Saturday, 16 April 2016 11:04

“ጉማ” - ሚናውን ያለየ የፊልም ሽልማት?!

Written by  ጄ.ኬ
Rate this item
(0 votes)

      ሽልማት ለተለያዩ ባለሙያዎች በግለሰብም ሆነ በተቋም ደረጃ በስራቸው ላስመዘገቡት የላቀ አስተዋጽኦ  የሚበረከት ማበረታቻ ነው፡፡ የሽልማቱ አይነት ከቦታ ቦታ እንደየዘርፉ መመዘኛ የተለያየ ቢሆንም አላማው በዋነኛነት የሰራን ማመስገን፣ ማበረታታት፣ ተገቢውን እውቅና መስጠት፣ ሌሎችም በዚሁ የትጋት መስመር እንዲያልፉ የተወዳዳሪነት መንፈስ መፍጠርና የጥራት ደረጃ (standard) ማበጀት ላይ ያነጣጠረ ነው፡፡ ይህን ተከትሎም ተሸላሚው የሚያገኛቸው የገንዘብ የዕውቅናና ሌሎች በርካታ ተያያዥ ጥቅሞችን ልብ ይሏል ፡፡
እነዚህ ከላይ የጠቀስናቸው ዋና ዋና ነጥቦች በአንድ ሀገር ውስጥ “የሽልማት ድርጅቶች” መኖር አስፈላጊና ወሳኝ መሆኑን ያሳያሉ፡፡ በሀገራችን የተለያዩ የሽልማት ድርጅቶች በተለያዩ ጊዜያት መቋቋማቸውን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ይሁንና አይበርክት ተብለን የተረገምን ይመስል አንዳንዶቹ በጅምር ሲቋረጡ፣ ሌሎቹ ትንሽ ተጉዘው ሲከስሙ መመልከት የተለመደ ነው፡፡
በንጉሱ ዘመን በ1960ዎቹ የተቋቋመውና የቀዳማዊ ኃ/ስላሴ የሽልማት ድርጅት የሚል ስያሜ የነበረው  የሽልማት ተቋም ለአራትና አምስት ዓመታት ገደማ ከዘለቀ በኋላ ግባተ መሬቱ ተፈጽሟል። በኢህአዴግ መንግስት በርካታ የሽልማት ድርጅቶች ብቅ ብለው የከሰሙ ሲሆን በተለይ ሜጋ ኪነ-ጥበባት የጀመረውና  በመንግስት የበላይ ጠባቂነት የተቋቋመው የስነጥበብና መገናኛ ብዙሃን ሽልማት  ተጠቃሽ ነው፡፡ እሱም ታዲያ አልዘለቀም፤ ከሁለትና ሦስት ዓመታት በኋላ ከስሟል፡፡
በዚህ ረገድ የኢትዮጵያ ኢንተርናሸናል ፊልም ፌስቲቫል ላለፉት 10 ዓመታት ያለምንም መቋረጥ መዝለቁ በጋሜ (ጅምር) መቅረት እርግማን አለማሆኑን ለማሳየት የቻለ ይመስለኛል፡፡ ይህ የፊልም ፌስቲቫል የፈጠረው መነቃቃትና የፊልም ስራ ማበብን ተከትሎ በአሁኑ ወቅት የተለያዩ የሽልማት ድርጅቶች ብቅ ብቅ ማለት ጀምረዋል። እነዚህ የሽልማት ተቋማት በምን አይነት አግባብ እንደተቋቋሙና  ምን አይነት አሰራር እንዳላቸው ማወቅ የሁላችንም ሀላፊነት ይመስለኛል።
ይህ ፅሁፍ በቅርቡ በተካሄደው የ“ጉማ” ፊልም ሽልማት ተቋም ላይ ያተኩራል፡፡ ተቋሙ የ3ኛ ዙር ሽልማቱን ባለፈው የካቲት 23 ያካሄደ ሲሆን በዚህ ፅሁፍ የማተኩረው በአሰራሩና በአደረጃጀቱ ላይ ይሆናል፡፡
“ጉማ” - አደረጃጀቱን ያልለየ ተቋም
ከላይ ለመጥቀስ እንደሞከርነው የተለያዩ የሽልማት ድርጅቶች በተለያዩ ዘርፎች ይቋቋማሉ። በፊልም ዘርፍ ከዝነኛው ኦስካር ጀምሮ በመላው ዓለም እስከሚገኙ ሀገር አቀፍና ዓለም አቀፍ ፊልም ፌስቲቫሎች ይጠቀሳሉ። በአሰራር ረገድ ኦስካር ከሌሎቹ የተለየና ንግድ-ተኮር (commercial) የፊልም ሽልማት ድርጅት ሲሆን የፊልም ፌስቲቫሎች ደግም ንግድ ተኮር ያልሆኑና (non-commercial) መሠረታዊ በሆኑ አሰራሮች የጋራ መለያ ያላቸው ናቸው፡፡
የኦስካር ፊልም አመራረጥና አሸላለም ረጅም ጊዜ የሚወስድና ውስብስብ ነው፡፡ በየዓመቱ ለኦስካር ለሚወዳደሩት ፊልሞች የሚከናወን ምንም አይነት የተሳትፎ ምዝገባ (entry call) የለም፡፡ ፊልሞች ለተሳትፎም ሆነ ለሽልማት የሚመረጡት ከ6ሺ በላይ በሆኑ የድርጅቱ ቋሚ አባላትና ባለሙያዎች ነው። እጩና አሸናፊዎች የሚወሰኑትም እነዚሁ አባላት በሚሰጡት ድምፅ ነው፡፡ የሽልማት ስነ-ስርዓት ከመካሄዱ በፊት የሚዘጋጅ ምንም አይነት ከፊልም ጋር የተያያዘ ፕሮግራም (ዎርክሾፕ፣ ሴሚናር፣ ሲምፖዚየም፣ የፓናል ውይይት) የለም፡፡ የድርጅቱ ሁሉም ዝግጅቶች የሚከናወኑትና የሚደመደመው በአንድ ተሲያት በሚዘጋጅ የሽልማት ስነ-ስርዓት ነው። ለዚህ ይመስላል ንግድ ተኮር የሚል ተቀፅላ ስያሜ የተሰጠው፡፡ ይህን መሰል አሰራር ያላቸው የሽልማት ድርጅቶች በዓለማችን ላይ በጣት የሚቆጠሩ ሲሆኑ እነሱም ለእውቅና ያልበቁ ናቸው።
ሌሎች በፊልም ላይ የሚሰሩ የሽልማት ድርጅቶች የሚባሉት የፊልም ፌስቲቫሎች ናቸው፡፡ በአሁኑ ወቅት  በመላው ዓለም በሺ የሚቆጠሩ ሀገር አቀፍና ዓለም ዓቀፍ የፊልም ፌስቲቫሎች ይገኛሉ። እነዚህ ፊስቲቫሎች የተቋቋሙበት የየራሳቸው አላማና ግብ ሲኖራቸው ሁሉም የሚያመሳስላቸው የጋራ ጠባያት አሏቸው፡፡ ከነዚህም መካከል ሁሉም ለተሳታፊ የፊልም ባለሞያዎች የምዝገባ ጥሪ (entry call) የሚያከናውኑ መሆናቸው፤ ዝግጅታቸው በአንድ ቀን ተከናውኖ የሚያልቅ ሣይሆን ቀናትን የሚፈጅ መሆኑ፤ በዝግጅቱ ሁሉም ተሳታፊ ፊልሞች ለህዝብ ዕይታ መቅረባቸው፣ የፊልም ባለሙያዎች የሚገናኙበትና በተለያዩ የፊልም ርዕሰ ጉዳዮች የተለያዩ ፕሮግራሞች (ዎርክሾፕ፣ ሴሚናር፣ ሲምፖዚየም፣ የፓናል ውይይት) የሚከናወንባቸው መሆኑ ከብዙ በጥቂቶቹ ናቸው፡፡ አንዳንድ ፌስቲቫሎች በሽልማት ስነ-ስርዓት የሚጠናቀቁ ሲሆኑ ሌሎች ደግሞ ከላይ የተጠቀሡትን ዝግጅቶች ብቻ በማከናወን ይጠናቀቃሉ፡፡ በዚህ ምክንያት ፌስቲቫልና - ፌስቲቫል እንዲሁም ሽልማት በመባል ይታወቃሉ። የፊልም ፌስቲቫሎች የሚያዘጋጁት ሽልማት የተከበረና ንግድ ተኮር ያልሆነ የሚያስብላቸውም ለቀናት በሚቆየው ዝግጅት ባለሙያዎችና ስራዎቻቸው የሚታዩበት፤ የሚገበያዩበት በመሆኑና በዎርክሾፕ፣ ሴሚናር፣ ሲምፖዚየም፣ የፓናል ውይይት ወዘተ በርካታ ሀሳቦች የሚንሸራሸሩበት፤ ልምድና ሀሳቦች የሚቀሰሙበት፤ ለዘርፉ እድገት ገንቢ አስተዋጽኦ የሚያደርጉ ተፅዕኖ ፈጣሪ ሀሣቦች የሚፈልቁበት መድረኮችን ያካተቱ በመሆኑ ነው። ለዚህ እንደ ምሳሌ ከአሜሪካ Sundance Film festival ከአውሮፓ Cannes film Festival እና Venus Film festival ከአፍሪካ ደግሞ Fespaco እና Zanzibar Film festival በዋናነት ይጠቀሳሉ። እነዚህ የሽልማት ድርጅቶችና አሰራራቸውን ከተመለከትን ዘንዳ ወደ ሀገራችን የጉማ ፊልም ሽልማት እንመለስ፡፡
የጉማ ፊልም ሽልማት አደረጃጀት ከማንም ጋር የሚገጥም አይመስልም፡፡ እንደ ኦስካር አይነት ነው እንዳይባል የተሳትፎ የምዝገባ ጥሪ ሲያደርግና በሀገሪቱ በአመቱ የወጡ ሁሉም ፊልሞችን ሲያካትት አናይም፡፡ የፊልም ፌስቲቫል ቅርጽ አለው እንዳይባል ለተሳትፎ የተመዘገቡት ፊልሞች የትም ቦታ ለዕይታ የማይበቁ ሲሆን ከፊልም ጋር በተገናኘ ምንም አይነት ፕሮግራም ሳይዘጋጅ መክፈቻም መዝጊያም ሣይኖረው፣ ቢበዛ ለሁለት ሰዓታት በሚቆይ ፕሮግራም ሽልማቱ ይከናወናል። በዚህ ምክንያት ጉማ የትኛውን የአደረጃጀት መንገድ እንደያዘ ለማወቅ አዳጋች ነው፡፡
የራሱ የሆነ አዲስ አሰራር ዘርግቷል የሚል መከራከሪያ ሊነሳ ይችላል፡፡ ይህም ቢሆን ሌሎች በርካታ ጥያቄዎች ማስነሳቱ አይቀርም፡፡ ላለፉት ዓመታት እንደተከታተልኩት የጉማ ፊልም ሽልማት ሶስቱንም ጊዜ ወቅቱን ጠብቆ ተከናውኖ አያውቅም። በዚህ በዋዠቀ የጊዜ ቀጠሮ በሚከናወነው ዝግጅት የሚሸለሙት የአመቱ ምርጥ ፊልምና የፊልም ባለሙያዎች ናቸው፡፡ ሌላው የዳኞችን አመራረጥ ይመለከታል፡፡ ከአዘጋጆቹ በየጊዜው እንደሚገለጸው፤ ዳኞቹ ከመቶ በላይ ናቸው፡፡ በአለማችን እጅግ የተከበሩት እነ ካን ፊልም ፊስቲቫልና ቬኒስ ፊልም ፊስቲቫል እንኳን ከ15 በላይ ዳኞች የሏቸውም፡፡
ይሁን ይህም አዲስ አሰራር  ሊሆን ይችላል፡፡ ግን እነዚህ ዳኞች እነማን ናቸው? የሚመርጣቸውስ ማነው? ለመሆኑ ሀገራችን ከ100 በላይ የሚሆኑ የፊልም ባለሞያዎች አሏት? በጭራሽ! በኢትዮጵያ በትምህርት የተረጋገጠላቸው (certified) የፊልም ባለሙያዎች በጣት የሚቆጠሩ ሲሆኑ አብዛኞቹም ኑሮአቸውን በውጪ አገራት ያደረጉ ናቸው። ታዲያ እነዚህ መቶ የሚባሉት ባለሙያ ዳኞች ከየት የመጡ ናቸው? (ከጎረቤት ሀገራት ካልተዋስን በቀር?) የሚመርጣቸውስ ማነው? በምን መስፈርት? ይህ አንገብጋቢና ወሳኝ ጥያቄ ግልፅ የሆነ ምላሽ ይፈልጋል።  
ከዚህ ሌላ ላነሳው የምሻው አብይ ጉዳይ ከአላማ ጋር የተገናኘ ነው፡፡ ጉማ ፊልም ድርጅት አላማው ምንድነው? ባለሙያን መሸለም ያለው ጥቅምና ዓላማው ጠፍቶኝ አይደለም፡፡ ይሁንና ጉማ በዚህ ረገድ የተምታታ መሰመር ላይ የቆመ የሚያስመስሉት እውነቶች ስላሉት ነው፡፡ እስከ ዛሬ እንደተከታተልኩት የሚሸለሙት አብዛኛዎቹ ባለሙያዎች በየኢትዮጵያ ኢንተርናሸናል ፊልም ፌስቲቫል የዓመቱ ምርጥ በሚል የተሸለሙት ናቸው፡፡ በተመሣሣይ ስራ የተሰማራ የሽልማት ተቋም እያለ እንደገና ይህንን አሠራር መገልበጥ ምን ጥቅም አለው? ይህን የምለው በአንድ ሀገር ውስጥ ምንም እንኳ በተመሳሳይ ስራ ላይ የተሰማሩ ተቋማት ቢኖሩም እንኳ በቅርፅና በይዘት ግን የግድ መለያየት ስላለባቸው ነው ፡፡
በሀገራችን ያሉትን መሰል የፊልም ሽልማት ድርጅቶችን በምሳሌነት ብንወስድ’ኳ አንዱ ከሌላው  ይለያያል፡፡ Color of Nile film festival በአፍሪካ ፊልምች ላይ ያተኮረና ሽልማቱንም ለአፍሪካውያን ያደረገ ተቋም ነው፡፡ አዲስ ፊልም ፊስቲቫልን ብንመለከት ትኩረቱን በዶክመንተሪ ፊልሞች ላይ ያደረገ ድርጅት ነው፡፡ Image that matter የተሰኘውን የፊልም ፊስቲቫል ብንወስድ በአጫጭር ፊልሞች ላይ ብቻ ያተኮረ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ የኢትዮጵያ ኢንተርናሸናል ፊልም ፌስቲቫል ደግሞ በአገር ውስጥ ፊልሞች ላይ የሚሰራ ነው፡፡
እነዚህ ድርጅቶች ሁሉም በፊልም ላይ የሚሰሩ ቢሆኑም በአይነትና በይዘታቸው የተለያዩ  ናቸው፡፡     ይህ በሆነበት ሁኔታ ጉማ ለምን የተለየ ይዘትና ቅርጽ ያለው ተቋም ሆኖ አልመጣም? ይህ አይነቱ አቀራረብ ተመልካች የተለያዩ ዝግጅቶችን እንዲታደም እድል ከመስጠቱም ባሻገር ለሃገሪቱ የፊልም እድገት ወሳኝ ሚና ይጫወታል፡፡ ሌላው የሚሰራውን መድገም ፋይዳው ምንድን ነው?
ከዚህ ሌላ የምጨምረው ስያሜውን በተመለከተ ይሆናል፡፡ ጉማ የተሰኘው ስያሜ  የተወሰደው ሚሸል ፓፓታሲል [ነፍሳችውን ይማርና] ከሰሩትና “ጉማ” ከተሰኘው የመጀመርያው ባለ ቀለም ፊልም ነው። ጉማ ማለት በኦሮሞ ባህል አንድ ሰው በስህተት እጁ ላይ ሰው ሲጠፋበት ሽማግሌዎች በሚወስኑት መሰረት ለሟች ቤተሰቦች ካሳ የሚከፈልበት ባህላዊ መንገድ ነው፡፡ ይህ ርእስ ጉማ ለተሰኘው ፊልም ከታሪኩ ጋር የሚሄድ ትክክለኛና ተገቢ ርእስ ነው። ታድያ ይህ ቃል በምን አግባብ ለዚህ የሽልማት ድርጅት ስያሜ ይሆናል? ሞትና ቅጣት፣ ዕርቅና ካሣ ከሽልማት ጋር ምን ያገናኛቸዋል?
መደምደሚያ
ይሁንና እኒህን መሰል ተቋማት ሚናቸው ከጠራ ሊበረታቱ እንደሚገባ ሳልጠቁም አላልፍም፡፡ ይህ አስተያየቴ በጎና ገንቢ እንደሚሆን አስባለሁ፡፡ ጉማ እያከናወነ ያለው ተግባር አስፈላጊና ሊበረታታ የሚገባው ነው፡፡
በተለይ ስነስርዓቱ የተዋጣ እንደሆነ ሁላችንም ተመልክተነዋል፡፡ ከላይ የሰጠሁት አስተያየት በግሌ የታዘብኩትና ሊታረም ይገባል ብዬ ያመንኩበት ነው። መነጋገርና መወያየት ለዕድገት መሠረት በመሆኑ አስተያየቴ በቀና እንደሚወሰድና ለውይይት መነሻ እንደሚሆን እምነቴ ነው፡፡

Read 2009 times