Saturday, 14 May 2016 12:53

ከመጻሕፍት ጋር የሚያወዳጅ - ባርና ሬስቶራንት

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ከ10 ብር እስከ 34 ሺ ብር የተገዙ መጻህፍት ይገኛሉ
በቅርቡ “The Book Cafe” ይከፈታል ተብሏል
ካፌው ሲከፈት በዓመት 3 መጻህፍትን በነጻ ያሳትማል

     በተለምዶ 22 ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ልዑል ሲኒማ የሚገኝበት “አናት ህንፃ” ፊት ለፊት አንድ ባርና ሬስቶራንት ያገኛሉ፡፡ ከስሙ ጀምሮ ከለመድናቸው ባርና ሬስቶራንቶች በእጅጉ ይለያል። እግርዎ አንዴ ወደ ውስጥ ከዘለቀ ወደ የትኛውም ክፍል ሲገቡ (መፀዳጃ ቤትና በረንዳውን ጨምሮ) በሚያዩት ነገር ግራ ሊጋቡ አሊያም ሊደመሙና ሊደነቁ ይችላሉ፡፡ ባሩም ሬስቶራንቱም፣ መፀዳጃ ቤቱም፣ በረንዳውም የሚያመሳስላቸው በመጻሕፍት የተከበቡ መሆናቸው ነው፡፡ በዓለም ላይ አሉ የተባሉ ዝነኛ መፅሐፍት እዚህ ይገኛሉ፡፡ ምን መፅሐፍት ብቻ ---- በአገሪቱ ያሉ የህትመት ውጤቶችም አይቀሩም፡፡ ደንበኞች መፅሄትና ጋዜጦችን ከትኩስ ቡና ጋር ያወራርዳሉ፡፡ ንባብ ክፍያ የለውም፡፡  
መፅሐፍቱ አይነታቸው ብዙ ነው፡፡ የርዕዮተ ዓለም ቢሉ፣ የፍልስፍና አሊያም ግለ ታሪኮች፣ የ60ዎቹ ፖለቲካ መጻህፍት፣ የአማርኛ ልብወለዶች፣ የጥናትና ምርምር ሥራዎች --- ብቻ የሚነበብ ሞልቷል፡፡ ይህ በከተማችን ምናልባትም በአራችን ለየት ያለ የመዝናኛም የማንበቢያም ቦታ #ዘ ቡክ” ባርና ሬስቶራንት ይባላል፡፡ ለስጋም ለነፍስም የሚሆን ምግብ የሚገኝበት ሥፍራ በሉት፡፡ እንዲያው ለነገሩ ባለቤቶቹን ምን አሳስቧቸው ይሆን ለደንበኞቻቸው መረጃና ዕውቀት እንዲህ ጭንቅ ጥብብ ያሉት፡፡ ለነገሩ ሌላም ዕቅድ አላቸው፡፡ በቅርቡ “ዘ ቡክ ካፌ” የተባለ ቡና ብቻ እየተጠጣ የሚነበብበት ካፌ እንደሚከፍቱ ለአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ለናፍቆት ዮሴፍ ነግረዋታል፡፡ ይህ ካፌ ሲከፈት ኢትዮጵያ ውስጥ በገንዘብ ማጣት መፅሐፍ ማሳተም ያቃተው ፀሐፊ (ደራሲ) አይኖርም፤ይላሉ የባርና ሬስቶራንቱ ባለቤት አቶ ሀብቶም ገ/ሊባኖስ፡፡ እንዴት? የመጀመሪያ ድግሪያቸውን በማኔጅመንት፣ሁለተኛ ድግሪያቸውን በሂዩማን ሪሶርስ እንዳገኙ ከሚናገሩት አቶ ሀብቶም ገ/ሊባኖስ ጋር ሪፖርተራችን ያደረገችውን አስደማሚ ቃለምልልስ እንዲህ አጠናቅረነዋል፡-  
 “ሰለብሪቲ” የተሰኘውን ባርና ሬስቶራንት እንዴት እንደከፈቱ ቢያጫውቱኝ?
አዎ፤“ሰለብሪቲ” የተከፈተው የኢትዮጵያ አርቲስቶች የሚገናኙበትና ሰብሰብ ብለው የሚጨዋወቱበት ሥፍራ እንዲሆን ታስቦ ነው። ውጤታማ ሆነና ጥሩ ነገር አየን፤ከዚያ ደግሞ “ዘ ቡክ”ን ከፈትን፡፡
“ዘ ቡክ” ባርና ሬስቶራንትን ለመክፈት እንዴት አሰቡ፤ምክንያቱም በአገራችን የተለመደ አይደለም----
እንደሚታወቀው በተለይ የኢትዮጵያ ፀሐፊያንና ደራሲያን በየቦታው ነው ያሉት፤መፅሐፋቸውም ዲስፕሌይ የለውም፡፡ ምናልባት በዓመት አንድ ጊዜ የሚዘጋጅ አውደ ርዕይ ጠብቀው ነው መፅሃፋቸውን የሚያሳዩት፤ስለዚህ አንድ ዲስፕሌይ ማግኘት አለባቸው በሚል ነው የ “ዘ ቡክ”ን ሀሳብ ያመጣነው። ለወንድሞቼ ሳማክራቸው በጣም ደስተኞች ነበሩ። ወንድሞቼ አንድ ሀሳብ ስታቀርቢላቸው፣እንዴት እንደሚያዳብሩት ብታይ ይገርምሻል፡፡ ጎበዞች ናቸው፡፡ አሁን “ዘ ቡክ” ለዚህ በቃ ማለት ነው፡፡
“ዘ ቡክ” የተከፈተው መቼ ነው? ምን ያህል መፅሐፍትን ይዞ ጀመረ? አሁንስ ምን ያህል መፅሐፍት በውስጡ ይገኛሉ?
የተከፈተው ከሶስት ወር በፊት ነው፤ሲከፈት መኖሪያ ቤታችን ውስጥ የነበሩ አንድ ሺህ ሀምሳ (1050) መፅሀፍት አምጥተን ነው የደረደርነው። አሁን ከሁለት ሺህ በላይ አለም ላይ አሉ የተባሉ መፅሐፍትን ይዘናል፡፡ ይህን አላማችንን ያዩ ምሁራን፣ እዚህ ሻይ ቡና ለማለት የሚመጡ ደንበኞች በስጦታ እየሰጡን ቁጥራቸው ከፍ እያለልን ይገኛል። መፅሀፍት እቤትሽ አንብበሽ ስታስቀምጫቸው ጌጥ ብቻ ነው የሚሆኑት፤እንዲህ ዓይነት ቦታ ስታመጫቸው ግን በርካታ ሰው ያያቸዋል፤ብዙ ሰው ቡና ፉት እያለ አንዳንድ ቁም ነገሮችን ጨብጦበት ይወጣል፡፡ የማንበብ ልማድ ይዳብራል፤በርካታ ጠቀሜታ አለው፡፡
 በእርግጥ እናቴ መፅሐፍቱን ከቤታችን ይዤ ስወጣ፣ ቤቱ ጭር አለብኝ ብላ ቅሬታ ተሰምቷት ነበር፡፡ ወይ ተኩልኝ አለበለዚያ መኖሪያዬን እዚህ አድርጉልኝ እስከማለት ደርሳለች፤እስከ 8ኛ ክፍል ተምራለች፤ጥሩ የማንበብ ልምድም አዳብራለች፡፡
ተዘዋውሬ እንዳየሁት ብዙ አይነት መፅሐፍት አሉ፡፡ እንደው በዋጋ ደረጃ ውድ የሚባለው የትኛው መፅሐፍ ነው? እኔ መንገድ ላይ አግኝቼ የገዛሁትን የአቤ ጉበኛ መፅሐፍም እዚህ አይቸዋለሁ ----
በነገራችን ላይ መፅሐፍን በዋጋ መተመን ያስቸግራል፡፡ አንድ መፅሀፍ ይነስም ይብዛም የራሱ የሆነ ፋይዳ ይኖረዋል፡፡ ዋጋው መብዛቱና ማነሱ የመፅሀፉን ይዘት አይወክልም፡፡ የሆነ ሆኖ የአቤ ጉበኛ መፅሐፍ የተፃፈው በእንግሊዝኛ ቢሆን ከ60ዎቹ የፖለቲካ መፅሀፍት ግንባር ቀደም ይሆን ነበር፡፡ በአማርኛ ቋንቋ በመገደቡ ዛሬ መንገድ ላይ አስር ብርና ከዚያ በታች ቢሸጥ አይገርመኝም፡፡ እኛ እዚህ ሼልፍ ውስጥ ስናስቀምጠው ሰው እቤቱ ጥሎት ከነበረ አስታውሶ እንደገና ሌላ ሰው እንዲጠቀምበት ያደርጋል፡፡ አሁን እኛ ጋ የፕሮፌሰር ጆሴፍ ስቲግሊትዝ ከመጀመሪያው እስከ መጨረሻው “Globalization and Its Discontents” እስከሚለው ድረስ አለን፡፡ ይህ ሰው የኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ ሌክቸረር፣ የዓለም ባንክ ከፍተኛ ኢኮኖሚስት ሆኖ ያገለገለ ነው፡፡ በተለይ የመጨረሻው መፅሐፉ ከኢኮኖሚ አንፃር ኢትዮጵያንና መለስ ዜናዊን አስመልክቶ የሰጠው ትንታኔ በጣም የሚገርም ነው፡፡ የዚህ ምሁር “Free Fail” የተሰኘ መፅሀፍ አለ፤በአንድ ሺህ ሰባት መቶ ዶላር ከለንደን ነው ያስመጣነው፡፡ እዚህ እኛ ባርና ሬስቶራንት ውስጥ ይገኛል፡፡ ትልቁም ዋጋ እስካሁን ይሄ ነው፡፡ በዋጋ ደረጃ ቅድም እንዳልሽው ባለ 10 ብርና ባለ 1700 ዶላር አለ ለማለት ነው፡፡ ይዘታቸው ሲመዘን ግን የ10 ብሩ ከ1700 ዶላሩ የሚተናነስ አይደለም፤ የጊዜና የመገኘት ሁኔታው ልዩነት እንጂ፡፡
በዚህ ባርና ሬስቶራንት ውስጥ የሚገኙ መፅሐፍትን ደንበኞች በምን መልኩ ነው መጠቀም የሚችሉት?
ደንበኞች እዚህ ቡና እየጠጡ የትኛውንም መፅሀፍ፣ ጋዜጣም ሆነ መፅሄት አንብቦ የመመለስ መብት አላቸው፡፡ በሌላ በኩል እዚህ የታሪክ፣ የርዕዮት ዓለም፣ የልቦለድ፣ የጥናት ውጤቶች ወዘተ-- ምንም የሌለ የለም፡፡ አንድ ሰው መጥቶ ይህን መፅሐፍ ለጥናትና ምርምር እፈልገዋለሁ፤በማጣቀሻነት እጠቀመዋለሁ፤ ለአገሪቱ ይበጃል፤የሚል ከመጣ ደግሞ ደግመን የማናገኘው የመጨረሻ ውድ መፅሐፍ እንኳን ቢሆን በውሰት እንሰጣለን፡፡ እዚህ ዲስፕሌይ የሆነው ለጌጥ ሳይሆን ለዚህ ዓይነት ፋይዳ ነው፡፡ የራሴ ኮርነር እንዲኖረኝ ፍቀዱልኝ የሚል ደራሲም ካለ ኮርነር ይሰጠዋል፡፡ በረንዳ ላይ የአዳም ረታ ኮርነር እንዳለ ተመልክተሻል፡፡ ቤቱን እኛ እንክፈተው እንጂ የህዝብ መማሪያ እንዲሆን ነው የምንፈልገው፡፡
አንድ ግለሰብ መፅሐፍ መዋስ ቢፈልግ፣ በምን ዋስትና መዋስ ይችላል?
እንግዲህ እኛ መፅሐፍ አውሱኝ ለሚለው ሁሉ አናውስም፡፡ ለምናውሳቸው ደግሞ መታወቂያ አንጠይቅም፡፡ ደንበኞቻችንን እናውቃለን፤ እንመዝናቸዋለን እናውሳለን፡፡ እስካሁን ወስዶ ያስቀረብን የለም፤ ሲያቆዩ እንኳን ደውለው ፊልድ ወጥቼ ነው፣ እንዲህ ሆኜ ነው ብለው ያሳውቃሉ፡፡
ባርና ሬስቶራንቱን ሲያስጎበኙኝ በቅርቡ ለሚከፈት ቤተ-መፃህፍት የተዘጋጀ ቦታ አሳይተውኛል፡፡ መቼ ነው የሚከፈተው? ያኔ በሬስቶራንቱ ውስጥ ያሉት መጻህፍት ተሰብስበው ቤተ-መፃህፍት ይገባሉ ማለት ነው?
እነዚህ የ “ዘ ቡክ” ባርና ሬስቶራንት ናቸው፤አይነኩም፡፡ ቤተ-መጻህፍቱ በሌሎች በግዢም በስጦታም በሚሰበሰቡ መፅሐፍት ነው የሚሞላው፡፡ የ“ዘ ቡክ ካፌ” ስራ ከላይብረሪው ነው የሚጀምረው፡፡ በረንዳ ላይ አንዱ ዲስፕሌይ በየሶስት ወሩ በአዳዲስ መፅሀፍት ይቀየራሉ፡፡ ሌሎቹ ቋሚ ናቸው፡፡
 ቤቱ ምግብና መጠጥ ይሸጣል፡፡ ንባብና መጠጥ አብረው ይሄዳሉ ብለው ያስባሉ?
ጥሩ ጥያቄ ነው፤ስለተነሳ አመሰግናለሁ፡፡ አብዛኛው ሰው ቡና እየጠጣ ነው የሚያነበው። እኛ  ዋና አላማችን ሰው እየጠጣ ባያነብ እንኳን መፅሐፍቱን አይቷቸው፣ ነገ ቤቱ ሲሄድ ስራ እንዲሰራባቸው እንዲያነባቸው ማስታወሻ መስጠት ነው፡፡ በነገራችን ላይ ቢራም ዋይንም እየተጎነጩ በተመስጦ የሚያነቡ አሉ፡፡
ቤቱም ብዙ ጫጫታና የሚጮህ ሙዚቃ የለበትም፡፡ እዚህም የሚመጡ ደንበኞች በአብዛኛው ከቤቱ ድባብ ጋር አብረው የሚሄዱ ናቸው፡፡ ለምሳሌ ፀሐፊዎች፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች፣ ምሁራን ---ወዘተ፡፡ መቀመጫውም ድጋፍ ያለው ምቹ ሶፋ ነው፡፡ ብዙዎቹ አንድ ሁለት እያሉ በጥልቀት የሚወያዩ ምሁራን ናቸው፡፡ ቤቱ ሰዎች እንዲሰክሩ የሚጋብዝ ድባብ የለውም፡፡ ሰው ቡና ወይ ሻይ ብቻ እየጠጣ፣ ቀን ብቻ እየተገናኘ መወያየት፣ ማንበብ ሊሰለቸው ይችላል፡፡ ይሄ እንደ አማራጭ ከስራ በኋላ ሰዎች ተሰባስበው ፍሬ ያለው ነገር የሚወያዩበት ነው፡፡
ባር ሁሌ መስከሪያና የፀብ መነሻ መሆኑ ቀርቶ ሰዎች እያረፉ የሚዝናኑበት፣እውቀት የሚገበዩበት የማይሆነው ለምንድን ነው ከሚል እሳቤ ነው ይህን ሁሉ የምንደክመው፤ግን ደስተኞች ነን፤ዓላማችንም ግቡን የሳተ ሆኖ አላገኘነውም፡፡ አንዳንዴ ሰዎቹ እየተጎነጩ የሚያነሷቸው ሀሳቦች የሚገርሙ ናቸው። እዚህ ተዋውቀው ጓደኛ የሆኑ፣ መፅሐፍ እስከ መዋዋስ የደረሱ ሰዎችን ስመለከት ደስታ ይሰማኛል፡፡
 ከዚሁ ከመፅሐፍት ጋር ግንኙነት ያለው አዲስ ስራ እንዳሰባችሁም ሰምቻለሁ፡፡ እስቲ ስለሱ ያጫውቱኝ?
እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ በቀጣዮቹ ስድስት ወራት ውስጥ “The Book Cafe” የተሰኘና ቡና እየተጠጣ ብቻ የሚነበብበት ካፌ ለመክፈት ዝግጅት ጨርሰናል፡፡ ይህ ካፌ ሲከፈት ኢትዮጵያ ውስጥ በገንዘብ ማጣት መፅሐፍ ማሳተም ያቃተው ፀሐፊ (ደራሲ) አይኖርም፡፡
ያብራሩልኝ ---- እንዴት ማለት?
በዓመት ሶስት መፅሐፍትን በነፃ ለማሳተም እቅድ ይዘናል፡፡ ካፌው የኢትዮጵያን ቡና ያስተዋውቃል፤ ኢትዮጵያ ውስጥ የተፃፉ መፅሐፍት ማሰባሰብ ላይ ይተጋል፣ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ለህትመት በቅተው የነበሩ በማንኛውም ጉዳይ ላይ የሚያተኩሩ መፅሐፍት ተለቅመው፣ ታድነው ወደ ካፌው ይገባሉ፡፡ ይሄ ማለት የግል የሆነ ልክ የወመዘክር አይነት ቤት ነው የሚሆነው፡፡ ይሄን በወንድሞቼ በኩል አሳካለሁ፡፡ እኔ ኖርኩም አልኖርኩም እነሱ ያሳኩታል፡፡
ሥራችሁ ከመጻህፍት ከአርቲስቶችና ከኪነጥበብ ጋር ጥብቅ ቁርኝት ያለው ይመስላል፡፡ ከዚህ ቀደም በስራቸው ውጤታማ የሆኑ አርቲስቶችን እንደሸለማችሁና ነገም በዚሁ ሬስቶራንት የትግርኛ ዘፈን ግጥም ደራሲውን ዳዊት ሰለሞንን እንደምትሸልሙ ሰምቻለሁ ----
አዎ ኪነ ጥበቡም አንዱ እሴታችን ነው፡፡ ከዚህ በፊት የሸለምናቸው አሉ፡፡ አሁን የትግርኛ ዘፈን የጀርባ አጥንት የሆነውን ዳዊትን እሁድ ምሽት እንሸልማለን፤ሽልማቱ ሰርፕራይዝ ስለሆነ ዝርዝር ነገር አልናገርም፤ በሰዓቱ ተገኝተሽ መመልከት ትችያለሽ፡፡     



Read 1815 times