Monday, 04 April 2016 09:08

መምህር ግርማ ወንድሙ፤ ለበጐ አድራጐት ድርጅቶች ድጋፍ አደረጉ

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(4 votes)

      መልአከ መንክራት ግርማ ወንድሙ (መምህር ግርማ) በውጭ አገር የሚኖሩ 200 ያህል የወንጌል ተማሪዎችን አስተባብረው በላኩት 20 ሺ ዶላር እህልና አስፈላጊ ቁሳቁስ ገዝተው ለሙዳይ በጎ አድራጎት ማኅበርና የወደቁትን አንሱ ነዳያን ማኅበር ድጋፍ ሰጡ፡፡
ሰሞኑን በየማኅበራቱ ጽ/ቤቶች በተደረገው የርክክብ ሥነ ስርዓት መምህር ግርማ ባደረጉት ንግግር፤ እሳቸውና ባልደረቦቻቸው የሙዳይን በጎ አድራጎት ማኅበርና የወደቁትን አንሱ ነዳያን ማኅበር ጎብኝተው፣ በእርግጥም መረዳት እንዳለባቸው አምነው ዕርዳታውን ለመስጠት መወሰናቸውን ተናግረዋል፡፡
ዓላማችን በዚህ ብቻ ሳንወሰን፤ በአገራዊና ማኅበራዊ ጉዳዮች መሳተፍ ነው ያሉት መምህር ግርማ፤ በቅርቡ ከቀይ መስቀል ጋር በመተባበር በድርቅ ለተጎዱ ወገኖቻችን ድጋፍ እናደርጋለን። የሕዳሴ ግድቡንም እንረዳለን፤ የአቅማችንን በማድረግ ከጎናችሁ ነን ለማለትና ለሌሎች አርአያ ለመሆን በማሰብ ነው ብለዋል፡፡
ይህን ያህል ሰው ቀርቶ ቤተሰብ መመገብ ይከብዳል ያሉት የፕሮግራሙ አስተባባሪ አቶ ጣሰው እሸቴ፤ ለሙዳይ በጎ አድራጎት ማኅበር ለአንድ ወር ወይም ለወር ተኩል ሊያገለግል የሚችል እስከ 250 ሺ ብር ግምት ያለው 60 ኩንታል የተፈጨ ጤፍ፣ ስንዴ፣ ምስር፣ ባቄላ፣ አተር፣ ዘይት፣ በርበሬ፣ ለተማሪዎች ደብተር፣ እስክሪብቶ፣ እርሳስ፣ የተለያዩ አልባሳት፣ የመፀዳጃ ቁሶች … ማበርከታቸውን ገልጸዋል፡፡
የሙዳይ በጎ አድራጎት ማኅበር መስራችና ዋና ሥራ አስኪያጅ ወ/ሮ ሙዳይ ምትኩ ለተደረገላት ድጋፍ አመስግና፣ ስራውን ከጀመረች 16ኛ ዓመቷን እንደያዘች፣ ከአገር ውስጥም ሆነ ከውጭ በቡድን ትልቅ ድጋፍ ሲደረግላት የዕለቱ የመጀመሪያው እንደሆነ ገልጻለች፡፡
ሙዳይ በጎ አድራጎት ከ300-400 ያህል ሰው በቀን ሶስት ጊዜ እንደሚመግብ ጠቅሳ፣ ከፍተኛው ችግራቸውና ወጪያቸው ምግብ እንደሆነ በቀን አንድ ኩንታል ጤፍና 50 ኪ.ግ ማካሮኒ እንደሚጠቀሙ፣ በወር ለምግብ ብቻ 250 ሺህ ብር ወጪ እንደሚሆን ተናግራለች፡፡ የተደረገልንን ድጋፍ ሁሉንም አላየሁትም፡፡ ጤፍ በእርግጠኝነት ለአንድ ወር ወይም ከዚያ በላይ ሊመግብ ይችላል ብላለች፡፡
በወጣትና በጉልምስና ዕድሜያቸው ለአገር ታሪክ የሰሩ አረጋውያን መጨረሻ ላይ ጧሪ ቀባሪና አስታማሚ አጥተው የወደቁ ባለውለታዎቻችንን ማሰብና መደገፍ አለብን ያሉት መምህር ግርማ፣ ለአረጋዊያኑ 150 ሺህ ብር ግምት ያለው 40 ኩንታል ጤፍ፣ ሽሮ፣ በርበሬ፣ ዘይት፣ ምስር፣ አተር፣ የመፀዳጃ ቁሶች፣ ራሳቸውን መቆጣጠር ለማይችሉት ደግሞ መገልገያ ዳይፐር፣ … መሰጠቱን ገልጸዋል፡፡
በ1991 ዓ.ም የተቋቋመው የወደቁትን አንሱ ነዳያን ማኅበር፣ 100 አረጋውያንን እንጦጦ ኪዳነ ምህረት አካባቢ በአራት ቤት አስቀምጦ እየተንከባከበ መሆኑን የጠቀሱት የማኅበር መስራችና የተረጂዎቹ የፋይናንስ ኃላፊ አቶ ስንታየሁ አበጀ፤ የወደቁትን አንሱ፣ የሞቱትን ቅበሩ፣ ያሉትን አስተምሩ በሚለው የማኅበሩ ውስጠ ደንብ መሰረት እየሰሩ መሆኑን፣ ኅብረተሰቡ በሚያደርግላቸው ድጋፍና የከተማው አስተዳደር በሰጣቸው ቦታ ላይ ባለ 4 ፎቅ ሕንፃ እያሰሩ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

Read 3305 times