Saturday, 16 April 2016 11:42

ልጅነት፣ ፍቅርና ተስፋ “የደመና ሳቆች” ውስጥ

Written by  -ሶፎንያስ ሆሳዕና-
Rate this item
(2 votes)

 ደረጀ በላይነህን ከዚህ በፊት በአጫጭር ልብወለዶቹና አዲስ አድማስ ላይ በሚያቀርባቸው በሳል ጽሁፎች እንዲሁም ግጥሞች ላይ በሚሰነዝራቸው ነጻ ሂሶች አውቀዋለሁ፡፡ ታዲያ የዚህ ምርጥ ደራሲ አዲስ መጽሀፍ መውጣቱን እንደሰማው ነበር ለማንበብ የጓጓሁት፣እናም አነበብኩት፡፡ መጽሀፉ “የደመና ሳቆች” ይሰኛል፡፡ በዚህ መጽሀፍ ሁለት ክፍሎች ሀያ ሰባት ምዕራፎችን የምናገኝ ሲሆን በመጀመሪያው ክፍል ውስጥ አስራ ዘጠኝ ምዕራፎች፣ በሁለተኛው ክፍል ደግሞ ስምንት ምዕራፎችን አካቷል፡፡
እነዚህ በመጀመሪያው ክፍል የተካተቱ ምዕራፎች፣ በጠቅላላው ከልጅነት እስከ ጉርምስና ያሉትን ግዜያት አንድ በአንድ ምናልባትም ደራሲው በመግቢያው ላይ ‹‹እኔም በልጅ ልብ የሚኖሩ … በወጣትነት ዘመን እንደ እሳተ ገሞራ እየተንፈቀፈቁ የሚወጡ ግንፍል ስሜቶች የሚታፈኑበት፣ማህበረ-ፖለቲካዊ፣…ማህበረ ባህላዊና ማህበረ-ኢኮኖሚያዊ ቀውሶች የነበሩበትን ትውልድና ምጡን፣ደመና የዋጠው ድምጹንና ሣቁን፣ደረቅ ሳሉንና አልደርቅ ያለ እንባውን ለማሰብና  ለማስታወስ ነፍሴ ግድ ብላኛለች›› በማለት ያስቀመጠውን ውሳጣዊ ግፊት የሚያጠነክርልን ይመስለኛል፡፡ ደረጀ በልብ ወለዱ ውስጥ የቀረጻቸው ገጸ -ባህሪያት እስከ መጨረሻው ማለት በሚቻል መልኩ በንባባችን ውስጥ የማይለዩን፣ ደራሲውም ‹‹በበዓልም ሆነ በአዘቦት ብዙ የማልለያቸው ጓደኞቼ ሳርኬ ፣ሻረው ፣ ምንዳና ዳመና ናቸው›› ብሎ የገለጻቸው የሰፈር አብሮ አደጎቹን ይዞ ረጅሙን ምዕራፍ ለነዚሁ ለማይለዩት ገጸባህሪያት ሰውቶ ማለፉ፣ ልብ ወለዱን በተቀቀለ እንቁላል እንድመስለው ግድ አለኝ፡፡
     የተቀቀለ እንቁላል አስኳሉን ለማግኘት ቅርፊቱን አንድ በአንድ በጥንቃቄና የእንቁላሉ አስኳልን ይዞ  እንዳይገኝ ተጠንቅቀን እንደምንልጥ ሁሉ ደራሲውም የድርሰቱን አስኳል ለመጠበቅና የልጅነቱ ቅርፊቶች እርጋፊ እንዳይቀላቀሉበት በሚል ልጅነቱን ቀስ እያለ በአስራ ዘጠኝ ምዕራፍ ተርኮልናል፡፡
     ክፍል አንድ ልጅነት፡-
        የልቦለዱ ተራኪ ደጀኔ እንዲሁም ደግሞ ጓደኞቹ እድሜያቸው በግልጽ ያልተቀመጠ፣የትምህርት ደረጃቸውም ቢሆን ያልተነገረን ሲሆን እንደ ልጅነታቸው ትምህርት ቤት ካላቸው ህይወት ይልቅ መንደር ውስጥ በሚያደርጉት እንቅስቃሴና በተቀመጠላቸው ልክ እንድንለካቸው ግድ ይለናል፡፡ ነገር ግን አንዳንዴ ከሚያወሩትና ከሚያደርጉት ነገር ተነስተን፣ ዕድሜያቸውን ከፍ አድርገን እንድንገምትና በደንብ አቀላጥፈው መጻፍና ማንበብ ይችላሉ ብለን እንድናስብ እንገደዳለን፡፡ ለምሳሌ አሰለፈች ለተባለችውና ደጀኔ ‹‹…አሰለፈችን ግን በቡድን እንወዳታለን፡፡ ሁላችንም እናፈቅራታለን…›› ላላት በእድሜ ለምትበልጣቸው የመንደራቸው ሴት፣ የፍቅር ደብዳቤ ጽፈው መልስ ሲጠባበቁ (ከገጽ 12-13) ስናይ፣ ደጀኔ ስለ ትርሲት የሚያስበውንና ከትርሲት ጋር የሚወያዩትን፣ደጀኔ ለተቃራኒ ጾታ ያለውን ምልከታ ስናስብ ………. ደጀኔና ጓደኞቹ ውሰጥ የሚመላለሱትን ጥያቄዎች ስንመለከት ……..የትምህርት ደረጃቸውን ገፋ አድርገን እንድናስብ ብንገደድም በሌላ በኩል ደግሞ ሰነፍ ተማሪ ነው የሚሉት ሻረው ‹‹የቄስ ተማሪ ነው፡፡ ወደ ቄራ ገበያ ሲኬድ በስተግራ በሸንበቆ ግጥምጥም ተደርጋ በተሰራች እልፍኝ ውስጥ ነው የሚማሩት፡፡›› (ገጽ 23) የሚል ገለጻ ስናነብ፣ ሰነፍ የተባለው እኩያቸው ሻረው የቄስ ተማሪ ከሆነ እነርሱስ በስንት ክፍል ቢበልጡት ነው ደብዳቤ ለመጻፍ የበቁት? አንድ ተማሪ ስንተኛ ክፍል ላይ ሆኖ ነው የፍቅር ደብዳቤ መጻፍ የሚጀምረው? የሚል ጥያቄ ያጭርብናል፡፡
   ሌላው የልብ ወለዱ ዋና ተራኪ ደጀኔ ከእርሱና እርሱን ከመሰሉ እኩዮቹ የዕድሜ  ደረጃ የማይጠበቅ የኑሮ ሀሳብና ጭንቀት ውስጥ ሲወድቅ ፣ስለ ወደፊት ህይወቱ ሲብከነከንና ‹‹ከተማስ ቢሆን? እማራለሁ፡፡ ሥራ እይዛለሁ፡፡ አገባለሁ፡፡ ከሚስቴ ጋር እንሳሳማለን፤ምናልባት እንደንሳለን፤ወይም እስክስታ እንወርዳለን፡፡ ሠርግ ሲኖር እንዘፍናለን፤ለቅሶ ቤት ሄደን ከንፈር እንመጣለን፤ወይ እናለቅሳለን፡፡ ልጆቻችንን እናስተምራለን፡፡ ከዚያ እንሞታለን፡፡›› (ገጽ 57) እያለ ገና ጨዋታ ባልጠገበ ልጅነቱ በምናቡ ባላየውና በማያውቀው የከተማ ኑሮ ውስጥ ተስፋውን ወልዶ ተስፋውን መቅበር ----- አቅሙን ከየት አመጣው? ‹‹…ወንዝ ተራሮችሽ ድንግል መሬትሽ…›› (ገጽ 68) ‹‹እየዘመርን እያለ ምንዳ ከዚያኛው ሠልፍ ተስቦ መጣና ‹ኢትዮጵያ እንደ አሰለፈች ልጃገረድ ነች እንዴ?› ብሎ በጆሮዬ አንሾካሾከብኝና ሣቁ ሲመጣ በእጁ ሸፈነው፡፡›› (ገጽ 69)  በእነርሱ እድሜ ድንግልናንና ልጃገረድነትን ለይተው ለመጫወትና ለማላገጥ እንዴት ደረሱ? ደራሲው በልብወለዱ ውስጥ በቀረጻቸው ገጸ ባህሪያት የልጅነት ጫንቃ ላይ ከባድ የአዋቂነት ሸክም አልጫነባቸውም ወይ? ብለን እንድንጠይቅና የተራኪውንና በዙሪያው የከበቡትን ህጻናት እድሜ ለመጠራጠር መንደርደር ስንጀምር፣ የብስለቱን ምክንያት እንዲህ ያስቀምጥልንና ከጥያቄያችን ነጥሎ ወደ ሌላ ጉዳይ እንድንሸጋገር ይጋብዘናል ‹‹ልጅም ሆኜ - እንዲህ ለምን አስባለሁ እል ነበር፤ግን አንዳንዱ ትልቅ ሆኖም አያስብም፤ አንዳንዱ ትንሽ ሆኖ ያስባል፡፡››
   ደጀኔና ፍቅር
  ደጀኔ (የልብ ወለዱ ተራኪ) ከልጅነቱ ጀምሮ ፍቅር አለው፤ ብቻውን የሚወዳት ፣ ማንም እንዲያውቅበት የማይሻው ፍቅር አለው ‹‹ከእኛ ቤት ቀጥሎ የጎረቤታችን የአባባ ገብሬ ቤት አለ፡፡ የአባባ ገብሬን ቤት ሳይ ትዝ የምትለኝ ትርሲት ናት፡፡ የትርሲት ነገር አይሆንልኝም፡፡ ጓደኞቼን ሁሉ ብወድም እንደሷ አይሆኑልኝም፡፡ ግን ማንም አያውቅብኝም፡፡›› (ገጽ 12) ትርሲትም ትወደዋለች ፤ ታዲያ ለተራኪው በምድር ላይ ትልቁ ነገር ፍቅር ይመስላል፣ለትምህርት ሀገር ሲለውጥ ከእናቱ አብልጦ የሚያስብላት ሴት አለች፣ በችግር ውስጥ ሆኖ የሚያስባት ሴት አለች፣ውትድርናም ሄዶ የሚያስባት ሴት ነች፤ በተራኪው ደጀኔ ህይወት ላይ ከሀገርም ከእናቱም በላይ ነጻነቱም ሆነ ደስታው የሚታየው በተቃራኒ ጾታ ላይ የሚያሳድረው ፍላጎትና የሚሰጠው ትኩረት በመሆኑ፣ ‹‹ትርሲትን ማግባት አለብኝ፡፡ ግን ትርሲትን ለማግባት ደግሞ ጠንክሮ መማር የግድ ነው፡፡ ቹቹ እንዳለው ዋጋም የለን፡፡ በሙሉ ልብ መማር የሚቻልበት ዘመን አይደለም፡፡›› (ገጽ 127) እንዲህ የሚያስብላትንና እሷም በደብዳቤዋ‹‹ ያለ እርሱ መኖር የማልችል ሰው አለኝ›› ብላ የመሰከረችለትን ትርሲትን፣ለወደፊት ተስፋው ግብአት የሆነችውን ትርሲትን፣ ከምንም በላይ ሲያስባትና ሲያስብላት የኖረችውን ትርሲት ትቶ ሙሉ ከተባለችው ሴት ጋር አንሶላ እስከመጋፈፍ ያደረሰው ምን ይሆን? እጣ ፈንታውስ ገላዋን ከቀመሳት ሙሉ ወይስ በጠረንዋ ብቻ ከሚደሰትባት ትርሲት ይሆን?  እንደኔ እንደኔ ፍቅርና ናፍቆት ደጀኔ ለሰነቀው ተስፋ፣የልጅነት ቅርፊታቸው ቀስ እያለ የተላጠላቸው የልብ ወለዱ ዋና አስኳሎች ናቸው፡፡
   ክፍል ሁለት - ውትድርና
     ይህ ክፍል በስምንት ምዕራፎች የተወሰነና ደራሲው በመግቢያው ላይ እንደጠቀሰው፤‹‹…ከፊል ዘመኖቼን ያሰብኩበት ብሔራዊ ውትድርናና የብላቴውን የከፍተኛ ትምህርት፣ የሀገሪቱን ምስቅልቅል፣…በሌላ በኩል ደግሞ የቀዳሚዎቹን ዘመነኞች ጡንቻማ ፍልሚያ ወላፈን ከሕጻናት ሕይወት ጋር እጅ ለእጅ ለማጨባበጥና ለማስታወስ ፈዛዛ ምስሎች በትንሷ ኪሴ ወሽቄያለሁ፡፡›› ሲል በዚህ ድርሰት ውስጥ ቀደም ብዬ እንደገለጽኩት አንባቢ ስለ ትርሲት ደብዳቤ ጠንካራነት፣ ስለ ሙሉ የማይገታ ፍቅር ይረዳ እንደሁ እንጂ ደራሲው በሀገር ጉዳይ እንደ አንድ ተማሪ ወታደር አብዝቶ ሲብከነከን አይስተዋልም፤ ስለ ፍቅር ግን ሙሉ ጊዜውን ሰጥቶ ያስባል፤ ይጨነቃል፡፡ አሁን እነዛ ሁሉ የአበባ ወራቶች አልፈዋል፣የልጅነት ጊዜያት ትዝታዎች አልፈው የቀሩት  የፍቅር ህይወቱ መቋጫና መደምደሚያን ሴት መምረጫ ጊዜው ናቸው፣ዕድል ከማን ታላትመው ወይም ከማን ታስተቃቅፈው ይሆን?
ደረጀ በላይነህ ከዚህ በፊት በአጫጭር ልብወለድ ላይ ትኩረቱን በማድረጉና ረጅም ልብ ወለድ የመጀመሪያው በመሆኑ ትንፋሽ ያጥረው ይሆን? የሚል ስጋት አድሮብኝ ነበር፡፡
ሆኖም አንብቤ ስጨርስ ስጋቴ ከንቱ እንደነበር ተገነዘብኩ፡፡ ይልቁንም የደረጀን “የደመና ሳቆች” በተለይ ልጅነትን አጉልቶ ከማሳየት አንጻር ከእነ አዳም ረታ (ግራጫ ቃጭሎች)፣ ከእነ አለማየሁ ገላጋይ (የብርሃን ፈለጎች) ተርታ ልመድበው አስገድዶኛል፡፡ እናንተስ? አንብቡትና ፍርዳችሁን ስጡ፡፡

Read 3656 times