Saturday, 21 May 2016 16:10

ሰውና ድክመቱ፤ እዚህም እዚያም!

Written by  ዓለማየሁ ገላጋይ
Rate this item
(2 votes)

የዛሬ አሥራ ሁለት … ወይም አሥራ ሦስት ዓመታት ገደማ …
…. ሀዋሳን ለመጀመሪያ ጊዜ አየኋት፡፡ ነገር ፈላጊ ዝናብ ተንኩሷት የሚፏልለው አቧራዋ አድፍጧል፡፡ ሁሉን መርማሪ ልሁን ባይ ነበርኩና አጎንብሼ መሬቱን ዳሰስኩት፡፡
ዱቄት የተነሰነሰበት አምባሻ የዳሰስኩ እስኪመስለኝ ለስልሷል፡፡ ሙቀቷ ግን ለዝናቧ አልተጎናበሰም፡፡ እንደውም “ምን ሲደረግ?” ያለ ይመስል በወበቅ ልብስ ለማስወለቅ ይተናነቃል …
… ሀዋሳን ሳላውቃት በጋዜጣ ለማስተዋወቅ መምጣቴ ለእኔው አስገርሞኝ ፈገግ አልኩ፡፡ የማያውቅ ያስተዋውቃል? ስል እራሴን ጠየኩ፡፡ ወለፈንዲ ይሏል ይሄ ነው፡፡ የሥነ ማህበረሰብ (Anthropology) ዘመናዊ ድምዳሜ እንደ እኔ ያለ እንግዳ ሰው፣ ለእንግዳ ማህበረሰብ ጥናት ልከኛ እንደሆነ ይጠቁማል፡፡
እንደውም በሁሉም ነገር መደነቁ ሳይረግብ ጥናቱን ቢያከናውን ይመረጣል ይላል፡፡ አለበለዚያ ይላመድና ችላ የሚለው ይበዛል፡፡
ሀዋሳ ኮረዳ ከተማ ናት፡፡ ነባርና ባህላዊ መሽኮርመሟን ዘመናዊ ግዴለሽነት ሊረታው የሚተናነቃት፡፡ ጉራማይሌነት የጎላባት፡፡ የራሷ የሆነና ያልሆነ ፍልሚያ የገጠመበት መልክ አላት፡፡ ለእኔ ሁሉም ነገር አዲስና እንግዳ ነገር ነበር፡፡ ሌላው ቀርቶ በጋሪ ላይ የተጫኑት ሙዞች ግራ አጋብተውኝ እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡ እንደ መጥረቢያ ብረት የተጠፈጠፈ ሙዝ ስመለከት የመጀመሪያዬ ነበር፡፡ የሙዝ ዝንጥፍ ከእነ ቅርንጫፉ ጃርት መስሎ መቅረቡ ለእኔ እንግዳ ነገር ነበር፡፡
ያኔ ሀዋሳን ለማስተዋወቅ ከጣርኩበት ውጣ ውረድ በላይ ሀዋሳ እኔን ከተፈጥሮዬ ጋር ያስተዋወቀችበት ገጠመኝ የዕድሜ ልክ ስንቄ ሆኖ ቀርቷል፡፡ ያኔ ሰው ሌላውን ከሚያስተዋውቅ እራሱን ቢጠይቅ ምን ያህል በበጀው ስል የደመደምኩበት ገጠመኝ ነበር፡፡ እንዲህ…
… ወደ ሀዋሳ ጤና ቢሮ ጎራ ብዬ አንዳንድ መረጃዎችን ቃረምኩ፡፡ መረጃዎቹ ኤችአይቪን ከመከላከል አኳያ ተስፋ የሚጣልበት ድርጅት እንደተቋቋመ ጠቆሙኝ፡፡ ሊቀመንበሯ ወ/ሮ ብርሃኔ ነበረች፡፡ አገናኙኝ፡፡ ክብ ፊት፡፡ የቀነበረ መልክ አላት፡፡ በፈገግታ ተቀበለችኝ፡፡ (ባልሳሳት) የማህበሯ ሥም “ንጋት የሀዋሳ ሴቶች የፀረ ኤችአይቪ ማህበር” ነበር፡፡ ወ/ሮ ብርሃኔ ቀደም ሲል “የተስፋ ጎህ ኢትዮጵያ” የሀዋሳ ቅርንጫፍ ኃላፊ ነበረች፡፡ እሱን ትታ ነው ፆታ ነክ ማህበር ያቋቋመችው፡፡
ለምን?
ወ/ሮ ብርሃኔ ፊቷ ላይ የወጣችው ፀሐይ የጠለቀች  መሰለች፡፡ ለአፍታ ዝም ብላ ቆየችና በረጅሙ ተነፈሰች፡፡ ጠበኳት፤ “እንዴት እንደምነግርህ አላውቅም …” አለችኝ፡፡ “ግዴለም እንዴትም አድርገሽ ንገሪኝ” አልኳት፡፡
የተደላደለ ሰውነቷ በጥልቅ መሰረት ላይ እንደተገነባ ሁሉ መነቃነቅ ጭንቁ ይመስላል፡፡ ግን ያላትን ያህል ቅልጣፌ አላጣችም፡፡ በመነሳት የቃለ ምልልስ ቅርፅ የያዘ አቀማመጣችንን አፍርሳ አጠገቤ ተቀመጠች፡፡
“አየህ፤ ተራ የፆታ መቆርቆር ኖሮ ይሄን ማህበር አላቋቋምኩትም፡፡ በተጨባጭ ሳየው የቆየሁት ነገር ህመም እየሆነ ስላስቸገረኝ ነው” አሁንም በረጅሙ ተንፍሳ፤ “ስንቴ እንበደል?” ስትል ጠየቀችኝ፡፡
የምለው ግራ ገብቶኝ ዝም አልኩ፡፡
“የተስፋ ጎህ ቅርንጫፍ ሀላፊ እያለሁ የሚያሙ ብዙ ነገሮች አጋጥመውኛል፡፡ አብዛኛዋ ሴት ለህመሙ የተጋለጠችው በራሷ ምክንያት አይደለም፡፡ በተለይ ባለትዳር ሴት … እሱን እንተወውና እዚያ አዲስ አበባ ያሉት የማህበሩ አንዳንድ አመራሮች ፊውዳልነት እየተሰማቸው ከመጡ ቆዩ፡፡ አዲስ ሴት አባል መጥታ እዚህ ስትመዘገብ መልከ መልካም ከሆነች ፎቶዋን እያዩ ወደ አዲስ አበባ እንድትላክላቸው ይጠይቃሉ፡፡ ያማል! ያቺ ሴት ወደዚያ ከሄደች በመደለል ወይም በማስፈራራት ሌላ ነገር …. ስንቴ እንበደል? እነዚህን ሴቶች ነፃ ለማውጣት ያቋቋምኩት ማበር ነው፡፡”
ዝም! የተደላደለ እውነትን የሚያዛባ መልስ ነበር፡፡ ያኔ በግለሰቦችና በጥቂት ሰዎች ላይ እንዳኮርፍ የሚገፋፋ ስሜት አድሮብኝ እንደ ነበር አስታውሳለሁ፡፡ ሰዎቹ በግል ድክመታቸው ተጠልፈው እንደተወለካከፉ ቆጥሬው እነሱን ባላገኝም ከምስላቸው ጋር ተሟግቼ ለመርታት ዳድቶኝ ነበር፡፡ የሰው ልጅን እና ዓለምን ፍፁም አንፅቶ መመልከት የሚያስከትለው ድምዳሜ ድክመቴ እንደሆነ እስካውቅ ድረስ ቁጣው ከእኔ ጋር ቆየ፡፡ ሰውንና ዓለሙን በምልአት ማወቅ አይከጀል ይሆናል፤ ያም ሆኖ “ሰውን ሰው ያደረገው ድክመቱ ነው” ለማለት የሚያስችሉ ምሳሌዎችን ለማግኘት የሚገድ አይሆንም፡፡ ያኔ ለሰው ልጅ አፈጣጠር ማዘን ይከተላል፡፡ “በእንዴት ያለ ድክመቱ ላይ እንዴት ያለ መስቀል ተሸክሞ፣ ምን ያለ ተራራ እንዲወጣ ተፈረደበት?” ያስብላል፡፡ “በእኛ ይብቃ፣ ትውልድ ይዳን” የሚል መሪ ቃል ሥር እንኳን ሆን ተብሎ በስህተትም የሚዛነፍ ነገር የሚኖር አልመሰለኝም ነበር፡፡ ሁሉም አእምሮውንና ልቡን በገዛ ጓጉንቸር እንዳይከፈት አድርጎ በዘጋበት በዚያ ወቅት ለመጠቋቆሚያነት እራስን አሳልፎ ከመስጠት ወዲያ ምን አለ? ጊዜ የፈቀደው ነብይነት አልነበረም? የሰው አይን እንደ አንበሳ የሚሰብረው ፍለጋ ሐሜትን ፈለግ አድርጎ በሚንጎማለልበት በዚያ ወቅት “ኑ እዚህ አለሁ” ማለት ከሰውነት ውጭ አያስመድብም? … ግን እዚያም ሰውና ድክመቱ አሉ፡፡ ወ/ሮ ብርሃኔ እንደ አውሎ ነፋስ የገለበችው “ክንብንቤ” መራቆት እንዲሰማኝ አደረገኝ፡፡ የተነገረኝ እውነት ሆነ አልሆነ እዚያ ሰውና ድክመቱ አሉ፡፡ ሥጋ በመንፈስ ላይ ቢያደፍጥ እንጂ ጨርሶ አይረታም፡፡ የመብላትና የፍትወት ፍላጎት ከመናኒያን ደጅ እንኳን ጨርሶ ፈቅ የማይሉ የሰው ልጅ ሁሉ ንቁ ጠላቶች ናቸው፡፡ በይበልጥ እንደ ልቡ መብል ያገኘ ያለ ፍትወት ጥያቄ ማደር የማይወጣው አቀበቱ ነው፡፡ መንፈሳዊዎቹን እንኳን “ህልመ ሌሊት” እና “ሶፊያ” በሚል የሚጠሩት የፍትወት እንቅፋት መንገዳቸውን ሞልቶታል፡፡ ምክንያቱም እዚያም ሰውና ድክመቱ አሉና፡፡
በተፈጥሮ ህግ መብላት ህይወትን ማቆየት ነው፡፡ ህይወት የሚቆየው ደግሞ ዘር ለመተካት ነው፡፡ ዘር መተካት ዞሮ ህይወት ማቆየት ይሆናል፡፡ የሰው ልጅ የዚህ አዙሪት ተሽከርካሪ ባለዕጣ ነው፡፡ ህይወት ለሰው ልጅ ፍርጃ ከመሆን እራሷን የምትሸሽገው በመብላትና በፍትወት ውስጥ ደስታን በማኖሯ ብቻ ነው፡፡ ደስታን በመሻት በህይወት ተኮድኩደን በኑሮ እንገፈግፋለን፡፡ ዘር መተካት እስከመጨረሻዋ እስትንፋስ ድረስ የምንከፍለው ዕዳችን ነው፡፡ ስለ ዘር መተካት አካል ቢደክም እንኳን ፍላጎት አይረግብም፡፡ ዓለም እራሷ የመብላትና የፍትወት ውጤት ናት፡፡ “የከንቱ ከንቱ፣ ከንቱ ነው” እስክንለው ድረስ የምናከማቸው መብላትና ፍትወትን ነው፡፡ ወርቅ ውስጥ የመብላትና የፍትወት ልኬቶች አሉ፡፡ ሐብት መከመር፣ ህንፃ መገተር፣ አየር ማሽከርከር … ከበስተጀርባው መብል የመራብና ፍትወት የመጠማት ፍርሃት አለ፡፡ ከመጥገብና ከወሲብ በኋላ ዕዳን የመክፈል ፍፁም ሰላምና ድካም የሚሰፍነው ለዚህ ነው፡፡
ማርቀቅና ማጥለቁን ትተን ወደ “መሬት” እንውረድ፡፡ ብርሃኑ ዘሪሁን እንደ ቡና ሥርዓት በሦስት የሚያከትም ታሪክ ቀመስ ልቦለድ አለው፡፡ “ማዕበል - የአብዮት ዋዜማ፣ የአብዮት መባቻ እና የአብዮት ማግሥት” የሚል፡፡ ለአብዮቱ መፈንዳት በማቀጣጠያነት በአይን ጐብኝቶ ልቦለዱን እንደፃፈው “የካቲት” መፅሔት በ1972 ዓ.ም ባደረገለት ቃለ ምልልስ ላይ ገልጿል፡፡ እዚያ ረሃብ በለሸለሸውና ባሟሸሸው ህዝብ መካከል ሰውና ድክመቱ አልቀሩም፡፡
እንዲህ ይገልፀዋል፡-  “ሕይወት እስካለ ድረስ የተፈጥሮ ፍላጐቶች፣ የተፈጥሮ ስሜቶችና ባህርዮች አሉ፡፡
በዚያ በተጨናነቀ ሰፈር (መጠለያ) መካከል ወንድና ሴት በጋቢ ውስጥ ተሸፍነው በደከመ ሰውነት የፍቅር ስሜታቸውን ይወጣሉ፡፡ ሌሎች አይተው እንዳላዩ ያልፏቸዋል፡፡ ለደስታና ለምቾት ኑሮ ተስፋ ቆርጠው የመጨረሻ ኃይላቸውን ለወሲብ ስሜታቸው ብቻ በማዋል እንደተቃቀፉ ምናልባትም ከጭንቀት የተነሣ እንደተጣበቁ ሞተው የሚገኙ ባልና ሚስት አሉ፡፡ ሞት በሚወስደው ህይወት መጠን በዚያ መጠለያ ውስጥ ብዙ ህይወት ይዘራ ነበር” (ገፅ 81)
ተፈጥሮ ጨካኝ አራጣ በሊታ ናት፡፡ ከሰጠችን ይልቅ የምታስገፈግፈን የትየለሌ ነው፡፡ ታመን አንተኛም፣ ደክመን አናርፍም፡፡ ተርበን እንኳን ዕዳ ከመገፍገፍ አንታገስም፡፡
ኡፍፍፍፍ!!  

Read 3824 times