Saturday, 04 June 2016 12:48

ኮንጎ የዓለማችንን ትልቁን ግድብ በ14 ቢ. ዶላር ልትገነባ ነው

Written by 
Rate this item
(4 votes)

ፕሮጀክቱ የአፍሪካን 40 በመቶ የሃይል ፍላጎት ያሟላል ተብሏል

ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ በዓለማችን በትልቅነቱ ቀዳሚውን ስፍራ ይይዛል የተባለውን የኤሌክትሪክ ሃይል ማመንጫ ግድብ በ14 ቢሊዮን ዶላር ወጪ በጥቂት ወራት ውስጥ መገንባት እንደምትጀምር ተዘገበ፡፡
የአገሪቱ ግዙፍ ፕሮጀክት የመጀመሪያ ክፍል የሆነውና በኮንጎ ወንዝ ላይ የሚገነባው ኢንጋ 3 የተባለው ይህ የኤሌክትሪክ ሃይል ማመንጫ ግድብ፣ በአምስት አመት ጊዜ ውስጥ ግንባታው ሙሉ ለሙሉ ተጠናቅቆ ሃይል ያመነጫል ተብሎ እንደሚጠበቅ የዘገበው ዘ ጋርዲያን፤4 ሺህ 800 ሜጋ ዋት የማመንጨት አቅም እንዳለውም ጠቁሟል፡፡
ይህ ግዙፍ ግድብ የሚያመነጨው የኤሌክትሪክ ሃይል፣ 20 ትላልቅ የኒውክሌር ሃይል ማመንጫዎች ሊያመነጩት ከሚችሉት ሃይል ጋር የሚመጣጠን ነው መባሉን የጠቀሰው ዘገባው፤የፕሮጀክቱ ቀጣይ አካል የሆነና 40 ሺህ ሜጋ ዋት የማመንጨት አቅም ያለው ሌላ ግድብ በ100 ቢሊየን ዶላር ለመገንባት መታቀዱንም ገልጧል፡፡
የኤሌክትሪክ ሃይል ማመንጫ ፕሮጀክቱ 40 በመቶ ያህሉን የአፍሪካ የሃይል ፍላጎት ማሟላት ይችላል መባሉን የጠቆመው ዘገባው፤አለማቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችና የአካባቢ ተቆርቋሪዎች ግን ፕሮጀክቱ በሁለቱም ክፍሎቹ በድምሩ 60 ሺህ ያህል ዜጎችን ያፈናቅላል በሚል እንደተቹት ገልጧል፡፡

Read 2249 times