Saturday, 30 April 2016 11:50

የእናቶች ሞት ቅኝትና ተገቢ ምላሽ...

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ
Rate this item
(1 Vote)

    ሚያዝያ 12 እና 13 ቀን 2008 በአዲስ አበባ አንድ አገር አቀፍ ሲምፖዚየም ተካሂዶአል። ሲምፖዚየሙም ያተኮረው በመላ አገሪቱ ባሉ የጤና ተቋማት አማካኝነት የተመዘገበውን የእናቶች ሞት መጠንና ምክንያት እንዲሁም ተገቢው ምላሽ ምን መሆን አለበት የሚል ነበር። ሲምፖዚየሙን ያካሄዱት የኢፊድሪ ጤና ጥበቃ ሚኒስር ከአለም የጤና ድርጅት እንዲሁም ከሌሎች አጋር ድርጅቶች ጋር በመተባበር ሲሆን ተሳታፊዎቹም ከመላ አገሪቱ የመጡ የጤና ባለሙያዎች ናቸው። ሲምፖዚየሙን ያስተባበሩት በኢፊድሪ ጤና ጥበቃ ሚኒስር በተለያየ የስራ ድርሻ ላይ የተሰማሩ ባለሙያዎች ሲሆኑ ከእነርሱም መካከል አቶ ስንታየሁ አበበ በሚኒስር መስሪያ ቤቱ በእናቶችና ሕጻናት ዳይሬክቶሬት የእናቶች ጤና ቡድን አስተባባሪ ይገኙበታል። አቶ ስንታየሁ አበበ ሲምፖ ዚየሙን በሚመለከት የሚከ ተለውን ማብራሪያ ሰጥተዋል።
 የሲምፖዚየሙ ዋና አላማ የእናቶች ሞት ቅኝትና ተገቢ ምላሽ የሚለውን አሰራር ከተጀመረ ማለትም ከ2006 ዓ/ም ጀምሮ ያለውን አፈጻጸም መመልከት ነው። ቀደም ሲል ፓስተር ይባል በነበረው በኢትዮጵያ ፐብሊክ ኼልዝ ኢንስቲትዩት በመላ አገሪቱ የሚያጋጥሙ የእናቶች ሞት ሲመዘገብ ቆይቶአል። ስለዚህም ይህን መረጃ መነሻ በማድረግ ያሉት ጠንካራ ጎኖች ምን ነበሩ ?ደካማዎቹስ የትኞቹ ናቸው ?ወደፊትስ የእናቶችን ሞት ለመቀነስ ከምን ላይ ትኩረት አድርገን ብንሰራ ይሻላል ? ቅድሚያ የሚሰጣቸው ነገሮች የትኞቹ ናቸው? የሚለውን ለመነጋገርና ከመረጃው በመነሳት በተሰራው የዳሰሳ ጥናት ደግሞ እናቶች በዋነኛነት የሚሞቱት በምን ምክንያት ነው? እርሱንስ ለመቅረፍ በምን መንገድ መስራት ይገባናል? የሚለውን ሲምፖዚየሙን ለመሳተፍ ከየክልሉ ከመጡ የጤና ባለሙያዎች እንዲሁም ከአጋር ድርጅቶች ወኪሎች ጋር ለመወያየት ያቀደ ሲምፖዚየም ነው።
ጥያቄ፡ የእናቶች ሞት ምክንያት በየክልሉ ተመሳሳይነት አለውን? ወይንስ?
መልስ፡ ከሁሉም ክልሎች እንደሚታየው ከሆነ እናቶች በተለያየ ምክንያት ቢሞቱም በተመሳሳይ ግን በከፍተኛ ሁኔታ የሚሞቱበት ምክንያት የደም መፍሰስ ነው። ይህ ምክንያት በሀገር አቀፍ ደረጃም ለእናቶች ሞት ምክንያት ሆኖ የቀረበ ነው። የእናቶች ሞት ቅኝትና ተገቢ ምላሽ የሚለው አሰራር ዋና አላማው እናቶች የሚሞቱበትን ምክን ያት ለይቶ ያንን ችግር በመቅረፍ ሌላ እናት በተመሳሳይ ምክንያት እንዳትሞት ማድ ረግ ነው። ስለዚህም እናቶች በደም መፍሰስ ምክንያት እንዳይሞቱ ለማድረግ በዚህ ሲምፖዚየም ክልሎች ለወደፊቱ ስራቸው እቅድ አውጥተዋል።
አቶ ታደለ ፀሐይ ከጋምቤላ ጤና ቢሮ ተወክለው በስብሰባው ላይ ተሳትፈዋል። አቶ ታደለ እንደሚገልጹት፡-
 “...በጋምቤላ እናቶች ከሚሞቱባቸው ምክንያቶች አንዱ በጤና ጣብያ ያለው ሽፋን ዝቅተኛ መሆን ነው። በሪፖርታችንም እንደተገለጸው በዚያ የሚጎዱ እናቶች መጠን ወደ 24/ከመቶ ይደርሳል። ከዚህ ውጤት እንደሚታየውም እናቶች በቤት የሚወልዱበት አጋጣሚ ብዙ ነው። በቤታቸው ከወለዱ ደግሞ የባለሙያ እገዛ እንደማያገኙ እሙን ነው። የአምቡላንስ አጠቃቀምና የሪፈራል ሲስተሙም አንዱ ለእናቶች ሞት ምክንያት ከሚባሉት መካከል ነው። ለምሳሌ እናቶች ወደ ጤና ተቋም ሲጉዋጉዋዙ የአምቡላንስ ነዳጅም ሆነ የአሽከርካሪ ክፍያ የማይመለከታቸው ሲሆን ነገር ግን አብዛኛዎቹ ወረዳዎች በጀት ባለመያዘቸው ምክንያት ለአገልግሎት እንደ አንድ እንቅፋት ይታያል። ይኼም እናቶቹ በትክክል የጤና ተቋማቱን እንዳይጠቀሙ ከአቅም አንጻር ስለሚያውክ ይህም አንዱ ለእናቶች ሞት አስተዋጽኦ ከሚያደርጉት መካከል ነው የሚል እምነት አለን። በእርግጥ በእናቶች ሞት ቅኝትና ተገቢ ምላሽ አሰራር በትክክል የእናቶች ሞት ምክንያት ይህ ነው ብሎ ለመናገር በአሁኑ ወቅት የማያስችሉ ሁኔታዎች ያሉ ሲሆን ወደፊት ግን በትክክል መለየት የሚያስችል አመዘጋገብና አሰራር ይኖረናል። ”ብለዋል።
ለእናቶች ሞት መንስኤ የሚባሉ ሶስት መዘግየቶች ናቸው።
1ኛ መዘግየት:
እናቶች ወደጤና ተቋም ሄደው ለመውለድ ለመወሰን አለመቻል (ከልማድ ወይንም ከተለያዩ ሁኔታዎች የተነሳ...)
2ኛ መዘግየት:
እናቶች ለመውለድ ወደጤና ተቋም ለመሄድ የሚያስችላቸው (የመጉዋጉዋዣ እና የመንገድ...ወዘተ አለመኖር)
3ኛ መዘግየት:
በጤና ተቋም የአገልግሎቱ አለመሟላት ናቸው።
በተጠቀሱት መዘግየቶች ምክንያት እናቶች እንዳይጎዱ አስቀድሞውኑ ማለትም ምጥ ሳይይዛቸው ወደጤና ተቋም በመሄድ የመውለጃ ቀናቸውን እንዲጠባበቁ ለማድረግ የእናቶች መቆያ ቤት አስፈላጊ ሆኖ በአለም አቀፍ ደረጃ ሲሰራበት የቆየ በአገራችንም በስፋትም ባይሆን ጅምሮች የታዩበት ነው። ይህንን በሚመለከት ዶ/ር ሰናይት በየነ በኢፊድሪ ጤና ጥበቃ ሚኒስር የእናቶችና ሕጻናት ዳይሬክቶሬት የእናቶች ኬዝ ቲም ኦፊሰር ናቸው።
 “...አብዛኛዎቹ እናቶች የሚሞቱት በታዳጊ አገሮች ነው። ምክንያቱም በሰለጠነ የሰው ኃይል የማዋለድ ልምዳችን ዝቅ ያለ ስለሆነ ነው። እናቶች ለምን በጤና ተቋም አይወልዱም ሲባል እናቶች ወደተቋማቱ ለመምጣት ላይፈልጉ ይችላሉ። ወይንም ደግሞ ወደተቋሙ የሚጉዋጉዋዙበት መንገድ ላይኖር ይችላል። እንዲሁም ወደተቋሙ ከደረሱም በሁዋላ በተለያዩ ምክንያቶች አገልግሎቱን ላያገኙ ይችላሉ። ስለዚህ ይህንን ችግር ለማቃለል በምን መልክ ማገዝ ይቻላል? በምን መንገድ የእናቶችንና ጨቅላ ሕጻናቱን ጤና መጠበቅ እንችላለን የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ ከሚያስችሉት መካከል አምቡላንሶች ህብረተሰቡን ተደራሽ ባደረገ መልኩ በስፋት ተገዝተው እንዲቀርቡ የሚለው ሲሆን አምቡላንስ እማይደርስበትስ ?ተብሎ ሲታሰብ ደግሞ የእናቶች መቆያ ቤቶችን ስራ ላይ ማዋል የሚለው ከግንዛቤ ገብቶአል። በእርግጥ የእናቶች መቆያ ቤት ሀሳቡ ከብዙ መቶ አመታት በፊት በአለም የነበረ ሲሆን በተለይም በአውሮፓ አገራት ልጆች ያልተፈለገ እርግዝና ሲያጋጥማቸው ቤተሰቦቻቸውም ስለማይቀበሉ ተደብ ቀው ወልደው የመጣል አዝማሚያ ስለነበረ ያንን ለመከላከል አስቀድሞውኑ እናቶቹን ወስደው ማቆያ ቤት ያሳርፉ ነበር። በዚህም ጽንስ ማቋረጥን እና የሚወለዱት ልጆችም እንዳይ ሞቱ ይከላከሉ ነበር። በእርግጥ ይህን ያደርጉ የነበሩት ጤና ተቋማት ሳይሆኑ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ሲሆኑ ለምሳሌም የካቶሊክ ቤተክርስቲያን አንዱዋ ነች። ይህንን ተደራሽነት በተለይም ከግማሽ ክፍለዘመን ወዲህ በስፋት ተግባር ላይ እንዲውል የተደረገ ሲሆን በኢትዮጵያም እንደአውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1976 ዓ/ም አጣጥ የሚባል ሆስፒታል በጉራጌ ዞን ውስጥ የእናቶች መቆያ ቤትን በሆስፒታሉ አደራጅቶ እየሰራበት ይገኛል። በሌሎች ቦታዎችም በአንዳንድ ጤና ተቋማት ውስጥ ማቆያው ስራውን የጀመረበት ሁኔታ አለ። ”ብለዋል።
እናቶች በእርግዝና ወቅት የህክምና ክትትል ሲያደርጉ ቢቆዩም በስተመጨረሻው ለመውለድ ሲቃረቡ ግን ከቤ ብወልድ ይሻለኛል ብለው ሊወስኑ ይችላሉ። የዚህም ምክንያቱ እርግዝናው ቀኑ እየገፋ በሄደ ቁጥር እናትየው እሩቅ መንገድ መሄድን ማስወገድ እንዳለባት ወይንም መጉ ዋጉዋዣው ባይኖር አለዚያም የገንዘብ እጥረት የመሳሰሉት ነገሮች ወደሁዋላ ሊያስቀሩዋት ይችላሉ። ነገር ግን የእርግዝና ክትትል በምታደርግበት የህክምና ተቋም የእናቶች ማቆያ ቤት መኖሩን ካወቀች ከመውለጃዋ ቀን አስቀድማ ሄዳ በመቆያ ቤቱ የምታርፍ ስለሆነ ካለችግር ልጅዋን ልትገላገል ትችላለች።
ከሶማሌ ክልላዊ መስተዳድር ጤና ቢሮ የተወከለው ባለሙያ እንደገለጸው፡-
 “... በክልሉ ለእናቶች ሞት ምክንያት ተብለው ከተያዙት ነጥቦች መካከል እናቶች ወደጤና ተቋም መጥተው ለመውለድ መወሰን አለመቻላቸው ነው። ሌላው እናቶች ባሉባቸው አካባቢዎች የአምቡላንስ እጥረት ሊኖር የሚችል ሲሆን አንዳንድ ቦታዎች የህዝብ መጉዋጉዋዣ ጭምር አለመኖሩ እናቶች ወደጤና ተቋም መጥተው እንዳይወልዱ ከሚያደርጉዋቸው ምክንያቶች መካከል ናቸው። የእናቶች መቆያ ቤትን በሚመለከት በክልሉ የሚገኙ አራት ሆስፒታሎች ያላቸው ሲሆን ወደፊት ግን ለሁሉም የጤና ተቋማት አስፈላጊነቱ ታምኖበት ደረጃውን የጠበቀ የእናቶች ማቆያ ቤት ስራ ላይ እንዲውል ፕሮጀኪት ተነድፎአል። ” ብለዋል።
ማንኛዋም እናት፡-
ኢሰብአዊ ከሆነ ህክምና ወይም ተያያዥ ጥቃት የመጠበቅ
በሚሰጣት የህክምና አገልግሎት ላይ በቂ መረጃ የማግኘት
በሚሰጣት የህክምና አገልግሎት ላይ በእውቀት ላይ የተመሰረተ የመስማማት ወይም ያለመስማማት
የሚሰጣት የህክምና አገልግሎት የመምረጥና በወሊድ ጊዜ አብሯት የሚሆን ሰው የመወሰን
የግል ህይወቷ፣ ግላዊነቷ እንዲሁም ሚስጥሯ የመጠበቅ...መብት አላት።

Read 2757 times