Saturday, 11 June 2016 13:14

በውዝግብ የታጀበው የ31ኛው ኦሎምፒያድ ተሳትፎ

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(4 votes)

በኦሎምፒክ ዓመት የውዝግብ አጀንዳዎች እየተለመዱ መጥተዋል
በየአራት ዓመቱ በሚካሄደው ኦሎምፒክ  ላይ በመካከለኛና በረጅም ርቀት ውድድሮች ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ስኬታማ ናቸው፡፡  ከ31ኛው ኦሎምፒያድ በፊት ኢትዮጵያ ተሳትፎ ባደረገችባቸው 12 ኦሎምፒያዶች በአጠቃላይ 21 የወርቅ፣ 7 የብርና 17 የነሓስ በድምሩ 45 ሜዳሊያዎችን በመሰብሰብ በምንግዜም የውጤት ደረጃ ከዓለም አገራት በ34ኛ ደረጃ ላይ  እንደምትገኝም ይታወቃል፡፡ ኢትዮጵያ በኦሎምፒክ መድረክ በተለይ በረጅም ርቀት በ10ሺ እና በ5ሺ ሜትር ውድድሮች እንዲሁም በማራቶን  በሁለቱም ፆታዎች ከፍተኛውን ውጤት ያስመዘገበች አገር ናት፡፡ ባለፉት 12 ኦሎምፒያዶች በ1956 ሜልቦርን 12፤ በ1960 ሮም 10፤ በ1964 ቶኪዮ 12፤ በ1968 ሜክሲኮ 18፤ በ1972 ሙኒክ 31፤ በ1980 ሞስኮ 45፤ በ1992 ባርሴሎና 20፤ በ1996 አትላንታ 18፤ በ2000 ሲድኒ 26፤ በ2004 አቴንስ 26፤ በ2008 ቤጂንግ 27 እንዲሁም በ2012 ለንደን 35 ኦሎምፒያኖች ኢትዮጵያን በመወከል በኦሎምፒክ መድረክ ተወዳድረዋል። በ12 ኦሎምፒኮች ለኢትዮጵያ የተገኙትን 22 የወርቅ ሜዳልያዎች ያስመዘገቡት 12 አትሌቶች ሲሆኑ እነሱም አበበ ቢቂላ ፤ ማሞ ወልዴ፤ ምሩፅ ይፍጠር፤ ፋጡማ ሮባ፤ ደራርቱ ቱሉ፤ ኃይሌ ገብረስላሴ፤ ገዘሐኝ አበራ፤ ሚሊዮን ወልዴ፤ ቀነኒሳ በቀለ፤ጥሩነሽ ዲባባ፤ መሰረት ደፋር እና ቲኪ ገላና ናቸው፡፡ በአጠቃላይ 25 አትሌቶችም በተለያዩ ደረጃዎች የኦሎምፒክ ሜዳልያ ተሸላሚዎች ነበሩ፡፡  የኢትዮጵያና ኦሎምፒክ ትስስር  ከ60 ዓመታት በላይ ሆኖታል፡፡ ይህም በኦሎምፒክ መድረክ ተጽዕኖ ከሚፈጥሩ አገራት ተርታ የሚያሰልፋት ነው፡፡ ካለፉት ሁለት ኦሎምፒያዶችም ወዲህ ግን የኢትዮጵያ  ተሳትፎ በኦሎምፒክ መድረኩ ዋዜማ እና ማግስት በሚነሱ የተለያዩ የውዝግብ አጀንዳዎች የሚጠመድ ሆኗል። ዘንድሮም በ31ኛው ኦሎምፒያድ ዋዜማ ወራት ላይ የተለመደው ውዝግብ ቀጥሏል፡፡ በየኦሎምፒያዱ የሚነሱት የውዝግብ አጀንዳዎቹ የተለያዩ ናቸው። በኦሎምፒክ ተሰላፊ አትሌቶች እና ቡድኖች ምርጫ ዙርያ የሚነሱ ቅሬታዎች እና ሙግቶች መደበኛዎቹ ችግሮች ናቸው፡ በአትሌቶች ዝግጅትና ስልጠና የሚፈጠሩ አለመግባባቶችም ተባብሰው ቀጥለዋል፡፡ በተጨማሪም በኦሎምፒክ ልዑካን አባላት አመራረጥና ተገቢነት  ጥያቄ የሚነሳባቸው አስተዳደራዊ ጥፋቶችም የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ በሌላ በኩል ከእያንዳንዱ ኦሎምፒክ  በኋላ በሚያሽቆለቁሉ ውጤቶች እና ደካማ ተሳትፎዎች ዙርያ በባለድርሻ አካላት በርካታ ትችቶችና ግምገማዎች ይቀርባሉ፤ ግን መፍትሄዎችን ሳያገኙ   ተድበስብሰው የሚቀሩበት ሁኔታም ይስተዋላል፡፡
ከ31ኛው ኦሎምፒያድ በፊት ባለፉት ሁለት ኦሎምፒያዶች ያጋጠሙ የውዝግብ አጀንዳዎችን ማስታወስ ይቻላል፡፡ በ2008 እኤአ ቤጂንግ ባስተናገደችው  29ኛው ኦሎምፒያድ ከተሳትፎው በኋላ የተፈጠረ ውዝግብ ነበር፡፡ ቤጂንግ ላይ ኢትዮጵያ ያስመዘገበቻቸው አራት ወርቅ ሜዳልያዎች በሁለቱ ታላላቅ አትሌቶች ጥሩነሽ ዲባባ እና ቀነኒሳ በቀለ ብቻ መገኘታቸውን ተከትሎ የተተኪ ችግር እንዳለ ተጠቅሶ ባለድርሻ አካላቱን ያነታረከው አጀንዳ ማለት ነው። በ2012 እኤአ ላይ ለንደን ባስተናገደችው 30ኛው  ኦሎምፒያድ ጋር በተያያዘም  ከተሳትፎው በፊት እና በኋላ ያጋጠሙት የውዝግብ አጀንዳዎችም ይታወሳሉ። በለንደን ኦሎምፒክ ዋዜማ በተለይ የአበባ አረጋዊ ጉዳይ የማይዘነጋ ሲሆን አትሌቷ በኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ቡድን የመሳተፍ እድሏ በፌደሬሽኑ ብልሹ አሰራር ተስተጓጉሎባት ዜግነቷን በመቀየር ለስዊድን ተወዳድራ በ1500 ሜትር የወርቅ ሜዳልያ በማግኘቷ በቁጭት ብዙዎችን ያወዛገበ ነበር፡፡  በሌላ በኩል ከኦሎምፒክ ልዑካን አባላት  መካከል ትልልቅ አሰልጣኞች እና መሄድ ያለባቸው የሚዲያ ተቋማት እድል ተነፍገው በርካታ የፌደሬሽንና የኦሎምፒክ ኮሚቴ  ሃላፊዎች ያለአግባብ   እንዲጓዙ የተደረገበት አስተዳደራዊ ቅሌት  በአጨቃጫቂነቱ የታለፈ ነበር፡፡ ከውጤት ማሽቆልቆል በተያያዘም በለንደን ኦሎምፒክ በ10ሺ ሜትር ወንዶች የተበላሹት የሜዳልያ ክብሮችን ምክንያት በማድረግ በስልጠና፤ በቡድን ታክቲክ እና በተተኪ ማፍራት ዙርያ የቀረቡ ትችቶችና ግምገማዎች አትሌቲክሱን ያተራመሱ ነበሩ፡፡
የአትሌቶች ተቃውሞ   ወቅቱን አልጠበቀም
ከ31ኛው ኦሎምፒያድ በፊት ባሉት የዋዜማ ወራት የተፈጠሩት የውዝግብ አጀንዳዎች ደግሞ ካለፉት ኦሎምፒያዶች የተሻገሩ ከመሆናቸውም በላይ በተቃውሞ ይዘታቸው የስፖርቱን አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረስ የሚያመለክቱ ናቸው፡፡  በተለይ በሳምንቱ መጀመርያ ላይ በአዲስ አበባ ስታድዬም ጥላ ፎቅ በርካታ አትሌቶች ያልተጠበቀ ልዩ ስብሰባ ማድረጋቸው በአትሌቲክሱ ያሉ ችግሮች ውስብስብ ደረጃ ላይ መድረሳቸውን ያመለከተ ነበር፡፡  ከ31ኛው ኦሎምፒያድ ጋር ተያይዞ የተካሄደው ስብሰባው በተለይ ከጅምሩ አወዛጋቢ ለመሆን በበቃው የማራቶን አትሌቶች ምርጫ ዙርያ ቢቆሰቆስም፤ አትሌቶች  በአትሌቲክስ ፌደሬሽኑ አጠቃላይ አሠራር ስርነቀል ለውጥ መፈለጋቸውን የመከሩበት እና  ተድበስብሰው የቆዩ ብሶቶቻቸውን ያንፀባረቁበት ሆኗል፡፡  በአዲስ አበባ ስታድዬም ጥላፎቅ የተካሄደው ይህ ስብሰባ በአትሌቲክስ ፌደሬሽኑ  እውቅና የተነፈገው ቢሆንም  ታላላቅ የቀድሞ ኦሎምፒያኖች፤ አንጋፋ አትሌቶች፤ ታዳጊ እና ወጣት አትሌቶች፤ አሰልጣኞቻቸውና ማናጀሮቻቸውን በማሳተፍ መብታችን ለማስከበር የማንም ፍቃድ አንጠይቅም  በሚል አቋም የተካሄደ ነበር፡፡
በጥላ ፎቁ ስብሰባ ላይ የአትሌቲክስ ፌደሬሽኑን አስተዳደራዊ አምባገነንት የሚያወግዙ አስተያየቶች ተሰምተዋል፡፡  ፌደሬሽኑ በቂ  ልምድ፤ እውቀትና የስራ ፍላጎት በሌላቸው የስራ አስፈፃሚ አባላት እየተመራ ነው የሚሉ ትችቶች ቀርበዋል፡፡  ከተመሰረተ ሁለት ዓመት እንኳን ያልሞላው የአትሌቶች ማህበርም ክፉኛ ተብጠልጥሏል፡፡  ማህበሩ እንደማይወክላቸው፤ እውቅና እንደማይሰጡት እና በአዲስ መልክ እንዲደራጅ  ፍላጎት መኖሩም በአስተያየቶቻቸው ተንፀባርቋል፡፡ በተለይ የአትሌቶች ማህበር ለአትሌቶች ከመቆም ይልቅ ‘ለፌደሬሽኑ የወገነ’ በማለት የገለፁት አቋም ይጠቀሳል፡፡
በአጠቃላይ በአትሌቲክስ ፌደሬሽኑ እና በአትሌቶች ማህበር አሰራር መከፋታቸውን የገለፁት አትሌቶች በጥላ ፎቅ ያደረጉትን ስብሰባ ያጠቃለሉት ከማህበሩ ውጭ   የሚወክሏቸውን 10 የኮሚቴ አባላት በመምረጥ ነበር፡፡ ከኮሚቴው አባላት መካከል አትሌት ሀይሌ ገብረ ስላሴ፣ ቀነኒሳ በቀለ፣ ገዛህኝ አበራ፣ ገብረእግዚአብሄር ገብረማርያም፣ አሰለፈች መርጊያ፣ ፋንቱ ምጌሶ፣ የማነ ፀጋዬ ይጠቀሳሉ፡፡ የአትሌቶች ማህበር ጠቅላላ ጉባኤ እንዲጠራ ፍላጎት ያለው ኮሚቴው አትሌቶች በሚያነሷቸው ጥያቄዎች ዙሪያ መፍትሔን ለማፈላለግ እንደሚሰራ ተገልጿል፡፡
አትሌቶች ጥያቄዎቻቸው ምላሽ ካላገኙ ሰለፍ ለመውጣት እንደሚወስኑም በጋራ ተስማምተዋል፡፡
ከዓለማችን የረጅም ርቀት የምንግዜም ምርጥ አትሌቶች ግንባር ቀደም ተጠቃሽ የሆነው አትሌት ቀነኒሳ በቀለ ከሪዮ ኦሎምፒክ መቅረቱ በአገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ሚዲያዎችም ያነጋገረ ነበር፡፡ ቀነኒሳ ከማራቶን ቡድኑ ውጭ መሆኑን በመቃወም በከፍተኛ ደረጃ ቅሬታውን ሲገልፅ፤ ምርጫው ግልፅነት የጎደለው፤ ከዓመት በፊት የተመዘገቡ ሰዓቶችን የተንተራሰ እና ወቅታዊ ብቃትን ከግምት ያላስገባ ነው ብሎ በማለት አጣጥሎታል፡፡ ለአትሌቶች ማህበር የሚሰጠው እውቅና አለመኖሩን በይፋ የገለፀው አትሌቱ በፌደሬሽኑ አጠቃላይ አሰራር ሞራሉ እንደተነካም ጨምሮ ተናግሯል። በብሔራዊ ፌዴሬሽኑና በወቅታዊው የአትሌቲክሱ ሁኔታ ከመቼውም ጊዜ በላቀ ሁኔታ በመሟገት ላይ ካሉ ታዋቂ አትሌቶች  መካከል ኃይሌ ገብረሥላሴም ይጠቀሳል፡፡ ፌደሬሽኑ፤ የአትሌቶች ማኅበር አመራሮች እና የአትሌቲክሱ ማህበረሰብ ጋር ዘላቂነት ያለው የመፍትሔ አቅጣጫ ለማስቀመጥ ተቀራርበው መምከር እንዳለባቸው በተደጋጋሚ እየተናገረ ነው፡፡ የብሔራዊ ፌዴሬሽኑ መዋቅራዊ ይዘት ኋላቀር ነው ብሎም ትችት ያቀርባል፡፡ አሁን ባለው የፌደሬሽን አመራር  ተተኪ አትሌቶች የማግኘት ተስፋ መመናመኑን ፤ ሙያተኞችና ልምድ ያላቸውን አትሌቶች በማያሳትፍ ደካማ አሠራር መማረሩን ይገልፃል፡፡ በአትሌቲክሱ እየተፈጠረ ስላለው ችግር ታዋቂ አትሌቶች በተለይ ካለፉት ስምንት ወራት ወዲህ ሲነጋገሩ መቆየታቸውን የሚያመለክቱ መረጃዎች  በሚነሱ ቅሬታዎች ዙርያ አጥጋቢ ምላሾች እና መፍትሄዎች አለማገኘታቸው ውዝግቡን እንዳባባሰው ያረጋግጣሉ፡፡ ብዙዎቹ አትሌቶች በስፖርቱ ከፍተኛ ልምድ ባላቸው አትሌቶች እና ባለሙያዎች አትሌቲክሱ መመራት አለበት የሚል አቋም እንደያዙ ናቸው፡፡
የፌደሬሽኑ አመራሮች አቋም አጠያያቂ ሆኖ ቀጥሏል
ከጥላ ፎቁ ልዩ ስብሰባ በኋላ በሳምንቱ አጋማሽ ላይ ደግሞ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴና ለሪዮ ኦሎምፒክ በሁለቱም ፆታዎች በማራቶን ኢትዮጵያን የሚወክሉ አትሌቶች በጋራ ሆነው መግለጫ ሰጥተዋል፡፡ የፌደሬሽኑ አመራሮች፤ የአትሌቶች ማህበር፤ በማራቶን የሚወዳደሩ ኦሎምፒያኖች እና የኦሎምፒክ ኮሚቴው ተወካዮች ያሳተፈው መግለጫ አትሌቶች በጥላ ፎቁ ላይ ባደረጉት ድንገተኛ ስብሰባ  አፀፋዊ ምላሽ ለመስጠት እንዳልተዘጋጀ በማሳወቅ  የተካሄደ ነበር፡፡ በማራቶን ቡድኑ ምርጫ ፌደሬሽኑ የተጠቀመው መስፈርትን ለአትሌቶች ዘግይቶ ማድረሱ እና አጠቃላይ የምርጫ ሂደቱ አወዛጋቢ ሆኖ ብዙዎችን ቅር በማሰኘቱ ይቅርታ መጠየቁ በመግለጫው ትኩረት ከሳቡ አጀንዳዎች ዋንኛው ሆኖ ይጠቀሳል። የአትሌቲክስ ፌደሬሽኑ ሃላፊዎች ከይቅርታው ባሻገር የማራቶን ተሳታፊዎችን በመረጠበት አሰራር ሃላፊነቱን እንደሚወስድ በሚመዘገበው ውጤት መሰረት ተጠያቂ እንደሚሆን ገልፀው፤ ምርጫው በየትኛውም ጫና እንደገና የሚፐወዝበት ሁኔታ እንደማይኖርም አረጋግጠዋል፡፡ ለአትሌቶች ማህበር እና ለአትሌቲክስ ፌደሬሽኑ የቅሬታ ማመልከቻ በማስገባት የተሟገቱት ቅሬታ ያላቸው አትሌቶች ከ12 በላይ ነበሩ፡፡ ምርጫው ወቅቱን ያልጠበቀ፤ በማወዳደርያ መስፈርቶቹ ግልፅነት የጎደለው እና አላግባብ የተቀያየረ ፤ ከአገር ጥቅም ይልቅ የግለሰቦች ፍላጎትን የተንፀባረቀበት፤ ወቅታዊ ብቃት እና አቋምን ከግምት ያላስገባ እንዲሁም አሳማኝ ያልሆኑ የምርጫ መስፈርቶች ተግባራዊ የሆኑበት በማለት እንዳወገዙት ይታወቃል፡፡ ቅሬታቸውንም በተለያዩ የአገር ውስጥ እና ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ማሰማታችው ይታወቃል፡፡ የማራቶን ኦሎምፒያኖች ምርጫው ልምድ ያላቸው አንጋፋ አትሌቶች፤ የአትሌቶች ማህበር፤ የማራቶን አሰልጣኞችን እንዲሁም ማናጀሮችን ማካተት እንደነበረበት ተከራክረዋል፡፡ በተለይ ደግሞ በዋናነት ምርጫውን ያከናወነው የፌዴሬሽኑ ቴክኒክ ኮሚቴ በአባላት ስብስቡ የማራቶን አሰልጣኝ አለማካተቱን ክፉኛ መንቀፋቸውም አይዘነጋም፡፡
በጥላ ፎቁ የአትሌቶች ስብሰባ ላይ ፌደሬሽኑ ስር ነቀል ለውጥ እንደሚያስፈልገው፤ ስፖርቱን ለመምራት ብቁ አመራር እንደሌለው በመግለፅ የተንፀባረቁ አቋሞች ላይም የአትሌቲክስ ፌደሬሽኑ ሃላፊዎች በሰጡት መግለጫ ምላሽ ነበራቸው፡፡ አትሌቲክስ ፌደሬሽኑ በሚከተለው አሰራር፤ ባሉት የስራ አስፈፃሚ አባላት የሙያ ብቃት እና የአካዳሚ እውቀት በአፍሪካ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ምሳሌ እንደሚሆን የተገለፀበት ነው፡፡ ፌደሬሽኑ ህጋዊ ስርዓትን ተከትሎ  የሚንቀሳቀስና ስልጣኑን በሰጠው ጠቅላላ ጉባኤ የሚመራ ተቋም መሆኑን ያስገነዘቡት ሃላፊዎቹ በአትሌቲክሱ ቀድሞ በነበረ ስምና ዝና ብቻ የሚናድ አሰራር የለውም በሚልም ተሟግተዋል፡፡
የአትሌቶች ማህበር ፈተና ውስጥ  ገብቷል
በአትሌቲክስ ፌደሬሽኑ ምርጫ በሪዮ ኦሎምፒክ ቡድን የታቀፉ ዋና እና እጩ ኦሎምፒያኖች በጥላፎቁ ስብሰባ አልነበሩበትም፡፡ ከፌደሬሽኑ ቅጣት እንዳይጣልባቸው በመስጋት አለመሳተፋቸውን እንደምክንያት ያቀረቡ መረጃዎችም ነበሩ፡፡ በሌላ በኩል ግን የአትሌቶች ማህበር መሪዎች እና የአትሌቶች ተወካይ ስለሺ ስህን እና መሰረት ደፋር  አልተገኙበትም፡፡ ጥቂት በማይባሉ አትሌቶች እውቅና የተነፈገው የአትሌቶች ማህበር ከተቋቀመ ሁለት ዓመት እንኳን አልሞላውም፡፡ ማህበሩ ከተቋቋመ በአጭር ጊዜ ውስጥ ካከናወናቸው ጉልህ ተግባራት አትሌቶች በማናጀሮቻቸው ተወስዶባቸው የነበረውን ከ450 ሺህ ዶላር በላይ  በማስመለስ የፈፀመው ተግባር ብቻ ነው፡፡ በርካታ አትሌቶች ከሚሰጧቸው አስተያየቶች አንፃር ሁሉንም አትሌቶች ያቀፈ አመራር  አለመሆኑን ለመገንዘብ አያዳግትም፡፡ በርግጥ አትሌቶች በጋራ የሚንቀሳቀሱበት እና ለመብታቸው የሚቆምላቸው ማህበር ያስፈልጋቸዋል፡፡ አሁን ያለው ማህበር የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽንን የሚወግን አድርገው ማየታቸው ግን የሚያሳስብ ነው፡፡ ማህበሩ በተሟሉ አባላት እና ተቀባይነት በድጋሚ መደራጀት እንደሚያስፈልገው ያጋጠሙት ሁኔታዎች ያመለክታሉ፡፡፡ የአትሌቶች ማህበር አመራር በበኩሉ በጥላፎቅ የተደረገውን የአትሌቶች ድንገተኛ ስብሰባ ከሪዮ ኦሎምፒክ በኋላ በሁሉም ባለድርሻ አካላት ሊደረግ የታቀደውን ምክክር ያፈረሰ መሆኑን በመግለፅ ተቃውሞታል፡፡ በጥላፎቁ ስብሰባ የተቋቋመው ኮሚቴ ህጋዊ መሰረት እንደሌለው እና ማህበሩም እንደማያውቀው ጨምሮ ተገልጿል፡፡
የውዝግቦቹ አሳሳቢ ሁኔታዎች እንደመደምደሚያ
በአጠቃላይ ኢትዮጵያ በምትሳተፍባቸው ዋና የአትሌቲክስ ውድድሮች እስከዛሬ በተረጋጋ እና በተሟላ ሁኔታ ዝግጅቶች እየተካሄዱ አለመሆናቸው ሥጋት ይፈጥራል፡፡ በተለይ በኦሎምፒክ ውጤታማነታቸው የሚታወቁ ታላላቅ አትሌቶች በብሔራዊ ፌዴሬሽኑ አጠቃላይ አሰራር በተደጋጋሚ ተቃውሞ ማብዛታቸውን የተሳታፊ ኦሎምፒያኖችን ትኩረት ከማዛባቱም በላይ የርስበርስ ግንኙነቱን በተለያዩ ችግሮች የሚያወሳስበው ይሆናል፡፡ በተቃውሞ ላይ የሚገኙት አትሌቶች በተነሱት አወዛጋቢ አጀንዳዎች ዙሪያ ከአመራሮች ጋር በመወያየት የጋራ መግባባት ላይ ደርሰው ለውጥ ለማምጣት ይፈልጋሉ፡፡ በፌደሬሽኑ በኩል ግን ይህን አቋም ወደ ጎን ያደረጉ እርምጃዎች መስተዋላቸው ውዝግቦቹን እያባባሳቸው ይገኛል፡፡
በአትሌቶቹ የተነሳው ተቃውሞ ከኦሎምፒክ በፊት ሆነ በኋላ  ወደ ጎን የሚተው አይደለም፡፡ ይሁን እንጂ ሁሉንም ባለድርሻ አካላት አገናኝቶ መፍትሔው ለማምጣት በቂ ጊዜ ያስፈልግ ነበር፡፡ ውዝግቦቹ የኦሎምፒክ ቡድኑን ዝግጅት ማስተጓጎላቸው አልቀረም፡፡ በሞራል፤ በበቂ የዝግጅት ጊዜ እና መርሃ ግብር ለመስራት እና በተጠናከረ የቡድን መንፈስ የሪዮ ኦሎምፒክን ለመሳተፍ እንቅፋቶች መብዛታቸውም ያስደነግጣል፡፡
የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኑ በዘርፈ ብዙ ችግሮች ሲተማ የቆየ ነው፡፡ ሯጮችን በእኩልነት የማያስተዳድር፤ በሙስና የተውተበተበ፤ በብሔርና በፖለቲካ አጀንዳዎች  የተከፋፈለ፤ ታላላቅ እና ልምድ ያላቸውን አትሌቶች ያገለለ፤ የታዳጊ አትሌቶችን የወደፊት ተስፋ በሚያጨልም ደካማ አሰራር የሚንቀሳቀስ፤ የስፖርቱ ፍቅር በሌላቸው አመራሮች የተበላሸ… ወዘተረፈ እየተባሉ የሚነሱ ስሞታዎችን መዘርዘር ይቻላል፡፡
በአትሌቲክሱ ዙርያ በአትሌቶች፤ በፌደሬሽኑ አስተዳደር እና በሌሎች ባለድርሻ አካላት በየጊዜው ስብሰባ እየተደረጉ ችግሮች ቢነሱና መፍትሄዎች ሲቀርቡ በተደጋጋሚ ቢያጋጥምም ምንም ለውጥ ሲፈጠር አይታይም፡፡ በአትሌቶች እና በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን መካከል በተደጋጋሚ የሚፈጠሩ ቅራኔዎች ዘላቂ መፍትሄዎች ሲገኝላቸው አለመስተዋሉ ሌላው አሳሳቢ አቅጣጫ ነው፡፡ አጀንዳዎች ሲድበሰበሱ፤ ውሳኔዎች እና እርምጃዎች ባለድርሻ አካላትን በአግባቡ ሳያስማሙ መቀጠላቸው ተገቢ አልነበረም፡፡
በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን እየሰሩ በሚገኙ አመራሮች  አትሌቶች ላይ ከፍተኛ በደል እንደሚፈፀም የሚያመለክቱ መረጃዎች ጥቂት አይደሉም፡፡ በፌደሬሽኑ ሃላፊዎች የተሰደቡ፤ የተገፉ፤ የተንገላቱ፤ ሞራላቸው የወደቁ፤ ዜግነት የቀየሩ  በርካቶች ናቸው፡፡
በፌዴሬሽኑ አመራር ያጋጠሙ የሥነ ምግባር ጉድለቶቹ ጥቂት አይደሉም፡፡ በስፖርተኞች ምልመላ፤ የውጭ አገር ውድድር እድልን በማስፈፀም ረገድ ፌደሬሽኑ የሚከተላቸው አሰራሮች ብዙ አትሌቶችን ቅር ሲያሰኝ የኖረ ነው፡፡ በተለይ ከወራት በፊት የብሔራዊ ፌዴሬሽኑ የቴክኒክ ዘርፍ በዳይሬክተርነት ይመሩ የነበሩትና በአትሌቲክሱ ከ20 ዓመት በላይ አገልግሎት ሲሰጡ የቆዩት አቶ ዱቤ ጅሎ ከሃላፊነታቸው የተነሱበት ሁኔታ ከሪዮ ኦሊምፒክ በፊት የፈነዳው የመጀመርያው አወዛጋቢ ሁኔታ ነበር፡፡ በአትሌቶች ስም፣ አትሌቶች ያልሆኑትን አትሌቶች በማለት በፌደሬሽኑ አመራሮች የተፈፀሙት ከፍተኛ የአስተዳደር ወንጀሎች ፌደሬሽኑን ተዓማኒነት አበላሽቶታል፡፡
ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ በበኩሉ በአሁኑ ወቅት ከማራቶን ተወዳዳሪዎች ውጪ ቁጥራቸው ከ66 በላይ አትሌቶች በሆቴል ተሰባስበው ሁለተኛውን የዝግጅት ምዕራፍ ጀምረዋል እያለ ቢሆንም፤ አትሌቶች ከምርጫና ከሥልጠና ጋር በተገናኘ ‹‹ከእኛ በላይ ስለእኛ የሚያውቅልን አይኖርም›› የሚሉ ብሔራዊ አትሌቶች እንዳሉ እየተነገረ ይገኛል፡፡ አትሌቶች የማራቶን ተመራጮችን ጨምሮ፣ በርካታ ታዋቂ አትሌቶች በግል አሠልጣኞቻቸው ካልሆነ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ በመደባቸው አሠልጣኞች ለመሠልጠን ፈቃደኛ አይደሉም፡፡ አትሌቶች በፌደሬሽኑ ከቀረቡ ብሄራዊ አሰልጣኞች በሚሰሩበት ስልጠና ዙርያ ደስተኞች አለመሆናቸው ቀላል ችግር አይደለም፡፡ የኦሎምፒክ ቡድኑ ላይ ከተመደቡ አሰልጣኞች ጋር የመስራት ፍላጎት አለመኖሩም የሚያስጨንቅ ሁኔታ ነው፡፡ በአጠቃላይም በስልጣን ላይ የሚገኘው የኢትዮጵያ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን በአትሌቶች የተነሳበት ተቃውሞ በቀጣዮ የኦሎምፒክ ተሳትፎ እና ውጤት አጓጉል ተፅእኖዎችን በመፍጠር ላይ እንደሚገኝ  መገመት ይቻላል።  የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን አመራሮች፣ ክለቦችና አሰልጣኞች እንዲሁም ባለሞያዎች ተባብረው የሚሰሩበትን አቅጣጫ  አለመከተላቸው ተጠያቂ ያደርጋቸዋል።

Read 4394 times