Saturday, 18 June 2016 12:49

‹‹የእንባ መጽሐፍ››

Written by  ተፈሪ መኮንን
Rate this item
(1 Vote)

      ‹‹አዛኝና ርህሩህ በሆነው በአላህ ስም›› የሚል አንቀጽ በር አድርጎ የሚነሳ፤ ‹‹ኪታብ አል-ኢንባ›› የተሰኘ መንፈሳዊ  ሐተታ አለ፡፡ ይህ ሐተታ የተፃፈው በ12ኛው ክፍለ ዘመን በኖሩ አንድ ኢትዮጵያዊ ነው፡፡ አብደላ ባድር አል ሐበሺ ይባላሉ፡፡
እኒህ ኢትዮጵያዊ፤ የሸኽ አል-አክባር ሙህይዲን አብን አራቢ የተባሉ፤ በ12ኛው ክፍለ ዘመን የኖሩ ታላቅ መንፈሳዊ መምህር ተማሪ ነበሩ፡፡ ኢብን አል አራቢን ብዙዎች ያውቋቸዋል፡፡ ኢስላማዊ አሰላሳይ (Thinkers) ከሚባሉት ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ኢብን አል አራቢን ኢትዮጵያዊውን ተማሪያቸውን እጅግ ያቀርቧቸው ነበር፡፡ እኔ ስለ ኢትዮጵያዊው አብደላ ባድር አል ሐበሺ ለማወቅ የቻልኩት፤ ‹‹ይህ መጽሐፍ ለተማሪዬ ለአብደላ ባድር አል-ሐበሺ መታሰቢያ ይሁንልኝ›› ብለው ያሰፈሩትን አበርክቶ አይቼ ነው፡፡ ስለዚህ ስለ አብደላ ባድር አል-ሐበሺ የሚታወቀው መምህራቸው ሸኽ ኢብን አል አራቢ በተውት መረጃ ነው፡፡ በስተቀር ስለ ሸኽ ኢብን አል አራቢ የህይወት ታሪክና በመቶዎች የሚቆጠሩ መፅሐፎቻቸውን የሚያወሱ ሰነዶች ሁሉ ስለ እኚሁ ኢትዮጵያዊ አንዳችም ነገር አይናገሩም። የተለያዩ ፀሐፍት ስለ አል ሐበሺ ሳይጠቅሱ ማለፋቸው በሁለት ገፅ የሚታይ ምክንያት እንዳለው ይታሰባል። በአንድ በኩል፤ ዝምታው ማህበራዊ ምንጫቸው ዝቅተኛ ከመሆኑ ጋር የተያያዘ ሊሆን ይችላል፡፡ በሌላ በኩል፤ የ‹‹ኪታብ አል ኢባን›› ልዩ ማህተም ከሆነው ራስን ዝቅ ዝቅ የማድረግ ልዩ ትህትና ጋር ሊያያዝ ይችላል፡፡ ከከንቱ ውዳሴ ከመራቅ፤ ራስን ከመካድ (Self effacement) ፍላጎት በመነጨ ምክንያትም ሊሆን ይችላል፡፡
የሸኽ ኢብን አል አረቢ ተማሪ የሆኑት አል ሐበሺ በፃፉት መፅሐፍ፤ ራሳቸውን ገለል አድርገው የመምህራቸውን ቃል በመጥቀስ ተወስነው ፅፈዋል፡፡ መምህራቸውን በፍቅርና በለጋስ ውዳሴ አስጊጠዋቸዋል፡፡ እኚህ ኢትዮጵያዊ የትውልድ ዘመናቸው መቼ እንደሆነ አይታወቅም። በየትኛው የሐገራችን ግዛት እንደተወለዱም የሚያውቅ የለም፡፡ እስከ ዕለተ ሞታቸው በፍፁም ታማኝነት ከተከተሏቸው መምህራቸው ጋር እንዴት እንደተዋወቁም የሚያስረዳ ነገር አልተገኘም፡፡
ሆኖም በ595 (ሂጅራ) ከመምህራቸው ጋር አብረው እንደነበሩና በዛ ዓመት ከእርሳቸው ጋር ወደ ስፔን ስለመመለሳቸው የሚገልፅ የፁሁፍ መረጃ አለ፡፡ እንደሚባለው ኢብን አል አራቢ ከፃፏቸው በመቶዎች የሚቆጠሩ መፃህፍት፤ ‹‹ማውናቂ አል-ኑጁንም” (Mawnaqi-al-nujunm) የተሰኘውን መጽሐፍ፤ በመንፈስ ቅዱስ (ሩህ አል ቅዱስ) ተነሳስተው በጻፉ ጊዜ፤ ከአብደላ ባድር አል ሓበሺ የኢሻራ (የህልም) ማረጋገጫ እንደመጣላቸው ይገለጻል፡፡ በዚሁ መጽሐፍ የሰፈሩ አንዳንድ ሐሳቦችም በአብደላ ባድር አል ሐበሺ መጽሐፍ ‹‹ኪታብ አል ኢንባ›› ተካትተው ይገኛሉ። ኢብን አል አራቢ፤ ለተማሪያቸው ለአል ሐበሺና ለሌሎች ማስተማሪያ የሚሆኑ በርካታ መጻሕፍትን ጽፈዋል። ‹‹ሐዲስ ቅዱስ›› ሲሉ በሰየሙት መጽሐፋቸውም፤ ‹‹አብደላ አል ሐበሺ እንዳለው›› እያሉ አንዳንድ ትውፊቶችን ጽፈዋል፡፡
ኢትዮጵያዊው አል ሐበሺ መምህራቸውን ተከትለው  መካ (600)፣ ሞሱል (601)፣ ካይሮ (603)፣ ሄደዋል፡፡ ኢብን አል  አራቢ በ611 ኤልፖ በተባለች ቦታ ኖረዋል፡፡ በዚያ ጊዜ በአብደላ ባድር አል ሐበሺና በሌሎች ተማሪዎቻቸው ጥያቄ፤ ‹‹ቱርጁማን አል-አሽዋት›› በተባለ መጽሐፍ ላይ አስተያየትና ማብራሪያ ጽፈዋል፡፡ አል ሐበሺ መምህራቸውን ለ23 ዓመታት ሲከተሉ ኖሩ፡፡ በመጨረሻም በ618 አካባቢ ‹‹ማላትያ›› በተባለች ሥፍራ ከዚህ አለም በሞት ተለዩ፡፡
አል ሐበሺ ‹‹ኪታብ አል ኢንባ›› በሚል የጻፉት ሐቲት፤ በተለያየ ጊዜ፣ በተለያየ ርዕስ እየታተመ ቀርቧል፡፡ ዴኒስ ግሪል የተባሉ ሰው፤ ‹‹ኪታብ አል ኢንባ አላ ታሪቅ አላህ›› በሚል የታተመውን ቅጂ ወስደው ወደ እንግሊዝኛ ተርጉመውታል፡፡
አል ሐበሺ፤ በመጽሐፋቸው መክፈቻ አንቀጽ፤ ‹‹በጣም አዛኝ፤ በጣም ርህሩህ በሆነው በአላህ ስም፤ ፈጣሪዬ ሆይ ሥራዬን የተቃና አድርግልኝ። የአላህ ምህረት ባርያ የሆነውና ከአሳዳሪው ከአቡ አል ጋንይም ቢ. አል- ፍቱህ አል ሀራኒ (ኃያሉ ፈጣሪ ምህረቱን ይስጣቸውና) ከግዴታው ነጻ የወጣው (Freed Slave) አል ማሱድ አብደላ ባድር ቢ. አብደላህ አል-ሐበሺ እንዲህ ይላል፤›› ብለው ሐቲታቸውን ያስከትላሉ፡፡
‹‹ከእርሱ የሆነ ዕውቀትን የሚይዙና የእርሱ ጥብብ ግምጃ ቤት የሆኑ ልቦችን የፈጠረ አላህ የተመሰገነ ይሁን፡፡ እርሱ ረቂቅ ምስጢሩንና ዕውቀቱን በልባቸው አኖረ፡፡ እነዚያን ልቦችም የዝክሩና የጸጋው፤ የቅዳሴውና የውዳሴው አደባባይ ይሆኑ ዘንድ ከፍ ከፍ አደረጋቸው፡፡ የአላህ አንድነትና ሰላም በመሐመድና በቤተሰቡ ላይ ይውረድ›› የሚሉት አል-ሐበሺ፤ አያይዘው ‹‹የአላህን መንገድ ማወቅ›› በሚል በሰየምኩት በዚህ መጽሐፍ ከመምህራችን፤ ከሼኻችን፣ ከመሪያችን፤ እንዲሁም ፍጹም ንጹህ የዕውቀት ሰው እና አንጸባራቂ ከሆነው ከኢማማችን ከአቡ አብደላ ቢ. ዓሊ. ቢ. መሐመድ ቢ. መሐመድ አል-አራቢ አል-ሃቲሚ  አል አንዳሉሲ (አላህ በእርሳቸው ደስ ይበለውና) ከእነዚህ ሰዎች የሰማኋቸውን አንዳንድ ቃላት እጠቅሳለሁ፡፡ አንባቢያን ይህን አጽንተው እንዲይዙ፣ እንዲጠብቁ፣ እውነተኛ ምክር መለገስ ምኞቴ ነው፡፡ አላህ ይህን ሥራ ለሁሉ ጠቃሚ የሚሆን ያድርገው›› ይላሉ፡፡
‹‹አብደላህ ባድር እንዲህ ይላል›› በማለት ይጀምራሉ፡፡ ከዚያም ‹‹አንድ ቀን ሸሃችን አቡ አብደላ ኢብን አል-አራቢ እንዲህ ሲሉ ሰማኋቸው፡፡ እግሩን እና እጁን ሰብስቦ የተቀመጠ ሰው ልቡን ያሳርፋታል። እግሩንና እጁን ስድ ያደረገ ሰው ልቡንም ያማስናታል። አስተውሉ፤  የልብ እረፍት የሚገኘው፤ የተገለጠውን ህግ በማክበር፣ በመተከተልና ምስጢሩንም በመገንዘብ መሄድ እስኪችሉ ድረስ ዓይንን፣ አፍንጫን….ሁሉ በመግታትና በመቆጣጠር ነው፡፡
‹‹ሰው ዓይኑ እንዲቅበዘበዝ የፈቀደለት እንደሆነ፤ ምናልባት ደስ ከሚያሰኝ ግን ከማይገኝ  ነገር (ቆንጆ ከሆነች ባርያ ልጃገረድ ወይም ከሚያምር ባርያ ላይ ያርፋል፡፡ ወይም ውብ ከሆነ መኖሪያ ቤትና ይህን ከመሰለው ነገር ያርፋል፡፡) ጆሮውን ያለ ልጓም መረን የሰደደ እንደሆነ መንፈሱን ምርኮኛ አድርጎ ከሚይዝና ለጆሮ ከሚጥም ቃልና ዜማ ያርፍ ይሆናል። ምላሱን አለልጓም የተወ እንደሆነ፤ የከፋ ውድቀት የሚያመጣበትን ቃል ይናገር ይሆናል። ሰው ሊጨበጥ ወይም ሊወገድ ከማይችል ነገር ውስጥ ሲገባ ይማስናል፡፡ ይታክታል፤ መንፈሱ በማይረባ ነገር ይጠመዳል፡፡ ህይወቱም ይበላሻል፡፡
‹‹እጅና እግር የሚሰማሩት በልብ ትዕዛዝ ነው። የጊዜ ፈቃዱን ለመሙላት የሚባዝን ልብ፤ በአላህ (ምስጋና ለእርሱ ይሁን) ድህነትን ለማግኘት ሊጣጣር አይችልም፡፡ እግሩም እጁም ያንኑ የማይረባውን ነገር ለማግኘት ሲፍጨረጨሩ ይገኛሉ እንጂ፡፡ የአላህን እርዳታ ያልያዘ እና ከመንፈሳዊ ክልል የወጣ ሰው ልቡ ይታወካል፤ ይዝላል፡፡ የዚህ ሁሉ ችግር ምንጩ ያለማስተዋል መኖርና ስሜትን እንዲባዝን ማድረግ ነው፡፡ በእውነቱ፤ እጁንና እግሩን ሐሳቡን የሰበሰበ ወይም የተቆጣጠረ ሰው ልቡ አይዝልም፡፡
ሸሪአው እንደሚያዘው፤ እግረ-ስሜትን መቆጣጠርና በማስተዋል መኖር ያስፈልጋል፡፡ የአላህ መመልከቻ የሆነው ልባችን፤ ከእርሱ ውጪ በሆነ በሌላ ነገር እንዳይጠመድ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ያ ከአላህ ውጪ በሆነ ነገር የተጠመደ ልብ፤ ዘወትር አላህን ከሚዘክር ልብ በደረጃ ያነሰ ነው፡፡
‹‹ነፍስ ኮርቻ የተጫነች፤ የተለጎመችና ሊጋልቧት የተዘጋጀች ቅብጥብጥ ፈረስ ነች፡፡ ይህችን ፈረስ በጋለብክ ጊዜ እጅህን በማስተዋል ልጓም ላይ አድርግ፡፡ ይህን ያደርግህ እንደሆነ ተርፈሃል፡፡ ይህን እጅህን ለስሜት አሳልፈህ የሰጠህ ከሆነ ጠፍተሃል፡፡ ምርጫው እንግዲህ ያንተ ነው፡፡ ልጓሙን በማስተዋል እጅ ለማስገባት ስትጥር ሁለቱንም እግርህን እርካብ ላይ አድርግ፡፡ በቀኝ እግርህ የተስፋን ርካብ፤ በግራ እግርህ የመፍራትን ርካብ እርገጥ፡፡
አንድ ቀን ልጓሙ ከማስተዋል እጅ ያፈተለከ እንደሆነ ፤ ነፍስ ከመንገድ ወጥታ በግራ ወይም በቀኝ በኩል ለመሄድ ትከጅላለች፡፡ ታዲያ ያን ጊዜ በግራው (በመፍራት) ርካብ ጎሸም አድርጋት፡፡ በተቃራኒው በመፍራት የተተበተበች ከሆነ በተስፋ ጎሰም አድርጋት፡፡ ነፍስ ሁል ጊዜም የሚጎዳት የመሰላት ነገር ሲነካት የግድ ከዚያ ነገር ትመለሳለች፡፡ በዚህም መንገዱን ሳትለቅ ቀጥ ብላ መጓዝ ትችላለች፡፡ በቆመች ጊዜ ማስተዋል ሊመራት ይችላል፡፡ ከእጅህ የወጣውን ልጓም ዳግመኛ ጨብጠህ በያዘችው ዝቅተኛ መንገድ ምራት፡፡ አስከትላት፡፡      


Read 3779 times