Saturday, 11 June 2016 12:22

የመምህራን ደሞዝ በእጥፍ ይጨምራል ተብሎ ይጠበቃል

Written by 
Rate this item
(204 votes)

5 ቢሊዮን ብር ተመድቧል
     የመምህራንን ደሞዝ ለማሻሻል በመንግስት የተመደበው የ5 ቢሊዮን ብር በጀት፣ የመምህራኑን ደሞዝ በእጥፍ ሊያሳድግ የሚችል ከፍተኛ ጭማሪ ነው፡፡ ለአስተማሪዎች “ትርጉም ያለው የደሞዝ ጭማሪ ይደረጋል” በማለት መንግስት በደፈናው መግለጫ ቢሰጥም፤ እስካሁን ዝርዝር መረጃ አላቀረበም፡፡ ጭማሪውም በዝርዝር ተሰልቶ ለትምህርት ተቋማት ገና አልተደላደለም፡፡
የዛሬ ሁለት ዓመት፣ ለመንግስት ሰራተኞች ደሞዝ ለመጨመር ውሳኔ ተላልፎ፣ ልዩ በጀት ተመድቦ እንደነበር የሚታወስ ሲሆን፣ ዘንድሮም በተመሳሳይ ሁኔታ ለመምህራን የደሞዝ ማሻሻያ፣ የ5 ቢ. ብር ልዩ በጀት ተመድቧል፡፡ ያኔ ለሁሉም የመንግስት ሰራተኞች፣ ለደሞዝ ማሻሻያ ተብሎ የተመደበው ልዩ በጀት 7 ቢ ብር እንደነበር የሚታወስ ሲሆን፣ በአማካይ የሰላሳ በመቶ የደሞዝ ጭማሪ ለማድረግ ውሏል፡፡
ከዚህ ጋር ሲነፃፀር ዘንድሮ ለመምህራን ብቻ የተመደበው የደሞዝ ጭማሪ በጀት 5 ቢሊዮን ብር መሆኑ ጭማሪው ከፍተኛ እንደሚሆን ያሳያል፡፡ የአገሪቱ የመምህራን ብዛት ሩብ ሚሊዮን እንደሚሆን የሚገመት ሲሆን፣ የወር ደሞዝ ጭማሪው በአማካይ 2500 ብር ገደማ ነው፡፡ ይህም የመምህራንን ደሞዝ በእጥፍ ለማሳደግ ያስችላል፡፡

Read 31138 times