Saturday, 18 June 2016 13:29

ወርልድ ቪዥን ኮሪያ፤ በ44 ሚ. ብር የወጣቶች ስልጠና ማዕከል ሊገነባ ነው

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(1 Vote)

     ወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ፤ ከወርልድ ቪዥን ኮሪያ፣ ከኪያ ሞተርስና ከኮሪያን ኮኦፕሬሽን ኢንተርናሽናል ኤጀንሲ (ኮይካ) ባገኘው 44.1 ሚ. ብር የአውቶ ሜካኒክ ማሰልጠኛ ማዕከል ሊገነባ ነው፡፡ ባለፈው ሳምንት ከሰዓት በኋላ ተክለሃይማኖት ጀርባ ፔፕሲ ፋብሪካ አጠገብ በሚገኘው ቦታ ቀዳማዊት እመቤት ሮማን ተስፋዬ፣ የወርልድ ቪዥን ካንትሪ ዳይሬክተር፣ የኪያ ሞተርስ ፕሬዚዳንት፣ ሚስተር ጂን ቹንግ፣ የኮይካ ፕሬዚደንት ሚስተር ኢን ሺክ ኪም፣ ከፍተኛ የመንግስት ኃላፊዎችና እንግዶች በተገኙበት የመሰረት ድንጋይ አስቀምጠዋል፡፡
በ2017 አጋማሽ ላይ ግንባታው ይጠናቀቃል ተብሎ የሚጠበቀው “ኮይካ ግሪን ላይት የስልጠና ማዕከል” በአምስት ዓመት ውስጥ 615 ወጣቶችን ለማሰልጠን እቅድ የያዘ ሲሆን 220ዎቹ በአውቶ መካኒክ፣ 395ቱ ደግሞ በእደ ጥበብ ስልጠና ያገኛሉ ተብሏል፡፡ ማዕከሉ ከአምስት ዓመታት በኋላ የራሱ የአስተዳደር መዋቅር የሚኖረው ሲሆን ወጣቶችንና ሴቶችን ማሰልጠኑን እንደሚቀጥልና በየዓመቱ መቶ ወጣቶችን በሙያቸው ሰርተው መኖር እንዲችሉ እንደሚያደርግ በእለቱ ተገልጿል፡፡ በሀበሻ ዊክሊ ፕሮሞሽን አስተባባሪነት በተካሄደው በዚህ ሥነ ሥርዓት ላይ ቀዳማዊት እመቤት ወ/ሮ ሮማን ተስፋዬ በሥነ ሥርዓቱ ላይ ባደረጉት ንግግር፤ የኢትዮጵያንና የኮሪያን የቆየ ወዳጅነት አስታውሰው፤ ይህም ፕሮጀክት የሁለቱን አገራት ወዳጅነት የበለጠ እንደሚያጠናክረው ገልፀዋል፡፡  


Read 1401 times