Saturday, 18 June 2016 12:36

መንግሥት በቴሌኮም ማጭበርበር ከ1 ቢሊዮን ብር በላይ ከስሯል

Written by 
Rate this item
(13 votes)

- 720 ሲም ካርዶችን መጠቀም የሚችል መሳሪያ ተይዟል
- በዘጠኝ ወራት ብቻ 165 የሳይበር ጥቃቶች ደርሰዋል
       በአራት የአገሪቱ ከተሞች በተፈፀሙ የቴሌኮም ማጭበርበር ወንጀሎች መንግስት ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ኪሳራ እንደደረሰበት ተገለፀ፡፡ በጅግጅጋ፣ በአዲስ አበባ፣ በሃረርና ድሬደዋ 400 የማጭበርበር ወንጀል ሲፈፀምባቸው የነበሩ መሳሪያዎች የተያዙ ሲሆን አንዳንዶቹ 8፣ አንዳንዶቹ ደግሞ እስከ 720 ሲም ካርዶችን የሚጠቀሙ እንደሆኑ ተገልጿል፡፡
የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ሜጀር ጀነራል ተክለብርሃን ወልደ አረጋዊ ከትናንት በስቲያ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዘጠኝ ወራት ዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርት ባቀረቡበት ወቅት እንደገለፁት፤ የቴሌኮም ማጭበርበር ወንጀል በአገሪቱ የቴሌኮም ዘርፍ የአገልግሎት ተደራሽነት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እየፈጠረ ሲሆን መንግስትንም ለከፍተኛ ኪሳራ ዳርጐታል፡፡  ባለፉት ዘጠኝ ወራት በጅግጅጋ፣ አዲስ አበባ፣ ሐረርና ድሬደዋ ከተሞች  በተካሄደ አሰሳ፣ 400 የቴሌኮም ማጭበርበር ወንጀል ሲፈፀምባቸው የነበሩ መሳሪያዎች የተያዙ ሲሆን መሳሪያዎቹ ከ8 እስከ 720 ሲም ካርዶችን የመጠቀም አቅም ያላቸው እንደሆኑ ተገልጿል፡፡  46  ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የጠቆመው ሪፖርቱ፤ በመንግስት ላይ ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ኪሳራ ማድረሳቸውን አስታውቋል፡፡
ለወንጀሉ መባባስ ምክንያቶች ናቸው ተብለው ከተጠቀሱት መካከል የቴክኖሎጂ መወሳሰብ፣ የባለድርሻ አካላት ንቃተ ህሊና ማነስ፣ የሲም ካርድ፣ የቮቸር ካርድና የኢቪዶ አገልግሎት ሽያጭ ከጥብቅ ቁጥጥር ጋር አለመተሳሰር ይገኙበታል፡፡
በአገሪቱ የሚፈፀሙ የሳይበር ጥቃቶችን የመለየት፣ የመመከትና ምላሽ የመስጠት ተልዕኮ የተሰጠው “ኢትዮ ሶርት” የተባለ ማዕከል ተቋቁሞ ሥራ መጀመሩን የገለፀው የኤጀንሲው ሪፖርቱ፤ ባለፉት ዘጠኝ ወራት 165 የሳይበር ጥቃቶች መድረሳቸውንና ማዕከሉ ጥቃቶቹን ማክሸፉን ጠቁሟል፡፡
በአሁኑ ወቅት ሳይበር በአገራችን ከዋና ዋና ወንጀል መፈፀሚያ ስልቶች አንዱ መሆኑን ሪፖርቱ ጠቅሶ፤ ይሄንን ለመከላከል የሚያስችል የሳይበር ወንጀል ህግ መፅደቁን አመልክቷል፡፡ የአገሪቱን የኤሌክትሮኒክስ ንግድና የኤሌክትሮኒክስ አስተዳደር አገልግሎቶች ደህንነት ለማስጠበቅ የሚያግዝ የዲጂታል ፊርማ ረቂቅ ህግ ተዘጋጅቶ ውይይት እየተደረገበት እንደሆነም ተገልጿል፡፡
ከመንግስት ባንኮችና ከተወሰኑ ተቋማት በስተቀር አብዛኛዎቹ የመንግስት ተቋማት የሳይበር ደህንነት ጉዳይን የተቋማቸው የስትራቴጂክና ኦፕሬሽናል አመራር አካል አድርገው እንደማይወስዱት ያመለከተው ሪፖርቱ፤  ለቁጥጥር አመቺ ያልሆኑ ሥርዓቶችን ስለሚዘረጉ በአገራዊ ደህንነት ላይ ስጋት እየፈጠሩ ነው ብሏል፡፡  

Read 8170 times