Saturday, 21 May 2016 17:34

የዶ/ር ወልደመስቀል ኮስትሬ ማስታወሻ

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(2 votes)

 መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ስላፅናናን ልባዊ  ምስጋና አቀርባለሁ -ያዕቆብ ወልደመስቀል
   ዶክተር ወልደመስቀል ኮስትሬ በኢትዮጵያ የአትሌቲክስ ስፖርት ታሪክ ባስመዘገቧቸው የላቁ ውጤቶችና ጉልህ አስተዋፅኦዎች ግንባር ቀደም ተጠቃሽ የሆኑ የስፖርት ባለሙያ እና አሰልጣኝ ነበሩ ፡፡ ባለፈው ሳምንት እሁድ በ69 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩ ሲሆን ባለፈው ማክሰኞ በመንበረ ፀባኦት ቅድስት ስላሴ ካቴድራል የቀብር ስነስረዓታቸው  ተፈፅሟል፡፡
በቀብር ሥነ ሥርዓቱ ላይ የኢፌዴሬ ወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር ሚኒስትር አቶ ሬድዋን ሁሴን፣ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት አቶ ብርሃነ ኪዳነማርያም፣ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ አለባቸው ንጉሴ እንዲሁም የኢትዮጵያ ስፖርት ጋዜጠኞች ማህበርን ጨምሮ የተለያዩ አገር አቀፍ የስፖርት ማህበራትና ፌዴሬሽኖችም የአበባ ጉንጉን አስቀምጠዋል። አሰልጣኝ ዶክተር ወልደመስቀል ኮስትሬ ያፈሯቸው በርካታ ታዋቂ አትሌቶች እና ሌሎች ስፖርተኞች  በቀብር ሥነ ሥርዓቱ ላይ ተገኝተዋል፡፡ ታላቆቹ አትሌቶች አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴና ደራርቱ ቱሉም የአበባ ጉንጉን አስቀምጠዋል።
የዶክተር ወልደመስቀል ኮስትሬ የበኩር ልጅ የሆነው ያዕቆብ ወልደመስቀል ሃዘኑ በገጠመን ጊዜ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ በተለያየ መንገድ ስላፅናናን ልባዊ  ምስጋና አቀርባለሁ ሲል በስፖርት አድማስ በኩል መልዕክቱን አስተላልፏል፡፡ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ አለባቸው ንጉሴ፤ የፌደሬሽኑ ዋና ፀሃፊ አቶ ቢልልኝ መቆያ፤ የኦሎምፒክ ኮሚቴ  እንዲሁም የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ባለድርሻ አካላት ፤ አትሌቶች እና መላው የስፖርቱ ቤተሰብም እንደሚያመሰግንም ተናግሯል፡፡ በተለይ የአትሌቶች ማህበር ፕሬዝዳንት የሆነው እና ከዶክተር ወልደመስቀል  ሰልጣኝ አትሌቶች አንዱ የሆነው ስለሺ ስህን  ከመጀመርያ እስከ መጨረሻ አብሮኝ ሆኖ ላከናወናቸው ተግባራት ከልቤ አመሰግናለሁ ብሏል- ያዕቆብ ወልደመስቀል፡፡
‹‹ በጣም ጠንካራ፤ ቆራጥ፤ አቋም ያለው፤ በዲስፒሊን የሚያምን፤ ስርዓት ያለው›› በማለት የአባቱን የዶክተር ወልደመስቀል ኮስትሬን ስብዕና የገለፀው ያዕቆብ፤ በባህርይው ቀጥተኛ እና ንፁህ ፤ አጭበርባሪ እንዳትሆን አዘውትሮ የሚመክር እና በመጥፎ ስሙ እንዳይነሳ የሚፈልግ ነበር ብሏል፡፡
የዶክተር ወልደመስቀል ኮስትሬ የአትሌቲክስ አሰልጣኝነት ዘመን ልዩ ትዝታዎቹን በማስታወስም ያዕቆብ  የአባቱን የሙያ ተመክሮ ለማመልከት ሞክሯል፡፡ ከሁሉ የማይረሳኝ  በሲድኒ ኦሎምፒክ ወቅት ያጋጠመው ሁኔታ ነው የሚለው ያዕቆብ፤ በወቅቱ በኢትዮጵያ የኦሎምፒክ ቡድን  አባላት የነገሩትን የታሪክ አጋጣሚ በማስታወስ ይናገራል፡፡ የኦሎምፒክ ቡድኑ አባላት በስታዲዬም ውስጥ ተቀምጠው በ10ሺ ሜትር ወንዶች የሚካሄደውን ሩጫ በከፍተኛ ጭንቀት እየተመለከቱ ናቸው፡፡ ኃይሌና ፖል ቴርጋት እግር ለእግር ተያይዘዋል፡፡  በወቅቱ ዶክተር ወልደመስቀል ከአትሌቶቻቸው ልምምድ ሲሰሩ እና በውድድር ላይ ሆነው ምክር ሲያቀብሉ እንደሚያደርጉት  የውድድር መነሻ እና መድረሻ አካባቢ ሆነው በርጋታ ሩጫውን እየተከታተሉ ናቸው፡፡ በእያንዳንዱ ዙር ሰዓታቸውን እየያዙ ከዚያም ከኃይሌ ጋር በመግባቢያ ኮዳቸው እየተመካከሩ  በልበሙሉነት የፉክከሩን መጨረሻ ይጠባበቃሉ፡፡ በ10ሺ ሜትሩ የመጨረሻው  ዙር 400 ሜ ላይ ፖል ቴርጋት አፈትልኮ ለመውጣት ሲያኮበኩብ የኦሎምፒክ ቡድን አባላት በሙሉ በባሰ ጭንቅት ተውጠው የሚይዙት የሚጨብጡት አጥተዋል፡፡ ዶክተር ወልደመስቀል ግን ምንም ሳይሸበሩ ውድድሩን ሲመለከቱ ያስተዋሉ የኦሎምፒክ ቡድኑ አባላት ተገርመው ነበር፡፡ በዚያን ወቅት ኃይሌ በመጨረሻዎቹ ሜትሮች ፖል ቴርጋትን በተንደረደረበት የአጨራረስ ፍጥነት ቀድሞት እንደሚገባ እርግጠኛ የነበሩት ዶክተር ብቻ ነበሩ፡፡ ኃይሌ አሸንፎ ከገባ በኋላ የኦሎምፒክ ቡድኑ አባላት ዶ/ር ወልደመስቀልን ጠጋ ብለው እንዴ ያን ሁሉ ስንጨነቅ ምን ተማምነው ነው የተረጋጉት?  ብለው ሲጠይቋቸው የዶ/ር ምላሽ በእያንዳንዱ ዙር ኃይሌም ሆነ ፖል ቴርጋት የነበራቸውን ፍጥነት በስሌት የሚያውቁት እንደነበር፤ ለኦሎምፒኩ አዲስ አበባ ላይ በነበራቸው ዝግጅትም ከኃይሌ ጋር በሰሩባቸው የልምምድ ሁኔታዎች ማንኛውንም ተፎካካሪ ቀድሞ እንደሚገባና እንደሚያሸንፍ እርግጠኛ እንደነበሩ እንደገለፁላቸው አስታውሰው ያጫወቱት እንደነበሩ ያዕቆብ በማስታወስ ለስፖርት አድማስ ተናግሯል፡፡
ሌላው የያዕቆብ ወልደመስቀል ትዝታ መነሻው በ2001 እ.ኤ.አ በካናዳ ኤድመንተን በተካሄደው የዓለም ሻምፒዮና የኬንያው ቻርልስ ካማቴ ኃይሌን በበማሸነፍ ካስመዘገበው አስደንጋጭ ውጤት በኋላ አባቱ ዶክተር ወልደመስቀል ኮስትሬ የሰሩት ተግባር ነው፡፡ ኃይሌ በካማተወ የተሸነፈበት ወቅት በጣም ብዙ የአትሌቲክስ ደጋፊን ያስደነገጠ ውጤት ነበር፡፡ ዶ/ር ወልደመስቀል ግን ከዚህ ሽንፈት መማር አለብን በሚለው ፍልስፍናቸው ለመሥራት የወሰኑት ወዲያው እንደነበር ያዕቆብ ያስታውሳል፡፡ ካማቴ በኃይሌ ላይ ከተጎናፀፈው ድል ከ2 ዓመት በኋላ የዓለም ሻምፒዮና በ2003 እኤአ የተካሄደው በፓሪስ  ነበር፡፡ ዶ/ር ወልደመስቀል በ10ሺ ሜትር የቡድን ስራ ይታወቁ የነበሩትን ኃይሌ፣ ቀነኒሳ እና ስለሺን የ10ሺን ክብር እንዲመልሱ በልዩ ስትራቴጂ እና የልምምድ ፕሮግራም ሲያዘጋጁ ሰንብተዋል፡፡   በፓሪሱ የዓለም ሻምፒዮና በ10ሺ ሜ. የኬንያው ቻርልስ ካማቴ ከ2 ዓመት በፊት ያስመዘገበውን ድል ለመድገም ተስፋ አድርጐ ገባ፡፡  ዶ/ር ወልደመስቀልና አትሌቶቻቸው (እነ ኃይሌ) በቀየሱት የአሯሯጥ ስትራቴጂ ግን የካማቴ ህልም ተጨናገፈ፡፡ 3ቱም አትሌቶች (ቀነኒሳ፣ ስለሺ፣ ኃይሌ) ሁሉንም ተፎካካሪዎቻቸውን ቆርጠው በመውጣት ባስደናቂ የበላይነት በዓለም ሻምፒዮናው ተከታትለው በመግባት ሜዳልያዎቹን ጠቅልለው ሊጎናፀፉ በቁ፡፡
በ1994 የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና ደቡብ አፍሪካ ላይ ሲካሄድም የዶ/ር ወልደመስቀል ኮስትሬ  የሥልጠና  አካሄድ ልዩ ተሞክሮ ማጋጠሙንም አስታውሶ ያዕቆብ ለስፖርት አድማስ አውግቷል፡፡ በዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮናው በረጅም ርቀት ላይ ኃይሌ ገ/ስላሴ ይወዳዳር ነበር፡፡ ከውድድሩ በፊት አንድ ጋዜጠኛ ቀረብ ብሎ  ስለ ውድድሩ ጠየቀው፡፡ ታሸንፋለህ ወይ? በማለት የኃይሌ ምላሽ አዎ! አሸንፋለሁ የሚል ነበር፡፡  ዶ/ር ወልደመስቀል ግን በዚህ ምላሹ ደስተኛ አልነበሩም፡፡ ሠርቻለሁ ተዘጋጅቻለሁ ይባላል እንጂ አሸንፋለሁ ተብሎ መናገር ጥሩ አይደለም፡፡ በውድድር ላይ የሚያጋጥምህን ነገር አታውቀውም ብለውም በቁጣ መከሩት፡፡ በውድድሩ ላይ ከኃይሌ ጋር ፖል ቴርጋትና ፖል ኮች የተባሉ የኬንያ አትሌቶች ተሳታፊ ነበሩ፡፡ በአገር አቋራጭ ውድድር እንደተለመደው በየቦታው እንደ መሰናክል የተቀመጡ ጉቶዎች ነበሩ፡፡ በመጨረሻ ዙር ላይ ኃይሌ መሪነቱን እንደያዘ መሮጥ ቀጥሏል፡፡ በአጋጣሚ የአፍሪካ ሙዚቃ እየተሰማ የሚጨፈርበትን ቦታ ዞር ብሎ ሲመለከት ጉቶ አደናቀፈውና ወደቀ፡፡ ፖልቴ ርጋት በላዩ ላይ በመዝለል አለፈና አሸነፈው፡፡  ኃይሌም ዶ/ሩን በዚህ ምክራቸው አመስግኖ ይቅርታ ጠይቋቸዋል፡፡ ከዚያም ጊዜ በኋላ የአለም አገር አቋራጭ ውድድር አልተወዳደረም፡፡
አትሌቶች ለቅሶ ለመድረስ ሲመጡ ብዙ ታሪኮችን እያጫወቱት እንደሆነ ልጃቸው ያዕቆብ  ወልደመስቀል ለስፖርት አድማስ ይናገራል፡፡ በተለይ  ደግሞ የ3ሺ ሜትር መሰናክል ሯጭ የነበረውና በ2000 እ.ኤ.አ ሲድኒ ኦሎምፒክ ላይ በማራቶን ተወዳድሮ 10ኛ ደረጃ ያገኘው አትሌት ስምረቱ አለማየሁ የነገረውን በመጥቀስ አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡ ዶክተር ወልደመስቀል  ከ100ሜ ጀምሮ እስከ ማራቶን ልዩ የማሰልጠን ብቃት ያላቸው ምርጥ አሠልጣኝ እንደነበሩ በማስታወስ ያወጋው አትሌት ስምረት ፤ በተለይ ከአደጋው በፊት ከዘራቸውን ሳይዙ ዶ/ር ወልደመስቀል ሠርተው የሚያሰሩ አብረው የሚያሯሩጡ፤ ጅምናስቲክ አብረውን የሚሰሩ ባለሙያ ነበሩም ብሎታል፡፡ ከውድድር በፊትና ከውድድር በኋላ ከአትሌቶች ጋር በቅርበት በመወያየት ፤ ግምገማ በማድረግና በግልጽ ምክር በመስጠት ባለውለታችን ነበሩ ሲል አትሌት ስምረት አለማየሁ ለልጃቸው ያዕቆብ ወልደመስቀል ውላታቸውን አስታውሶ ነግሮታል፡፡
ዶ/ር ወልደመስቀል ኮስትሬ በአሰልጣኝነት የሥራ ዘመናቸው በተለይ ሳይንሳዊ የሥልጠና መንገድን እንደሚከተሉ፤ ሂሳባዊ ስሌቶችን በመስራት፤ ግራፎችን በመንደፍ በምርምር እና በከፍተኛ ጥናት ስራቸውን ይሰሩ እንደነበርም ያዕቆብ ወልደመስቀል ለስፖርት አድማስ ያስረዳል፡፡ አትሌቲክስን በልዩ የሙያ ፍቅር ይሰሩበት ስለነበርም በመስራት ሌት ተቀን ሳይሰለች ይሰራ እንደነበር አብሬው ስኖር የታዘብኩት ነበርም ብሏል፡፡ ጠዋት ከአትሌቶቹ ቀድመው ከ11፡00  ሰዓት ይነሳሉ፡፡ ቀኑን ሙሉ በየጫካው በስታድዬም ትራክ ከዚያም በቢሮ ሲሰሩ ውለው አንዳንዴ እስከ ምሽቱ 5፡00 ሰዓት ቆይተው ወደ ቤት ይመለሱ ነበሩ፡፡   አንዳንዴም ለሊቱን ሙሉ የተለያዩ የስልጠና ዘዴዎችን በማስላት ግራፎችን በመንደፍ ሲሰሩ ያድሩ ነበር፡፡ ለአትሌቶቻቸው በሚነድፏቸው የስልጠና ስትራቴጂዎች ክትትላቸው በተለያየ የጊዜ መዋቅር ይቀምሩት እንደነበርም ይገልፃል፡፡ የሚያሰልጥኑት አትሌት ከኦሎምፒክ እስከ ኦሎምፒክ (4 ዓመት) ፤ ከዓለም ሻምፒዮና እስከ ዓለም ሻምፒዮና (2 ዓመት) እንዲሁም  በእለት በእለት  በሚሰራቸው ልምምዶች፤ በሚሳተፍባቸው ውድድሮች የሚያሳየውን ብቃት በመመዝገብ በንቃት ተከታትለው ይሰሩ ነበር፡፡ ብዙዎች የአባቴ ዶ/ር ወልደመስቀል የሥልጠና ሳይንስ በአግባቡ ተሰንዶ እንደማይገኝ እና  በጽሑፍ እንዳልተቀመጠ የሚናገሩት ትክክል አይደለም የሚለው ያዕቆብ፤ ከአጭር እርቀት እስከ ማራቶን ያዘጋጁትና የሰሩባቸው ምርምሮች፤ የልምምድ ፕሮግራሞች እና ጥናቶች እንዲሁም ዳጐስ ያለ የሥልጠና ማንዋል መኖሩን አረጋግጣለሁ ብሏል፡፡
አባቴ በሙያ ዘመኑ እና ህይወቱ የሚያስደስተውና ሁሌም የሚኮራበት ታሪክ ነበረው፡፡ ሁሌም የሚነግረኝም ይህንኑ ነበር ይላል ያዕቆብ፡፡ ‹‹ሀገሬን እወዳለሁ፣ ስደት አልፈልግም፣ ሰንደቅ አላማችን ከፍ ብሎ ሲውለበለብ እጅግ በጣም ደስ ይለኛል፡፡ ገንዘብ ባይኖረኝም የኢትዮጵያ ህዝብ ነው ሃብቴ፡፡ በሚሄድበት ቦታ ሁሉ ከመቀመጫው ተነስቶ የሚያከብረኝ ህዝብ ብዙ ታላቅ ሥራ እንደሠራሁ ያረጋግጥልኛል›› ይለኝ ነበር ብሏል በመጨረሻም፡፡
ዶክተርወልደመስቅሌ ከዚህ ዓለም በሞት መለየታቸውን ተከትሎ በርካታ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎችም ታሪካቸውን በማስታወስ አውስቷቸዋል፡፡ እኤአ ከ1980ዎቹ ወዲህ ኢትዮጵያ በረጅም ርቀት የአትሌቲክስ ውድድሮች ባስመዘገበቻቸው የላቁ ስኬቶች ጀርባ የነበሩ መሃንዲስ በሚል ያደነቃቸው የዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌደሬሽኖች ማህበር መግለጫ፤ አሰልጣኙ ጥብቅ በሆነ የሰነምግባር እና የዲስፕሊን አሰራራቸው ይታወቁ እንደነበር እና አትሌቶች ሪከርዶችን እያስመዘገቡ እንኳን ስነምግባራቸው ከተጓደለ ከመቅጣት አይመለሱም ነበር  በሚል አትቷል፡፡
አሰልጣኝ ዶክተር ወልደመስቀል ኮስትሬ በሙያቸው ካስመዘገቡት ስኬት አስደናቂነት ባሻገር በእንግሊዘኛ ቋንቋ ችሎታቸውም መገረማቸውንም በኢትዮጵያ የሃንጋሪ አምባሳሰደር መግለፃቸውን የአይኤኤኤኤፍ ዘገባ አውስቷል፡፡  ለ14 ዓመታት በትምህርት ባሳለፉባት ሃንጋሪ በ2004 በዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ሻምፒዮንሺፕ እንዲሁም በ2006 እኤአ በዓለንም የጎዳና ላይ ሩጫ ተገኝተውም እንደነበር አምባሳደሩ ሃዘናቸውን በገለፁበት ወቅት አስታውቀዋል፡፡
የዶክተር ወልደመስቀል ኮስትሬ    ትውልዳቸው በሰሜን ሸዋ ተጉለትና ቡልጋ ሲሆን ወላጆቻቸው ገበሬዎች ነበሩ፡፡  በግብርና ሙያቸው ይተዳደሩ በነበሩት ቤተሰባቸው ብዙውን ጊዜያቸውን በእርሻና በከብት ማገድ ስራ ያሳልፉ የነበረ ሲሆን ገና በታዳጊነታቸው የሚያፈቅሩትን ስፖርት በተለያየ መንገድ ያዘወትሩ እና ይከታተሉ ነበር፡፡ አባታቸው ኮስትሬ ልጃቸው በቤተክህነት ትምህርታቸው ገፍተው ቄስ እንዲሆኑ ፍላጎት የነበራቸው ሲሆን፤ እናታቸው ደግሞ በትምህርት ጥሩ ደረጃ ላይ እንዲደርሱ ይወተውቷቸው  ነበር፡፡ የ11 ዓመት ታዳጊ ሲሆኑ ከእናታቸው ዘመዶች እየኖሩ የሚማሩበት አጋጣሚ በመፈጠሩ የትውልድ መንደራቸውን ተሰናብተው አዲስ አበባ ገቡ፡፡  በአጭር ጊዜ ውስጥ ትምህርታቸውን በአዲስ አበባ ለመከታተል ከቻሉ በኋላ   በት/ቤቶች ውስጥ የሚካሄድ የስፖርት ውድድሮች ጠንካራ ተሳትፎ ነበራቸው፡፡  በተለይ በእግር ኳስ ተጨዋችነት  ንቁ ተሳትፎ ያደርጉም ነበር፡፡ በት/ቤት በምርጥ ችሎታቸው እና በጠንካራ የኳስ ምታቸው ያላቸውን ችሎታ  ካስመሰከሩ በኋላ ስማቸው ከቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ ጋር በተያያዘ መነሳት ሁሉ ችሎ ነበር፡፡
በወጣትነት ዘመናቸው ላይ ከእግር ኳስ ባሻገር በአጭርና መካከለኛ ርቀት የአትሌቲክስ ውድድሮች የሚሳተፉ ምርጥ አትሌት የመሆን ፍላጎት አድሮባቸው በዚያው አቅጣጫ በትጋት ተሳትፏቸውን ቀጥለዋል፡፡ በዚህ ልምዳቸውም  እነ ምሩፅ ይፍጠር በነበሩበት ዘመን በአዲስ አበባ ስታድዬም በሚካሄዱ ውድድሮች ተሳታፊ ነበሩ፡፡የከፍተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን እንዳጠናቀቁም ነፃ የትምህርት እድል አግኝተው ወደ ምስራቅ አውሮፓዋ አገር ሀንጋሪ ለትምህርት ከማምራታቸው ከሳምንታት በፊት  በ1964 እኤአ በቶኪዮ ኦሎምፒክ ለሚሳተፈው የአትሌቲክስ ቡድናችን በ800 ሜ እና 1500 ሜትር ለተወዳዳሪነት ተመርጠው ነበር፡፡ ነገር ግን ትምህርት ይሻለኛል በማለት ውድድሩን በመተው ወደ ሀንጋሪ አምርተዋል፡፡  በአጠቃላይ ለ2 ጊዜያት ተመላልሰው 14 አመታትን በወጣትነታቸው ባሳለፉባት  ሀንጋሪ በባዮሎጂ ሳይንስ የትምህርት ዘርፍ የዶክትሬት ዲግሪ ባለቤት ናቸው፡፡የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በአካል ማጎልመሻ ትምህርት ባገኙባት ሀንጋሪ በዩኒቨርሲቲ ጨዋታዎች ኮሌጃቸውን ወክለው በ5,000 ሜትርና 10,000 ሜትር ተወዳድረዋል፡፡ ወደ አገር ቤት ከተመለሱ በኋላ በኮተቤ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ በ1962 ዓ.ም. በስፖርት መምህርነት ሥራቸውን እየመሩ በተጓዳኝ ለብሔራዊ እግር ኳስ ቡድን በአካል ብቃት አሠልጣኝነት ከቆይታም በኋላ የቅዱስ ጊዮርጊስንም በተመሳሳይ አሠልጥነዋል፡፡ በስፖርት ኮሚሽን ውስጥ በከፍተኛ ባለሙያነት ሰርተዋል፡፡የአትሌቲክስ አሰልጣኝነትን የጀመሩት በኮተቤ ኮሌጅ አስተማሪ እያሉ በ70ዎቹ መጀመሪያ ላይ ሲሆን በ1972 የሙኒክ ኦሎምፒክ በሚሳተፈው ቡድናችን ውስጥ ዋና አሰልጣኝ ለነበሩት ንጉሴ ሮባ ምክትል አሰልጣኝ በመሆን ነበር፡፡
 በእነ አበበ ቢቂላ ዘመን ከአትሌቶቹ ውጤታማነት በስተጀርባ የሚጠቀሱት ባለሙያ አሰልጣኝ ንጉሴ ሮባ ነበሩ፡፡ አሰልጣኝ ንጉሴ ሮባ የአበበ ቢቂላ፤ የማሞ ወልዴ፤ የምሩፅ ይፍጠር እና ሌሎች የቀድሞ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ጀግኖችና አትሌቶች  ስኬት ላይ ከፍተኛ ሚና ነበራቸው፡፡
ዶክተር ወ/መስቀል የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ስፖርት በመቀላቀል በአሰልጣኝነት ማገልገል የጀመሩት የቀድሞው ዋና አሰልጣኝ ንጉሴ ሮባ በ1992 እ.ኤ.አ ከተደረገው የባርሴሎና ኦሎምፒክ በኋላ ራሳቸውን በጡረታ ካገለሉ በኋላ ነበር፡፡ በወቅቱም ዶክተር ወ/መስቀል ኮስትሬ በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሸን ውስጥ የቴክኒክ ሀላፊ በመሆን ተቀጥረዋል፡፡ በአጭር ጊዜ ውስጥም ውስጥ የመካከለኛና የረዥም ርቀት አትሌቶች ዋና አስልጣኝ ሆኖው ተሹመዋል፡፡ ከአሰልጣኝ ንጉሴ ሮባ የረዥም ዘመን ግልጋሎት በኋላ   ለኢትዮጵያ አትሌቲክስ የተገኙት ድንቅ ባለሙያ ደግሞ ዶ/ር ወልደ መስቀል ኮስትሬ ሆነዋል፡፡ በአሰልጣኝነት ስራቸውን ሲጀምሩ  የኢትዮጵያ አትሌቲክስ በከፍተኛ የውጤታማነት አቅጣጫ የተነሳበት ጊዜ ሊመጣ ችሏል፡፡ በዶክተር ወ/መስቀል ኮስትሬ አሰልጣኝ ዘመን በኢትዮጰያ አትሌቲክስ ሁለተኛው የውጤታማ አትሌቶች ምዕራፍ ሊከፈት በቅቷል፡፡ ታላቆቹ ሯጮች ደራርቱ ቱሉ፤ ጌጤ ዋሚ፤ ኃይሌ ገ/ስላሴ እና ሌሎች አንጋፋ አትሌቶች በረጅም ርቀት ዓለምን መቆጣጠር የጀመሩበት ጊዜ ተከሰተ፡፡ ከእነኃይሌ እና ደራርቱ በኋላም እነ ጥሩነሽ፤ ቀነኒሳ፤  ሊመጡ ችለዋል፡፡
በተለይ በረጅም ርቀት ስልጠናቸው ጉልህ ለውጥ በማምጣት በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በዓለም ደረጃ ከፍተኛ ዕውቅና ሊያገኙበት የቻሉበትን ስራ ማከናወን የቻሉ ታላቅ ባለሙያ ነበሩ፡፡
ኢትዮጵያ ለዓለም ካበረከተቻቸው ምርጥ ምርጥ አትሌቶች ጀርባ እኝህ ኮስታራ አሰልጣኝ ይገኛሉ፡፡ ከ1992 የባርሴሎና እስከ 2008 ቤጂንግ ኦሎምፒክ ለ16 ዓመታት በዘለቀው የዋና አሰልጣኝነት ዘመናቸው ኢትዮጵያ በዓለም አደባባይ ያኮሯትን የ5000 እና የ10,000 ሜትር አትሌቶች ለውጤት በማብቃት ተጠቃሽ ናቸው፡፡
ዶ/ር ወልደመስቀል የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ብሔራዊ ቡድንን እያሰለጠኑ በተሳተፉባቸው አምስት ኦሎምፒኮች ላይ 28 ሜዳሊያዎችን በድምሩ ለሀገራቸው አስገኝተዋል (13 ወርቅ 5የብር እና 10 የነሐስ ሜዳሊያዎችን) አስገኝተዋል፡፡ ከ8 በላይ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናዎች ላይ በመስራትም ተሳክቶላቸዋል፡፡፡፡ በአትሌቲክሱ ዓለም ለአሰልጣኞች የሚሸለመውን የዓመቱ ምርጥ አሰልጣኝነት ሽልማትን በ2006 ዓለም አቀፍ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የዓመቱ ምርጥ አሰልጣኝ የተባሉ ሲሆን በ2011 እኤአ የአፍሪካ ኮከብ አሰልጣኝ ተብለው በሞሮኮ ማራካሽ የተሸለሙ እና  በ2015 ደግሞ የበጎ ሰው ሽልማትን በስፖርት ዘርፍ አሸናፊም ነበሩ፡፡

Read 3374 times