Saturday, 04 June 2016 12:58

ግልፅ ደብዳቤ ለክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ

Written by  አብዱልመሊክ ሁሴን
Rate this item
(15 votes)

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር፤
የመልካም አስተዳደር ችግርን ለመፍታት ቁርጠኛ መሆንዎን በተለያየ ጊዜና ቦታ ከተናገሩት ቃል ለመረዳት ችያለሁ፡፡ ይህ ግልፅ ደብዳቤም በአሁኑ ወቅት የመንግሥትዎ ዋነኛ የትግል አጀንዳ በሆነው የመልካም አስተዳደር ጉዳይ ላይ የሚያተኩር ነው፡፡ በዚሁ ዓመት መጀመሪያ አካባቢ ከአንድ የቢቢሲ ጋዜጠኛ ጋር ባደረጉት አንድ ቃለ ምልልስ፤ የምርመራ ጋዜጠኝነትን የሚያደፋፍር ቃል መናገርዎን አስታውሳለሁ፡፡ ኧረ ብዙ ጊዜ ተናግረዋል፡፡ ይህም እኔን እና የሙያ ባልንጀሮቼን በብዙ ደስ አሰኝቶናል፡፡ ‹‹ፍፁም እንዳልሆንን እናውቃለን፡፡ በመሆኑም ከማንኛውም ጋዜጠኛ የሚቀርብብን ትችት ለመቀበል ዝግጁ ነን›› ሲሉ መናገርዎን፤ እንደ አዲስ ምዕራፍ ከፋች አዋጅ አድርገን በመውሰድ ተስፋ አሳድረናል፡፡ ሆኖም እኔ በዚህ ደብዳቤ ትችት ለማቅረብ አልተነሳሁም፡፡ ይልቅስ የተጀመረውን የመልካም አስተዳደር ትግል የሚያጠናክር መረጃ ለማቅረብ እሻለሁ፡፡      

ክቡር ሆይ!
ይህን ግልጽ ደብዳቤ የፃፍኩለዎ፤ ከሰሞኑ የአዲስ አበባ መሬት ማኔጅመነት ቢሮ ኃላፊ ‹‹ፍርድ ቤቶች በማይመለከታቸው የመሬት ጉዳይ ጣልቃ እየገቡ ሥራ መስራት አልቻልንም›› በማለት ሲናገሩ፤ በአንድ የውጭ ኩባንያ የተፈፀመና እስከ ዛሬ ድረስ ያልተፈታ አንድ ችግር ስላስታውሰኝ ነው፡፡ ከዚህ ተጨማሪ፤  የኢኮኖሚ፣ የገበያና የፍትሕ ስርዓቱን ወዘተ ጤናማነት በሚያውክ ተግባር የተሰማሩ የውጭ አገር ኩባንያዎች መኖራቸውን አልፎ አልፎ በመገናኛ ብዙሃን ከሚቀርቡ ዘገባዎች በመረዳት፣ መንግስት በዚህ ረገድ ትኩረት ሊሰጥ እንደሚገባ የሚያመለክት አንድ ጉዳይ ማንሳት ስለፈለግኩ ነው፡፡
የሐገራችንን ልማት የሚያግዝ ሥራ የሚሰሩ የውጭ ኩባንያዎች የመኖራቸውን ያህል፤ በአንጻሩ በኢንቨስትመንት ስም ወደ ሐገር ገብተው፤ ኢንቨስተር ተብለው ከቀረጥ ነፃ በሆነ መንገድ ወደ ሐገር ቤት ዕቃ የማስገባት መብት አግኝተው፤ ይህን መብት ተገን አድርገው ያልተገባ ጥቅም ለማግኘት የሚሞክሩ ኩባንያዎችን አይተናል፡፡
ከሰሞኑ በቀረበ የፋና ሬዲዮ አንድ ዘገባ፤ በኢንቨስትመንት ሥራ ለመሰማራት ፈቃድ ወስዶ ወደ ሐገር የገባ አንድ የውጭ ኩባንያ፤ ቀረጥ ሳይከፍል ያስገባውን ዕቃ በቀጥታ ለገበያ አቅርቦ ሲቸበችብ መቆየቱን ተረድቻለሁ፡፡
 ይህ ኩባንያ በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ተሰማርቶ ለሐገር ኢኮኖሚ ትልቅ ፋይዳ ያለው ሥራ ይሰራል ተብሎ ሲታሰብ፤ የህጋዊ ነጋዴዎችን የገበያ ተወዳዳሪነትና የድሃ ሐገራችንን ጥቅም የሚጎዳ ተግባር ውስጥ ተሰማርቶ ተገኝቷል፡፡
ሆኖም በበኩሌ በጣም አሳሳቢ ሆኖ የታየኝ ይህ አድራጎቱ ብቻ አይደለም፡፡ ጉዳዩን ለማጣራት ለሄደው ጋዜጠኛ ምላሽ ለመስጠት ፈቃደኛ አለመሆኑ ሳያንስ፤ በአሰራሩ ላይ ጥያቄ ያነሱ የራሱን ሠራተኞችን በመሣሪያ ጭምር ለማስፈራራት ያልተመለሰ ‹‹ኢንቨስተር ነኝ›› ባይ መሆኑ ነው፡፡
 እንዲህ እያስፈራራ በዚህች ሐገር ለመስራት ማሰቡ አስገራሚ ነው፡፡ ከሬዲዮ ፋና ዘገባ ለመረዳት እንደቻልኩት፤ ይህ የውጭ ኩባንያ በሐገሩ የወንጀል ሬከርድ ያለበትና ከንግድ ሚኒስቴር የተሠጠውን ትዕዛዝም ተላልፎ ለመንቀሳቀስ የሚሞክር ጭምር ነው፡፡ ታዲያ በተለያየ ጊዜ ከመገናኛ ብዙሃን የምንሰማው የአንዳንድ የውጭ ኩባንያዎች አድራጎት መንግስት የውጭ ኩባንያዎችን በመቆጣጠር ረገድ ከፍተኛ የአቅም ውስንነት እንዳለበት የሚያመለክት ነው፡፡ መንግስትዎ በተደጋጋሚ እንደሚናገረው፤ የኪራይ ሰብሳቢነት የፖለቲካ ኢኮኖሚ የበላይነት በያዘበት ሁኔታ፤ ትርፍን ብቻ በመሻት የሚመጡ የውጭ ኩባንያዎች ህግን አክብረው እንዲሰሩ በማድረግ ረገድ ያለን የቁጥጥር አቅም ደካማነት፣ አደገኛ ችግር ሊያስከትልብን ይችላል፡፡
እንደሚታወቀው፤ መንግስት በዕርዳታ ስም መጥተው አፍራሽ ተግባር ውስጥ የሚዘፈቁ የውጭ ድርጅቶችን ለመቆጣጠር የሚያስችል ህግ ደንግጎ በሥራ ላይ አውሏል፡፡ ነገር ግን መንግስት ለትርፍ የቆሙ የውጭ ኩባንያዎችን የመቆጣጠር አቅሙን ካልፈተሸ የተጀመረው የአገራችን ልማት ላይ የሚያመጣው ችግር ከፍተኛ እንደሚሆን የሚታዩት አንዳንድ ጉዳዮች በግልጽ ያሳያሉ፡፡

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር!
ቀደም ሲል እንደጠቀስኩት ለዚህ ደብዳቤ ቀስቃሽ የሆነው ጉዳይ የአዲስ አበባ የመሬት ማነጅመነት ለእርስዎ ያመለከተው ከመሬት ጋር የተያያዘ ችግር ነው፡፡ የቢሮ ኃላፊው እንደ ገለፁት፤ መሬት መተዳደር ያለበት በሊዝ አዋጅ፣ የከተማ መስተዳድሩ ባወጣው ደንብና መመሪያዎች ነው፡፡ ሆኖም የፌደራል ፍርድ ቤቶች በማይመለከታቸው የመሬት ጉዳይ ላይ ጣልቃ እየገቡ በስራው እንቅፋት እንደሆኑበትና የእርስዎ ጽ/ቤት ለዚህ ችግር መፍትሔ እንዲያስቀምጥ የመሬት ማነጅመነት ቢሮ ጥያቄ አቅርቧል፡፡ በዚህ ደብዳቤ፤ የፌዴራል ፍ/ቤቶች በአስተዳደር ሥራ ጣልቃ በመግባት የሚያሳልፉት ውሳኔ የፈጠረውን ቀውስና የውጭ ሐገር ኩባንያዎች በሐገራችን የሚፈጽሙት በደል ምንኛ የከፋ እንደሆነ በደንብ ሊያሳይዎ የሚችል አንድ አሳዛኝ ጉዳይ አቀርብለዎታለሁ፡፡ ይህ ጉዳይ የሼል ኩባንያ እና አቶ ኃይሉ ገብረ ሕይወት የተባሉ ሰውን ጉዳይ የሚመለከት ነው፡፡ በዚህ ጉዳይ የመስተዳድር አካላትና  ጉዳዩን የተመለከተው የፌዴራል ፍርድ ቤት የሰጡት ውሳኔ፤ ከአዲስ አበባ አስተዳደር የመሬት ማነጅመነት የቀረበው ጥያቄ ቀላል አለመሆኑን ያመለክታል፡፡ ይህ ጉዳይ የሕግ ተርጓሚውና ሕግ አስፈፃሚው በተቃርኖ ቆመው የታዩበት አጋጣሚን ብቻ ሳይሆን፤ የመንግሥት መመሪያ የተጣሰበትንና የዜጎች ሕገ መንግሥታዊ መብት የተረገጠበትን አጋጣሚም ያሳያል፡፡ ይህ ጉዳይ ዋነኛ የኪራይ ሰብሳቢነት ምንጭ እንደሆነ የሚገለፀውን የመሬት ጉዳይ የሚመለከትና የኢትዮጵያ በመቶዎች ሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ያጣችበትን ሁኔታ ያሳያል፡፡

ክቡር ሆይ፤
ነገሩ ግራ አጋቢ ነው፡፡ የአዲስ አበባ መስተዳድር፤ ‹‹ባለው መመሪያ መሠረት፤ የቦታው ሕጋዊ ባለይዞታ አቶ ኃይሉ ገብረ ሕይወት ናቸው›› ይላል፡፡ ጉዳዩን የተመለከተው ፍ/ቤት ደግሞ ሼል ኩባንያን ባለይዞታ አድርጎታል፡፡ አሁን ቦታውን የያዘው በውጭ ሐገር በተከናወነ ሽያጭ የሼል ኩባንያን የተካው ‹‹ኦይል ሊቢያ›› ነው፡፡ ነገር ግን፤ ‹‹የቦታው ሕጋዊ ባለይዞታ አቶ ኃይሉ ገብረ ሕይወት ናቸው›› የሚለው የአዲስ አበባ መስተዳደር ቂርቆስ ክፍለ ከተማ፤ ‹‹ያልተከፈለ የቦታና የቤት ግብር አለኝ›› በሚል በፍርድ ቤት ክስ አቅርቦ፤ ክሱን የተመለከተው የፌዴራል ፍርድ ቤት፤ አቶ ኃይሉ ገብረ ሕይወት ውዝፍ የቦታና የቤት ግብር እንዲገብሩ ወስኖባቸዋል፡፡
 በዚህ ውሳኔ መሠረት፤ ከ1968 ዓ.ም ጀምሮ የተጠየቁትን የአፈር ኪራይና የቤት ግብር ከነመቀጫው እንዲከፍሉ ተደርጓል፡፡ እስከዚህ ዓመት (2008 ዓም) ድረስ ክርክር ለተነሳበት የነዳጅ ማደያ ግብርና ኪራይ የሚከፍሉት አቶ ኃይሉ ገብረ ሕይወት ሲሆኑ፤ በቦታው የሚጠቀምበት ግን ‹‹ኦይል ሊቢያ›› ነው፡፡ የመሬት ማነጅመንት ያነሳው ጉዳይ ትኩረት የሚሻ ሆኖ የታየኝ፤ እንዲህ ዓይነት የተቃረኑ ውሳኔዎችን በመመልከቴ ነው፡፡   

ክቡር ሆይ፤
ሼል ኩባንያ፤ ከሐገራችን መንግሥት ድጋፍ እየተደረገለት፤ የሚያረካ ትርፍ እያገኘ ለረጅም ዓመታት ሲነግድ ቆይቶ በቅርቡ አገራችንን ለቆ ሄዷል፡፡ ሼል ኩባንያ ከሐገራችን ዓመታዊ በጀት 6 እጥፍ የሚበልጥ ዓመታዊ ትርፍ የሚያገኝ ዓለም አቀፍ ኩባንያ ነው፡፡ በ2001 ዓ.ም የኢትዮጵያ መንግሥትን አታሎ፣ ዕቃውን ጠቅልሎ ከሐገራችን ወጥቷል፡፡ ሼል ኩባንያ ጠንካራ የአስተዳደርና የፍትህ ስርአት በሌላቸው አገራት የሚያደርገውን ነውረኛ ተግባር በእኛም ሐገር ደግሞ ከሐገር ወጥቷል፡፡
ሼል ኩባንያ በ2001 ዓ.ም በእንግሊዝ ሐገር ባካሄደው የአክሲዮን ሽያጭ፣ የማታለል ተግባር መፈጸሙን ከአንድ ተቆርቋሪ የኩባንያው ሠራተኛ ጥቆማ የደረሰው የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን፤ ሠራተኞቹን ሎንዶን ከተማ ድረስ በመላክ ትክክለኛውን ሁኔታ በማጣራት ኩባንያውን 200 ሚሊዮን ብር ያህል ግብርና ታክስ ያስከፈለ መሆኑ ይታወቃል፡፡ የተፈፀመውን የግብር ማጭበርበር ተግባር ባለሥልጣኑ ተከታትሎ እርምጃ መውሰዱ የሚበረታታና አርያነት ያለው ቢሆንም፤ የኢትዮጵያ መንግስት ያገኘው ነገር ከታጣው ጋር ሲነጻጸር እጅግ አነስተኛ ነው፡፡
ዓለም አቀፉ ሼል ኩባንያ የደካሞቹን አገራት ባለሥልጣናት፣ የፍርድ ቤት ዳኞችና ሠራተኞች ከፍ ያለ ጉቦና መደለያ በመሥጠት የፈለገውን ጥቅም የሚያገኝ መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ለምሳሌ፤ በሙስና ቅሌት የዩናይትድ ስቴትስ መንግስት ሼል ኩባንያን እ.ኤ.አ በ2010 ዓ.ም በባህር ማዶ ሙስና ሰንጠረዥ ከተቀጡ ኩባንያዎች ቀደምት አድርጎታል፡፡
በናይጄሪያ በፈጸመው የሙስና ወንጀል ከ500 ሚሊዮን ብር በላይ መቀጫ እንዲከፍል ተደርጓል፡፡ እንዲሁም በኢንዶኔዢያ ከፍተኛ የፍ/ቤት ዳኞችን በጉቦ ሲደልል ተጋልጦ ተቀጥቷል፡፡
 እንዲህ ዓይነት ታሪክ ያለው ሼል ኩባንያ በኢትዮጵያ ያለው ታሪክ ተመሳሳይ መሆኑን ያሉት መረጃዎች በግልጽ ያሳያሉ፡፡
ሼል ኩባንያ ወደ ኢትዮጵያ ሲመጣ፤ በአገሪቱ ሕግ መሠረት የውጭ አገር ኩባንያ ወይም ዜጋ የቋሚ ንብረት ባለመብት መሆን ስለማይችል ከግለሰብ ባለርስቶች ላይ ለ25 ወይም ለ30 ዓመት የመሬት ኮንትራት ውል በመዋዋል፣ የውሉ ዘመንም ሲያበቃ ለባለርስቱ ቦታውንና ቤቱን አስረክቦ ሊለቅ ግዴታ በመግባት፣ የነዳጅ ማደያ ጣቢያዎች ገንብቶ ንግዱን ሲያከናውን ቆይቷል፡፡
 የደርግ መንግሥት የከተማን ቦታና ትርፍ ቤት የመንግሥት ንብረት ያደረገውን አዋጅ ስላወጀ፤ በወቅቱ የነበሩትን አራት የነዳጅ አከፋፋይ ኩባንያዎችን የሚመለከት በሚኒስትሮች ምክር ቤት አንድ መመሪያ ወጣ፡፡ ይህም መመሪያ፤ የነዳጅ ማደያ ቦታዎች አዲስ በወጣው አዋጅ መሠረት መንግሥት የቀድሞ ባለርስቶችን ስለተካ፤ ኩባንያዎቹ ከግል ባለርሰቶች ጋር ያደረጉት የቦታ ኪራይ ውል ዘመን ሲፈጸም፤ ስለ ኪራይ ተገቢው ጥናት እየተደረገ በሚሰጥ ውሳኔ፤ ከመንግሥት ጋር አዲስ የኪራይ ወለታ እንዲደረግ የሚያዝ መመሪያ ነበር፡፡
ሼል ኩባንያ ከባለርስቶች ጋር ያደረጋቸው ውሎች፤ ኢህአዴግ ስልጣን ከያዘ ወዲህ ባሉት የተለያዩ ዓመታት ያበቁ ቢሆንም፤ ይህን ዓቢይ ጉዳይ በመመሪያው መሠረት ተከታትሎ ለማስፈፀም የሞከረ የመንግሥት አካል ባለመኖሩ፤ ሼል ኩባንያ መመሪያው እንደሚያዘው ከመንግስት ጋር የኪራይ ውል ሳይገባና ለማደያዎች ተገቢውን የቤት ግብርና የመሬት ኪራይ ከ15 አመታት በላይ ማለትም እስከ 2002 ዓ.ም ድረስ ሳይከፍል በነፃ ሲነግድ ቆይቶ፤ ንግዱን ለ‹‹ኦይል ሊቢያ›› በእንግሊዝ አገር ሸጦ ከኢትዮጵያ ወጥቷል፡፡ በጠቅላላው በኢትዮጵያ ባሉት በመቶዎች የሚቆጠሩ ውላቸውን የጨረሱ የሼል ማደያዎች ሳይከፈል የቀረ ግብርና ኪራይ ቢሰላ መንግሥት ያጣው ገቢ ቀላል አይደለም፡፡
እዚህ ላይ መጠየቅ ያለበት ጉዳይ፤ ሼል ኩባንያ በአክሲዮን ሽያጭ ሽፋን መሬትን ‹‹ለኦይል ሊቢያ›› እንዴት ሊያስተላልፍ ቻለ? ሽያጩስ በኦይል ሊቢያ ስም በንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር እንዴት ሊመዘገብ በቃ? የከተማውን ቦታ ለማስተዳደር ሥልጣን ከተሰጠው ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምን ዓይነት የመሬት ይዞታ ማስረጃ አቀረበ? መቼም መሬቱን አልገዛው? ከመንግስት በውል አልተከራየው? በስጦታ ወይም በውርስ አላገኘው? እንግዲህ ለማደያዎቹ ኪራይና ግብር ለረጅም  ዓመታት ሳይከፍል በነጻ ሲነግድና ሲጠቀም ዝም መባሉ ሳያንስ፣ ቋሚ ንብረት ሲያስተላልፍ እንዴት ዝም ተባለ? በዚህ ወንጀልስ ተጠያቂው ማን ነው ?
ክቡር ሆይ!!
ከሁሉም በላይ የሚያሳዝነው፤ ሼል ልማታዊም ሆነ ኪራይ ሰብሳቢ ‹‹ኢንቨስተር›› ራሱ መርጦ፤ በጋዳፊ መንግሥት ስር የሆነውን ኦይል ሊቢያን በእርሱ እግር ገብቶ እንዲነግድ መወሰን መቻሉ ነው፡፡ እንደሚታወቀው ሼል ኩባንያ ወደ አገራችን ሲመጣ፤ የነዳጅ ስርጭቱን ለመሥራት ሐገሪቱ ብዙ አቅም አልነበራትም፡፡ በመሆኑም፤ ሼል ራሱ ነዳጅ እያስመጣ በመቸርቸር፤ ክፍ ያለ ትርፍ ያገኝ ነበር፡፡ ዛሬ ይህ ሁኔታ ፍፁም ተቀይሯል፡፡
 በአሁኑ ጊዜ፤ ለአገራችን ነዳጅ በብቸኝነት የሚያስመጣው የመንግሥት ተቋም የሆነው ‹‹የኢትዮጵያ ነዳጅ ድርጅት›› ነው፡፡ እናም ሼል፤ የኢትዮጵያ መንግሥት በራሱ የውጭ ምንዛሪ የሚያስመጣውን ነዳጅ ተረክቦ የሚያሰራጭ፤ በሐገሪቱ መደበኛ የልማት ሥራ ላይ ተሳትፎ የሌለውንና የወጭ ምንዛሪም የማያመጣ ቸርቻሪ ኩባንያ ተክቶልን ሲሄድ በመንግሥት በኩል ትኩረት አለማግኘቱ ድክመታችንን ይጠቁማል፡፡
የሼል ኩባንያ በአዲስ አበባ ከተማ ቁልፍ በሆኑ 42 ቦታዎች እንዲሁም በሌሎች ክልሎች በመቶዎች የሚቆጠሩ የነዳጅ ማደያ ቦታዎች ነበሩት፡፡ እነዚህ ቦታዎች ያለምንም የቋሚ ንብረት ማስረጃ ሼል ኩባንያ፣ ለኦይል ሊቢያ አስተላልፏቸዋል!! በነዚህ ንብረቶች ላይ መንግሥት ማግኘት የሚገባውና ሳያገኝ የቀረው ገቢ እና ጥቅም ምን ያህል እንደሆነ የሚያረጋግጥ አንድ ቡድን ተቋቁሞ ለመንግሥትና ለኢትዮጵያ ሕዝብ ግኝቱን ቢያሳውቅ፣ በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠር ብር ሳይሆን እንደማይቀር መገመት አያዳግትም! ይህ ሁሉ ዘረፋ ሲፈፀም መንግስት ዝም ማለቱ ለምንድነው? ዝምታውስ እስከመቼስ ነው?

ክቡር ሆይ!!
ሼል ኩባንያ ለማደያዎቹ ምንም ዓይነት የይዞታ ማስረጃዎች ስላልነበሩት በአስተዳደር በኩል መሄድ ሲያቅተው፤ ፍርድ ቤትን አቋራጭ መንገድ አድርጎ የፈለገውን ማስፈጸም እንደቻለ በተግባር ተመልክተናል፡፡ አቶ ኃይሉ ገ/ሕይወት የተባሉት ኢትዮጵያዊ “ለሼል የሸፍጥ ሥራ ተባባሪ አልሆንም” በማለታቸው፤ ኩባንያው ፍርድ ቤትን መከታ በማድረግ የማይታመን በደል አድርሶባቸዋል፡፡ ከእርስዎ ቢሮ የአስር ደቂቃ የእግር መንገድ ወረድ ብሎ ካዛንቺስ ቂርቆስ ክ/ከተማ ወረዳ 8 በሚገኘው የነዳጅ ማደያ ከ40 አመታት በላይ በስማቸው ንግድ ፈቃድ አውጥተው ሲነግዱ ቆይተዋል፡፡ ስለዚህ የአዲስ አበባ መስተዳደር በዚህ የነዳጅ ማደያ ቦታ፤ ደረጃ እና መለያ የካዳስተር ቁጥር ቢል ሰጥቷቸዋል፡፡ የቦታው ሕጋዊ ባለይዞታ አቶ ኃይሉ ገብረ ሕይወት መሆናቸውን በመግለፅ የቦታና የቤት ግብር እንዲገብሩ በፍርድ ቤት ክስ አቅርቦ፤ የተጠየቁትን የአፈር ኪራይና የቤት ግብር ከ1968 ዓ.ም ጀምሮ ከነመቀጫው እንዲከፍሉ በፍ/ቤት አስወስኖ አስከፍሏቸዋል፡፡
በተቃራኒው ሼል ኩባንያ የቦታው ግብር በስሙ እንዲዛወር አስተዳደሩን ጠይቆ፤ አስተዳደሩ ይህን ለማድረግ መመሪያው እንደማይፈቅድና እንደማይቻል በተደጋጋሚ ስለገለጸለት፤ በአስተዳደር በኩል ቀዳዳ እንደሌለ ሲረዳ፤ በአቶ ኃይሉ ገብረ ሕይወት ላይ ክስ መስርቶ፣ አስተዳደር ለፍ/ቤት የቦታው ሕጋዊ ባለመብት “አቶ ኃይሉ ገብረ ሕይወት ነው” እያለ ፍ/ቤት ሼል ኩባንያን ባለይዞታ አድርጎታል፡፡      

ክቡር ሆይ!
ይዞታው የሚገኝበት ወረዳ እና ክፍለ ከተማ የነበሩ የአስተዳደር ኃላፊዎች ፍ/ቤቱ ክርክሩን ለማጣራት ላቀረበላቸው ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት ኮሚቴ በማቋቋም፤ ማስረጃዎችን በአግባቡ በመመርመር፤ ሕጋዊ ባለይዞታ አቶ ኃይሉ ገ/ሕይወት መሆናቸውን በማረጋገጥ በጽሁፍ ለፍ/ቤቱ መልስ ሰጥተዋል፡፡
በመቀጠልም፤ የሚመለከታቸው የአስተዳደር ከፍተኛ ኃላፊዎች፤ ማለትም የክፍለ ከተማው የመሬት ግንባታና አስተዳደር ዋና ኃላፊ እና የወረዳው ዋና ስራ አስፈጻሚ፣ ማስረጃዎችን ይዘው ፍርድ ቤት ቀርበው ያላቸውን መመሪያ አብራርተው፤ የማደያው ይዞታ ባለመብት አቶ ኃይሉ ገብረ ሕይወት መሆናቸውን ገልፀው፤ ካርታ በስማቸው እንዲሰራ ቢጠይቁን መሥፈርቱን ያሟሉ ስለሆነ እናስተናግዳቸዋለን በማለት አረጋግጠዋል፡፡ በአንጻሩ ሼል ኢትዮጵያ ለቦታው ምንም ዓይነት የይዞታ ማስረጃ የሌለውና በወረዳውም ሆነ በክፍለ ከተማው ለቦታው በስሙ የተከፈተ ማኅደር እንኳን አለመኖሩን በማረጋገጥ የምስክርነት ቃላቸውን ሰጥተዋል፡፡
ሆኖም የጠ/ፍ/ቤት፤ የከተማው አስተዳደር ኃላፊዎች የሰጡትን ማስረጃ እና ምስክርነት እንኳ ሳይጠቅስ፤  የማደያው ይዞታ ለሼል ኩባንያ እንዲተላለፍ ወሰነ፡፡ ይግባኙም ለሰበር ጉባዔ አይቀርብም ተባለ!! ሼል ኢትዮጵያም በአስተዳደር የተነፈገውን መብት በፍ/ቤት እንዲያገኝ ተደረገ!!
የሼል ኩባንያ ተተኪ የሆነው ኦይል ሊቢያ፤ በፍ/ቤት ወሳኔ ቦታውን ከአቶ ኃይሉ ገብረ ሕይወት የተረከበው በ2004 ዓ.ም ሲሆን፤  ግብር እስከ አሁን ድረስ (2008 ዓ.ም) የሚከፍሉት አቶ ኃይሉ ገብረ ሕይወት ናቸው፡፡ የውጭ አገር ዜግነት ያለው ኦይል ሊቢያ፤ ቦታውን ተረክቦ ኪራይና ግብር ሳይከፍል፣ በቦታው ላይ በነጻ እየነገደ ትርፉን ወደ ውጭ አገር ይወስዳል፡፡
 አቶ ኃይሉ ገብረ ሕይወት ደግሞ ቦታውን አስረክበው፣ ኪራይና ግብር ለመንግስት ይከፍላሉ!! እንዲህ ዓይነት ችግር አለ፡፡

ክቡር ሆይ
መንግስት በፀረ ሙስና እና በኪራይ ሰብሳቢነት ትግሉ ውጤታማ እንዲሆን፣ ሁሉም ዜጋ አስተዋፅዖ ለማድረግ ቁርጠኝነት እንዲነሳ፤ እንዲህ ያሉ ህዝብ የሚያውቃቸውን የአደባባይ ዝርፊያዎች ማስቆም ያስፈልጋል፡፡ አስተያየቴን አበቃሁ፡፡
በጥረትዎ ሁሉ ፈጣሪ ያበርታዎ፡፡


Read 8066 times