Saturday, 23 April 2016 10:33

ደራስያን እንደ አባት ሲፈተሹ...

Written by  ዓለማየሁ ገላጋይ
Rate this item
(3 votes)

እንደ ውስጥ ደዌ ጤና የሚነሳ “ታሪክ” አለ፤ እንደ ግርፋት ገላ የሚሸነትር፤ በመጠቃት ልብ የሚመትር። የበዓሉ ግርማን ቅንጫቢ ታሪክ ከአንድ አዛውንት ጓደኛው የሰማሁ ቀን እንደ ያዕቆብ እግዚአብሔርን “ካልባረከኝ” ሳይሆን “ካልነገርከኝ አለቅህም!” ብዬዋለሁ፡፡ ለምን? ለምን? ለምን እንዲህ አደረከን? ስል ተሟግቼዋለሁ፡፡ መቼም ከእርሱ በላይ ማንም የለ!
… ያንን ሸንታሪ የበዓሉን ቅንጫቢ ታሪክ እንዳለጌታ ከበደ አጭር ልቦለድ አድርጎ “ፅላሎት” የተሰኘ መፅሐፉ ውስጥ አካትቶ አንብቤዋለሁ፡፡ ያኔ እንዳለጌታ በታሪኩ እውነትነት ላይ እምነት ስላጣ ወደ ልቦለድነት የቀየረው መስሎኝ ነበር፡፡ ነገር ግን አሁን በቅርቡ ያሳተመው “በዓሉ ግርማ - ህይወትና ሥራዎቹ” ውስጥ አካትቶት ድጋሚ አነበብኩት። ድጋሚ ታመምኩ፤ ድጋሚ ፈጣሪን “ለምን ተውከን?” ብዬ መጠየቅ አሰኘኝ፤ ለምን ለመሰቀልና ለመወገር ብቻ ትፈጥራለህ? …
ታሪኩ እንዲህ ነው ….
…. በዓሉ ግርማ “ደርግ” ከተባለ “ዛር” ጋር ተጣልቶ፣ ተጠልቶ በመንፈስ ደዌ ተይዟል፡፡ የሚሄድበት ሁሉ የሚከተሉት መልአከ ሞት መሰል ጠባቂዎች ተመድቦበታል፡፡ በዓሉ “ያዳቆነው” ደርግ “ሳያቀስ” እንደማይለቀው ቢገባውም ከመሸሽና ከመደበቅ ይልቅ፤ የበለጠ ለእይታ ይጋለጥ ጀመር። ቀን በብርሃን ብቻ ሳይሆን ሌት በጨለማም እጅግ ዘግይቶ ቤት ይገባል፡፡
አደጋ ላይ መሆኑን የሚያውቁ ወዳጆቹ ስጋት ተጠናወታቸው፡፡ “ምን ይሻላል?” ተባባሉ፡፡ በተለይ መዲና ግሮሰሪ ለረጅም ጊዜ በዓሉንና ጓደኞቹን በማስተናገዱ ወዳጅነት የፈጠረው መሐመድ በሁኔታው ግራ ተጋብቷል፡፡ ብቻውን መብሰክሰኩ አላዋጣ ቢለው አንድ የበዓሉ የቅርብ ወዳጅ ጋ ቀርቦ አቤቱታ አቀረበ፡፡
“ምንድነው?” አሉ አቤቱታው የቀረበላቸው አስፋው ዳምጤ፡፡
“የበዓሉ ነገር ነው” አለ መሐመድ፡፡
“ምን ሆነ?”
“ምን ይሆናል፤ ብቻ እዚህ እስከ እኩለ ሌሊት ያመሻል፤ ምናለ በጊዜ ወደ ቤቱ ቢሄድ? ያለበትን ሁኔታ እያወቀው …”
ጋሽ አስፋው በዓሉን በመሐመድ አንደበት ወቀሱት፡፡
በዓሉ ወቀሳውን ሰምቶ ዝም አለ፤ ተከዘ፡፡
“ተናገራ! ለምን ታመሻለህ?”
“ነገሩ ወዲህ ነው” አለ በዓሉ፡፡ ከዚህ በኋላ የተናገረውን ከእንዳለጌታ መፅሐፍ ላይ ልተርከው፡- “አሳዳጆቼ ቤተሰቦቼ ፊት፣ ልጆቼ ፊት፣ ደሜን እንዲያፈሱት አልፈልግም፡፡ …. ልጆቼ ፊት እርምጃ የተወሰደብኝ እለት ነው መልሰው መላልሰው እንደገደሉኝ የሚሰማኝ … የትም ልሙት … የሞቴን ፅዋ ግን ልጆቼ ፊት አልጨልጣትም፡፡ የትም ልሙት፣ እነሱ (ልጆቼ) ፊት እንዳይገድሉኝ ብዬ ነው እዚህ ዝግጁ ሆኜ የምጠብቃቸው …” (ገፅ 425)
እንደ ውስጥ ደዌ ጤና የሚነሳ “ታሪክ” ነው። በዓሉ “ይቺ ፅዋ ከእኔ ትለፍ” ማለት እንዳልቻለ ገብቶታል። “መስቀሉ” ከፊቱ እንደተዘጋጀችም ተረድቶታል፡፡ በተስፋ መቁረጥ የጠየቀው ትንሽ ነገር ሞቱ በልጆቹ ፊት እንዳይሆን ነው፡፡ ግን ያ ምኞቱ ባይሳካ፣ ወይም እንዲሳካ በማምሸትና ማምሻውን ቦታ ባይቀያይር ኖሮ፣ ልጆቹ አሁን ባሉበት ሁኔታና ጤና ባልተገኙ ነበር፡፡ በዓሉ መጥፋት እየቻለ ያልሞከረው ለልጆቹና ለቤተሰቡ ሥጋት ስለገባው ሳይሆን አይቀርም፡፡ ልጓማችን ምንድነው? ማበቻችን ያለው የት ነው? እንደምን ሰው ሞቱ ቀርባ ሳለ አይሸሻትም? ስቃዩን አያመልጣትም? …. ይሄኔ ነው ፈጣሪን “ካልነገርከኝ አለቅህም” ማለት፡፡
እንደ በዓሉ ግርማ በልጆቹ የታበተች አንድ የገጠር እናት ጭቆናና ስቃይ ቢበዛበት እንዲህ ስትል ገጠመች አሉ፡-
“ልጅ ማሰሪያው፣ ልጅ ገመዱ፣
ጎጆማ ምን ይላል ዘግተውት ቢሄዱ፤”
ልጅ ማሰሪያ ነው፤ ልጅ ገመድ ነው፤ ሌላው ሌላው ትርፍ ነው፡፡ “ጎጆ” (ትዳር) እንኳን ጣጥለውት ለመሄድ የሚያዳግት ተፈጥሯዊ ማሰሪያነት የለውም። ልጅን፣ ትውልድን በተመለከተ ተፈጥሮ አምባገነን ናት፡፡ ህጓ የማይታለፍ፣ ቅጣቷ የማይዛነፍ ነው፤ ግን ስውር ህግ፣ ድብቅ ቅጣት …
… ፈረንሳዊው Victor Hugo በ1837 ዓ.ም አንድ የፃፈው ግጥም አለው፡፡ “my thoughts”  ይለዋል። የልጅ መታሰሪያውን፣ የልጅ ገመዱን… እንቆንጥር፡-
My thoughts?
Far from the roof
Sheltering you, my thoughts
Are of you my children, and the hopes
that lie in you, my summer days
….
ሀሳቤ?
ከክዳን ቆርቆሮው ከሰቀላው በላይ
እንዲያ ወደ ሰማይ
ከችግር፣ ችጋር ጠል
እናንተን ሊጠልል
እናንተን ፣ ልጆቼን፣ እና ተስፋዎቼን
ፀደይ ብራ ቀኔን ፀናሽ ወላጆቼን፡፡
ሁጎ እና በዓሉ የታበቱበት “ዘለበት” አንድ ነው፡፡ እወዲያ ሥጋት አለ፤ ሐሳብ ተዳብሎታል፡፡ እወዲህ በልጆች ተስፋ ማድረግና ሐሴት ማግኘት ጣምራ ሆነው ቆመዋል፡፡ የሁጎ ባለ ስድስት አንጓ ግጥም መላልሶ የሚደቀድቀው እነዚህን ጥንድ መንቶ ያልተረጋገጡ ማበቻ ግዶች ነው፡፡ ሁጎ ልጆቹ ሲስቁ ይሰጋል፤ ሲያለቅሱ ይመናተላል፤ መጨነቅ መጠበብ የአባትነት ዕጣው ይሆናል፡፡ እነዚህ ተጠራቅመው የበዓሉን ግድ ይሆናሉ፡፡ ሰውነትን ወደ ልጆች ከለላነት መቀየር፡፡
የልጅ ፍቅር አቅል ነስቷቸው “ከለላነታቸው” ቅጥ የሚያጣ አባቶችም አሉ፡፡ ሁሉን ለልጆቻቸው የሚደነግጉ፣ ከልምዳቸው ተነስተው የልጁን ህይወት በድምዳሜ የሚያሳርጉ አባቶችም አሉ። አሜሪካዊው ደራሲ ኤርነስት ሔሚንግዌይ ለዚህ ምሳሌነት ቢጠቅስ ግብሩ የተሟላ ይሆናል፡፡ ሔሚንግዌይ በ1931 ዓ.ም ጀርመን በርሊን ውስጥ ሆኖ ያየውን ስለጠላ፣ ለአንድ ልጁ እንዲህ ሲል ፃፈ፡-
Never trust a white man
Never kill Jew
Never sign a contract,    
Never rent a pew.
Don’t enlist in armies;
Nor marry many wives;
Never write for magazines;
Never scratch your hives.
 ሔሜንግዌይን ልጅ እንደ ዛር ተጠናውቶ አስጓራው እንጂ እሱስ እንዲህ በብዕር የሚባትል አልነበረም፡፡ የልጁ ነጮችን አለማመን፣ ፅዮናውያንን አለመግደል፣ መቀመጫውን አለማከራየት፣ ብዙ ሴት አለማግባት፣ ለመጽሔት አለመፃፍ የመሳሰሉት አሳስቦት በብዕር ጐራዴ የሚያስፎክረው ኖሯል። ለዚህ የእኛ አባቶች ምሳሌ አያጡለትም፡፡ “ልጅ ያለ ልጅ አከለ” የሚል፡፡ አንዳንድ አባት ደግሞ አለ፤ ልጅ እና የዓላማ አጋር የተምታታበት፡፡ Groucho marx ለዚህ ልከኛ አብራሔ ነው፡፡ ለልጁ ለአርተር የፃፋቸው ደብዳቤዎች ሁሉ ኮሚኒስታዊ ኾምጣጣነት የተሞሉ ነበሩ፡፡ እንደውም ወደ መጨረሻ ሰሞን ልጁን “ጓድ አርተር” እያለ መጥራት ጀምሮ ነበር አሉ፡፡ የተፈጥሮ ማበቻው እንዲህ ላያስርቅ የሚያስጉዝ መሆኑ አይደንቅም፡፡
የአባት ማሰሪያው፣ የአባት ገመዱ ልጁን “የእኔ” ብሎ ማሰቡ ነው፡፡ አንዳንድ ምሁራን ይሄ ልጁን “የእኔ” ብሎ ማሰብ የተፈጥሮ ግዳጅ ሳይሆን የማህበራዊ ኑሮ ማሳለጫ ዘዴ የጫነበት ግዱ ነው ይላሉ፡፡ ለምሳሌ ዶክተር ማርጋሬት ሚድ እንዲህ ያለ አቋም አላት፡-
“አባትነት ከተፈጥሮ የተቸረ ሳይሆን አብሮ ለመኖር ስለሚበጅ በሴቶች የተፈጠረ ዘዴ ነው” ትላለች፡፡ ጥንታዊው ወንድ ዘላን ነበር አሉ፡፡ በጊዜ ሂደት ግን በእናቶች ሥልጠና ይሰጠው ጀመር፡፡ አንድ ወንድ ልጅ ለማኅበራዊ ግልጋሎት ዕድሜው ሲደርስ ሴቶችንና ልጆቻቸውን የመመገብ ግዴታ እንዲገባ የሚያደርግ ይሄ ግዴታ በብዙ ወንዶች ኩብለላ የተነሳ ሊሳካ ባለመቻሉ ሌላ ዘዴ አስፈለገ። በመሆኑም ወንዶች “የእኔ” የሚሉት ሴት እና ልጆችን መመደብ፡፡ “ትዳር” ልንለው እንችላለን፡፡ በዚህ ዘዴ ወንድ “አባት” መባል ጀመረ፤ ከእናቶች ጋርም “እሹሩሩን” ዘፈነ፡፡
አባትነት የተፈጥሮ ሆነ የልምድ (by nature of nurture) ውጤት የልጅን ግፊት ሲቋቋሙ የሚታዩ ወንዶች በታሪክ ተከስተዋል፡፡ ለዚህ ምሳሌ የምናደርጋቸው የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ በላይ ዘለቀ ናቸው፡፡ ጣሊያንን ላይ ታች እያሉ ቢያንገበግቡት ልጃቸውን ሻሼን ያዘ፡፡ “ልጅህን ልሰቅላት ነው፣ እጅህን ስጥ” አላቸው፡፡ የበላይ ምላሽ ከበዓሉ ይለያል፡፡ “ከሀገር ማን ይበልጣል? ልጄን ከሀገሬ አላስበልጥም” ጣሊያን እንደፎከረው አላደረገም፡፡ ቢያደርግስ እውነትም ከሀገር ማን ይበልጣል?
(ልብ በሉ!) “ሀገር” እንጂ “ሥልጣን” አላልኩም። ስለዚህ የበላይ ዘለቀን ከኰሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም ታሪክ ጋር ማዛነቅ ተገቢነት የለውም ማለት ነው፡፡ ኰሎኔሉ ገና በአፍላ የሥልጣን ዘመናቸው አደረጉት የተባለው ከበዓሉ ግርማ ውሳኔ ጋር ፍፁም በተፃራሪ የሚቆም ነበር፡፡ ኮሎኔል መንግሥቱን ከፊታቸው ገለል እንዲሉላቸው ብቻ አዲስ አበባ የላኳቸው አለቆቻቸው ነገሮች እንዳሰቡት ሳይሆኑ መቅረታቸው ሃሳብ ላይ ጣላቸው አሉ፡፡ ስለዚህ ኮሎኔሉ ወደ እናት ክፍላቸው እንዲመለሱ ጠየቁ፤ አልሆነም፡፡ ደብዳቤ ፃፉ፣ መልስ አላገኙም፤ በመሆኑም እዚያው ሐረር የቀሩ የኮሎኔሉን ቤተሰቦች አግተው፣ ኮሎኔሉ ወደ ሐረር ካልተመለሱ እንደሚፈጇቸው ዛቱ፡፡ ኮሎኔሉ መወላወል አልታየባቸውም፡፡ ሌላው ቀርቶ የጨቅላዎቹን ልጆቻቸውን መጥፎ ዕጣ - ፈንታ መልሰው መላልሰው ለማሰብ ጊዜ አልሰጡም፡፡ ወዲያውኑ ምላሻቸውን አሳወቁ፡፡
“ቀቅላችሁ ብሏቸው!”
አጥፊና ጠፊነት እዚች ጋ ድንበሯን ታኖራለች። “አጥፊው” የቆረጠውን ያህል “ጠፊው” ልቡ ቢደነድን ኖሮ ዛሬ በዓሉ ግርማ በህይወት ይኖር ነበር፡፡ ቤተሰቦቹ ግን እንጃ! እናስ? የተፈጥሮን ሆነ የማህበራዊ ኑሮ ድንጋጌን የተቀበለ፤ ልቡን ወለል አድርጐ የከፈተ፣ ርህራሄን ትልሙ ያደረገ የልበድንጋይ ጭዳ መሆኑ አይቆጭም? ከፈጣሪ ጋር አያሟግትም? ሳትነግረኝ አለቅህም አያሰኝም?


Read 1445 times