Saturday, 07 May 2016 13:31

‹ፌስዳቢዬ ናና…›

Written by  ዲ/ን ዳንኤል ክብረት
Rate this item
(17 votes)

እነሆ በሀገራችን አዲስ ጎሳ መፈጠሩ ተሰማ፡፡ እስከ ዛሬ ድረስ ሰዎች የጎሳ ማንነታቸውን ለማስከበር፣ ባህላቸውንና ታሪካቸውን ለመግለጥ ሲታገሉ ነበር የምናየው፡፡ ታሪክ የማያልቅባት ኢትዮጵያ የነባር ጎሳዎችን መብት ማስከበር ብቻ ሳይሆን አዳዲስ ጎሳዎችንም መመሥረት አለብኝ ብላለች፡፡ በርግጥ በሕገ መንግሥቱ ላይ ነባር ጎሳዎችን በተመለከተ እንጂ አዲስ ጎሳ እንዴት እንደሚመሠረት፣ ቢመሠረትም እንዴት ዕውቅና እንደሚያገኝ የተጻፈ ነገር የለም፡፡
ይሄ አዲስ ጎሳ “ፌስዳቢ” ይባላል፡፡ ትርጉሙም ‹በፌስ ቡክ በኩል ተሳዳቢ› ማለት ነው ሲሉ የጎሳው ዋና መሪ ፌስ ቡከኛ ጨርግደው በቀደም ዕለት መግለጫ ሰጥተው ነበር፡፡ የዚህ ጎሳ መገኛ ክልል ‹ፌስቡክ› የተባለው አካባቢ ሲሆን የጎሳው ቋንቋ  ደግሞ ‹ስድብ› ይባላል፡፡ ‹ስድብ› በተባለው ቋንቋ ወግ መሠረት አማርኛን ሆነ ትግርኛን፣ ኦሮምኛንም ሆነ ሶማልኛን፣ እንግሊዝኛንም ሆነ ዐረብኛን መጠቀም ይቻላል፡፡ ዋናው የቋንቋው ሰዋሰው ሕግ የሚያዘው በእነዚህ ሁሉ ፊደላትም ሆነ ቋንቋዎች ‹ስድብ› መተላለፉን ነው፡፡ ‹ስድብ› የተባለው ይህ የ‹ፌስዳቢዎች› ቋንቋ አምስት አካባቢያዊ ዘዬዎች እንዳሉት በጥናት ተረጋግጧል፡፡ ልክ አማርኛ የጎጃም፣ የጎንደር፣ የሸዋ፣ የወሎ እየተባለ በዘዬ እንደሚከፈለው ማለት ነው፡፡  አምስቱ ዘዬዎች ናቂ ስድብ፣ ጨርጋጅ ስድብ፣ ባለጌ ስድብ፣ ተንኳሽ ስድብና ፈጥሮ አደር ስድብ ናቸው፡፡
‹ናቂ ስድብ› የሚባለው ዘዬ ማኅበረሰቡን የናቀ፣ ያዋረደና ለዕውቀትና ለኅሊና ቦታ የሌለው ዘዬ ነው፡፡ ‹እገሊት ባኞ ቤት ውስጥ ራቁቷን ሆና የሆነ ነገር እየሠራች ናት፡፡ ሙሉውን ለማየት ላይክና ሼር አርጉኝ› በሚለው አባባሉ ይታወቃል፡፡ መንግሥት በየመሥሪያ ቤቱ ኪራይ ሰብሳቢ እዋጋለሁ ሲል እዚህ ፌስቡክ ላይ ደግሞ ‹ላይክና ሼር ሰብሳቢዎች› ተፈጥረዋል፡፡ ናቂ ስድብ እነዚህ ላይክና ሼር ሰብሳቢዎች የሚግባቡበት የስድብ ዓይነት ነው፡፡ ናቂ ስድብ አሠሥ ገሠሡን እያቀረቡ ማኅበረሰቡን ለማበሳጨትና ፌስቡክ ከሚባለው ክልል ጨዋዎችን ለማፈናቀል፣ ብሎም  ፌስቡክ የተባለው ክልል  በ‹ፌስዳቢዎች› ለመሙላት የሚጥሩ የጎሳው አባላት የሚጠቀሙበት ቋንቋ ነው፡፡ በእነዚህ ‹ናቂ ስድብ› ዘዬ ተጠቃሚዎች ምክንያት ብዙ ዐዋቂ ፌስቡከኞች ከክልሉ ወጥተው ወደ ሌላ ክልል ለመሄድ ተገድደዋል፡፡ ‹እስኪ እነዚህን ቆንጆዎች ተመልከቷቸው? ዐሥር ሺ ላይክና ሼር ይገባቸዋል› የሚለው የዚህ ዘዬ ታዋቂ ተረቱ ነው፡፡
‹ጨርጋጅ ስድብ› የሚባለው ዘዬ ደግሞ ታላላቅ የምንላቸውን፣ የምናከብራቸውን፣ በሁለት እጅ የማናነሳቸውን ሰዎች ገጽታ ለማጥቆርና ብሎም ‹የገጽታ ግድያ› ለማድረግ በማሰብ በስድብ የሚጨረግድ ዘዬ ነው፡፡ በሰውዬው ወይም በሴትዮዋ ላይ ምን ያስከትላል፣ ልጆቹስ ምን ይላሉ፣ አድናቂዎቹ ወይም ወዳጆቹ ምን ይሰማቸዋል፣ ይህንን የሚያነቡ አዳጊ ልጆች ምን ያስባሉ፣ ውጠቱስ ምን ይሆናል? የሚለውን ማሰብ አይፈልጉም፡፡ እንዴው ዝም ብሎ መጨርገድ ብቻ ነው፡፡ የሚባለው ነገር እውነት ወይም ሐሰት ለመሆኑ ማሰብ አይፈልጉም፤ ማረጋገጥ የሚፈልጉት መጨርገዳቸውን ብቻ ነው፡፡
‹ባለጌ ስድብ› የሚባለው ዘዬ ደግሞ አፋቸውን ያልተጉመጠመጡና ምላሳቸውን ያልገረዙ ‹ፌስዳቢዎች› የፈጠሩት ዘዬ ሲሆን በየመንደሩ የጠፉትን የባለጌ ስድቦች በሙሉ ሰብስበው በዚህ ዘዬ ውስጥ ጨምረዋቸዋል፡፡ ያልታጠበ ኅሊና፣ ያልታጠነም ልቡና ይዘው፣ ገና ራሳቸውን ከማስተካከላቸው በፊት ፌስቡክ ድንገት በስልካቸውና በኮምፒውተራቸው በኩል የመጣባቸው የጎሳው አባላት የሚናገሩት ዘዬ ነው ‹ባለጌ ስድብ› ማለት፡፡ አበው ‹ከባለጌ ጡጫ፣ ከዳገት ሩጫ› ያድንህ ይላሉ፡፡ ለምን ከባለጌ ጡጫ? ቢሉ ባለጌ የት ላይ መማታት እንዳለበት አስቦ አይማታም፡፡ እጁን መሠንዘሩን ብቻ ነው የሚያየው፡፡ ስለዚህም ድንገት ብሽሽትህን መትቶ ጸጥ ያደርግሃል ሲሉ ነው፡፡ ይሄ ምርቃት ለሽማግሌዎች ሸንጎ ቀርቦ ‹ከባለጌ ፌስቡከኛ አቋራጭ ከሚወድ መንገደኛ ያውጣህ› ተብሎ መዘመን አለበት፡፡
‹ተንኳሽ ስድብ› የሚባለው የ‹ፌስዳቢዎች› ዘዬ ደግሞ ጎሳዎችን፣ ነገዶችን፣ እምነቶችን፣ ፓርቲዎችን፣ ግለሰቦችን፣ ድርጅቶችንና ሌሎችንም እየተነኮሰ ማብሸቅ፣ ማናደድ፣ ማጋጋልና ለጠብ እንዲፈላለጉ ማድረግ ነው ዓላማው፡፡ በዚህ ዘዬ የሚጠቀሙ ‹ፌስዳቢዎች› የትንኮሳ ስድባቸውን ሲረጩ ለአንደኛው ወገን እንደሚቆረቆሩ መስለው ነው፡፡ አንዳንዴም የአንድን ማኅበረሰብ ወይም ተቋም ውክልና የያዙና የዚያ ማኅበረሰብን ወይም ተቋምን ሐሳብ እንደሚያንጸባርቁ መስለው ስለሚቀርቡ፣ ያንን የሚመለከቱ ሌሎች ማኅበረሰቦችና ተቋማት ጉዳዩን የግለሰብ አድርገው እንዳይወስዱት ያደርጋቸዋል፡፡
‹ፈጥሮ አደር› የስድብ ዘዬ ድንገት አንድን ነገር ፈጥሮ በማራገብ የታወቀ ነው፡፡ እገሌ ሞተ፣ እገሌ ታሠረ፣ እገሌ ከሰረ፣ እገሌ ጠፋ፣ እገሌና እገሊት ተፋቱ፣ እገሌና እገሊት ተጋቡ፣ እገሌና እገሌ ተደባደቡ እያለ አንዳንዴም በተቀናበረ ፎቶ እያስደገፈ ይበትናል፡፡ ‹እስኪጣራ ማን ይጉላላል‹ እንዳለቺው ዕንቁራሪቷ፤ ወሬው እስኪጣራ ብዙ ሰው ይጉላላል፡፡ በአንዳንድ ሀገሮች ለ‹አፕሪል ዘፉል› ቀን በዓመት አንድ ‹ጊዜ ብቻ የሚደረገውን እነዚህ ግን ዓመቱን ሙሉ ‹አፕሪል ዘፉል› ያደርጉታል፡፡ ቀንጨር በበዛበት እርሻ እህል እንደሚጠፋው ሁሉ እንደዚህ ዓይነት ሰዎች እየተበራከቱ መምጣት ፌስቡክ ከተባለው ክልል ብዙ ባለ አእምሮዎችን እያስወጣ ነው፡፡
‹ፌስዳቢ› በተባለው ጎሳ ባህል ውስጥ አንድ ወጥ ስም የሚባል ነገር አይታወቅም፡፡ ዐሥር፣ ዐሥራ አምስት ዓይነት ስም ሊኖርህ ይችላል፡፡ ትግሬን መሳደብ ሲያምርህ የአማራ ስም፣ አማራን መሳደብ ስትፈልግ የኦሮሞ ስም፣ ኦሮሞን መሳደብ ስትፈልግ የአማራ ስም መያዝ ትችላለህ፡፡ ያ ካልሆነ ደግሞ የቁስ ስምም ቢሆን ይዘህ መሳደብ ነው፡፡ በጎሳው ሥርዓት መሠረት፤ በመታወቂያህ ላይ ፎቶህን ለመለጠፍ አትገደድም፡፡ ብትፈልግ ባዶ ትተወዋለህ፣ ብትፈልግ የሌላ ሰው ፎቶ ትጠቀማለህ፣ ብትፈልግ ደግሞ ስድብ ታደርገዋለህ፡፡ ዋናው ምሽግ ይዘህ ለመሳደብ መቻልህ ነው፡፡
በጎሳው ባህል ውስጥ ሁለት ነገሮች የሉም፡፡ ዕውቀትና ሐሳብ፡፡ ‹ፌስዳቢዎች› ከዕውቀት የደነገሉ ናቸው፡፡ ዕውቀት በዞረበት አይዞሩም፣ ዕውቀትም በዞሩበት አይዞርባቸውም፡፡ ዋናው የጎሳው ባህል በስድብ ላይ የተመሠረተ ስለሆነ ዕውቀት አያስፈልገውም፡፡ በሚጽፉት ነገር አዳዲስ ስድብ መማር ይቻላል እንጂ አዳዲስ ዕውቀት ማግኘት አይቻልም፡፡ ለነገሮች ሁሉ የሚሰጡት ምላሽ በዕውቀት ወይም በማስረጃ ላይ የተመሠረተ አይደለም፡፡ በሐሳብህ ካልተስማሙ የስድብ ብዕራቸውን ነጥቀው ወረራ ማካሄድ ብቻ ነው፡፡ ለምን ተቃወሙ? ልዩነታቸው የት ላይ ነው? እነርሱ ምን የተሻለ ሐሳብ አላቸው? የሚለው ጉዳያቸው አይደለም፡፡ እንዲያውም ቋንቋቸውን ያጠኑ የሥነ ልሳን ሊቃውንት በቋንቋው ውስጥ ‹በለው› የሚለው ቃል ይበዛል ይላሉ፡፡
‹ሐሳብ› የሚው ቃል ራሱ በ‹ፌስዳቢዎች› ቋንቋ ውስጥ የለም ይባላል፡፡ ለዚህም ነው ሐሳቡን ትተው አሳቢውን የሚጨረግዱት፡፡ እንትን ስለሆንክ ነው፣ የእንትን ጠላት ነህ፣ ፀረ እንትና ነህ እያሉ ሰውዬው ላይ መረባረብ ነው፡፡ ሐሳብን በሐሳብ መርታት ስለማይችሉ በሚጽፉት ነገር ውስጥ ክርክር፣ ውይይት፣ ትንታኔ፣ የሚባሉ ነገሮችን ከማግኘት ሳዑዲ ዓረቢያ ውስጥ ወንዝ ፈልጎ ማግኘት ይቀላል፡፡ የእነዚህን ሰዎች ሁኔታ ያጠኑ አንትሮፖሎጂስቶች እንደሚሉት ከሆነ ለወደፊቱ የ‹ፌስዳቢዎች› ምላስና እጅ እየረዘመ፣ ጭንቅላታቸው ግን እንደ ራግቢ ኳስ ሾጣጣ እየሆነ ይሄዳል ብለዋል፡፡ ለዚህ የሰጡት ሞያዊ ምክንያት ደግሞ ‹ፌስዳቢዎች› አንድን መረጃ ወይም ሐሳብ ሲያዩ ወይም ሲያዳምጡ፣ መረጃውን ወይም ሐሳቡን ለማብላላት፣ ለመረዳት ወይም ደግሞ ለመሞገት አይፈልጉም፡፡ ምን? ለምን? እንደተባለ እንኳን ሳያረጋግጡ ካጠራቀሙት ስድብ ውስጥ እየመዠለጡ መወርወር ብቻ ነው፡፡ የተጻፈው ስለ ሰማይ ቢሆንም እነርሱ ግን ስለ ምድር የተዘጋጀ ስድብ ከመልቀቅ አይመለሱም፡፡ በዚህ የተነሣ ለስድብ የሚተጉበት ምላሳቸውና እጃቸው ሲሰላ ጭንቅላታቸውን ግን ስለማይጠቀሙበት እየቀነሰ ይሄዳል ባይ ናቸው፡፡የስድብ ሰዋሰው በሚያዘው መሠረት ‹ፌስዳቢዎች› የሚጽፉት ነገር በጣም አጫጭር ነው፡፡ ለዚህ ባለሞያዎቹ የሚሰጡት ምክንያት ሁለት ነው፡፡ አንደኛው የ‹ፌስዳቢዎች› ዋና ዓላማ መልስ መስጠት እንጂ ምላሽ መስጠት ስላልሆነ ነው፡፡ ስለዚህም ከስድብ መዝገበ ቃላታቸው ውስጥ ስበው ፌስቡክ ላይ መለጠፍ ብቻ ይበቃል፡፡ ሌላው ምክንያታቸው ደግሞ ‹ፌስዳቢዎች› ለስድብ ያላነሱ ለዕውቀት ያልደረሱ ናቸው፡፡ ስለዚህም ተንተን፣ ዘርዘር አድርጎ ለመጻፍ የሚበቃ ነገር ያጥራቸዋል፡፡  
‹ፌስዳቢ› የተባለው ጎሳ በልዩ ልዩ ቤተሰቦች የተከፋፈለ ነው፡፡ የመጀመሪያው ቤተሰብ ‹የእምነት ቃር› ይባላል፡፡ ይሄ ቤተሰብ ለስሙ ሃይማኖተኛ ነኝ ይላል፡፡ የሃይማኖት ጥቅሶችንና ሥዕሎችን ይለጥፋል፡፡ አንዳንድ ጊዜም በየቤተ እምነቱ ሄዶ የተነሣቸውን ፎቶዎች ያወጣል፡፡ እምነቴ ተነካ ብሎ ያሰበ ዕለት ግን በዕውቀትና በሐሳብ፣ በተጠየቅና በማስረጃ እምነቱን ለማስረዳት አይፈልግም፡፡ ሽፍን ማንነቱን አውልቆ ይጥልና ዋነኛውን ማንነት ያመጣዋል፡፡ ‹ሚካኤል ሰይጣንን አልሰደበውም› ብሎ ሲለጥፍ የነበረው ሰውዬ እርሱ የስድቡን ዓይነት ከየተደበቁበት ሰብስቦ አምጥቶ ያዥጎደጉደዋል፡፡ የእርሱ አማኝነት ስድቡን በፈጣሪ ስም ስለሚጀምር ብቻ ነው፡፡
ሁለተኛው ቤተሰብ ደግሞ ‹የጎሳ ቃር› ይባላል፡፡ ራሱን የጎሳው ዋና ጠበቃና ጠባቂ አድርጎ የሾመ፣ የጎሳዬ ዑቃቤ መልአክ ነኝ ብሎ የሚያምን ፌስቡከኛ ነው፡፡ ስለ ራሱ ጎሳ ማንነት፣ ታሪክ፣ ባህል፣ ቅርስ፣ አነዋወር መጻፍ አይሆንለትም፡፡ እጽፋለሁ ብሎም ከተነሣ ረስቶት ሌሎችን ወደ መሳደብ ይገባል፡፡ ሌሎችን ካልተሳደበ የራሱን ነገር የተናገረ አይመስለውም፡፡ ጠላት ቢያጣ እንኳን ራሱ ጠላት ይፈጥርና ከዚያ ጠላት ጋር በስድብ ይዋጋል፡፡ በስድብ ያሸንፋል፡፡
ሦስተኛው ደግሞ ‹የሰብእ ቃር› ይባላል፡፡ ይሄኛው ቤተሰብ የሚደግፈው፣ የሚከተለው የሚወደው፣ የሚያደንቀው ሰው አለው፡፡ ስለዚያ ስለሚወደው፣ ስለሚከተለው፣ ስለሚያደንቀውና ስለሚደግፈው ሰው ምን በጎ ነገር አይናገርም፡፡ ‹ሞያ በልብ ነው› ያለ ነው፡፡ እርሱ ገሚደግፈውና የሚያደንቀው ሰው ተነክቷል ብሎ ያሰበ ጊዜ ግን የስድብ ጅራፉን ያጮኻል፡፡ የተባለው እውነትም ይሁን ውሸት አያዳምጥም፡፡
የስድብ ምላሽ ይሰጣል፡፡ ስለሚወደው ሰው የራሱን ሐሳብ አይሰጥም፣ የራሱን መረጃ አይሰነዝርም፣ የራሱን መከራከሪያ አያቀርብም፡፡ ብቻ ተነካ ብሎ ያሰበ ቀን በለው ነው፡፡
አራተኛው ደግሞ ‹የድርጅት ቃር› ይባላል፡፡ አባል የሆነበት፣ ወይም የሚደግፈው፣ ወይም ነጻ ያወጣኛል የሚለው፣ አለያም ደግሞ የሚንሰፈሰፍለት ድርጅት ይኖረዋል፡፡ ያ ድርጅት በማንም በምንም መነካት የለበትም ብሎ ያምናል፡፡
እርሱ ተነክቷል ብሎ ያሰበ ጊዜ አባልነቱን ወይም ደጋፊነቱን አለያም ደግሞ ተቆርቋሪነቱን የሚያስመሰክረው የሰማይ ስባሪ የሚያህል ስድብ በማውረድ ነው፡፡ ድርጅቱን የሚጠብቀው በስድብ አጥሮ፣ በርግማን ከትሮ ነው፡፡
ዋና ዋናዎቹ ‹የፌስዳቢ› ጎሳ ቤተሰቦች እነዚህ ቢሆኑም አነስተኛ አባላት ያሏቸው ሌሎች ታናናሽ ቤተሰቦችም እንዳሉ ተረጋግጧል፡፡ እንደዚህ ጎሳ ውጥንቅጡ የበዛ ጎሳ የለም ይባላል፡፡ የአንድነታቸው መሠረት ቋንቋቸው ስድብ መሆኑ ነው፡፡ በጎሳው ዘንድ እጅግ ተወዳጅ የሆነው ባህላዊ ዘፈን ‹ፌስዳቢዬ ናና› የተሰኘው ዘፈን ሲሆን አርቲስት ጥረጊው በዘመናዊ መልኩ ተጫውታዋለች፡፡
‹ፌስዳቢዬ ናና
ጨርግደህ፣ ጠራርገህ፣ ለድፈህ፣ መርገህ
የቋሚውን አንገት ታስደፋለህና፡፡
‹ፌስዳቢዬ ናና
እንደ አጭር ምንሽር ስድብ ታጠቅና
እንደ ፀጉር ሠሪ ስድብ ጎንጉንና
ሲሄድ ያየኸውን ብሎ ቀና ቀና
ጥረበው ፍለጠው ፌስዳቢዬ ናና ›

Read 11811 times