Saturday, 11 June 2016 12:41

መልቲውና ዱርዬው ሩሶ!!

Written by  ተፈሪ መኮንን
Rate this item
(5 votes)

ዣን ጃኮቢስ ሩሶ በ1712 ዓ.ም ተወለደ፡፡ በ1778 ዓ.ም ከዚህ ዓለም ተለየ፡፡ ስለዚህ በዚህች ምድር ለ66 ዓመታት ተመላልሷል፡፡ የሩሶን ህይወት በተመለከተ ድንቅ ጽሑፍ የጻፈው በርትራንድ ሩሴል ነው፡፡ እንደሱ ሩሶን ጠንቅቆ የሚያውቅ የለም ይላሉ። ‹‹የሩሶ ኤክስፐርት›› እያሉ የሚጠሩት ስለዚህ ነው።
በርትራንድ ሩሴል፤ ‹‹በአሁኑ ዘመን ብያኔ ሩሶ ፈላስፋ ሊባል አይችልም›› ይላል፡፡ ‹‹ሩሶ የጥበብ ወዳጅ እንጂ ፈላስፋ አይደለም›› ሲል፤ የሩሴል ዘመን ፍልስፍና በሚጠይቀው የሐሳብ አካሄድ ያልተደራጀ አቀራረብ ስላለው ይሆናል፡፡ ይሁንና፤ ሩሶ በፍልስፍና የጥናት መስክ ከባድ ተጽዕኖ ያሳደረ ሰው መሆኑን አይክድም፡፡ በርትራንድ ሩሴል ለመዘርጠጥ ወደ ኋላ አይልም፡፡ ለሩሶ ግን የሚራራ ይመስለኛል። እርሱ በሩሶ ላይ የሚጨክንበት አንጀት የለውም፡፡
ስለዚህ፤ ‹‹እንደ አንድ አሰላሳይ ስለ ሩሶ የሚኖረን አስተያየት ምንም ይሁን ምን፤ ሩሶ በህብረተሰብ ህይወት ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ያሳደረ ሰው መሆኑን ሳናመነታ መቀበል ይኖርብናል›› ይላል በርትራንድ ሩሴል፡፡
‹‹ሂትለር ያራምደው የነበረው የፖለቲካ ፍልስፍና እንዲፈጠር በማድረግ ረገድ ሩሶ ቀጥተኛ ኃላፊነት ነበረው›› የሚለው ሩሴል፤ ይህንንም የፖለቲካ ፍልስፍና ‹‹ሐሳዊ-ዲሞክራሲያዊ አምባገነንነት›› (pseudo-democratic dictatorships) ይለዋል፡፡
እንደሚታወቀው፤ ሂትለር በጣም የሚወደው ፈላስፋ ፍሬድሪክ ኒች ነው፡፡ ኒች በ1887 ዓ.ም ግድም በጻፈው አንድ ማስታወሻ፤ ባርነትን ለማስወገድና የሰዎችን እኩልነት ለማረጋገጥ ይቀርብ የነበረውን ‹‹ፕሮፓጋንዳ›› በመቃወም  የጻፈው አስተያየት አለ። ኒች በዚህ ማስታወሻው፤ ‹‹ሰው በተፈጥሮ መልኩ ሲገኝ መልካምነት አለው›› በሚል ሩሶ ያቀረበውን ሐሳብ ይነቅፋል፡፡ እንደ ኒች ሐሳብ፤ የሩሶ ፍልስፍና ምንጭ የመሳፍንታዊ ባህል ጥላቻ ነው፡፡ Born out of a hatred of aristocratic culture ይለዋል፡፡ ኒች በገነፈለ ቁጣ ይህን ተቃውሞ ጽፏል፡፡
ሆኖም የበርትራንድ ሩሴል ሐሳብ፣ ከኒች ፍፁም የተለየ ነው፡፡ እርሱ የሩሶን ሐሳብ የሚያያይዘው፤ ከ‹‹sensibilité›› ጋር ነው፡፡ ‹‹sensibilité›› በቀመር እና በስሌት ላልታሰረና ስሜትን ከፍ ሊያደርግ ለሚችል የኑሮ ዘዬ (the way of living that elevates feeling over mere calculation) የሚያደላ አመለካከትን የሚያመለክት ቃል ነው። ‹‹ሩሶ የወሸኔአዊነት (Romanticism) መስራች አባት ነው›› የሚባለውም ለዚህ ነው፡፡ ወሸኔአዊነት (Romanticism) በሥነ ግጥም፣ በሥነ ስዕል እንዲሁም በፍልስፍና መስክ የታየ ንቅናቄ ነው። ይህ ንቅናቄ ከአዕምሮ ብልጠት ይልቅ የስሜት ልግስናን አብልጦ የሚያይ ነው፡፡ ረብ ካላት አንዲት አስቀያሚ ላም ይልቅ፤ እጹብ፣ ኃይለኛና ረብ የለሹ ነብር ይሻላል የሚል ነው፡፡
የሩሶን የህይወት ታሪክ የተለያዩ ሰዎች ጽፈውታል፡፡ ኮስታራ ነገር የሚወዱ የፍልስፍና ምሁራንን ቀልብ የመሳብ አቅም ቢያጣም፤ የብዙ የታሪክ ፀሐፊዎችን ልብ የሚያሸንፍ የሩሶ ታሪክ የተፃፈው፣ በራሱ በሩሶ ነው፡፡ ሩሶ ‹‹ንስሐ›› (Confessions) ሲል በጻፈው መጽሐፍ፤ የራሱን ህይወት ታሪክ ይተርክልናል፡፡
በእርግጥ ሩሶ የጻፈው ታሪክ ግድፈቶች የሚታዩበት ቢሆንም፤ የገዛ ታሪካቸውን ከፃፉ ሌሎች ሰዎች የተለየ ይዞታ ያለው አስደሳች ትረካ አበርክቶልናል፡፡ ለሩሶ ሥራ ውብ ገጽታ ካጎናጸፉት ነገሮች አንዱ፤ መልቲነቱን እያኳሸና እያጋነነ የመተረክ ዘዬው ነው፡፡ ከሩሶ ሌላ ‹‹ንስሐ›› በሚል የግል ህይወታቸውን የተረኩ አንድ ሰው አሉ፡፡ እኒህ ሰው ቅዱስ አጉስጦስ ናቸው፡፡ ሆኖም የሩሶ ‹‹ንስሐ››  እንደ ቅዱስ አጉስጦስ አይደለም፡፡ ቅዱስ አጉስጦስ በእያንዳንዷ የዕለት ህይወታቸው የፈፀሙትን እኩይ ተግባር (ፒር የሚባል ፍሬ ስለ መስረቃቸው፣ ጓደኛቸው በሞተ ጊዜ ስላደረባቸው ሐዘን ወዘተ) እየተረኩ ያጫውቱናል፡፡ የሩሶ እንዲህ አይደለም፡፡ ሩሶ የሚናዘዘው ከባድ ሐጢያቶቹን ነው፡፡
ለምሣሌ፣ የሚኖርበት ቤት ለማግኘት ሲል ዋሽቶ ‹‹የካቶሊክ እምነትን ተቀብያለሁ›› ስለማለቱ፤ የሰው ዕቃ ሰርቆ የእርሱን ሐጢያት በአንዲት የቤት ሠራተኛ ላይ እንደደፈደፈ፤ ያቺን ሴት በሐሰት እንዴት እንዳዋረዳት ይነግረናል፡፡ አንድ ልጁን (ሊያጋጥም ይችላል) ወይም ሁለት ልጆቹን (ይህ እንኳ ከንቱነት ነው) ሳይሆን፤ ከአብራኩ የወጡ አምስት ልጆቹን ለማደጎ ቤት እንደሰጠም ይተርክልናል፡፡
በአጭሩ ሩሶ መልቲ ነው፡፡ ግን እያንዳንዱን ክፋቱን ወይም መጥፎ ስራውን አንዳች ሳይሳቀቅ፤ ኧረ እንዲያውም በጋለ ስሜት፤ ዝርዝር አድርጎ ይተርክልናል፡፡ ሩሶ ‹‹ካቶሊክ እምነትን ተቀብያለሁ›› እያለ ብዙ ጊዜ አታሏል፡፡ የሚያታልለው (በሁሉም አጋጣሚዎች) የሆነ ጥቅም ለማግኘት ነው፡፡ ይህ የውሸት መሐላ የሚጀምረው፤ ሩሶ  የትውልድ ሐገሩን ጀኔዋን ለቅቆ በተሰደደ ጊዜ ነው፡፡ ጀኔዋም የአጥባቂ ‹‹ካልቪኒስቶች›› ማዕከል ነበረች፡፡
ታዲያ ሩሶ በዕደ ጥበብ ሥራ የሚተዳደሩ አጎቱን የማገዝ ኃላፊነት መቀበልን ጠልቶ ወይም ሥራን ሸሽቶ ጀኔዋን ለመልቀቅ ወሰነ፡፡ በዚህ ወቅት ከአንድ የዋህ የካቶሊክ ቄስ ተገናኘ፡፡ ሩሶ ወንበዴ ልቡ የምታስበውን ነገር ደብቆ ቄሱን እንዴት እንዳታለለ ያጫውተናል፡፡ አንዲት የቤት ሠራተኛ ልጃገረድን እንዴት እንደካዳት ያወጋናል፡፡ ያችን ምስኪን ልጃገረድ የካዳት፤ የካቶሊኩ ቄስ ልከውት ሄዶ፤ ቅቤ በሆነ አፉ አጭበርብሮ ከአንዲት ሐብታም መሳፍንታዊ (aristocratic) ሴት ቤት ገብቶ የመኖር ዕድል ባገኘ ጊዜ ነው፡፡
ይህች ባለጸጋ ሴት፤ ከብር የተሰራ ጌጥ ያለበት አንድ ሪቫን ነበራት፡፡ ሩሶ ይህን ሪቫን ሰረቀ። ‹‹ሪቫኑን ያነሳው ማነው?›› ቢባል፤ ሐጢያቱን በምስኪኗ ልጃገረድ ላይ ደፈደፈ፡፡ ሩሶ ስለዚህ ክህደት ሲጽፍ፤ ከሥነ ልቦና አንጻር የሚታይ አንድ አስገራሚ ምልከታ ያነሳል፡፡ እንዲህ ይላል፤ ‹‹በዚያች ጨካኝ ቅጽበት እኩይነት ከኔ አልራቀችም ነበር፡፡ ነገሩ ግርቢጥ ሊመስል ይችል ይሆናል፡፡ ሆኖም እኔ ያቺን ምስኪን ልጃገረድ በሐሰት የከሰስኳት፤ ልጅቷን እወዳት ስለነበረ ነው፡፡ ልጅቱ በህሊናዬ ጓዳ ሥፍራ ይዛ ነበር፡፡ ስለዚህ ድንገት ሲያፋጥጡኝ፤ ሐጢያቴን በህሊናዬ ቀድሞ ብቅ ባለው ሰው ላይ ጣልኩት›› ይላል፡፡
ሩሶ ታሪኩን ሲተርክ፤ አስቀያሚ ክስተቶቹን በዝርዝር እያነሳ ነው፡፡ ያን ሪቫን የሰረቀው፤ በእንግድነት የተቀበለችው ሴት በሞተች ጊዜ ነበር፡፡ ሲያነሳው ማንም አያየኝም ብሎ ነው፡፡ ሆኖም ነገሩ እንዳሰበው አልሆነም፡፡ ይህን ጉዳይ አስመልክቶ ሲተርክ፤ ‹‹በዚያ ቤት ያሉት ሰዎች እያንዳንዷን ሐብት በጥንቃቄ የሚይዙ ናቸው፡፡ ጌታ ሎሬነዚና እመቤት ሎሬንዚ ንብረታቸውን አጥብቀው የሚቆጣጠሩ ሰዎች በመሆናቸው፤ ንብረት ሲቆጣጠሩ የማድሞዜል ፖንታል ንብረት የሆነችና አዘውትረው ያደርጓት የነበረች ፒንክና ብርማ ቀለም ያላት አንዲት የአንገት ልብስ ከማጣታቸው በቀር፤ ከቤቱ ንብረት አንድ የጠፋ  ነገር አልተገኘም፡፡ በእርግጥ ልቤን ዷ ያደረገችው ያቺ ሪቫን ሰለሆነች እርሷን አነሳሁ እንጂ የበለጠ ዋጋ ያላቸው በርካታ ነገሮችን ለማንሳት የምችልበት ዕድል ነበረኝ፡፡ ያቺን ሪቫን ሰርቄ ከወሰድኩ በኋላ፤ ሰው እንዳያይ አድርጌ ለመደበቅ ብዙ አልተጨነቅኩም፡፡ ስለዚህ ወዲያው አገኟት፡፡ ‹ከዚያ ይህን ሪቫን ከየት አግኝተህ ወሰድክ› ብለው አፋጠጡኝ፡፡ በነገራቸው ትንሽ ግራ ተጋባሁ። ትንሽ አንገራገርኩ፡፡ እንዲያ በግራ መጋባት ስሜት እንደ ተዘፈቅኩ፤ ‹ማሪዮን ነች የሰጠችኝ› አልኳቸው።››
ከዚያም ሩሶ የማዕድ ቤት ሠራተኛ የሆነችውና ‹‹ማለፊያ ሾርባ ትሰራለች›› እያለ የሚያመሰግናት ማሪዮን ምን እንደምትመስል ወደ መግለጽ ይሻገራል፡፡ እንዲህ ይላል፤ ‹‹ማሪዮን ቆንጆ ልጃገረድ ብቻ አልነበረችም፡፡ በተራሮቹ በሚኖሩት ሰዎች ዘንድ ብቻ የሚታይ አይነ ግቡ የቆዳ ቀለም ያላት፤ ከሁሉም በላይ አመለሸጋ የሆነችና ትሁት ባህርይን የታደለች  በመሆኗ ያያት ሁሉ የሚወዳት ሴት ነች፡፡ ማሪዮን፤ ደግ፣ የጠራ ምግባር ያላትና በሥራዋ እንከን  የማይገኝባት ጥንቁቅ ሴት ናት፡፡ ‹ማሪዮን ሰጠችኝ› ብዬ ስለዋሸሁ፤ ተጠርታ በመጣች ጊዜ በዚያ ያያት ሰው ሁሉ ተገረመ፡፡ በእኔ ላይ ያላቸው አመኔታ ከእርሷ የሚተናነስ አልነበረም፡፡ ስለዚህ ማንኛችን እንደ ሰረቅን ማረጋገጡ አስፈላጊ ሆኖ ታያቸው፡፡ ማርዮን ተጠራች፡፡ የ‹‹ዴላ ላሮክ›› ገዢን ጨምሮ በርካታ ሰዎች በእልፍኝ ነበሩ፡፡ ማሪዮን መጣች። ሪቫኑን አሳይዋት፡፡ ጠየቋት፡፡ እኔ ድርቅ ብዬ ሐጢያቱን ለእርሷ አሸከምኳት፡፡ እርሷም በጣም ግራ ተጋብታ የምትናገረውን አጣች፡፡ ጨርሶ ዱዳ ሆነች፡፡ ዲያቢሎስን እንኳ ሊያንበረከርክ የሚችል ኃይል ባለው የንፁህ ሰው ዓይን አየችኝ፡፡ ሆኖም ጨካኙ ልቤ ተቋቁሞ ፀና›› ይላል፡፡
ሩሶም እንደ ቅዱስ አጉስጦስ፣ እኩይ ምግባሩን እያፍታታ ይዘረዝራል፡፡ እንዲህ እያለ ይቀጥላል፤  ‹‹እርሷም ያለ አንዳች ቁጣ ፍርጥም ብላ አስተባበለች። ወደ ልቤ እንድመለስ እያደፋፈረች፤ ክፋት አድርጋብኝ የማታውቅ ንፁህ ሴትን ከመጉዳት እንድቆጠብ እየወተወተች ተናገረች። እኔም በሲኦላዊ ጋጠወጥነት  በእርሷ ላይ ክሴን አፀናሁ፡፡ እዚያው ከፊቴ እንደ ቆመች ሪቫኑን እሷ እንደ ሰጠችኝ ተናገርኩ፡፡ በዚያ ጊዜ፤ ያች ምስኪን ልጃገረድ፤ ‹‹አቤት ሩሶ!! እኔ ጨዋ ያሳደገህ ትመስለኝ ነበር፡፡ አሁን በጣም አስከፋኸኝ፤ ያም ሆኖ እኔ ራሴን ወደ አንተ ቦታ ማውረድ አልፈልግም›› አለች፡፡
ማሪዮን ስሜቷን እንዴት እንደ ተቆጣጠረችው ሲገልጽ፤ ‹‹ለመገመት የሚያስቸግር በደል በደልኳት። በአንድ በኩል ዲያቢሎሳዊ ምስክርነት፤ በሌላ በኩል መልአካዊ ገርነት ተፋጥጠውው ቆሙ›› ይላል። በመጨረሻም፤ አገረ ገዢው ሁለቱንም በአንድ ቃል አንድ ላይ ጠፍረው ሸኟቸው፤ ‹‹የወንጀለኛ ህሊና በንፁሃን ላይ ለበቀል ይነሳል›› ነበር ያሉት። ሩሶ ቀጥሎ፤ ‹‹ያቺ ሴት በሁሉም ረገድ ለእርሷ ባህርይ ተቃራኒ በሆነ ጨካኝ ፍረጃ እንደጎበጠች የምትኖር ይመስለኛል›› እያለ ይተርካል፡፡ በሌብነት መጠርጠር ብቻ አይደለም፡፡ ሩሶን በፍቅር ለማሸነፍ የምትፈልግና ይህም ነውር ሲጋለጥ ሽምጥጥ አድርጋ የካደች ሴት ተደርጋ ታስባለች፡፡ ታዲያ ሩሶ በዚህች ሴት ላይ ባደረሰው በደል ዕድሜ ልክ እንደ ተሰቃየ ኖሯል፡፡ በህልም እርሷን እያየ ይቃዣል፡፡
ይሁንና ሩሶ ጨርሶ መጽናኛ የሚያጣ ሰው አይደለም፡፡ ዓለም እንደ ሩሶ መልከ መልካም ወጣት የሆነን ሰው፤ ወዳጃቸው ለማድረግ የሚሹ በርካታ ባለፀጋ ሴቶች የሚገኙባት ነች፡፡ ስለዚህ መልቲው ሩሶ ጨርሶ መጽናኛ አላጣም፡፡ ከዚያ በኋላ በነበሩት አስር ዓመታት፣ በማዳም ዲ ሳቮይ (Madame de Savoy) ቤት የመኖርና በሂደትም የእሳቸው ውሽማ ለመሆን በቅቷል፡፡ ሩሶ ማዳም ዲ ሳቮይን የወሸማቸው፤ ከእርሱ በፊት የያዙት ወዳጅ እያለ ነው፡፡ እንዲያውም ሦስቱ የተዋጣላቸው ወዳጆች ሆኑ፡፡
ሩሱ ማዳምን ‹‹Maman›› እያለ ይጠራቸው ነበር፡፡ እርሳቸውን በወዳጅነት ይዞ፤ የሚጽፈውን እየጻፈ፤ በዕድሜ የሚበልጡት ወዳጁን ንብረት የሚወርስበትን ቀን ይናፍቀው ነበር፡፡ ይህን የሚነግረን ራሱ ነው፡፡
እናንተ የሩሶን ገመና ከዚህ በላይ ለመስማት ፈቃደኛ አትመስሉኝም፡፡ እርሱ ግን ከበደሉ ያስቀረው ሳይኖር በዝርዝር ጽፎታል። እንዲያው እንዲህ ይላል፤ ‹‹በዕድሜ ዘመኔ የሰራሁትን ኃጢያት በሙሉ በዚህ መጽሐፍ ደጉሼ ስላኖርኩት፤ ክርስቶስ በዳግም ምጽአት ሲመጣ፤ የኔን ሐጢያትና በደል ለማወቅ አይንገላታም፡፡›› መልቲው እና ዱርዬው ሩሶ፤ ሁላችንንም የነፍስ አባቱ አድርጎናል፡፡                               


Read 4331 times