Saturday, 30 April 2016 11:30

የፊልምና ድራማዎቻችን ሥጋት፣ “ቃና” ወይስ ...?

Written by  አስናቀ ሥነስብሐት
Rate this item
(3 votes)

የቴሌቪዥን ድራማዎቻችን ብቃትና ጥራት ሲፈተሽ ---
 (ካለፈው የቀጠለ)
በመጀመሪያው ክፍል ጽሑፌ፣ “ቃና ቴሌቪዥን; የውጭ አገራት ተከታታይ ፊልሞችን በአማርኛ ተርጉም ማቅረቡን ተከትሎ፣ የኪነ-ጥበብ ማኅበራት ያወጡትን መግለጫ መነሻ በማድረግ፣ የፊልምና የቴሌቪዥን ድራማዎቻችንን ሥጋት የሚፈትሽ ጥቅል ሐሳብ አቅርቤ ነበር፡፡ በዚህ ጽሑፍ ደግሞ ይህንን ሐሳቤን በዝርዝር ለማቅረብና በአሁኑ ወቅት የቀረቡትንና በመቅረብ ላይ የሚገኙትን የቴሌቪዥን ድራማዎች የብቃትና ጥራት ደረጃ በተመልካች ዕይታ በጥቅሉ ለመገምገም እሞክራለሁ፡፡
በመጀመሪያ ግን፣ ባለፈው ጽሑፍ ላይ አንስቼው ያለፍኩትን አንድ ነጥብ ለማብራራት እፈልጋለሁ፡፡ የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች ማኅበራቱ በመጋቢት 21 መግለጫቸው፤ ”ሥጋቶች” ብለው ካነሷቸው ነጥቦች መካከል የባሕል ወረራን የሚጠቅሰው ከቴሌቪዥን ድራማ ሕልውና ጋር ተያይዞ የቀረበውን ሥጋት ለመደገፍ የመጣ እንጂ ከመቆርቆር የመነጨ ነው ብዬ እንደማላምን ገልጬ ነበር፡፡ ምክንያቴን ላስቀምጥ፡፡
እነዚህ ማኅበራት እውነት ለባሕል ተቆርቋሪ ከሆኑ፣እስከ ዛሬ ድረስ ስንትና ስንት ባሕል ሸርሻሪ ሥራዎች በአገር ውስጥ ሲሠሩና ከውጭ እየመጡ ሲቀርቡ ለምን ዝም አሉ? ዛሬ በ“ቃና ቲቪ; እየቀረቡ ከሚገኙት ድራማዎች መካከል የተወሰኑት በሌሎች ቻናሎች የቀረቡና ለዕይታ በቀረቡባቸው አገሮች (ለዚያውም ጥብቅ የባሕል ጥበቃ ሥርዓት ባለባቸው) ቅሬታ ያልቀረበባቸውና ያልታገዱ መሆናቸውን ሳያውቁ ቀርተው ነው? ደግሞስ፣ ማኅበራቱ ለዕይታ በቀረቡት ፊልሞች ላይ አስተያየት ከመስጠታቸው በፊት ምን ያህል ፊልሞችን ተመልክተዋል? አንዳንድ የማኅበራቱ አባላት የተወሰኑትን መመልከታቸውንና ጥሩ ያልሆኑ የፊልሞቹን ክፍሎች አስመልክቶ ለ“ቃና” ኃላፊዎች አስተያየት መስጠታቸውን ሲናገሩ የሰማሁ ይመስለኛል፡፡ የትኞቹ ፊልሞች እንደሆኑና የተሰጣቸውን ምላሽ ግን ወይ እነርሱ አልተናገሩም፣ ወይ እኔ አልሰማሁም፡፡ እኔ የተወሰኑትን ፊልሞች በኤምቢሲ ቻናሎች ላይ የተመለከትኩ ሲሆን ስለተቀሩትም  ፊልሞች ዝርዝር መረጃዎችን ከተለያዩ ድረ-ገጾች ለመመልከት ሞክሬያለሁ፡፡ ባገኘሁት ውጤት ታዲያ እነዚህ ፊልሞች ጉልህ የሆነ ሞራልና ሥነ-ምግባርን የሚያጎድፍ ይዘት እንዳላቸው የሚያሳይ ነገር አላገኘሁም፣ አለ ቢባል እንኳ ”ቃና” በኃላፊነት መንፈስ ከዕይታ ሊያወጣቸው የሚችል እንጂ በእኛው አገር እየተሠሩ ከሚቀርቡት መሰል ሥራዎች ብዙም ያልተለዩ እንደሆኑ ነው የሚታየው (እዚህ ላይ ”ተሳስተሃል” ብሎ በማስረጃ የሚሞግተኝ ካለ ለማድመጥና ካስፈለገም ለመታረም ዝግጁ ነኝ)፡፡ እናም፣ የባሕል ወረራው ”ሥጋት” ደጋፊ ብቻ ሆኖ የቀረበ እንጂ በተጨባጭ ማስረጃ ሊረጋገጥ የሚችል አይደለም ባይ ነኝ፡፡         
ዋናው ችግር ምንድን ነው?    
የመጀመሪያውን ክፍል ጽሑፍ ሳጠቃልል ፤“…ዋነኛው ችግር የሥራዎቹ በተገቢው ደረጃ ያለመቅረብ እንጂ የ “ቃና” መምጣት አይደለም…” ብዬ ነበር፡፡ “ሥራዎቹ በተገቢው ደረጃ አልቀረቡም” ስንል ምን ማለታችን ነው? ይህንን ጥያቄ ለመመለስ አንድ የኪነ-ጥበብ ሥራ ”ደረጃውን ጠብቋል” የሚያሰኙት ነጥቦች ምን ምን እንደሆኑ በቅድሚያ መመልከት ተገቢ ይመስለኛል፡፡
”ኪነ-ጥበብ” ስንል በይበልጥ የሚታዩና የሚደመጡ ጥበባዊ ሥራዎችን (ክዋኔዎችን) ማለታችን ነው፡፡ እነዚህ ክዋኔ-ጥበቦች በእንግሊዝኛ ”Performing Arts” የሚባሉት ሲሆኑ ሙዚቃን፣ ቴአትርን፣ የመድረክና የቴሌቪዥን ድራማን፣ ሲኒማንና የመሳሰሉትን ያጠቃልላሉ፡፡ ኪነ-ጥበባዊ ሥራዎች ለተመልካችና ለአድማጭ ከመቅረባቸው በፊትም ሆነ ከቀረቡ በኋላ በተደራሲያን፣ በባለሙያዎችና በሐያሲያን የሚገመገሙባቸው የተለያዩ መስፈርቶችና የደረጃ መስጫ ነጥቦች አሉ፡፡ የባለሙያዎችና የሐያሲያኑን ነጥቦች ባለቤቶቹ በስፋት ሊያብራሩት የሚችሉት ቢሆንም፣ በእኔ በኩል ጥቂቶቹን ብገልጽ ደስ ይለኛል፡፡
በዴንማርክ  የአርሁስ ዩኒቨርሲቲ (University of Aarhus) ባልደረቦች የሆኑት ካረን ሃና፣ ዮርን ላንግስቴድና  ቻርሎቴ ሮድሃም ላርሰን ”Evaluation of Artistic Quality in the Performing Arts” በሚል ርዕስ እ.ኤ.አ. በ2003 ዓ.ም. ባሳተሙት ጥናታዊ ጽሑፍ፤ የአንድ ኪነ-ጥበባዊ ሥራ የጥራት ደረጃ (Artistic Quality) በሦስት ነጥቦች እንደሚፈተሽ ይገልጻሉ፡፡ እነዚህ ነጥቦች፤ ዓላማ (Intention)፣ አቅም (Ability)፣ እና አስፈላጊነት (Necessity) ናቸው፡፡ በእነዚህ ነጥቦች ጥምረት ኪነ-ጥበባዊ ሥራዎችን ለመገምገም የሚረዳ The IAN Model የሚል ስያሜ የሰጡትን ሞዴል አጥኚዎቹ አስተዋውቀዋል (IAN= Intention, Ability, Necessity)፡፡ በዚህ ሞዴል አማካይነት ኪነ-ጥበባዊ ሥራዎችን ከተለያዩ አቅጣጫዎች መገምገም እንደሚቻል ጥናቱ ይገልጻል፡፡
ሙያዊ የሆነውን ይህንን የመገምገሚያ መንገድ ዝርዝር ጉዳይ ለባለሙያዎቹ ልተወውና፣ “እንደተደራሲ ኪነ-ጥበባዊ ሥራዎችን እንዴት እንገመግማለን?” የሚለውን ጥያቄ፣ ከግል ተመክሮዬና ምናልባትም ብዙሃኑ ተደራሲ ይጋራኛል ብዬ ከማስበው በመነሳት መልስ ልስጥ፡፡ ማንኛውም ኪነ-ጥበባዊ ሥራ በብቸኝነት የሚቀርበው ለተደራሲው (audience) ነው፡፡ ተደራሲው (አድማጭ/ተመልካች) የኪነ-ጥበብ ሥራውን ለመመልከት ወይም ለማድመጥ ሲዘጋጅ ከሥራው የሚጠብቃቸው ጥቅሞች አሉ፡፡ ከእነዚህ ጥቅሞች መካከል የተወሰኑት መዝናናት፣ መመሰጥ፣ መማር፣ የማሰቢያና የመወያያ ርዕስ ማግኘት፣ ወዘተ ናቸው፡፡ ለአንድ ኪነ-ጥበባዊ ሥራዎችን በሙሉ ትኩረት ለሚከታተል ተደራሲ፣ እነዚህን ጥቅሞች ማግኘት ትልቁ ትርፉ ሲሆን ማጣቱ ደግሞ ኪሳራው ይሆናል፡፡ በዚህም ምክንያት ኪነ-ጥበባዊ ሥራዎችን ”ጥሩ” ወይም ”መጥፎ ” ብሎ ደረጃ ለመስጠት እነዚህና ሌሎችንም ነጥቦች በመጠቀም ግምገማ ያደርጋል፡፡ በግምገማው ውጤት መሠረትም የሚፈልገውን ሥራ ይመርጣል፡፡ ከላይ የተዘረዘሩትን የተደራሲ ፍላጎቶች መሠረት አድርገን፣ የአገራችንን የኪነ-ጥበብ ሥራዎች የብቃት ደረጃ ብንገመግም፣ ከጥቂት ሥራዎች በስተቀር ሙሉ በሙሉ የተደራሲን ፍላጎት አርክተዋል የሚባሉ ሥራዎችን በስፋት አናገኝም፡፡
በተለይ አሁን ርዕሰ-ጉዳያችን በሆኑት ፊልሞቻችንና የቴሌቪዥን ድራማዎቻችን ላይ የበዛ እንከን እንደሚገኝ አልጠራጠርም፡፡ እስካሁን በዚህ ላይ የተደረገ ጥናት ስለመኖሩ መረጃው የለኝም፤ ቢኖረንና ብንመለከተው የበለጠ ለመተማመን ይረዳን ነበር፡፡ ባደጉት አገሮች የሚሠራበት የግምገማ ሥርዓት (Rating System) የሚያስፈልገን ለዚህ ጊዜ ነበር፡፡  
ይህ ሥርዓት ቢተገበር ውጤቱ ቀደም ብዬ  ከጠቀስኩት እንደማይለይ በእርግጠኝነት መናገር እችላለሁ፡፡የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎቻችንም ይህንን ሐቅ አይክዱትም ብዬ አምናለሁ፡፡ ”ለምን ይህ ሆነ?” የሚለው ጥያቄ ብዙ የሚያነጋግር ይመስለኛል፡፡
 ተደጋግሞ የሚገለጸው፤ የተማረ የሰው ኃይል እጥረት፣ የመሣሪያዎች ውድነትና በቀላሉ አለመገኘት፣ የታክስ ጫና፣ የመሥሪያ ቦታ አለማግኘት፣ …አሁንም በችግርነት የሚነሳና እኔም የምስማማበት ቢሆንም፣ ዋነኛው ችግር ግን ይህ አይመስለኝም፡፡
በመጀመሪያው ክፍል ጽሑፌ ላይ ለመጠቆም እንደሞከርኩት፤ ጥራት ያላቸውን የቴሌቪዥን ድራማዎች የመሥራት ጉዳይ በአብዛኛው በወረቀት ላይ ሊያልቅ የሚችል ነው፡፡ “በወረቀት ላይ” ስል ”በድርሰቱ ላይ” ማለቴ ነው፡፡
 የድራማው ደራሲ(ዎች) ሊጽፉበት ስላሰቡት ሐሳብ በቂ ጥናትና ምርምር ያደርጋሉ? መጻሕፍትንና መዛግብትን ያገላብጣሉ? ባለሙያዎችንና ሌሎች መረጃ ሊሰጡ የሚችሉ ሰዎችን ያነጋግራሉ? የጻፉትን ድርሰት በሌሎች ያስገመግማሉ? በውይይትና በአስተያየት ያዳብራሉ? ጥርት ያለ ሥራ እስኪሆን ድረስ ደጋግመው ያሹታል? እነዚህን ጥያቄዎች መመለስ ይመስለኛል የችግሩን ምንጭ የሚጠቁመን፡፡
(ይቀጥላል)

Read 2996 times