Saturday, 23 April 2016 10:12

በዘውዲቱ ሆስፒታል የእንቅርት ታካሚዋ ለሃሞት ጠጠር ህክምና ሆዷ ተከፈተ

Written by  መታሰቢያ ካሣዬ
Rate this item
(34 votes)

- የህክምና ስህተቱን የፈፀሙት ሃኪም ከሥራ ተባረዋል
- “የሃሞት ጠጠሩ በነፃ ስለወጣልሽ ዕድለኛ ነሽ” ሲሉ ዋሽተዋታል

   በዘውዲቱ ሪፈራል ሆስፒታል ውስጥ በተፈፀመ የህክምና ስህተት ሣቢያ እንቅርት ለማስወጣት የሄደችው ታካሚ በስመ ሞክሼ በተፈጠረ ስህተት ለሃሞት ጠጠር ህክምና ሆዷ ተከፈተ። ታካሚዋ ከሁለት ዓመታት ወረፋ ጥበቃ በኋላ ተራዋ ደርሶ በአንገቷ ላይ የወጣውን እንቅርት ለማስወጣት ነበር ወደ ሆስፒታሉ የሄደችው፡፡
ሠላም ደሞዜ የተባለችው ታካሚ በአንገቷ ላይ የወጣውን እንቅርት ለማስወጣት አስፈላጊውን ምርመራ አድርጋ በሆስፒታሉ አልጋ ትይዛለች። በሌላ በኩል ሰላም ኪሮስ የተባለች ታካሚ ደግሞ ለሃሞት ከረጢት ጠጠር ህክምና ወረፋ ጠብቃ ቀጠሮዋ በመድረሱ ነበር ወደ ሆስፒታሉ ያመራችው፡፡ ወጣቷ በቀዶ ህክምና ከህመሟ ለመፈወስ አስፈላጊውን ምርመራ አከናውና በተመሳሳይ ክፍል ውስጥ እንድተኛ ይደረጋል፡፡
ባለፈው ረቡዕ ሁለቱም ህሙማን የቀዶ ህክምና ሊደረግላቸው ቀጠሮ ተይዞላቸው ሲጠባበቁ ከቆዩ በኋላ ለእንቅርት ህክምና ወደ ሆስፒታሉ ያመራችው ሰላም ደሞዜ በቅድሚያ ወደ ቀዶ ህክምናው ክፍል ትገባለች። የእንቅርት ታካሚዋ በቀዶ ህክምናው ክፍል ከገባች በኋላ ለሃሞት ከረጢት ጠጠር ህክምና ሆዷ ይከፈታል፡፡ ይሁን እንጂ በታካሚዋ ሃሞት ውስጥ ለቀዶ ህክምና የሚያበቃ ችግር አለመኖሩን ያስተዋሉት የቀዶ ህክምና ባለሙያው፤ ሆዷን መልሰው በመዝጋት የእንቅርት ማውጣት ህክምናውን ያደርጉላታል፡፡
ጉዳዩ ከፍተኛ መደናገጥ የፈጠረባቸው ሃኪሙ፤ በወቅቱ ስለተፈፀመው ሁኔታ አንዳችም ነገር ሳይናገሩ የቀዶ ህክምና ክፍሉን ለቀው ይወጣሉ። ከስፍራው ያገኘናቸው ምንጮች እንደገለፁልን፤ የሀኪሙ ረዳቶችና በስፍራው የነበሩ የህክምና ባለሙያዎች ችግሩን ለመሸፈንና የተፈጠረውን ስህተት ለመደበቅ ከፍተኛ ጥረት ያደረጉ ሲሆን፤ ታማሚዋ ለእንቅርት ቀዶ ህክምና ወደ ሆስፒታሉ ቢመጡም የሃሞት ከረጢት ጠጠር ችግር ስለተገኘባቸው ህክምናው በነፃ እንደተደረገላቸውና በዚህም ዕድለኛ እንደሆኑ በመንገር ቤተሰቦቻቸውን ለማሳመን ጥረት አድርገዋል ተብሏል፡፡ ሁኔታው ያልተዋጠላቸው የታማሚዋ ቤተሰቦች ቀደም ሲል ምንም ዓይነት የህመም ምልክት ባልታየበት፣ ምርመራና ቅድመ ህክምና ባልተደረገበት ሁኔታ በድንገት ለሃሞት ጠጠር ቀዶ ህክምና የሚያበቃ ችግር ሊፈጠር አይችልም በሚል ከሆስፒታሉ አስተዳደርና ከህክምና ባለሙያዎቹ ጋር ውዝግብ ይፈጥራሉ፡፡ ጉዳዩ የሆስፒታሉ አስተዳደር  ኃላፊዎች ጋር ደርሶም እንዲጣራ ከተደረገ በኋላ ትልቅ የህክምና ስህተት መፈጠሩ ታምኖበት፣ የህክምና ባለሙያዎቹና አስተዳደሩ ቤተሰቦቿን ይቅርታ በመጠየቅ ለታካሚዋ የቅርብ የህክምና ክትትል እንዲደረግላት የተወሰነ ሲሆን የቀዶ ህክምና ባለሙያውና ረዳቶቹ ላይ እርምጃ ተወስዷል፡፡
በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ እንዲሰጡን የጠየቅናቸው የዘውዲቱ ሪፈራል ሆስፒታል ዋና ሥራ አስኪያጅ ዶ/ር ተረፈ አሰፋ፤ የህክምና ስህተቱ መፈፀሙን አምነው ስህተቱ የተፈፀመው በወቅቱ የቀዶ ህክምናውን ያደረጉት ሃኪምና ረዳቶቻቸው ታካሚዋ በትክክል የመጣችው ምን ዓይነት ህክምና ልትፈጽም መሆኑንና ሌሎች ሁኔታዎችን በአግባቡ ሳያረጋግጡ ህክምናውን በመጀመራቸው ነው ብለዋል፡፡
አንድ ሰው የቀዶ ህክምና ከማድረጉ በፊት በአግባቡ ሊደረግ የሚገባው “ሰርጂካል ሴፍቲ ቼክ ሊስት” መኖሩን የጠቆሙት ዶ/ር ተረፈ፤ በዚህች ወጣት ታካሚ ላይ ይህ ጥንቃቄ ሳይደረግ በመቅረቱ ስህተቱ መከሰቱን አስረድተዋል፡፡
የስህተቱ መፈፀም ሳያንስ በወቅቱ ስህተቱ አምኖና ስለ ሁኔታው ለቤተሰቦቿ ትክክለኛ መረጃ ሰጥቶ ይቅርታ መጠየቅ ተገቢ የነበረ ቢሆንም ይህም አለመደረጉን ሥራ አስኪያጁ ገልፀዋል፡፡
“አሁን ታካሚዋ ለህይወቷ የሚያሰጋት ምንም አይነት ችግር የሌለባት መሆኑ በህክምና ባለሙያዎች በሚገባ ስለተረጋገጠ ስለጉዳዩ ለቤተሰቦቿ በቂ መረጃ በመስጠት ይቅርታ ጠይቀናቸዋል፡፡ ታማሚዋ ግን ከሆስፒታሉ እንድትወጣ በሃኪሞቿ ቢፈቀድላትም ሁለት ቀዶ ህክምና በማድረጓ በቅርብ ሆና የጤናዋን ሁኔታ እንድንከታተላት ስለፈለግን አሁንም በሆስፒታሉ ውስጥ ትገኛለች፡፡ የጤናዋ ሁኔታ ግን በጣም ጥሩ ነው” ብለዋል - ዶ/ር ተረፈ አሰፋ፡፡ ስህተቱን የፈፀሙት የቀዶ ጥገና ሃኪም በኮንትራት የተቀጠሩ መሆናቸውን ያመለከቱት የሆስፒታሉ ስራ አስኪያጅ፤ ከሥራና ከደመወዝ እንዲታገዱ በማድረግ የዲሲፕሊን እርምጃ እንዲወሰድባቸው ጉዳዩን ለሚመለከተው አካል ማስተላለፋቸውን ተናግረዋል፡፡
ትልቁ ስህተት የቀዶ ሃኪሙ ቢሆንም ሥራው ላይ የተሳተፉት የሀኪሙ ረዳቶችም ከተጠያቂነት ሊያመልጡ እንደማይችሉ ጠቁመው እነሱም የዲሲፕሊን እርምጃ ተወስዶባቸዋል ብለዋል - ዶ/ር ተረፈ፡፡  


Read 11253 times