡፡ ይልቅ የአረዳድ መዛባት ማስከተሉን ለማሳየት ያህል ፍሮይድን ተረድቼበታለሁ ባለው አግባብ የጠቀሳቸውን ሀሳቦች ብቻ ላንሳ፡፡ ፍሮይድ፤ ‹‹The  appearance  of contradiction  has  probably  come  about because  I  have  dealt with  complicated matters  too  hurriedly›› ያለውን ‹‹እየገለጽኩት ነው›› ብሏል ብሎ አስረግጦለት ሲያበቃ፣ ‹‹ፍሮይድ እንዲህ የሚወዛገበው ኮኬይን ተጠቃሚ ስለነበረ ነው›› እንድንል ይጋብዘናል፡፡ ፍሮይድ በመጽሐፉ የIllusion እና የErrorን ልዩነት ሲገልጽ፤Illusion የሚለውን ቃል ከቀድሞ አገባቡ በተለየ ሰፋ ባለ አገባብ ማብራራቱን ሳያነሳ ‹‹የራሱንም ስራ Illusion ነው ብሎታል›› ብሎ አንባቢም ዝም ብሎ እንዲቀበለው አስቧል፡፡ ነገር ግን እንዲህ ዓይነት አቀራረብ ሀሳብን በደፈናው ከማጣጣል ባለፈ የውጤትና-ተገብሮ ተዛምዶ ማየት የሚሹ አንባቢዎችን አያሳምንም፡፡ እነኝህ አንባቢዎች ወደ ጉዳዩ ተመልሰው በዕውቀቱ ‹‹መጣጥፎቼ የልግጫና የእንጉርጉሮ›› ናቸው ማለቱ የጽሑፎችን ጥንካሬ ያወርዳል ወይ? የፍሮይድ የኮኬይን ወይ የጫት ምርቃና በጽሑፉ ላይ ተፅዕኖ አሳድሮበት እርስ በርስ የሚቃረን አድርጎታል ወይ? አሳማኝ ነው ወይስ አይደለም? ብለው ይጠይቃሉ፡፡ ከጠየቁም ጌታሁን ያልሔሳቸውን ግን ወደ ቀመስ ደረጃ የወረዱበት ምክንያት ሊገባኝ አልቻለም ሲል ያለፋቸውን ስራዎችና ሳይጠቅስ የተወውን የፍሮይድን ማብራሪያ አንብበው ያገኛሉ፡፡ እናም የበዕውቀቱ ‹‹የልግጫና የዕንጉርጉሮ›› አገላለጽም ሆነ የፍሮይድ ኮኬይን ተጠቃሚነት (ዕውነት ቢሆን እንኳ) ጌታሁን ከሚገመግማቸው ስራዎቻቸው ጋር አንዳች ጠቀሜታ እንደሌላቸው ይረዳሉ፡፡
እነኝህን የመሳሰሉ ገለጻዎቹን እዚህ ያነሳሁት፣ ጌታሁን መጽሐፉ ላይ የወጡ ጭብጦችን ትቶ አንዳንዴ ከኮሜዲያኑ፣ ሌላ ጊዜ ከደራሲው፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ ከቁም ነገረኛው በዕውቀቱ ጋር መውጣት መውረዱ ግምገማውን ምን ያህል እንዳደከመበት ለማሳየት ነው። ባጭሩ መጽሐፉን በገምጋሚ ዓይን አላየውም፡፡ በዚህ አካሔዱ በዕውቀቱን በኮሜዲያንነቱም ሆነ በኮሚክነቱ አልያዘልንም፤ፍሮይድንም ከነተቃርኖው አላገኘልንም፡፡ የዚህ ዓይነት Logical Falacy የሚከሰተው የተነሳውን ሀሳብ የምናፈርስበት የሕገ-አልዮት ደማሚት ስናጣ የምናሳብብበት ማደናገሪያ ስንፈልግ ይመስለኛል፡፡
የሒስ መንፈሱ (argument tone) በአከራካሪ ጉዳዮች እንኳ መፈናፈኛ የሚነፍግ ነው፡፡
የጌታሁን ክርክር መፈናፈኛ ይነፍጋል፤ ሳይንሳዊም አይደለም የምለው በዕውቀቱ ‹‹ኢ-አማኒ መሆኑ መብቱ ነው… ውሳኔው ይከበርለታል›› የሚል ቃል አስፍሮ ሲያበቃ በሒሱ ግን ለበዕውቀቱ right to skepticism ቅቡልነት ሲሰጥ ባለማስተዋሌ ነው፡፡ የተጠቀሰው ቄስ ኦስካር ፊስትነር እንኳ ምላሽ የጻፈው ለፍሮይድ አዲስ ሀሳብና ለሀሳቡ የመከራከር ነፃነት ዕውቅና ሰጥቶ ነው፡፡ ጌታሁን ሒሱን ያቀረበው አስቀድሞ ዕውቅና በመንፈግ በሚመስል ክርክር ነው፡፡ እንደ ጥቅል አነጋገር አይወሰድብኝ እንጂ የሒሱ አቀራረብ ‹‹ተሸወደ፤ አለቀ፤ በቃ›› የበዛበት አሳሳች ሙግት (False Dilemma) ውስጥ የሚከት ቃና ይጫነዋል፡፡ ከሒሱ ርዕስ ‹‹በዕውቀቱና ድፍረቱ›› ጀምሮ ‹‹ተሳስተሃል፤ ሳታውቅ ቀርተህ ነወይ? ሌላ ጉድ ላሳያችሁ፣ የአላዋቂነት ድፍረት፣ የፈጸማቸው ተራ ስህተቶች፣ የክስ መዓት እያዘነበ፣›› የሚሉ በሳይንሳዊ መከራከሪያ ጉዳይ የሌላቸው ሀሳበ-አጋኖዎች ይበዛሉ። እንዲህ ያሉ አገላለጾች የሚበዙበት መጣጥፍ የሀሳብ አፈና ውስጥ እንደተዘፈቀ ወይም ‹‹ልክ ልኩን ነገርኩት›› በማለት በገለልተኛ ወገን ያልተረጋገጠ አሸናፊነት (self declared victory) ለማወጅ የመቸኮል ውጤት እንደሆነ መጠራጠር ይቻላል፡፡ አብዛኞቹ ሒሱን የቀመረባቸው ቃላትና ዓ.ነገሮች ሀሳብን በአመክንዮ ሳይሆን በስሜት ለማስጣል የሚወረወሩ ዓይነት ናቸው፡፡
ይህን ስል የጌታሁንን ሒስ (አንዳንዶች እንደሚያደርጉት) በማስፈራራት ሀሳብን ለማስለወጥ መሞከር (Appeal to Force) አድርጌ አልወሰድኩትም። ዘና ያለ ተከራካሪ ነው ለማለት ግን ይቸግረኛል፡፡ ዘና ያለ ተከራካሪ በመጀመሪያ ለአከራካሪው ጉዳይ ሌላ ገጽ ዕውቅና ይሰጣል፤ በሁለተኛ ደረጃ የሚገጥመውን ክርክር ተቀብሎ ተከራካሪውን ከርዕሰ-ነገሩ ለይቶ ሒሱን በዚሁ አንፃር ይቃኛል፡፡ በሶስተኛ ደረጃ በባዶው የሚያጋንኑ ወይም የሚያጣጥሉ ቃላትን አብዝቶ አይጠቀምም፡፡ ከጉዳዩ የማይዛመዱ ማጠቃለያዎችንም እንዲሁ ከመሬት ተነስቶ አያዋልድም፡፡
ለምሣሌ ‹‹ሌላ ጉድ ደግሞ በገጽ 228 ላይ ይገኛል›› የሚለን በማጋነን አካሔዱ እንጂ በ‹‹ከአሜን ባሻገር›› ገጽ 228 ላይ የሚገኝ ጉድ የሚያሰኝ ነገር የለም፡፡ በገጽ 228 የሰፈረው ጽሑፍ ጌታሁን፤ ‹‹…የታሪክ መዘውሩን ወደ ራሱ አቅጣጫ ለማሾር ሲል ሆደ ሰፊነታቸውን ከክርስትና ጋር ሳይሆን ከሰብዕናቸው ጋር ለማዛመድ ይዳክራል›› እንደሚለው ሳይሆን በዕውቀቱ ግንዛቤውን ያቀረበበት ገለጻ ነው፡፡ ልጥቀሰው፡፡
ራስ ጉግሳና ወራሾቹ ባገራችን ብዙ ያልተለመደውን የብዙ ዕምነት ባህል ለማስተዋወቅ ሞክረዋል፡፡ ሙከራቸው ከዘመኑ ርምጃ የቀደመ መሆኑ የሚገባን በሊቃውንት የተሰጠውን ምላሽ ስናይ ነው፡፡
በዕውቀቱ ለዚህ ግንዛቤው አስረጅ አድርጎ የጠቀሰው አለቃ አጥሜ፤ ‹‹ናፖሊዮን በምድረ ግብጽና በኢትዮጵያ መካከል ያሉ እስላሞችን ተባብረን እንውጋቸው ብሎ ወደ ራስ ጉግሳ ቢልክም ጉግሳ መልስ አልሰጠም…›› ማለቱን ነው፡፡ በዕውቀቱ ራስ ጉግሳና ወራሾቹ ክርስቲያን አልነበሩም የሚል ግንዛቤ የያዘውም ‹‹ራስ ጉግሳ ክርስቲያን መሰለ›› ሲል የጉግሳን ክርስቲያንነት የተጠራጠረውን አለቃ አጥሜን ዋቢ አድርጎ ነው፡፡ አለቃ አጥሜ ‹‹መሰለ›› ሲል ክርስቲያንነቱን ተጠራጥሯል ማለት ነው፡፡ በአለቃ አጥሜ ‹‹ክርስቲያን መሰለ›› የተባለው ራስ ጉግሳና ‹‹ወራሾቹ ባገራችን ብዙ ያልተለመደውን የብዙ ዕምነት ባህል ለማስተዋወቅ›› መሞከራቸውን የሚያደንቀው ግን በዕውቀቱ ነው፡፡ ይህን በገጽ 228 ላይ ያነበበው ጌታሁን ደግሞ ‹‹በክርስትና እምነታቸው የሚታወቁት ራስ ጉግሳና ወራሹ ራስ ዓሊ›› ሲል ‹‹ራስ ጉግሳ ክርስቲያን መሰለ›› ካለው አለቃ አጥሜ ማጠቃለያ በከፊል መለየቱን ያመለክታል፤ ከአለቃ አጥሜ ይልቅ ጌታሁን በራሶቹ ክርስቲያንነት እርግጠኛ የሆነ ይመስላል። በዚህም የራሶቹን መልካም ስራ ከክርስትና ጋራ ሊያገናኘው ሞክሯል፡፡
በዕውቀቱ የራሶቹን ክርስቲያንነት የሚጠራጠር ማስረጃ ሲያቀርብ፣ ጌታሁን ግን የራሶቹን ክርስቲያንነት የሚያስረግጥለት አስረጅም ሆነ ሆደ-ሰፊነታቸው ከክርስቲያንነታቸው መያያዙን የሚያሳይለት ትንታኔ አላቀረበም፡፡ ለእኔ ይህም ቢሆን ብዙ ችግር የለውም። ምክንያቱም እዚህ ዋናው ጉዳይ ራሶቹ ሆደ-ሰፊ የሆኑት በክርስትና እምነታቸው ነው ወይስ በራሳቸው ሰብዕና ነው በሚሉት ዙሪያ እንደሚቀርቡት መረጃዎች፣ አንባቢ ለሁለቱም ክርክሮች ቅቡልነት ሊሰጥ ይችላል። ይህም ማለት ጉዳዩ (የራሶቹ ሰብዕና፣ ክርስቲያንነትና ድርጊት) መቸም ቢሆን አከራካሪነት አያጣውም ማለት ነው። ጌታሁን ግን ይህን የጉዳዩን አከራካሪነት የተቀበለ አይመስልም፡፡ የበዕውቀቱ ርዕስ እንኳ ‹‹የንቀት ውሃ ሙላት ሲወስድ እያሳሳቀ ነው›› የሚል እንጂ የራሶቹ ክርስቲያን መሆን አለመሆን አላሳሰበውም፡፡፡ ያደረገው ነገር የበዕውቀቱን የመከራከር ነፃነት ነፍጎ ሲያበቃ፣ በዕውቀቱ የራሶቹን ሰብዕና በማድነቁ ሲያታልል እንደደረሰበት ሁሉ This guy is attempting to cheat us! ሲል ብቻውን መደናነቅ ነው፡፡ የርዕሰ-ነገሩን አከራካሪነት ቢያጤነው ኖሮ የበዕውቀቱ ግንዛቤ በዚህ መንገድም ማየት ይቻላል የሚያስብል እንጂ ‹‹በዕውቀቱ መጥፎውን ስራቸውን ከክርስቲያንነታቸው፣ መልካሙን ከሰብዕናቸው ጋር ለማያያዝ ባለ በሌለ ኃይሉ ተግቷል›› የሚል ከነፋስ የተቀዘፈ (Non Sequitur) ማጠቃለያ ባልሰጠ ነበር፡፡
ጌታሁን እነኝህን በመሳሰሉ ግድፈቶቹ ‹‹ባለ በሌለ ኃይሉ በክርስትና ላይ ዘምቷል›› የሚለው በዕውቀቱን ብቻ ሳይሆን ስለ ፍሮይድ በጠቃቀሳቸው አንቀጾችም ፍሮይድም ኃይማኖትን (በዚያውም ክርስትናን) አንዳች ጠቀሜታ የለውም ያለ የሚያስመስል ስዕል ሰጥቶታል። ፍሮይድ እንደሚለው፤ የእርሱ (የፍሮይድ) ትንበያ ከኃይማኖት ትንበያ የሚለየው መፈናፈኛ የሚከለክል ባለመሆኑ ነው፡፡ የጌታሁን መከራከሪያ (ቢያንስ በዚህ አቀራረቡ) ከበዕውቀቱ ትንታኔ የሚለየው መፈናፈኛ የማይሰጥ አስመስሎ ስላቀረበው ነው፡፡ አጥብቆ መከራከርና ለአከራካሪው ጉዳይ ሌላ ገጽ ዕውቅና ሰጥቶ መከራከር የተለያዩ ነገሮች ናቸው፡፡ ጌታሁን ለሌላው ገጽ ዕውቅና በመንፈግ አጥብቆ የተከራከረ ሲሆን በእያንዳንዱ ክርክሩ መዝጊያ ጥብቅ ማስጠንቀቂያ ወይም ‹‹አያችሁልኝ የምሔሰው መጽሐፍ ደራሲ ኮሜዲያንና ኮሚክ ነው፤ ያነበበው መጽሐፍ ደግሞ ፍሮይድ ኮኬይን በመጠቀም የጻፈው Illusion ነው፡፡ የበዕውቀቱ ጥሪ የሚያመዝነው ከውይይት ይልቅ ለልግጫና ለስድብ ነው›› የሚል አዋጅ አይጠፋውም፡፡ ይህ ደግሞ ሒሱን ተዓማኒነት ያሳጣበታል፡፡
 የበዕውቀቱን የቃላት አጠቃቀም ወደ ስድብ ያዘነበለ ለማስመሰል ብዙ ደክሟል፡፡  
ጌታሁን ‹‹የበዕውቀቱን የውይይት ግብዣ ሁሌም በጥርጣሬ ዓይን›› እንደተመለከተው ነው፡፡ ለዚህ ማረጋገጫ አድርጎ ያቀረባቸው ደግሞ በዕውቀቱ ተጠቀመባቸው የሚላቸውን ለውይይት የማይመቹ ቃላትን ነው፡፡ በ‹‹ከአሜን ባሻገር›› ያሉትም የሌሉትም የሃይማኖት አባቶችን “የሃይማኖት እበቶች”፣ የምልክት ቋንቋን “የዱዳ ቋንቋ”፣ ቤተመቅደስን “አዳራሽ” ማለቱን በአስረጅ ጠቅሶበት ሲያበቃ፣‹‹የውይይት መድረክ ጠፋ ብሎ ቡራ ከረዩ ማለቱን ምን አመጣው?›› ሲል ይጠይቀዋል፡፡ ‹‹የውይይት ጽንሰ ሐሳብ ሀሁ የሚጀምረው የሌሎችን ሐሳብ ከማክበርና ስህተቶችን በጨዋ ደንብ ከማረም›› በመሆኑ ላይ ከጌታሁን ጋር እስማማለሁ፡፡ የሚያስከፉ ቃላትና አነጋገሮች ለውይይትም ሆነ ለክርክር ተስማሚነት የላቸውም፡፡ የስድብ ቃላት እየተወራወሩም በውይይትም ሆነ በክርክር አንድ ምዕራፍ መራመድም አይቻልም፡፡ ግን በ‹‹ከአሜን ባሻገር›› መጽሐፍ ውስጥ ‹‹የሀይማኖት እበቶች›› የሚል አባባል አለ ወይ? እኔ ፈልጌ አላገኘሁም፡፡ አገኘሁ ያለ ጓደኛም የለኝም፡፡ አባባሉ በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ከተገኘ ለማስተባበል ገፍቼ የምሔደው የፊደል ግድፈት ከሆነ ብቻ ነው፡፡ ካለ ማስተባበያውን ራሱ ባለቤቱ ይስጥ፡፡ ጌታሁን ይህን ቃል ከየት እንዳመጣው ባላውቅም ‹‹ከአሜን ባሻገር››ን እንደማይመለከት ግን እርግጠኛ ነኝ፡፡ ስለተባለም አንድ ቃል አንድ ትርጉም ብቻ ያለው እየመሰለን ፈጥነን ማጠቃለያ ላይ መድረስና ጸጉር ስንጠቃ መግባት የቋንቋ ሊቃውንት እንደሚሉት semantic trap ነው፡፡ ችግሩ አንድ ቃል ሁልጊዜም አንድ ትርጉም ብቻ ይኖረዋል የሚል መነሻ ነው። በተለይ ጽንሰ-ሀሳቡ የውጭ ሆኖ በእኛ አገላለጽ ስንተካው፣ የቀድሞ ጥቅሙን ሊጥል ወይም ሌላ አሉታዊ ብቻ ሳይሆን አዎንታዊ ትርጉምም ሊሸከም ይችል ይሆናል፡፡ የቋንቋ ሊቃውንት የሚሰጡትን ዳኝነት እየጠበቅሁ፣ በበኩሌ ጌታሁን እንደ ስድብ አድርጎ ያነሳቸው ቃላት በ‹‹ከአሜን ባሻገር› መጽሐፍ ጥቅም ላይ የዋሉበት አግባብ ለምሣሌም ‹‹የምልክት ቋንቋ›› ‹‹የዱዳ ቋንቋ››ን ይተካዋል ወይ? ብለን ስንጠይቅ በምንሰጠው ምላሽ የሚወሰን ይመስለኛል፡፡
ጌታሁን የበዕውቀቱን በቅንነት የመከራከር ጥያቄ እንዲጠራጠር ካደረጉት ምክንያቶች አንዱ በቃላት አጠቃቀሙ ለምሣሌም  ‹‹የዱዳ ቋንቋ›› ከሚል ‹‹የምልክት ቋንቋ›› ማለት ይችል ነበር በማለት ይመስለኛል፡፡ ነገር ግን ጉዳዩን በቅንነት ከተረዳነውና ጠንቃቃ አንባቢ ከሆንን በዕውቀቱ በኮሚዲያንነቱ ይሁን በኮሚክነቱ መውጫ አያጣም። ‹‹የላሊበላ አዳራሾችን ምን ብለን እንጥራቸው?›› ሲል የሚጠይቀው በዕውቀቱ፤ ከአድናቆቱ ብዛት መጥሪያ ቃላት፣ መግለጫ ስዕል፣ ማናቸውም ሰውኛ ቋንቋዎችና መግለጫዎች አነሱኝ ካለ ተስማሚው አባባል ‹‹የምልክት ቋንቋ›› ሳይሆን ‹‹የዱዳ ቋንቋ›› ይመስለኛል፡፡ የበዕውቀቱ የተጋነነ የአድናቆት አገላለጽ ቤተመቅደሶችን ላላየ ሰው ለመግለጽ የሚያስችል ሰውኛ ቃላት ወይም ስዕል በጠቅላላውም የሰው ቋንቋ የለም የሚል ነው፡፡ ‹‹የምልክት ቋንቋ››ን ከተጠቀመማ እነኛን ድንቅ የላሊበላ ቤተ-መቅደሶች የሚገልጽበት ሰውኛ ቋንቋ አላጣም፤ ቢያንስ በምልክት ቋንቋ መግለጽ ችሏል ማለት ነው፤ ይህ ከሆነ ደግሞ አድናቆቱ ይቀንሳል፡፡ እናም የተጋነነ አገላለጹን ከተቀበልን ‹‹የምልክት ቋንቋ›› ‹‹የዱዳ ቋንቋ››ን ይተካዋል ማለት አያስኬድም፡፡
ሁለተኛው ምክንያት ‹‹የምልክት ቋንቋ›› ይጠቀም ብንል እንኳ ‹‹የምልክት ቋንቋ›› መስማት ለተሳናቸው እንጂ ማየት ለተሳናቸው (ለዓይነ-ስውራን) አይሆንም፡፡ በዕውቀቱ ስለ ላሊበላ ድንቅ ስራዎች ለመናገር የፈለገው ለሁሉም ነበር ብለን ከወሰድን ‹‹የምልክት ቋንቋ›› መስማት ለማይችሉ ማየት ግን ለሚችሉ (ሁለቱም ሔደው ስላላዩ) እንጂ ማየት ለማይችሉ (ለዐይነ-ስውራን) አያገለግለውም፡፡ ሶስተኛው ምክንያት ለመሆኑ ‹‹የዱዳ ቋንቋ›› ምንድን ነው? ስድብ ብቻ ነው ወይስ አዎንታዊ ትርጉምም አለው? ብለን ስንጠይቅ በምንሰጠው መልስ ይወሰን ይሆናል፡፡ የቋንቋ ሊቃውንት ይዳኙን። የላሊበላ ጥበብ ለበዕውቀቱ የሰው ልጅ ቋንቋ የተባለ ሁሉ ከሚገልጸውም በላይ እንደሆነበት ከተረዳን፣ ‹‹ልክ ቃል ለማውጣት እንደማይችል ዱዳ ሆንኩ›› ዓይነት ነው፡፡ ዱዳ እዚህ ምን አሉታዊ ትርጉም አለው?
አንዳንዴ ከምንተቸው ጽሑፍ ስህተት ለመፈለግ አጥብቀን ከመትጋታችን የተነሳ እንደ በዕውቀቱ የፈጠራ ብርቱ ንጉሥ፣ ‹‹ከዘንባባ ዝንጣፊ ሾተል›› ለመስራት ይዳዳናል፡፡ በአድናቆት ከተጻፈ ድንቅ አንቀጽ ውስጥ አንዲት ቃል ወስደን፣ ሌላውን ሁሉ የገለጸበት አድርገን እንመስለዋለን፡፡ በጌታሁን ትችት፤ ‹‹ኑብያዎች በድንበራችን ላይ ዘንባባ ተክለዋልና እንውጋቸው›› እንዳለው የንጉሥ አማካሪ ‹‹የጦር አውርድ›› አባዜ ባላይበትም በዕውቀቱ በአድናቆት ለስያሜ የተቸገረላቸው ቤተ-መቅደሶች መጠሪያ ለጌታሁን የኢ-አማኒ ድፍረት ተደርገው የተወሰዱት በአንድ በኩል ‹‹ከዘንባባ ዝንጣፊ ሾተል የመሳል አባዜ›› ሊሆን እንደሚችል እጠረጥራለሁ። በሌላ በኩል ምናልባት የቋንቋና የቃላት አጠቃቀማችን ዘፈቀደነት የጋራ ችግር ፈጥሮ እንደሆነ የቋንቋ ሊቃውንት የሚያውቁትን ዕውቀት እንዲያካፍሉን እጠይቃለሁ። ማለቴ ለምሣሌ ‹‹መቅደሶች›› የሚባሉት በአማኞች ከሆነ፣ እንደ በዕውቀቱ ያለ ‹‹ኢ-አማኒ›› ጎብኚ ደግሞ ስማቸው አነሰብኝ ካለ አማኝ ያልሆኑ ወይም የሌላ እምነት ተከታዮች የሆኑ ኢትዮጵያውያን ወይም የውጭ ዜጎች ምን ብለው ይጥሯቸው? ለውጭ ዜጎች እኛ በምንጠራበት ስማቸው ጥሯቸው ብለን መመሪያ መስጠት እንችል ይሆናል። ለእኛ ግን የጋራ ውርሶቻችን ናቸውና የጋራ መጠሪያ ያስፈልጋቸዋል፡፡ ‹‹መቅደሶች›› የሚለው መጠሪያቸውና ‹‹ውቅር አብያተ-ክርስቲያናት›› የሚለው ከእምነት ጋር የሚገናኝ ስያሜያቸው፣ በእግረ መንገድም መቅደሶቹ የተሰሩት በመላዕክት ነው የሚል ስለሚከተላቸው፣ የግድ ለሁላችንም የሚሆን የጋራ መጠሪያ አያስፈልጋቸውም? ቸር እንሰንብት!!



Read 1480 times