Saturday, 07 May 2016 13:26

ከአምስቱ የፋሺስት ወረራ ዓመታት ምን እንማራለን?

Written by  ሀብታሙ ግርማ (ከጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ)
Rate this item
(0 votes)

      ከ1920ዎቹ አጋማሽ ጀምሮ የኢትዮጵያን ድንበር ጥሶ የዘለቀው የፋሺስት ኢጣሊያ ጦር፣ አንዳንድ የጠረፍ አካባቢዎችን ከመቆጣጠር አልፎ ቀስ በቀስ እግሩን እያሰፋ መላ አገሪቱን በእጁ ለማስገባት መንቀሳቀሱን ተከትሎ የአገር ህልውና አደጋ ላይ ወደቀ:: የፋሺስት ትምክህት አይሎ ከሃምሳ ዓመታት በፊት በዓድዋ  የጦር አውድማ የደረሰበትን ሽንፈት ለመበቀል ጦሩን አደራጅቶ በማይጨው መሸገ:: የማይጨው ጦርነት ውጤት የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት የሚያረጋግጥ ወይም የኢጣሊያን ቅኝ ገዢነት የሚያውጅ ነበር፡፡ በጦርነቱ ዘመናዊ መሳሪያ ተጥቆ የነበረው የኢጣሊያ ሰራዊት የበላይነት ያዘ፥ የወገን ጦርም አፈገፈገ::
የጦሩ ጠቅላይ አዛዥ የነበሩት ቀዳማዊ ኃይለስላሴ ኮረም ላይ ጦሩን አሰባስበው ወደ ውጊያ ተመልሰው ለመግባት ባሰቡ ጊዜ የንጉሱ የቅርብ ሰዎችና የጦር አበጋዞቻቸው በዚህ የንጉሱ ወሳኔ ለሁለት ተከፈሉ፤ ንጉሱ በአገር ቤት ሆነው ጀግኖች አርበኞችን እያስተባበሩ፣ የኢጣሊያንን ጦር በዱር በገደሉ መጋፈጥ አለባቸው የሚሉ መኳንንትና መሳፍንት የሚኖራቸውን ያህል፣የለም የግርማዊነታቸው ኮረም ላይ መዋጋትና መሞት ጠላትን  ከመጥቀም በቀር ፋይዳ የለውም ብለው የተከራከሩም ነበሩ:: ኢትዮጵያዊው የታሪክ ባላባት ተክለ ጻዲቅ መኩሪያ “ከአጼ ቴዎድሮስ እስከ ቀዳማዊ ኃይለ ስላሴ” በሚለው መጽሀፋቸው እንዳሰፈሩት፤ንጉስ ነገስቱ በጉዳዩ ላይ የሚኒስትሮች ምክር ቤት እንዲወስን ጠይቀው፣በዚህም ድምጸ ውሳኔ ተካሂዶ፣ ምክር ቤቱ ሃያ አንድ ለሶስት በሆነ ድምጽ ንጉሰ ነገስቱ አገር ለቀው እንዲወጡ ወሰነ፡፡ ከዚህ በኋላ ግርማዊ ንጉሰ ነገስት፤‘የኔ ወደ አዲስ አበባ መመለስ ለህይወቴ መሳሳት ሳይሆን ለኢትዮጵያና ለህዝቦቿ ጠቀሜታ ያደረጋችሁት መሆኑን ቃል ግቡልኝ’ ብለው ጳጳሱ ከገቡላቸው በኋላ እንግዲያውስ የተረፈውም ጦር እንዲመለስ ንገሩ ብለው ከተሰበሰበ በኋላ ደጀን እየሆኑ ጉዞ ወደ አዲስ አበባ ጀምረው፣ ሚያዚያ 3 ቀን 1936 (እ.ኤ.አ) ከኢትዮጵያ ተነስተው ከተወሰነ ቀን በኋላ ወደ ጄኔቭ አመሩ::
የአዲስ አበባ መያዝ አይቀሬ ነበርና የንጉሰ ነገስቱ መቀመጫን መቀየር ያስፈልግ ነበር፤ እናም የት ይሁን በሚለው ጉዳይ ላይ የተለያዩ አስተያየቶች ቢመጡም የብላቴን ጌታ ሎሬንዞ ታዕዛዝን ያህል ግን ሚዛን የሚደፉ አልነበሩም፡፡ ሎሬንዞ ታዕዛዝ የመንግስቱ መቀመጫ እንዲሆን ብለው ያጯት ጎሬ ነበረች፡፡ የሎሬንዞ ታዕዛዝ ተቀባይነት በማግኘቱ ቀዳማዊ አጼ ሀይለስላሴ የመንግስታቸውን መቀመጫ ወደ ጎሬ አንዲዞር፣ የዘውዳዊውን መንግስት እንዲጠብቁ ደግሞ ልዑል ራስ እምሩ ሀይለ ስላሴን ሰይመው፣ አዲስ አበባን ለቀው በባቡር ወደ ጅቡቲ፣ ከዚያም በመርከብ ተሳፍረው ወደ አውሮፓ ተጓዙ፡፡ በማርሻል  ግራዚያኒ የተመራው የፋሽስት ኢጣሊያ  ጦርም ሚያዚያ 27 ቀን 1927  ዓ.ም አዲስ አበባን ተቆጣጠረ፡፡
ጠላት አዲስ አበባ ከተማ  ከመድረሱ ኢትዮጵያዊያን ከባህላቸውና ማንነታቸው እንዲፋቱ ለማድረግ ያለሙ ተግባራትን በዘመቻ መልክ ፈጸመ:: ፋሺስት ያደረገው የመጀመሪያው ተግባር ታሪኩን መበረዝና የሀሰት ታሪክን መፈብረክ ነበር፣ የኢትዮጵያዊያንን ታሪክ ለማውደም የተጠቀመበት ስትራቴጂ ደግሞ ኢትዮጵያዊያን ምሁራንንና ታላላቅ ጸሀፍትን ከያሉበት እያደነ ማሰር፣ መግደልና በአማርኛና በግዕዝ የተጻፉ መጻህፍትን በዘመቻ ማቃጠል ነው፡፡ ፋሺስት የባህላዊውን ትምህርት እንዲቆም በማድረግ፣ራሱ አስኳላ በሚል የሰየማቸውን ትምህርት ቤቶች በመላው ኢትዮጵያ በማቋቋም፣ የትምህርት ስርዓቱ የራሱን ፕሮፓጋንዳና አጀንዳ ማስፈጸሚያ መሳሪያ ለማድረግ ሞከሯል::
ወራሪው የፋሺስት ሀይል በማይጨው የጦር አውድማ ድል ቢቀናውም፣ ተረጋግቶ ኢትዮጵያውያንን ለመግዛት ግን አልተቻለውም:: ኢትዮጵያዊያን ለአገራቸው ነጻነት ሲሉ ከዳር እስከ ዳር አንድ ሆነዉ በመነሳት በዲፕሎማሲውና  በጦር ግንባር የሞት ሽረት ትግል አድርገዋል::  
የአርበኞች ትግል
ጀግኖች አርበኞች በገጠርና በከተማ፣ በአገር ቤትና በውጭም ሆነው በተለያዩ የጦር አበጋዞች ተደራጅተው ፋሺስትን ፋታ አልሰጡትም ነበር:: ለአገራቸው ሉዓላዊነት ቀናኢነት የነበራቸው ጀግኖቻችን ህዝቡን እያስተባበሩ በፋሺስት ላይ እንዲነሳ አድርገዋል፣ ትግሉንም መርተዋል:: ከእነዚህም መካከል ራስ ዕምሩ ሀይለ ስላሴ፣ ደጃዘማች ከበደ ተሰማ፣ራስ ደስታ ዳምጠው፣ ከበደች ስዩም፣ በላይ ዘለቀ፣ የሰላሌው ታዳጊ አቢቹ፣ ሀዲስ አለማየሁ፣ ስንዱ ገብሩ፣ ወዘተ.......... ለአብነት መጥቀስ ይበቃል:: በከተሞችም እንዲሁ ትግሉን ያፋፋሙ አርበኞች በርካታ ናቸው:: በአዲስ አበባ ከተማ የአብረሃም ደቦጭና ሞገስ አስገዶም ገድል፣ የአቡነ ጴጥሮስ ሰማዕትነት፥ በፋሺስት መናገሻ ሮም ከተማ የአብዲሳ አጋ ጀግንነት አለምን አጃኢብ ያሰኙ ነበሩ::  ወራሪው የኢጣሊያ ሀይል አርበኞቹን በኢትዮጵያ የቄሳርን ገዢነት አምነው ከተቀበሉ ከእስር እንደሚፈታቸው፣ዳጎስ ያለ ጉርሻን እነሆ ቢላቸውም ፈጽሞ አሻፈረኝ በማለት፣አገርን በምንም መለወጥ እንደማይቻል፣ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ምን ማለት እንደሆነ ፋሺስት እንዲገነዘብ አድርገዋል::
በዲፕሎማሲው ዘርፍ የተደረጉ ጥረቶች
የፋሺስትን ሀይል በጦር ማሸነፍ አልሆነምና ሌላ የትግል ስልት መፈለግ የግድ ነበር፤ከእነዚህም አንዱ ፋሺስትን በዲፕሎማሲው ግንባር መግጠም ነበር፡፡ በኢኮኖሚና ወታደራዊ መስክ እጅጉን ኋላ ቀር የነበረችው ኢትዮጵያ፤በአለም አቀፍ መድረኮች ከፍጸኛ ተጽዕኖ ፈጣሪ የነበረችውን ሃያሏን ኢጣሊያን በዲፕሎማሲው ግንባር ለመፋለም ስትነሳ ‘በየትኛው አቅሟ ብለው የተሳለቁ ብዙዎች  ቢሆኑም ይህን ፉርሽ ያደረጉ የዲፕሎማሲ ጀግኖች  አሉን::  በአምስቱ የፋሺስት ወረራ ዓመታት ወቅት የንጉሰ ነገስቱ ተወካይ ሆነው የተለያዩ አገራት እየተዘዋወሩ ጉዳይ አስፈጽመዋል፤ የኢትዮጵያን በደልና ብሶት ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በማሳወቅ ወራሪውን የፋሺስት መንግስት የዲፕሎማሲ ጫና ስር እንዲወድቅ ብዙ ሰርተዋል፡፡ በዚህ ረገድ ራስ ቢትወደድ መኮንን እንዳልካቸው፣ ብላቴን ጌታ ህሩይ ወልደ ስላሴ፣ ብላቴን ጌታ ሎሬንዞ ታዕዛዝ ተጠቃሽ ናቸው::
የአምስቱ ዓመታት የፋሺስት ወረራ ምን አጎደለብን?
የፋሺስት ወረራ በኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊያን ላይ ያደረሰው ሰብዓዊ፣ ቁሳዊና መንፈሳዊ ሀብት ውድመት ከባድ ነበር:: በአምስቱ ዓመታት ብዙ ሺህ ኢትዮጵያዊያን አርበኞች ሞተዋል፥ ቆስለዋል::
ተሾመ ዋጋው የተባሉ ምሁር፤‘Education in Ethiopia: Prospect and Retrospect’ በሚል እ.ኤ.አ በ1979 ዓ.ም ባሳተሙት  የምርምር ስራቸው እንዳሰፈሩት፤ ከ1928 እስከ 1933 ዓ.ም በዘለቀው ወረራ ኢትዮጵያ ሰባ አምስት በመቶ (75%) የሚሆኑትን የተማሩ ዜጎቿን አጥታለች:: ወረራው ጥሎት ያለፈው ማህበራዊ ስንክሳርም ቀላል አይደለም:: ደራሲ አሰፋ ገብረ ማርያም ‹እንደወጣች ቀረች› በተሰኘው የስነ ጽሁፍ ስራው፤የፋሺስት ወረራ የዝሙት አዳሪነት፣የትምባሆ ሱስ እንዲስፋፋ ስለማድረጉ ጽፏል::
ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም “አዳፍኔ: ፍርሃትና መክሸፍ” በተሰኘው መጽሃፋቸው እንዳሰፈሩት፤የፋሺስት ወረራ የኢትዮጵያን አንድነትን የሸረሸረ ነበር፡: ተጽዕኖውም ዛሬም ከ75 ዓመታት በኋላ ይታያል:: ምንም እንኳን ኢትዮጵያ በቁሳዊ ሀብትና ኋላ የቀረች ቢሆንም ለውጭ ወራሪዎች እጅ ሳትሰጥና ህልውናዋ ሳይከሽፍ የቆየበት ምክንያቱ የመንፈሳዊው ስልጣኔ መገለጫ የሆኑትና ለዘመናት የኢትዮጵያ ህዝብ ንብረት ሆነው በኖሩት እሴቶች ማለትም አርቆ አሳቢነት፣ ሀይማኖተኝነትና ፈሪሃ እግዚአብሄር፣ መልካም  ስነ ምግባር፣ መንፈሰ ጠንካራነት፣ ለክብርና ኩራት ቅድሚያ መስጠት፣ ለአገር ነጻነትና ሉዓላዊነት መስዋዕትነት ተጋድሎ ማድረግ ወዘተ…. ናቸው፡፡ ታዲያ ይህ መንፈሳዊ ስልጣኔ እስከ መጨረሻው የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ አልተቻለውም፡፡ የአምስቱ ዓመታት  ወረራ የኢትዮጵያ ስልጣኔ እሴቶችን ያመነመነ ነው:: የኢትዮጵያ ሉአላዊነት መሰረት የሆኑት እነዚህ እሴቶች መሸርሸር ደግሞ የአገር አንድነት አደጋ ላይ እንዲወድቅ አድርጓል::
ብልህ ከሁለት ይማራል፣ አንድም ከፊደል ሀ ብሎ፣ አንድም ከመከራ ዋ ብሎ እንዲሉ፤ ከአምስቱ የመከራ ዓመታት ምን ትምህርት አገኘን የሚለው ወሳኝ ጉዳይ ይመስለኛል:: በመሰረቱ የፋሺስት ወረራ የተሳካው በውስጥ ድክመታችን የተነሳ ነው:: እንደ ህዝብ፣ እንደ መንግስት የምንወስደው ሃላፊነት አለብን::  ኢተዮጵያዊያን ለዘመናት የኖርነው የህይወት ዘይቤና ፍልስፍና ስራን የሚያበረታታ አለመሆኑና ህዝቡ ለቁሳዊ ሀብት ያለው ግምት ዝቅተኛ መሆን  ኢትዮጵያን ከሌላው ዓለም በኢኮኖሚ በእጅጉ ወደ ኋላ አስቀርቷታል፡፡
በእርግጥ በተለያዩ የዘመን ማዕቀፎች ኢትዮጵያን ያስተዳደሩ አብዛኞቹ መሪዎች ህዝቡ ይህን አስተሳሰብ እንዲያዳብር አይፈልጉ እንደነበር ተደጋግሞ ቢጻፍም ህዝቡ ከተወቃሽነት አይድንም፥ መሪዎች ህዝቡን ይመስላሉ የሚለውን መርሳት የለብንም:: የሆነው ሆኖ የኢጣሊያ ጦር ዘመናዊ መሳሪያ ታጥቆ፣ በምድርና በአየር በወገን ጦር ላይ መዓቱን ሲያወርድ፣ኢትዮጵያዊያን አርበኞች ግን ከሃምሳ አመታት ቀደም ብሎ በአድዋ ጦርነት ታጥቀው የዘመቱትን ባህላዊ መሳሪያዎች ነበር የታጠቁት፡፡ ፕሮፌሰር መስፍን እንዲህ ጽፈዋል፡-
ኢትዮጵያ ያለችበትን በጣም ዝቅተኛና ቆሞ ቀር ደረጃ በተግባር አስመሰከረች፤ይህ አዲስ ዕውነት የኢትዮጵያ ህዝብ ለዘመናት የነበረውን አልበገር ባይነት ከነኩራቱና ክብሩ ገፈፈው፤ የመንፈስ ሃይሉ ደቀቀ፤ አንገቱን ደፋ፡፡ (ከ“አዳፍኔ: ፍርሃትና መክሸፍ”፣ገጽ 133 ላይ የተወሰደ)
ለማይጨው ጦርነት መሸነፍ ሌላው ሰበብ፣ ጦሩን ያዘመቱና የመሩ ሹማምንት ከልባቸው አልነበሩም፣ ወኔ የከዳቸው ነበሩ የሚሉ መረጃዎች አሉ::
የዚህ ምክንያት ደግሞ የዘመኑ የኢትዮጵያ ፖለቲካና የአስተዳደር ስርዓት ለአገራዊ መግባባት በዝቅተኛ ደረጃ እንኳ እውቅና ያልሰጠ፣ ፍትህና መልካም አስተዳደር የማያውቅ፣ ደካማ መሆኑ ነበር:: የአሁኑ የኢትዮጵያ ገዢዎች ከዚህ መማር ያለባቸው ቁም ነገር ቢኖር፣ የሚከተሉትን የፖለቲካ ስርዓት መለስ ብለው መቃኘት እንደሚገባቸው ነው:: አስተዳደራቸውና ፖሊሲዎቻቸው በተለያየ ደረጃና ስልጣን ያሉ የመንግስት አካላትን የማይከፋፍል፣ የህዝብና መንግስትን ግንኙነት የማያሻክር መሆኑን ማረጋገጥ ያስፈልጋቸዋል::  ይህ ካልሆነ ግን ውስጣችንን አድክሞ የኢትዮጵያና ህዝቦቿን ሰላምና ብልጽግናን ለማይሹ የውጭ ሀይሎች ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል፥ የአገርና የህዝብ ህልውናም በእጅጉ አደጋ ላይ እንደሚወድቅ፣ ለራሳቸው ለፖለቲካው አራማጆችና (ገዥዎች) ጭምር የማይበጅ መሆኑን ከአጼ ሀይለ ስላሴና ባለሟሎቻቸው ስደትና የመንግስታቸው መፍረስ ሊማሩ ይገባል:: በመጨረሻም በየዓመቱ የድል ቀንን ስናከብር በደረሰብን ሰቆቃና ጥፋት እየተቆጨን ሳይሆን ውስጣችንን (ራሳችንን) እየመረመርን፣ ስህተቶቻችንን ነቅሰን ዳግም እንዳንሳሳት በምንጠነቀቅበት አግባብ መሆን አለበት እላለሁ:: መልካም የድል በዓል ለሰፊው የኢትዮጵያ ህዝብና የኢትዮጵያ ወዳጆች ሁሉ ይሁን!! ክብር ለጀግኖች አርበኞቻችን!!
ውድ አንባብያን፡- ከላይ የቀረበው ጽሁፍ አዘጋጅ የዘወትር ጸሃፊያችን ሀብታሙ ግርማ ሲሆኑ በጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ ዲፓርትመንት መምህር ናቸው፡፡ ጸሃፊውን ማግኘት የምትፈልጉ በሚከተሉት የኢሜይል አድራሻዎች ልታገኟቸው ትችላላችሁ፡፡
( This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ; This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. )


Read 2789 times