Saturday, 28 May 2016 15:27

ቬንዝዌላ - የቅዠት አገር

Written by 
Rate this item
(5 votes)

አገሪቱ ለሃብታሙም ለድሃውም ሲኦል ሆናለች፡፡ የፋብሪካ ባለቤት መሆን፣ እዳ ነው፡፡ ትንሽዬ ምግብ ቤት ከፍቶ መስራት እንኳ፤ ትዕግስትን ያስጨርሳል፡፡ በየአመቱ ሰላሳ አይነት የስራ ፈቃዶችን ለማሳደስ መንከራተት የግድ ነው፡፡
ለአንድ ምናብ ቤት ወይም ለአንድ ፋብሪካ ሰላሳ የፈቃድ እድሳት! እንኳን ሰላሳ፣ አንዱን የስራ ፈቃድ ብቻ ማሳደስም መከራ ነው፡፡ ቢቢሲ ያነጋገረው የፋብሪካ ባለቤት፣ በየእለቱ ከሚያጋጥሙት መዓት መከራዎች መካከል፣ ቀላል የሚመስል አንድ ችግር ብቻ በመጥቀስ አስረድቷል፡፡ የመንግስት የቁጥጥር ብዛት አይጣል ነው፡፡
ፋብሪካው በየወሩ ለሰራተኞች “ሶፍት” መስጠት አለበት በሚል የሚደረግ፣ ቁጥጥር ብቻ፣ መከራውን አይቷል፡፡ “ሶፍት” እንደማንኛውም ሸቀጥ፤ በመንግስት ሱቆች ነው የሚቀርበው፡፡ ባለፋብሪካው፣ ቀኑን ሙሉ ወረፋ ይዞ፣ ሁለት ሦስት ሶፍት መግዛት ይችላል - እድለኛ ከሆነ፡፡ ብዙ ጊዜ አይገባኝማ፡፡ ወዲያው ያልቃል፡፡ ሌላኛው አማራጭ፣ በኮንትሮባንድ የገባ ሶፍት መግዛት ነው፡፡ ነገር ግን የኮንትሮባንድ “ሶፍት” መግዛቱ ከታወቀ፤ ከመከራ አያመልጥም - ፋብሪካው ይወረስበታል፡፡ ለሰራተኞች ሶፍት ካላቀረበም፣ ፋብሪካው በመንግስት ይወረሳል፡፡
ማምለጫ የለውም፡፡ ሶፍት እስኪገኝ ድረስ የፋብሪካውን ስራ ለማስቆም ሲገደድ አስቡት፡፡
ግን ይህንንም ማድረግ አይችልም፡፡ ስራ ያቆመ ፋብሪካ በመንግስት ይወረሳል የሚል ህግ ታውጇል፡፡
ቢቢሲ እንደዘገባው፣ የቬንዝዌላ መንግስት ሶሻሊዝምን አስፋፋለሁ በማለት፣ ከአንድ ሺ በላይ ፋብሪካዎችን ወርሷል፡፡ ፋብሪካዎቹን ምርታማ አደርጋለሁ ብሎ ነው የወረሳቸው፡፡ ግን አልቻለም፡፡ አብዛኞቹ የመንግስት ፋብሪካዎች እየሰሩ አይደለም ብሏል - የቢቢሲው ጋዜጠኛ፡፡
የምርትና የሸቀጦች እጥረት እንዲህ እየተባባሰ፣ አገሪቱ ዛሬ ገደል አፋፍ ላይ ደርሳለች፡፡
ነዋሪዎችን በማነጋገር ከቬንዝዌላ ዘገባ ያቀረበችው የሲኤንኤን ጋዜጠኛ፣ የሚላስ የሚቀመስ ምግብ እየጠፋ ነው ብላለች፡፡ በዋጋ ቁጥጥር ሳቢያ፣ ሸቀጦች ሁሉ ከገበያ ጠፍተዋል፡፡
እናም የአገሬው ሰዎች፣ ዘይትና ዱቄት፣ ጨውና ስኳር፣ ቲማቲምና ሳሙና ለመግዛት ከመንግስት ሱቆች ደጃፍ ከንጋት እስከ ምሽት ይሰለፋሉ፡፡ የሱቁ ደጃፍ ላይ የተጀመረው ወረፋ፣ ጥጋጥጉን እስከ ማዶ ሄዶ፣ መስቀለኛው መንገድ ላይ ወደ ግራ ታጥፎ፣ ሩቅ ጫፍ ድረስ ይቀጥላል፡፡
ከአምስት ሰዓት በኋላ ወረፋ የደረሰው ጐልማሳ፣ ዱቄትና ወተት አላገኘም፡፡ ቢጨንቀው፣ ሁለት ሊትር ክሬም ገዝቶ ወጣ፡፡
 ሌላ ነገር የለም፡፡ ከሦስት ቀን በኋላ ተመልሶ እድሉን ይሞክራል፡፡ በየቀኑ መሄድ አይቻልም፡፡ በሳምንት ሁለት ቀን ብቻ ነው የሚቻለው፡፡ የአንዱ ቤተሰብ ተራ፣ ሰኞና ሃሙስ ሊሆን ይችላል፡፡
የሌላኛው ቤተሰብ ደግሞ ማክሰኞና አርብ፡፡ አንዳንድ የባሰበት እድለ ቢስ፣ ዛሬ የወዛደሮች በዓል ዋዜማ ነው ተብሎ ቀኑ ያልፍበታል፡፡ሆስፒታሎችና ፋርማሲዎችም እንዲሁ፣ የመድሃኒት መደርደሪያቸው ኦና ሆኗል፡፡ ስካይ ኒውስ ረቡዕ እለት ባቀረበው ልዩ ዘገባ፣ የዋና ከተማዋን ሆስፒታሎች አሳይቷል፡፡
የምርመራ መሳሪያዎች አይሰሩም - በየኮሪደሩ ተወዝፈዋል፡፡ የምርመራና የታማሚዎች ክፍሎች፣ ኮሪደሮችና መፀዳጃ ቤቶች ቆሽሸው ይዘገንናሉ፡፡ ውሃ የለም፡፡
የህመም ማስታገሻና አሞክሳስሊን የመሳሰሉ ተራ መድሃኒቶች እንኳ ብርቅ ሆነዋል (ከውጭ አገር ፓናዶልና አሞክሳስሊን ገዝቶ የሚልክ ወዳጅ ዘመድ ካልተገኘ በቀር) የ21ኛው ክፍለ ዘመን የሶሻሊዝም አብዮተኛ ነኝ የሚል መንግስት፣ ቬንዝዌላን የቅዠት አገር አድርጓታል፡፡
 አሳዛኙ ነገር፣ እንዲህ አይነት መንግስት በምርጫ አሸንፎ ስልጣን መያዙ ነው፡፡   


Read 4317 times