Saturday, 09 April 2016 10:24

የአለማችን ሃያላንን ቅሌት ይፋ ያወጡት “የፓናማ ሰነዶች”

Written by 
Rate this item
(3 votes)

ባለፈው እሁድ ማለዳ ላይ...
አለማቀፉ የምርመራ ጋዜጠኞች ጥምረትና ሱደች ዜቱንግ የተባለው የጀርመን ጋዜጣ፣ አለምን ያስደነገጠ ቁልፍ አለማቀፍ የቅሌት መረጃ ይፋ አደረጉ፡፡
የፓናማ ሰነዶች የሚል ስያሜ የተሰጠው ይህ ቁልፍ መረጃ፣ ባለፉት አራት አስርት አመታት በድብቅ የተከናወኑ የዓለማችን ገናና ፖለቲከኞች፣ ባለሃብቶችና ታዋቂ ግለሰቦችን የገንዘብ ቅሌት ለአለም ያጋለጠ አነጋጋሪ አጀንዳ ሆኗል፡፡
ያሳለፍነው ሳምንት የዓለማችን ታላላቅ መገናኛ ብዙሃን ቀዳሚ ትኩስ ዜና የፓናማ ሰነዶች ቅሌት ነበር፡፡ ይሄው ቅሌት የዓለማችን ስመ ገናና ፖለቲከኞችና ባለጸጎች በቢሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር ወደ ሌሎች አገራት ማሸሻቸውንና ግብርን ለማምለጥ ሲሉ በውጭ አገራት በድብቅ ባቋቋሟቸው ኩባንያዎችና የንግድ ተቋማት ረብጣ ትርፍ ማጋበሳቸውን ያሳያል፡፡
በአለማችን የመረጃ ማፈትለክ ታሪክ እጅግ ትልቁ ነው የተባለውና ሞዛክ ፎንሴካ ከተባለው የፓናማ የህግ አገልግሎት ተቋም አፈትልኮ የወጣው ይህ ቁልፍ ሚስጥር፣ 11 ሚሊዮን ያህል የቅሌት መረጃዎችን የያዘ ሲሆን፣ በ76 የአለማችን አገራት ከሚገኙ መገናኛ ብዙሃን የተውጣጡ 107 ያህል ጋዜጠኞችም ከአንድ አመት በላይ ለሚሆን ጊዜ በመረጃዎቹ ላይ ጥናት ሲያደርጉ ነበር ተብሏል፡፡  
እስካሁን በተገኘው መረጃ የ12 አገራት የወቅቱና የቀድሞ መሪዎች፣ ከ60 በላይ የአገራት መሪዎች ቤተሰቦችና ተባባሪዎች እንዲሁም ፖለቲከኞች በዚህ ቅሌት ውስጥ እንደተሳተፉ የታወቀ ሲሆን፣ ከቅሌቱ ጋር ንክኪ ያላቸው ኩባንያዎችና ተቋማት ቁጥርም 214 ሺህ ያህል እንደሚደርሱ ታውቋል፡፡ አነጋጋሪው መረጃ እ.ኤ.አ ከ1977 እስካለፈው ታህሳስ ወር የተከናወኑ ታላላቅ ቅሌቶችን የያዘ ሲሆን ጥብቅ ሚስጥሩን ለአመታት በእጁ ይዞ የቆየው የፎንሴካ የህግ ተቋምም መረጃው ከውጭ አካላት በተደረገበት ምንተፋ አምልጦት እንደወጣ በማስታወቅ፣ በቅሌቱ ተባባሪ ነው በሚል የቀረበበትን ውንጀላ አስተባብሏል፡፡
የፓናማ ሰነዶች ቅሌት በመገናኛ ብዙሃን ይፋ መደረጉን ተከትሎ በቅሌቱ ውስጥ ስማቸው ከተጠቀሱት የአገራት መሪዎች መካከል አስደንጋጩን ተቃውሞ ቀድመው ያስተናገዱት የአይስላንዱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሲግሙንዱር ዴቪድ ጉንላጉሰን ናቸው፡፡ በመሪያቸው ቅሌት ክፉኛ የተቆጡት በአስር ሺህዎች የሚቆጠሩ አይስላንዳውያን አደባባይ ወጥተው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስልጣናቸውን እንዲለቁ የጠየቁ ሲሆን፣ በብሪቲሽ ቨርጂን አይስላንድስ የንግድ ኩባንያ አቋቁመው ረብጣ ዶላር እያፈሱ ነው የተባሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩም በነጋታው ስልጣናቸውን በገዛ ፈቃዳቸው መልቀቃቸውን በቴሌቪዥን ባስተላለፉት መልዕክት ገልጸዋል፡፡
የሩስያው ፕሬዚደንት ብላድሚር ፑቲን በቅሌቱ ስማቸው ከተነሳ የአለማችን መሪዎች አንዱ ቢሆኑም፣ የአገሪቱ መንግስት ግን በመሪዬ ላይ የተሰነዘረ መሰረተ-ቢስ ውንጀላ ነው ሲል አጣጥሎታል፡፡ በመሰል ቅሌት የተጠቀሱት የዩክሬኑ ፔትሮ ፖሮሼንኮም ረቡዕ ዕለት ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፤ ራሳቸውን ከደሙ ንጹህ ለማድረግ ሞክረዋል፡፡ አሜሪካውያን ፖለቲከኞችና ታላላቅ ባለስልጣናት ምንም እንኳን እስካሁን ድረስ በቅሌቱ ስማቸው ባይነሳም፣ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ግን፣ የአገራቸው ታላላቅ ባለጸጎች ከመሰል ቅሌት ነጻ እንዳልሆኑ ረቡዕ ዕለት ተናግረዋል፡፡ በፓናማ ሰነዶች ቅሌት ውስጥ በራሳቸው አልያም በቤተዘመዶቻቸውና የስራ አጋሮቻቸው ተሳትፈዋል ተብለው ከተጠቀሱ አፍሪካውያን መካከል ኮፊ አናን፣ ጃኮብ ዙማ፣ ጆን ኩፎር እና ጆሴፍ ካቢላ ይጠቀሳሉ፡፡
በቅሌቱ ውስጥ አሉበት ከተባሉት ታዋቂ ሰዎች መካከልም፣ አሜሪካዊቷ ድምጻዊት ቲና ተርነር፣ አዲሱ የፊፋ ፕሬዚዳንት ጊያኒ ኢንፋንቲኖ፣ ታዋቂው የቦሊውድ የፊልም ተዋናይ አሚታባህ ባቻን፣ ታዋቂው የሆሊውድ ተዋናይ ጃኪ ቻን እና የአለማችን እግር ኳስ ኮከብ ሊዮኔል ሜሲ ይገኙበታል፡፡

Read 3279 times