Saturday, 04 June 2016 11:57

“ማንም በመኢአድ ስም ጉባኤ መጥራት አይችልም”

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(4 votes)

በአመራር ውዝግብ ውስጥ የከረመው የመላ ኢትዮጵያውያን አንድነት ድርጅት (መኢአድ)፤ ባለፈው ሳምንት ጠቅላላ ጉባኤውን በዝግ አካሂዶ አዳዲስ አመራሮች
ተመርጠዋል፡፡ ቀደም ሲል የፓርቲው ፕሬዚዳንት የነበሩት አቶ አበባው መሃሪ፣በድጋሚ መሪ መሆን እንደማይፈልጉ በመግለጻቸው ከውድድር ውጭ ተደርገው፣ዶ/ር በዛብህ
ደምሴ የመኢአድ ፕሬዚዳንት ሆነው በጉባኤው መመረጣቸው ተገልጿል፡፡ በሌላ በኩል የፓርቲው ህጋዊ አመራር ነን የሚሉ ሁለት ቡድኖች ተፈጥረዋል፡፡ አንደኛው በአቶ
ማሙሸት አማረ የሚመራ ቡድን ሲሆን ሌላኛው በአቶ እንድሪያስ ኤሮ የሚመራ ቡድን ናቸው፡፡ ፓርቲው ባለፈው ቅዳሜና እሁድ በጽ/ቤቱ ባካሄደው ጠቅላላ ጉባኤ
እነዚህን ሁለት ቡድኖች አላሳተፋቸውም፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ፤ አዲስ የተመረጡትን የፓርቲውን ፕሬዚዳንት ዶ/ር በዛብህ ደምሴን ፓርቲውን
በሚያወዛግቡ የተለያዩ ጉዳዩች ዙሪያ አነጋግሯቸዋል፡፡

ጠቅላላ ጉባኤውን ለምን በዝግ ለማካሄድ ወሰናችሁ?
ይሄን ጉባኤ ያደረግነው ያለፈው ስራ አስፈፃሚ በዝግ ይሁን ብሎ በወሰነው መሰረት ነው፡፡ ሌላው ምክንያት ግን የፓርቲ የውስጥ ስራ ስለሆነ ለሚዲያ መገለፁ አይቀርም በሚል ነው፡፡ ዋናው አስፈላጊ የነበረው የስብስባ ኮረም መሙላቱ ነበር፡፡ ያንን የምርጫ ቦርድ ሁለት ተወካዮች ተገኝተው አረጋግጠዋል፡፡ ለጋዜጠኞች ክፍት ያላደረግነው ስብሰባው ከተካሄደ በኋላ ውጤቱን መግለጽ ይበጃል ብለን ስላሰብን እንጂ እኛ በራችን ለሚዲያ ዝግ አይደለም፡፡
ፓርቲው ባለፉት ዓመታት በርካታ የአመራር ውዝግቦችን አስተናግዷል … በአሁን ወቅት በአንድ በኩል፤አቶ ማሙሸት አማረ የሚመሩት ቡድን አለ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ተ/ም/ፕሬዚዳንት የነበሩት አቶ እንድሪያስ ኤሮ የሚመሩት ቡድንም አለ … እነዚህን ቡድኖች በጠቅላላ ጉባኤው ላይ ለምን አላሳተፋችሁም?
ችግሩ ምን መሰለህ፤ እነዚህ ሰዎች ከኛ በላይ አዋቂ የለም፣ ስልጣን መያዝና ትግሉን መምራት ያለብን እኛ ነን ስለሚሉ ነው እንጂ ለድርጅቱ በቅንነት ቢያስቡ በጉባኤው ላይ እንጋብዛቸው ነበር፡፡ ይሄን ስል ለነሱ በሩን ዝግ አድርገናል ማለቴ አይደለም፡፡ በጉባኤው ላይ ቢገኙ ኖሮ እንዲናገሩ እድል እንሰጣቸው ነበር፡፡ ያም ሆነ ይህ ሰዎቹ ለኛ ስራ ቅን አመለካከት ስለሌላቸው፣ ቢገኙም እኛ ካልተመረጥን ነበር የሚሉት፡፡ ከእኛ ውጪ ሌላ ሰው ስልጣን ላይ መውጣት የለበትም የሚል አመለካከት አላቸው፡፡ እኛ ግን አሁንም ቢሆን በሰላማዊ መንገድ ከመጡ እንቀበላቸዋለን፡፡ የሰው ስም ከማጥፋት ግን መቆጠብ አለባቸው፡፡
የአቶ እንድሪያስ ቡድን ሌላ ጠቅላላ ጉባኤ በሐምሌ ወር አደርጋለሁ እያለ ነው፡፡ በዚህ ላይ የእርስዎ አስተያየት ምንድን ነው?
እነዚህ ሰዎች ፖለቲካ ምን እንደሆነ የተረዱ አይመስለኝም፡፡ ጉባኤ እንጠራለን የሚሉት ነገር አያዋጣቸውም፡፡ እኛ የምርጫ ቦርድን ደንብና አሰራር ተከትለን፣ ህጋዊ እውቅና ይዘን ነው ጉባኤ ያደረግነው፡፡ ከዚህ በኋላ በመኢአድ ስም የትኛውም አካል ጉባኤ መጥራት አይችልም … በህግ ተጠያቂ ይሆናል፡፡ እነዚህ ሰዎች ኢትዮጵያ ውስጥ እንደመሆናቸው፣ መንግስት ላወጣው ህግ ተገዢ መሆን አለባቸው፡፡ ህጋዊ ሳይሆኑ የትም ቦታ መሰብሰብ አይችሉም፡፡
ፓርቲያችሁ ገና ከአመራር ቀውስ ጨርሶ ሳይላቀቅ፣ባደረጋችሁት ጉባኤ ላይ የቀድሞ የአንድነት አባላት እንዲቀላቀሏችሁ ጥሪ አቅርባችኋል … አልቸኮላችሁም?
አንድነት ውስጥ በጣም አቅም ያላቸው ሰዎች እንዳሉ እናውቃለን፡፡ ወጣቶች ናቸው፣ በእውቀት፣ በችሎታ፣ በፋይናንስም ቢሆን አቅም ያላቸውና እኛን ሊተኩ የሚችሉ ልጆች አሉ፡፡  ከዚህ በፊትም ቢሆን ከፓርቲው ጋር ተስማምተን፣አንድ ለመሆን መጨረሻ ላይ ስንደርስ ችግር ተፈጥሮ ነው እቅዱ የከሸፈው፡፡ አሁን ግን እነዚህ ወጣቶች ከኛ ጋር ለመስራት ፍላጎት ካላቸው በደስታ ነው የምንቀበላቸው፡፡ አብረናቸው ለመስራት ዝግጁ ነን፡፡
አሁን የተመረጣችሁት አመራሮች እርስዎን ጨምሮ አዛውንቶች ናችሁ … በፓርቲው ውስጥ ለአመራር የሚሆኑ ወጣቶች የሉም ማለት ነው?
ወጣቶች አሉን፡፡ ማዕከላዊ ም/ቤት ከተመረጡት ውስጥ ከ50 በመቶ በላይ ወጣቶች ናቸው ማለት እንችላለን፡፡ የላይኛው አመራር ላይ ሽማግሌዎች መኖራቸው፣ ወጣቶቹ ከኛ መማርና ልምድ መቅሰም ስላለባቸው ነው፡፡ እኛ በፓርቲው ለብዙ ጊዜ ስለቆየን፣ (በቅንጅት ጊዜ አመራር የነበርን ሰዎች ነን፡፡) ወጣቶቹ ነገ ከነገ ወዲያ ይተኩናል፡፡ ወጣቱ ከኛ መማር አለበት፡፡
አንድ ሰው መሪ የሚሆነው ብዙ ከተማረ፣ ካነበበና ከበሰለ በኋላ ነው፡፡
መኢአድን ጨምሮ አንዳንድ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በውስጣቸው የአመራር ሽኩቻ ሲፈጠር ኢህአዴግን ተጠያቂ ያደርጋሉ፡፡ እናንተም ለውስጥ ችግራችሁ ኢህአዴግ ተጠያቂ ነው ብላችኋል …?
አሁንም ተጠያቂው ኢህአዴግ ነው፡፡ ለምን ብለህ ብትጠይቀኝ … ጠንካራ ተቃዋሚ ማየት አይፈልግም፡፡ ኢህአዴግ ቢገባው ግን ለዚህ ያደረሰው ተቃዋሚው ነው፡፡ በ97 ዓ.ም ቅንጅት የሰራው ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ ነው፡፡
መንግስት በትንሹ የከፈተውን በር በሰፊው አስከፍቶታል፡፡ አሁንም በትንሹ ቢከፈት በሰፊው ማስከፈት ቀላል ነው፡፡ ኢህአዴግን አጥብቀን የምንኮንነው፣ ተከፍታ የነበረችውን ትንሽ በርም ጥርቅም አድርጎ በመዝጋቱ ነው፡፡
በሰላማዊ ትግል የተዘጋን በር ማስከፈት አይቻልም እንዴ? ተቃዋሚዎች ግን አዲስ ስልትና አካሄድ ከመቀየስ ይልቅ ወቀሳና ውንጀላ ላይ ያተኩራሉ ይባላል፡፡ የተዘጋውን በር ማስከፈት አይቻልም ብለው ያምናሉ?
እኛ የምንለው፣በ97 የከፈታትን ትንሽ በር ቢከፍት፣ በርግጠኝነት ኢህአዴግ ብዙ አይቆይም፡፡ ለእኛ ኢህአዴግ ጠላት አይደለም፡፡
ተቀናቃኛችን ነው፡፡ ተቃዋሚን በጠላትነት ፈርጆ ለማጥፋት አናት አናቱን መቀጥቀጥ ግን ተገቢ አይደለም፡፡ እኔ ብቻ ነኝ ለዚህች ሀገር የማውቀው በሚል፣ ፈላጭ ቆራጭ ለምን ይሆናል ነው ጥያቄው፡፡ ተቃዋሚዎች ግፊት ስለፈጠሩ እኮ ነው ትንሽ ለውጥ መምጣት የቻለው፡፡ በሩ ቢከፈት ደግሞ የተሻለ ለውጥ ይመጣል፡፡
እኔ ከአውስትራሊያ በቀር ያልኖርኩበት የዓለም ክፍል የለም፡፡ የተቃውሞ ፖለቲካ እንደኛ አስቸጋሪ የሆነበት አገር ግን አላየሁም፡፡ ሁሉም ነገር የተዘጋጋ ነው፡፡
የተዘጋጋ ከሆነ ታዲያ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ተስፋ ምንድን ነው?
ተስፋችን አሁንም በዚሁ ትግል መቀጠል ነው፡፡ እኔ ተስፋ አልቆርጥም፡፡ እኛ ኢህአዴግን የምናስተምረው በሰላማዊ ትግል ነው፡፡ አንድ ቀን ለውጥ ይመጣል፡፡ በጠመንጃ የሚመጣ፣ በጠመንጃ ብቻ ነው የሚወርደው፡፡ ከዚህ በኋላ በዚህች ሃገር እንዲህ አይነት ጨዋታ አያስፈልግም፡፡
አብዛኛው ህዝብ በተቃዋሚዎች ተስፋ እየቆረጠ በመምጣቱ ተቀባይነታችሁ እየቀነሰ ነው ይባላል፡፡ በዚህ ላይ እርስዎ ምን ይላሉ?
አሁን አንተ የምትለኝ ነገር የውሸት ፕሮፓጋንዳ ነው፡፡ የኢህአዴግ ፕሮፓጋንዳ አካል ነው፡፡ ይሄን ልናሸንፍ የምንችለው ሰርተን በማሳየት የህዝቡን እምነት ስናገኝ ነው፡፡ ያ ስራ ደግሞ ለወደፊት የሚታይ ነው፡፡ ከዚህ በፊት የኢህአዴግ ተለጣፊ ናችሁ በሚል ታምተናል፡፡ ስራችን ግን ይሄን አይገልፅም፡፡ ለተበደሉት ስንቆም ህዝቡ አይቷል፡፡ የኛን ማንነት መመስከር ይችላል፡፡
ህዝቡ በተቃዋሚዎች ተስፋ አልቆረጠም እያሉኝ ነው?
እየውልህ ተስፋ የቆረጠ ሰው፣ ለሰላማዊ ትግሉ ያበረከትኩት አስተዋፅኦ ምንድን ነው ብሎ ራሱን መጠየቅ አለበት፡፡
ተቃዋሚዎች ምንም አይሰሩም እያለ የሚያስወራው ኢህአዴግ ሊሆን ይችላል፡፡
ከውጪ በጠመንጃ (በትጥቅ ትግል) መምጣት የሚፈልጉትም ይሄን ሊያስወሩ ይችላሉ፡፡ በኔ እምነት ግን የኛ ሰላማዊ ትግል እንደሚያሸንፍ አልጠራጠርም፡፡
በተቃዋሚ ፓርቲዎች ውስጥ በአብዛኛው ውዝግብ የሚፈጠረው የፓርቲ ስልጣንን ለመያዝ በሚደረግ ሽኩቻ ነው … የፓርቲ ስልጣን ለእርስዎ ምንድን ነው?
በእኔ እምነት የፓርቲ ስልጣን ምንም ፋይዳ የለውም፡፡ ዶ/ር በዛብህ ለዚህ ፓርቲ ምን አደረገ ብለህ ብትጠይቅ፣ በፋይናንስ መርዳቴ ሊሆን ይችላል፡፡ እኔ የምታገለው የእነ ፕ/ር አስራትን ውለታ ለመክፈል እንጂ ከዚህ በኋላ 100 ዓመት ብኖር ሊያኖረኝ የሚችል በቂ ሃብት አለኝ፡፡ የምታገለው ለገንዘብ አይደለም፡፡ ሀገራችን በአንድነት እንድትቀጥል ነው፡፡ እኔ የምታገለው ያስተማረኝን የኢትዮጵያ ህዝብ ላገልግል ብዬ እንጂ፣ የፓርቲ ፖለቲካ ራስን መስዋዕት ከማድረግ ሌላ የሚገኝበት ነገር የለም፡፡
ከዚህ በኋላ በፓርቲያችሁ ውስጥ ውዝግቦች ላለመፈጠራቸው ምን መተማመኛ አላችሁ?
በፓርቲ ውስጥ ዝም ብሎ ለስልጣን መመረጥ የለም፡፡ አንድ ሰው ለፓርቲው በሚሰጠው አገልግሎት ነው የሚመዘነው፡፡
በእኔ እምነት ህጋዊ ባልሆነ መንገድ የሚፍጨረጨሩ ግለሰቦች ከዚህ በኋላ አደብ ይገዛሉ ብዬ እገምታለሁ፡፡ ምክንያቱም የትም ቢሄዱ የሚያፈናፍናቸው ነገር የለም፡፡

Read 2131 times