Saturday, 04 June 2016 12:10

በሽብር የተከሰሱ ፖለቲከኞችና ጋዜጠኞች እንዲፈቱ ተጠየቀ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(20 votes)

“መንግስት የፀረ - ሽብር አዋጁን ተቃውሞን ለማፈን እየተጠቀመበት ነው”
   በሽብርተኝነት ተጠርጥረውና ተፈርዶባቸው በእስር ላይ የሚገኙ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች፣ ጋዜጠኞች፣ ጦማሪያንና የሰብአዊ መብት ተሟጋቾችን የኢትዮጵያ መንግስት በአስቸኳይ እንዲፈታ የኢትዮጵያ መንግስትን የጠየቁት ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ተቋማት፤ መንግስት የፀረ ሽብር አዋጁን ተቃውሞዎችን ለማፈን እየተጠቀመበት ነው ብለዋል፡፡
አምነስቲ ኢንተርናሽናልን ጨምሮ 9 የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች አባል የሆኑበት ማህበር ትናንት ባወጣው መግለጫ፤ የኢትዮጵያ መንግስት የፀረ ሽብር አዋጁን ጋዜጠኞችን፣ ፖለቲከኞችንና የሰብአዊ መብት ተሟጋቾችን ለማሳደጃነት እየተጠቀመ ነው ብሏል፡፡
በተለይ በኦሮሚያ ክልል የተፈጠረውን ግጭትና ተቃውሞ ተከትሎ ያለአግባብ በፀረ ሽብር ህጉ ተከሰዋል ሲል ከጠቀሳቸው መካከል የ “ነገረ ኢትዮጵያ” ጋዜጣ አዘጋጅ ጋዜጠኛ ጌታቸው ሽፈራው፣ የኦፌክ ም/ሊቀመንበር አቶ በቀለ ገርባ፣ የሰማያዊ ፓርቲ የቀድሞ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ዮናታን ተስፋዬ ይገኙበታል፡፡
የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ማህበሩን ጨምሮ የተባበሩት መንግስታት፣ የአውሮፓ ፓርላማ፣ የአሜሪካ መንግስትና ሌሎች ሀገራት የኢትዮጵያ መንግስት የፀረ ሽብር ህጉን ያለ አግባብ እንዳይጠቀም ተደጋጋሚ ጥሪ ቢያቀርቡም እስካሁን ተቀባይነት አላገኙም ብሏል - መግለጫው፡፡
በሽብር ህጉ የሚከሰሱ ግለሰቦች፤ በማረሚያ ቤትና በምርመራ ወቅት ኢ-ሰብአዊ ተግባራት እንደሚፈፀምባቸውም በመግለጫው ተጠቁሟል፡፡ ተመርማሪዎች የዓለማቀፍ የሰብአዊ መብት ድንጋጌዎችን በሚፃረር መልኩ ግርፋትና ስቃይ (ቶርች) ይደረጋሉ ያለው መግለጫው፤ ለዚህም በሽብርተኛነት ተከሰው የተረፈደባቸው ዘላለም ወ/አገኘሁና ባህሩ ደጉ አስረጂዎች እንደሚሆኑ አመልክቷል፡፡
በኦሮሚያ ከተከሰተው ተቃውሞና ግጭት ጋር በተያያዘ ታስረው በሽብር የተከሰሱት አቶ በቀለ ገርባን ጨምሮ 22 ተከሳሾች ለ4 ወር ያህል ከህግ አማካሪዎቻቸው ጋር ሳይገናኙ ምርመራ ሲካሄድባቸው እንደነበርም ተጠቅሷል፡፡

Read 4263 times