Saturday, 30 April 2016 11:28

ግራንድ ኢንኩዊዚተሩ

Written by  ፀሀፊ ፦ ፊዮዶር ዶስቶቭስኪ ተርጓሚ ፦ አሸናፊ አሰፋ
Rate this item
(4 votes)

(የመጨረሻ ክፍል)
“አንተው ነህ ለመንግስትህ ውድመት መንገዱን ያበጀኸው! ለዚህም ማንም አይወቀስም፤ አንተ እንጂ። ይህም ይሁን፤ ምን ነበር ግን ተሰጥቶኽ የነበረው? ሦስት ሀይሎች አሉ፣ በምድር ላይ ሦስት ልዩ ሀይሎች አሉ፤ እነዚህን ሰዎች የሚባሉ አማጺ ፍጡራንን ህሊና ሊያማልሉ የሚችሉ ሀይሎች ናቸው፤ እነዚህም ሀይሎች፦ ተአምር፣ ምስጢርና ስልጣን ናቸው። አንተ ሦስቱንም አልፈልግም አልክ፤ እንዲያ በማድረግም ለሰዎች ቀዳሚ ምሳሌ ሆንክላቸው። መራራውና ሁሉን አዋቂው መንፈስ አንተን የቤተመቅድስ ጫፍ ላይ አቁሞህ፦ “መላእክቱን ስለ አንተ ያዝልሀል፣ እግርህንም በድንጋይ ከቶ እንዳትሰናከል በእጃቸው ያነሱሃል፤ ተብሎ ተጽፎአልና የእግዚአብሔር ልጅስ ከሆንህ ራስህን ወርውር።” አለህ። እንዲያ ብታደርግ ኖሮ በአባትህ ላይ ያለህ እምነት በተረጋገጠ ነበር፤ አንተ ግን ያለውን አልተቀበልክም፣ ጥያቄውንም አልተገበርኽም። አቤት! እዚህ ጋ ያላንዳች ጥርጥር በታላቅ አምላካዊ ክብር ነው ክብርህን የጠበቅኸው! ግን እነዚህ ሰዎች፣ እነዚህ ደካማና አመፀኛ ፍጡራን እምቢታህን ሊረዱ የሚችሉበት አምላካዊ ብቃት አላቸውን? ሰዎች አማልክት ናቸውን? ግልፅ ነው አንተ ሁሉን ጠንቅቀህ ታውቅ ነበር፦ በዚያች ቅጽበት አንዲት እርምጃ ብትወስድ ኖሮ፣ ራስህን ወደታች ለመወርወር የሰውነትህን አንዲት ቅንጣት አንቀሳቅሰህ ቢሆን ኖሮ በዚያችኑ ቅጽበት “ጌታ አምላክህን” ትፈታተነው ነበር፣ በሱ ላይ ያለኽን እምነት በሙሉ ታጣ ነበር፤ ልታድናት የመጣኸው ምድር ላይ ተፈጥፍጠኽ የአፈር ብናኝ ትሆን ነበር፤ የሚፈትንህ ብልህ መንፈስ ባለድል እንዲሆንና እንዲፈነጥዝ አልፈቀድኽም። ሰዎች እንደ አንተ እንዲህ አይነት ፈተና ለመቋቋም የሚያስችል ጥንካሬ አላቸው ብለህ ለአፍታ አስበህ ታውቃለህ? ሰው ተፈጥሮው፣ ስሪቱና ቀመሩ እንዴት ነው? እጅግ ወሳኝ በሆነ የህይወቱ ቅጽበት፣ ህመም የሚፈጥሩና አወዛጋቢ ችግሮች ነፍሱን አሰጨንቀዋት ባሉበት ጊዜ ተአምርን ችላ ብሎ የልቡን ነፃ ስሜት እንዲያደምጥና እንዲከተል ተደርጐ ነው ሰው የተዋቀረው? አቤት! ይኽ የአንተ ድርጊት በመፅሐፍ እንደሚመዘገብና ለሚቀጥሉት ዘመናት በአለም ጥግ ሁሉ እንደሚደርስ ጠንቅቀህ ታውቅ ነበር፤ ሰው የአንተን ምሳሌ በመከተል እግዚአብሔርን እንደአመነ እንዲኖር ነበር የፈለግኸው፣ እምነቱን ለማደስ ተአምራት ሳያስፈልጉት ሁሌም እምነቱን ይዞ፣ በእምነት ፀንቶ እንዲቆይ ነው ተስፋ ያደረግኸው። ሰው ግን ተአምራትን ሲተው ያኔውኑ እግዚአብሔርንም እንደሚተው አላወቅህም። ሰው እግዚአብሔርን ከሚፈልገው በላይ ከእሱ “ምልክት” ይፈልጋል። ሰው ያለተአምራት መቆየት አይችልም፤  የፈለገው መቶ ጊዜ ያህል አመፀኛ፣ መናፍቅና ኢአማኒ እንኳን ቢሆን ያለ ተአምራት ከሚኖር የራሱን ተአምራት ይፈጥራል፤ አስማተኞችን፣ ጠንቋዮችንና ስራዎቻቸውን ማምለክ ይጀምራል። መስቀል ላይ ሳለህ ሰዎች እያላገጡና ራሳቸውን እየነቀነቁ፦ “ራስህን አድን የእግዚአብሔር ልጅስ ከሆንህ፣ ያኔ በአንተ እናምናለን” ሲሉህ ከመስቀል ላለመውረድ የፀናኸውም በዚሁ ስሌት ነው፤ ሰዎችን በተአምር ልትገዛቸው፣ የተአምር ባሪያ ልታደርጋቸው አልፈለግህም፤ ሰዎች ያላንዳች ተአምር በነፃ ፈቃዳቸው እንዲከተሉህ ነው የፈለግኸው። የተጠማኸው ነፃና ተፅእኖ የሌለበትን ፍቅራቸውን ነው፤ ባሪያዎች ለጌቶቻቸው የሚሰጡትን በወራዳ ስሜት የተጨማለቀ አድናቆትና ፍቅር አልፈለግህም። አሁንም ሰዎችን ከአቅማቸው በላይ ከባድ ግምት ነው የሰጠኻቸው፣ ሰዎች አማፂ ቢሆኑም እንኳ ባሪያዎች ናቸው። በቃ። እነሆ! አስራ አምስት ክፍለ ዘመናት አለፉ! እስኪ አሁን ዳግም መዝናቸው! እስኪ ወደ አንተ ደረጃ ከፍ ስታደርጋቸው የነበሩትን ሰዎች እያቸው! ሰው አንተ እንደምትጠብቀው ሳይሆን ደካማና ወራዳ ፍጡር እንደሆነ እምላለሁ። አንተ አደረግኸው የተባለውን ማድረግ ይችላልን? እጅግ ከሚገባው በላይ ክብር ስለሰጠኸው በልብህ ለሰው ፍቅር የሌለህ ይመስል ሁሉ ነበር፣ ምክንያቱም እጅግ ከፍ አድርገኽ ስላየኸው ከአቅሙ በላይ የሆነ ነገር ነው የጠበቅኽበት፣ እንዲህ ያደረግኸው ደግሞ አንተ ነህ፣ ከራስኽ በላይ ሰውን የምታፈቅረው አንተ። በቅጡ ብታከብረው ኖሮ፣ ከሰውም የምትጠብቀው በቅጡ ይሆን ነበር፣ ይህ ስለ ፍቅር ይቆጠር ነበር፤ ምክንያቱም ከሰው የአቅሙን ያኽል መጠበቅ ‘ቀንበሩን ልዝብ ሸክሙን ቀላል’ ያደርግለት ነበር። ሰው ደካማና ፈሪ ነው። አሁን በአለም ዙሪያ ሁሉ በኛ ፈቃድና ስልጣን ላይ ቢያምፅና በዚህ አመፅም ኩራት ቢሰማው ምን ይረባል? ይህቺ የተማሪ እርካሽ ኩራትና ተራ አለሁ ባይነት ናት። የህፃናት አመፅ ናት። ህፃናት ተማሪዎች አምፀው አስተማሪያቸውን ከክፍል እንደሚያባርሩት ያለች ቀሽም አመፅ ናት። ጥሬ የህፃን ደስታቸው በአጭር ይቀጫል፤ ለአመፃቸው በከባድ ይከፍላሉ።
“ሰዎች በጅምላ አለም አቀፍ መንግስት ለማቋቋም ሲጥሩ ኖረዋል። ታላላቅ ታሪክ ትተው ያለፉ ታላላቅ መንግስታትም ተቋቁመው ነበር። ሰዎች እንዲህ አይነት ታላላቅ መንግስታት ባቋቋሙ መጠን ደስተኝነትም የዚያኑ ያህል ይሸሻቸው ነበር። ታላቅ ግዛት ያለው መንግስት ማቋቋሙ በተሳካላቸው መጠን የዚያኑ ያህል አንድ የሆነ፣ ሁሉን አቀፍ የአለም መንግስት የማቋቋም አስፈላጊነቱ ይበልጥ እየታያቸው ይመጣ ነበርና። ቲሞርና ገንጂስ ካህንን የመሳሰሉ ታላላቅ ወራሪዎች እንደ ማእበል የምድርን ገፅ አጥለቅልቀው ያን ሁሉ ሕዝብ ሰጥ ለጥ አድርገው ለመግዛት ሞክረዋል። እነዚህ ታላላቅ ወራሪዎች የሰው ልጆች አንድ የመሆን ከፍተኛ ፍላጎት የወለዳቸውና ሳይታወቃቸው ይህንኑ ምኞት ለማሳካት የተነሱ መሳሪዎች ነበሩ። አንተም የተሰጠህን አለም ብትቀበልና የቄሳርን አክሊል ብትደፋ ኖሮ አንድ አለም አቀፍ መንግስት ማቋቋምና ሰላምን ማስፈን ትችል ነበር። ሰዎችን ህሊናቸውን ከማረከና ዳቧቸውን በእጁ ከያዘ ሌላ ማን ሊገዛቸው ይችላል? እኛ የቄሳርን ሰይፍ ወሰድን፣ ያንን በማድረግም አንተን ክደን እሱን ተከተልን። አቤት! ሰዎች የነፃ አስተሳሰባቸውን ውዥንብር መቼ አዩትና፣ የሳይንሳቸውን ውጤት የሚያጭዱበት ጊዜ ይመጣል፣ እርስ በርስ የሚባሉበት ጊዜ ይመጣላቸዋል። … መጨረሻቸው እርስ በርስ መበላላት ይሆናል። ያኔ ግን አውሬው ወደ እኛ ይመጣል፤ … እኛም አውሬው ጀርባ ላይ እንቀመጣለን፤ ዋንጫውንም ከፍ አድርገን እንይዛለን፤ ዋንጫው ላይ ምን እንደምንፅፍበት ታውቃለህ፦ “ምስጢር”፤ ያኔና ያኔ ብቻ ሰላም ይሰፍናል፤ ሰዎችም ደስታን ያገኛሉ። አንተ በተመረጡት ትኮራለህ፤ አንተ ያሉህ የተመረጡት ብቻ ናቸው፣ እኛ ግን ለተቀሩት ሁሉ እፎይታን እናስገኝላቸዋለን። አንተ ለተመረጡት፤ እኛ ለተቀሩት። በዚያም ላይ በአንተ ከተመረጡት ከሀያላኖቹ መሀል አንተን መጠበቅ ታክቷቸው የመንፈሳቸውን ሀይልና የልባቸውን ፍቅር ወደሌላው ካምፕ ያዞሩትና ለማዞር ዝግጁ የሆኑት እጅግ ብዙ ናቸው፤ በመጨረሻም አንተን በመቃወም ሰንደቃቸውን ያነሳሉ። አንተው ነህ ይህንን ሰንደቅ ከፍ ያደረግከው። ከእኛ ጋር ሲሆኑ ሁሉም ሰዎች ደስተኞች ይሆናሉ፤ በአንተ ነፃነት ስር ያደርጉ እንደነበሩት አያምፁም፤ እርስ በርስ አይጨራረሱም። ነፃ የሚሆኑት ነፃነታቸውን እርም ብለው፣ ወዲያ ጥለው ለእኛ ሲገዙ ብቻ እንደሆነ እንነግራቸዋለን። ልክ አይደለንምን? ዋሸን? ልክ እንደሆንን በደንብ ያምናሉ፤ምክንያቱም ያንተ ነፃነት ለምን አይነት ውዝግብና ለምን አይነት ቀንበር እንደዳረጋቸው ያስታውሳሉ። ነፃነት፣ ነፃ አስተሳሰብ፣ ሳይንስ የሚባሉ ነገሮች ወደማይገነዘቧቸው ድንቅ ነገሮችና ወደማይፈቷቸው ችግሮች ይመሯቸዋል። ያኔ አመፀኛና ሀይለኛ የሆኑት ሰዎች እራሳቸውን ያጠፋሉ ፤ አመፀኛ ግን ደግሞ ደካማ የሆኑት ሰዎች እርስ በርሳቸው ይጠፋፋሉ፤ ቀሪዎቹ ደካማና ምስኪን የሆኑት መጥተው እግራችን ስር ይንደባለላሉ፦ “አዎ፣ ልክ ናችሁ፣ ምስጢሩ ያለው እናንተ ጋ ብቻ ነው፤ ወደ እናንተ ተመልሰን መጥተናል። እራሳችንን ከራሳችን ታደጉልን።” ይሉናል።
“እራሳቸው ያፈሩትን እንጀራ ከእራሳቸው ወስደን መልሰን ለራሳቸው እንሰጣቸዋለን፣ ግልጽና ቀላል ነው፤ ምንም ተአምር የለውም፤ ድንጋዩን ወደ እንጀራ እንዳልለወጥንላቸው ጠንቅቀው ያውቃሉ፤ ግን ዳቦውን  ከማግኘታቸው ይልቅ ከእኛ እጅ በማግኘታቸው ደስ ይሰኛሉ። ያመሰግናሉ። ምክንያቱም ቀድሞ እኛ ሳንባርክላቸው በፊት ያገኙት እንጀራ እጃቸው ላይ ወደ ድንጋይ ይለወጥ ነበር፤ ወደ እኛ ሲመጡ ይህንኑ ድንጋይ መልሰን እንጀራ እናደርግላቸዋለን። ባሮች ናቸው፤ የባርነትን ጥቅም በደንብ ይረዳሉ። በደንብ። ይህን እስካላወቁ ድረስ ደስተኞች አይሆኑም። ለዚህ ተወቃሹ ማነው? ተናገር! ማነው መንጎቹን የበተናቸውና ወደማያውቁት አቅጣጫ ያሰማራቸው? እኛ ለዳካማ ነፍሶች የሚገባውን ደስታ እንሰጣቸዋለን። አንተ ወደ ራስህ ደረጃ ከፍ አድርገሀቸው ክብር እንዲሰማቸው አስተምረሀቸው ነበር፣ እኛ ክብር ምናምን አግባብ እንዳልሆነ እናሳምናቸዋለን። ደካሞች እንደሆኑ እናሳያቸዋለን፤ ምስኪን ህፃናት እንደሆኑ እንነግራቸዋለን፤ ከህፃንነት ደስታ የሚልቅ ደስታ የለም እንላቸዋለን። ሽቁጥጠቁጥ ይሆናሉ። ጫጩቶች ዶሮዋ ስር እንደሚሰበሰቡ እነሱም በፍርሀት መጥተው እኛ ስር ይሸጎጣሉ። በኛ ይደመማሉ። ለጉድ ይደነቃሉ። ይህን ሁሉ የታመሰ ሚሊዮን መንጋ በብልህነትና በሀይል ሰጥ ለጥ አድርገን በመግዛታቸን ይኮሩብናል። ስንቆጣ በአቅመ ቢስነትና በፍርሃት ይንቀጠቀጣሉ። አእምሮአቸው በፍርሃት ይሞላል።  እንደ ህፃናትና እንደ ሴቶች በቶሎ የሚያለቅሱትን ያህል ከእኛ አንዲት መልካም ምልክት ሲያዩ ደግሞ ለመሳቅና እንደ ህፃናት ለመቦረቅ ዝግጁ ናቸው። ስራ እንዲሰሩ እንፈቅድላቸዋለን፤ ከስራ ውጪ ያለውን ህይወታቸውን የህፃናት ጨዋታ አይነት እናደርግላቸዋለን፣ የህፃናት መዝሙር ይዘምራሉ፤ የህፃናት ዳንስ ይደንሳሉ። ደካሞችና ረዳት አልባ ስለሆኑ ሀጢአት እንዲሰሩ ሁሉ እንፈቀድላቸዋለን፤ ሀጢአት እንዲሰሩ ስለምንፈቅድላቸው በህፃን ፍቅር ዓይነት ያፈቅሩናል። እኛን አስፈቅዳችሁ እስከሰራችሁት ድረስ አይዟችሁ ሀጢአታችሁ ሁሉ ይስተሰረይላችኋል እንላቸዋለን፤ ስለምናፈቅራቸሁ የፈለጋችሁትን ሀጢአት እንድትሰሩ ፈቅደናል፤ የሀጢአታቸሁን ቅጣት እኛ እንቀበላለን ብለን እንነግራችዋለን። እንደ ዳኞቻቸውም ይቆጥሩናል። ከእኛ የተደበቀ አንዳችም ምስጢር አይኖራቸውም። ከፍቅረኛቸው ጋር አብረው እንዲሆኑና እንዳይሆኑ እንወስናለን፤ መታዘዛቸውን አይተን ልጆች እንዲኖራቸውና እንዳይኖራቸው የምንፈቅድላቸው እኛው ነን። በደስታና በሀሴት ይታዘዙናል። ህሊናቸውን የሚያስጨንቀውን ነገር ሁሉ፣ ሁሉም ሰዎች ይነግሩናል፤ ለሁሉም ጥያቄዎቻቸው ደግሞ መልስ አለን። መልስ ብለን የምንግራቸውን ሁሉ በደስታ ይቀበላሉ፤ ምክንያቱም ከአደገኛ ስቃይና ከከባድ ጭንቀት ያድናቸዋል፤ ለራሳቸው እራሳቸው ከመወሰን ጣጣም ይገላግላቸዋል። ያኔ ሁሉም ደስተኞች ይሆናሉ። ሁሉም። እነሱን ከሚገዙት ጥቂት መቶ ሺዎች በስተቀር ሁሉም ደስተኞች ይሆናሉ ። እኛ ምስጢሩን የምናውቀውና የምንጠብቀው ነን ደስታ የሚርቀን። አለም በሺህ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ደስተኛ ህፃናት የሞሉባትና በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ጥሩና መጥፎን ለማወቅ የደፈሩ ሰዎች በስቃይ የሚኖሩባት ቦታ ትሆናለች ። እነዚህ ደስተኛ ህፃናት በሰላም ያልፋሉ፤ በስምህ በሰላም ያርፋሉ። ይሞታሉ። ወደ መቃብር ይወርዳሉ። ከመቃብር ወዲያ ምንም የለም። ምንም። ሞት። ሞት ብቻ። በቃ። ይህን ምስጢር ግን አንነግራቸውም፤ ደስተኞች እንዲሆኑ ዘላለማዊነትና ገነት የሚባሉ ሽልማቶች ይጠብቋችኋል ብለን እናማልላቸዋለን። የወዲያኛው አለም ቢኖርና በወዲያኛው አለም የፈለገው አይነት ነገር ቢኖርም በእርግጠኝነት ለነሱ ቢጤዎች እንደማይሆን እናውቃለን። በድል እንደምትመጣ ትንቢት ተነግሯል፣ ከተመረጡት ጋር፣ ከጠንካራዎቹና ከኩሩዎቹ ጋር ትመጣለህ ተብሏል። ያንተን የተመረጡትን፣ ጠንካራዎቹንና ኩሩዎቹን እራሳችሁን ብቻ ነው ያዳናችሁት እንላቸዋለን፤ እኛ ግን ሁሉንም ነው ያዳነው። …  በመጨረሻው ጊዜም እኛ ለብዙሀኑ ደስታ ብለን ሀጢአታቸውን የወሰድንላቸው እንነሳና፦ “እኛ ላይ ለመፍረድ ወኔውና ብቃቱ ካለህ ፍረድ እስኪ!” እንልሀለን። እንደማልፈራህ እወቅ ። እኔም በምድረበዳ እንደነበርሁ እወቅ! እኔም ስራስርና አንበጣ በልቼያለሁ። እኔም ለሰው ልጆች የሰጠኸቸውን ነፃነት የማከብር ነኝ። እኔም ከምርጦችህ፣ ከጠንካሮቹና ከሀያላኑ አንዱ ለመሆን ጥሬያለሁ! ከምርጦቹ ጋር አብሬ ለመቆጠር ለፍቻለሁ። ቁጥሩን ለመሙላት ተግቼያለሁ። በኋላ ግን ባነንሁ። ነቃሁ። ስከተልና ሳገለግል የነበረው እብደትን እንደሆነ ገባኝ። ከእብደት ጋር ተፋታሁ። ያንተን ስህተት ካስተካከሉት ጋር ተቀላቀልሁ። ኩሩዎቹን ትቼ ወደ ምስኪኖቹ ሄድኩ። ለምስኪኖቹ ደስታ መልፋት ጀመርሁ። የምልህ ሁሉ ይፈጸማል። የኛ መንግስት ይመሰረታል። መጀመሪያ ያልኩህን እደግምልሀለሁ፤ ዛሬ አንተን አይተው ያሸረገዱት ሰዎች ነገ እንደ ዋዛ በእጄ ምልክት ሳሳያቸው አንተ የምትቃጠልበት እሳት ውስጥ ማገዶ ለመጨመር ይራኮታሉ። ስራችንን ልታጉል ነውና የመጣኸው። የእኛ እሳት የሚገባው ካለ አንተ ነህ። ነገ አቃጥልሀለሁ። ዲክሲ።”
(Dixi፦ I have said all that I had to say ማለት ነው። ተናግሬ ጨርሻለሁ። ላቲን ነው። ተርጓሚው።)
ኢቫን ወሬውን አቆመ። እራሱን አያውቅም ነበር። በስሜት ተወስዶ ነበር። ተናግሮ እንዳበቃ ድንገት ሳቀ።
አሊዮሻ በዝምታ ነበር ሲያዳምጥ የቆየው። ወደ መጨረሻ ግድም ግን ለመናገር እጅግ ፈልጎ ነበር፤ ኢቫንን ለማቋረጥ በተደጋጋሚ ዳድቶት ነበር። እንደምንም እራሱን ለጎመ። አሁን ቃላት ተግተልትለው መጡ፦
“ያልከው ነገር ሁሉ ወለፈንዴ ነው” አለ በከፍተኛ ድምጽ፤ አፍሯል፦ “ግጥምህ አንተ እንዳሰብከው ኢየሱስን የሚወቅስ አይደለም፤ ይልቁንም እሱን የሚያወድስ ነው። ስለ ነፃነት ያልከውንስ ቢሆን ማን ይቀበልሀል? ይህ ነው የነፃነት ትርጉም? እንዲህ ነው ነፃነትን የምትገነዘበው? በእኛ በኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን እምነት እንዲያ አይደለም … አንተ ያልከው መላውን ክርስቲያን አይወክልም፤ ሮምን ብቻ ነው የሚወክለው፤ ካቶሊኮችን ብቻ ነው፤ ከካቶሊኮችም ሁሉንም አይደለም … የጠቀስሀቸው ሰዎች የሚፈልጉት አንድ አለምአቀፍ የክርስቲያን መንግስት ማቋቋም ነው፤ ጳጳሱ እንደ ንጉሰ ነገስት ሆኖ … ይህ ደግሞ አንተ እንዳልከው ምንም የተደበቀ ምስጢርና የተቀደሰ ግብ የለውም፤ በቃ ተራ የስልጣን ጥምን ማርካትና እርካሽ የቁስ ረሀብን ማጥገብ ብቻ ነው አላማው … በእግዚአብሔር የሚያምኑም አይመስለኝም። አንተ ለሰው ልጆች ብሎ የሚሰቃየው የምትለው ግራንድ ኢንኩዊዚተር ዝም ብሎ ፋንታሲ ነው።”
“ተረጋጋ። ተረጋጋ።” ሳቀ ኢቫን፦ “ለጉድ ተቆጥተሀል። ፋንታሲ ነው ያልከው፤ ይሁን ግድ የለም። ፋንታሲ ነው በርግጥም። ቆይ ግን ላለፉት ክፍለ ዘመናት የሮማን ካቶሊክ ንቅናቄ አላማ ተራ የስልጣን ጥምን ማርካትና እርካሽ የቁስ ረሀብን ማጥገብ ብቻ ነበር? እንዲያ ብለው ነው ያስተማሩህ?”
“አይደለም። አይደለም። … አንተ ራስህ ሜሰን ሳትሆን አትቀርም። በእግዚአብሔር አታምንም።” አለ አሊዮሻ ወንድሙን በሀዘንን እያየ፤ ኢቫን አሊዮሻን በምፀት እያየው ነው።
“ግጥምህ እንዴት ነው የሚያልቀው? ወይስ አልቋል?” ጠየቀ መነኩሴው አሊዮሻ።
“ግጥሜ እንዲህ እንዲያልቅ ነው የወሰንኩት። ግራንድ ኢንኩዊዚተሩ አውርቶ ከጨረሰ በኋላ እስረኛው እንዲናገር ጠበቀው። ዝም። ዝምታው ከበደው። ዝምታው አስጨነቀው። እስረኛው በአትኩሮትና በትህትና ያደምጠው እንደነበር አስተውሏል። ሽማግሌው ግን መልሱ የፈለገ መራራና መጥፎ ቢሆንም በቃ የሆነ ነገር እንዲመልስለት ፈልጓል። እስረኛው፣ ሽማግሌውን ድንገት ተጠጋውና በዝምታ የሽማግሌውን ደምአልባ ያረጁ ከንፈሮች በስሱ ሳማቸው። ይህ ነበር መልሱ። ሽማግሌው ተርገፈገፈ። ከንፈሮቹ ተንቀሳቀሱ ። ወደ በሩ ሄደና ከፈተው። እንዲህም አለ፦ ሂድ! ዳግመኛ እንዳትመጣ! ጭርሱን እንዳትመጣ! ፈፅሞ! ፈፅሞ! … ወደ ጨለማው አስወጣው። እስረኛው ሄደ። ”
“ሽማግሌውስ?” አሊዮሻ ጠየቀ።
“ስሞሹ ልቡን አነደደው። በሀሳቡ ግን ጸና።”
“አንተም ከሽማግሌው ጋር ነህ አይደል? የሽማግሌው ደጋፊ ነህ አይደል? አንተ?” አለ አሊዮሻ እያዘነ።
“እርሳው አሊዮሻ። ምንም የሚረባ ነገር የለውም። ምንም። ሁለት የሰመሩ ስንኞች መፃፍ የማይችል የቀሽም ተማሪ ቀሽም ግጥም ነው። ለምንድነው በእንዲህ ያለ ቁም ነገር የወሰድከው? አሁኑኑ ተነስቶ የእሱን ስራ ለማስተካከል ከጀስዊቶቹ ጋር ይቀላቀላል ብለህ አላሰብክም መቼስ? አንዱም ነገር ይህቺን ታህል ጉዳዬ አይደለም። ነግሬኽአለሁ፤ አስከ ሰላሳ አመቴ መኖር ነው የምፈልገው … ከዚያ የህይወቴን ፅዋ እከሰክሳታለሁ …”
“ይኼን ሁሉ ገሀነም በልብህ ተሸክመህ እንዴት መኖር ትችላለህ?” ጠየቀ አሊዮሻ። ሀዘኑ አሁንም አለ።
“ሁሉን ነገር በፅናት ለመቋቋም የሚያስችል ብቃት አለ።” አለ ኢቫን።
“ማንኛውም አዘቅት ውስጥ መስጠምም እንኳ ቢሆን? ነፍስን ለጉድ ማቆሸሽም ቢሆን እንኳ?”
“እንዲያ ማለትም ሊሆን ይችላል! እስከ ሰላሳ። ከዚያ …”
አሊዮሻ ወደፊት አዘነበለ። የወንድሙን ከንፈሮች በስሱ ሳማቸው።
“ይህቺ ፕላጃሪዝም ናት።” አለ ኢቫን በከፍተኛ ድምፅ፦ “ይህቺን የሰረቅኸው ከግጥሜ ላይ ነው። ለማንኛውም አመሰግናለሁ። ተነስ አሊዮሻ። የሁለታችንም መሄጃ ደርሷል።”
ሄዱ። ቻዎ¡

Read 1498 times