Saturday, 23 April 2016 10:45

የዛምቢያ 13 ተቃዋሚ ፓርቲዎች ለገዢው ፓርቲ ድምጻቸውን እንደሚሰጡ ገለጹ

Written by 
Rate this item
(2 votes)

  - ገዢው ፓርቲ የጀመረውን ልማት እንዲቀጥል እንፈልጋለን ብለዋል
     በመጪው ነሃሴ ወር አገር አቀፍ ምርጫ ለማካሄድ በመዘጋጀት ላይ ባለቺው ዛምቢያ የሚንቀሳቀሱ 13 ተቃዋሚ ፓርቲዎች በምርጫው ገዢው ፓርቲ ወክለው ለሚወዳደሩት የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ኤድጋር ሉንጉ ድምጻቸውን እንደሚሰጡ መግለጻቸውን ኒውስዊክ ዘገበ፡፡
በተናጠል ይንቀሳቀሱ የነበሩት 13 አነስተኛ የአገሪቱ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ናሽናል ኦፖዚሽን አሊያንስ በሚል ጥምረት ፈጥረው በጋራ እየሰሩ እንደሚገኙ ያስታወሰው ዘገባው፣ ጥምረቱ ሰሞኑን በሰጠው መግለጫ በመጪው ምርጫ ለፕሬዚዳንቱ ድምጹን እንደሚሰጥ አስታውቋል፡፡
የጥምረቱ አባላት የሆኑ የአገሪቱ ተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮችም፣ ጥምረቱ በምርጫው ተሳትፎ የምክር ቤት አባል በመሆን ከገዢው ፓርቲ ጋር ተስማምቶ የፖለቲካ እንቅስቃሴውን እንደሚቀጥል ጠቁመው፣ የአባል ፓርቲዎቹ የግል መርሆዎች ግን ተጠብቀው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል፡፡
ኤድዊን ሳካላ የተባሉት የተቃዋሚ ፓርቲ መሪ ጥምረቱ ገዢው ፓርቲ የጀመራቸውን የልማት ፕሮጀክቶች ተፈጻሚ ማድረጉን እንደሚደግፍ በመጠቆም፣ በመሆኑም ለፓርቲው መሪ የምርጫ ድምጹን እንደሚሰጥ አቋም መያዙን ተናግረዋል፡፡

Read 1335 times