Saturday, 09 April 2016 10:22

ከ“ዳስ” ወደ “ክላስ”

Written by  መታሰቢያ ካሣዬ
Rate this item
(0 votes)

“የነገውን ብሩህ ቀን በልጆቼ አየዋለሁ”
                               
      አናት ከሚበሳው ፀሐይ የማታስጥል፣ እዚህም እዚያም የተቦዳደሰችና በቅጠልና በጭራሮ የተሰራች ዳስ ቢጤ ናት፡፡ ዙሪያዋ ክፍት ሆኖ መሃሏ እርስበርስ በተጠላለፉ የእንጨት ጭራሮ ለሁለት ተከፍላለች። ይህንኑ የጭራሮ ግድግዳ ተደግፎ ከቆመ ጥቁር ሰሌዳ ፊት ለፊት በርካታ የድንጋይ መቀመጫዎች በረድፍ በረድፍ ተደርድረዋል፡፡ ዳሷ የመማሪያ ክፍል፣ ድንጋዮቹ ደግሞ የተማሪዎች መቀመጫ ወንበሮች መሆናቸውን ለማመን እጅግ ይቸግራል፡፡ የአንደኛና የሁለተኛ ክፍል ተማሪዎችን የሚለየው የጭራሮ አጥር፣ የሁለቱ ክፍል ተማሪዎችን እርስበርስ ከመተያየት የሚከለክላቸው አይደለም፡፡
አደሃያም ቀሽት፣ ፀሐም ቀሽት፣ መዘል ቀሽትና ህጉር ቀሽት ከሚባሉት የገጠር ቀበሌዎች እየተሰባሰቡ ኩዶ ጣቢያ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ በሚገኘውና ህድሪ ከሚባለው ከዚህ ት/ቤት ዕውቀትን ፍለጋ የሚማስኑት ህፃናት በርካታ ናቸው። እንደ ወላፈን በሚጋረፍ ሙቀት በቅጠል ዳስ ስር በድንጋይ መቀመጫ ላይ ሆነው ከሚማሩት ህፃናት በርከት ያሉት ዕድሜያቸው ከ10 ዓመት በታች ናቸው፡፡ ነገ ትልቅ ሰው የመሆን ህልማቸውን ይዘው ዛሬን ይታትራሉ፡፡
መጋቢት 24 ቀን 2008 ዓ.ም ግን ለእነዚህ ህፃናት ብሩህ ቀን የወጣበት፣ ወደ ህልማቸው ለሚያደርጉት ጉዞ መንገዱ የተጠረገበት ልዩ ቀናቸው ነበር፡፡ “Imagine one day” በተባለና ጥራት ያለው ትምህርት ለሁሉም ህፃናት ለማዳረስ በሚሰራ ግብረሠናይ ድርጅትና  በአካባቢው ማህበረሰብ ትብብር የተሰሩት ዘመናዊ የመማሪያ ክፍሎች የካናዳ አምባሳደር ሚስተር ፊሊፕ ቤከርና የኢማጅን ዋን ዴይ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሚስተር ስኮት ኤሊየት እንዲሁም በኢትዮጵያ የድርጅቱ ዳይሬክተር አቶ ሰይድ አማን በተገኙበት ተመርቋል፡፡
ይህንን የምረቃ ፕሮግራም ለማክበር ከየአካባቢው ተሰባስበው የመጡት ወላጆችና ህፃናት ሥፍራውን አጥለቅልቀውታል፡፡ በህፃናቱ ፊት ላይ የሚታየው ጉጉትና ደስታ ልዩ ነበር፡፡ ዝግጅቱን ለመታደም ማልደው ከሥፍራው የደረሱት ወላጆችም ደስታቸውን በተለያዩ መንገዶች ይገልፃሉ፡፡ ከመሃል ያገኋቸውን አንድ አባት ተጠግቼ ጠየቅኋቸው፡፡ የቀሽት ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት አለቃ ገብረእግዚአብሔር ገብረህይወት፤ ደስታቸውን የሚገልፁበት ቃላት ያገኙ ባይመስሉም እንደምንም ተነፈሱ፡-
 “ልጆቼን ለማስተማር ፍላጐት ቢኖረኝም በአካባቢዬ ት/ቤት ስለሌለ በጣም እቸገር ነበር። የሶስት ሰዓታት የእግር መንገድ እየተጓዙ መማር እጅግ በጣም ከባድ ነው፡፡ አሁን ግን እንደገና የተወለድኩ ያህል ቆጥሬዋለሁ፡፡ ዕድሜዬን የምቆጥረው ከዚህ ት/ቤት መሠራት ጋር ነው። ለራሴ ያጣሁትን ልጆቼ አግኝተውት ከማየት የበለጠ ዳግም ውልደት አለ? በዚህ ዘመናዊ ት/ቤት ለማስተማር 3 ልጆቼን አስመዝግቤአለሁ፡፡ የነገውን ብሩህ ቀን በልጆቼ አየዋለሁ”
 የአለቃ ገ/እግዚአብሔርን ስሜት የሚጋሩ በርካታ የኩዶና አካባቢው ቀበሌ ነዋሪዎች የምረቃ በዓሉን አድምቀውታል፡፡ ፀሐም ቀሽት ከሚባለው መንደር እየመጣ በህድሪ ት/ቤት የሚማረው የ10 ዓመቱ ታዳጊ የማነ ክፍሎም በሚማርበት ት/ቤት ቅጽር ግቢ ውስጥ የተሰሩት ዘመናዊ የመማሪያ ክፍሎች ትንግርት ሆነውበታል፡፡ የክፍሎቹን ማማር፣ የመቀመጫ ዴስኮቹን ውበት፣ የወለሉን፣ የጥቁር ሰሌዳውን ----- ሁሉን አንስቶ አይበቃውም። “ግን እውነት ይህ ክፍል እኛ የምንማርበት ነው? ከዳስ ወደ ክላስ ልንገባ ነው?” ደጋግሞ ይጠይቃል፡፡
የትምህርት ቤቱ ርዕሰ መምህር አለፎም ገብረስላሴም በት/ቤቱ ላይ የተፈጠረውን ለውጥ አስደናቂ ነው ይላሉ፡፡ በ2000 ዓ.ም በሁለት መምህራን ሥራ የጀመረውና ለ1ኛ እና 2ኛ ክፍል ተማሪዎች ብቻ አገልግሎት ይሰጥ የነበረው የቅጠል ዳስ ት/ቤት፤ ዛሬ ዘመናዊ ክፍሎችና ቤተመፃሕፍት የተሟሉለት የመጀመሪያ ደረጃ ት/ቤት ሆኗል፡፡ ለትምህርት ቤቱ ግንባታ የአካባቢው ማህበረሰብም የገንዘብ ድጋፍ አድርጓል፡፡ ድርጅቱ በየአካባቢው በሚያከናውናቸው የልማት ሥራዎች ላይ ህብረተሰቡ ከ10-20% የገንዘብ እገዛ እንዲያደርግ ይጠይቃል፡፡ ይህ የሚደረግበት ዋንኛ ምክንያትም ህዝቡ የተሰሩት የልማት ሥራዎች የራሱ እንደሆኑ እንዲያስብ፣ ከእርዳታ ጠባቂነት ተላቆ በራሱ አንድ ነገር ማድረግ እንደሚችል እንዲያውቅና የተሰራው ሥራ የእኔ ነው ብሎ እንዲጠብቅና እንዲከባከብ ለማድረግ መሆኑን የድርጅቱ ካንትሪ ዳይሬክተር አቶ ሰይድ አማን ነግረውኛል፡፡
በተመሳሳይ ሁኔታም 36 ያህል ት/ቤቶች ተሰርተዋል፡፡ ድርጅቱ በሚንቀሳቀስባቸው የትግራይ ክልል 5 ወረዳዎችና በኦሮሚያ ክልል 5 ወረዳዎች ከተሰሩት ከእነዚሁ ት/ቤቶች በተጨማሪ 26 የውሃ ቦኖዎችና 40 የመፀዳጃ ቤቶችም ተሰርተው ለህብረተሰቡ አገልግሎት እንዲሰጡ ተደርገዋል። በትግራይ ክልል አብርሃ ወአፅብአ ቀበሌ ውስጥ የተገነባው ምንዳዕ የመጀመሪያ ደረጃ ት/ቤት መጋቢት 25 ቀን 2008 በተካሄደ ሥነስርዓት ተመርቆ ለተማሪዎች ክፍት ሆኗል፡፡
የኢማጅን ዋን ዴይ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሚስተር ስኮት ኤሊት በምረቃ ፕሮግራሙ ላይ ሲናገሩ፤ ድርጅቱ በመጀመሪያ ደረጃ ት/ቤቶች ላይ ትኩረት በማድረግ ሁሉም ህፃናት ጥራት ያለው ትምህርት ለማግኘት እንዲችሉ እየሰራ መሆኑን ጠቁመው፣ በኢትዮጵያ ውስጥ ላለፉት 8 ዓመታት በድርጅቱ የተከናወኑት ተግባራት አበረታች ናቸው ብለዋል። ትምህርት ቤት በሌሉባቸው አካባቢዎች የት/ቤት ግንባታዎችን መሥራት፣ የመፀዳጃ ቤቶችን መገንባት፣ ለትምህርት ጥራት የሚረዱ ቁሳቁሶችን ማሟላት ከድርጅቱ ተግባራት መካከል ዋንኞቹ እንደሆኑ የጠቆሙት የድርጅቱ ካንትሪ ዳይሬክተር፤ ከዚህ በተጨማሪ ወደ ትምህርት ገበታ ያልመጡ ህፃናት እንዲመጡ በማድረግ ረገድ አጥጋቢ ሊባል የሚችል ውጤት ማስመዝገባቸውንና እስከ አሁን ከ42ሺ በላይ ህፃናት ወደ ትምህርት ገበታ እንዲመጡ ማድረጋቸውን ተናግረዋል፡፡ ድርጅቱ በተለያየ መንገድ እገዛ በሚያደርግላቸው 487 ት/ቤቶች ውስጥ የሚገኙ ከ250 ሺ በላይ ህፃናትም ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡  
በአገሪቱ ገጠራማ አካባቢዎች የሁለተኛ ደረጃ ት/ቤቶች ባለመኖራቸው ሳቢያ በርካታ ተማሪዎች አነስተኛ ገቢ ያላቸው በተለይም ሴት ተማሪዎች 8ኛ ክፍልን ካጠናቀቁ በኋላ ወደ ከተማ ሄደው ትምህርታቸውን ለመቀጠል ባለመቻላቸው ምክንያት ትምህርታቸውን ለማቋረጥ ይገደዳሉ፡፡ ኢማጂን ዋን ዴይ፤እኒህ ተማሪዎች ትምህርታቸውን እንዲቀጥሉ ለማድረግ የሚያስችል ተግባር እያከናወነ ይገኛል፡፡ Graduate Fund በተባለው ፕሮጀክት በትምህርታቸው ጥሩ ውጤት ያስመዘገቡና አነስተኛ የኢኮኖሚ አቅም ካላቸው ቤተሰቦች የተገኙ ተማሪዎችን በማቀፍ ቤት ተከራይቶ አስፈላጊ የትምህርት ቁሳቁሶችን እያሟላ ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ ያደርጋል፡፡ በዚህ ፕሮግራም 218 ተማሪዎች ታቅፈው ትምህርታቸውን በመማር ላይ ይገኛሉ፡፡
ለተማሪዎቹ ከሚደረገው ድጋፍ በተጨማሪ ቤተሰቦቻቸው በገቢ ማስገኛ ሥራዎች ላይ ተሰማርተው ልጆቻቸውን ይረዱ ዘንድ ስልጠና በመስጠት፣ ለእያንዳንዳቸው ከ3500-4000 ብር ድጋፍ ያደርጋል፡፡ ይህም የስኮላርሽፑ ተማሪዎች በእርዳታ ነው የምማረው ከሚለው እሣቤ ተላቀው ቤተሰቦቻቸው እንዳስተማሯቸው እንዲያስቡ ለማድረግ እንደሆነም ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡ የስኮላርሽፑ ተጠቃሚ ከሆኑት የመጀመርያ ዙር 17 ተማሪዎች መካከል 14ቱ ወደ ዩኒቨርሲቲ ገብተዋል። ለስኮላርሽፑ በየዓመቱ ከ50-60 የሚሆኑ ተማሪዎችን ከየትምህርት ቤቱ ይቀበላል፡፡
ኢማጅን ዋን ዴይ፤ሁሉም ህፃናት በ2030 ዓ.ም ከእርዳታ ነፃ ጥራት ያለው ትምህርትን ያገኛሉ የሚለውን ተልዕኮውን ዕውን ለማድረግ የሚሰራ ድርጅት ሲሆን እ.ኤ.አ በ2030 ተልዕኮውን እንደሚያጠናቅቅም አቶ ሰይድ ገልፀዋል፡፡   

Read 1803 times