Saturday, 25 June 2016 12:18

የአፍሪካ ፍልስፍና ያደረገው አዕምሯዊ የአርነት ተጋድሎ

Written by  መልሰው ሉሌ
Rate this item
(0 votes)

ባለፈው ሳምንት “ዋግ የመታው አፍሪካዊ ፍልስፍና” በሚል ርዕስ በአቶ ደረጀ ይመር  ለተፃፈው ጽሁፍ ምላሽ መስጠቴ ይታወሳል፡፡ እርሳቸውም ያመኑበትን የ”መልስ መልስ”  ትችታቸውን ሰንዝረዋል፡፡ ይህ አካሄድ ፍልስፍናን ይጠቅማል፤ ምክንያቱም ዲሞክራሲያዊ ድስኩርን ያሳድጋል፡፡ የእይታቸው መነፅር ግን የተንሸዋረረ ነው፤ ማለትም የሰጡት  ሂስ የጽሁፌን ይዘት ያለ መልኩ መልክ በመስጠት  ላይ የተመረኮዘ ነው፡፡ የመሄስ መብታቸውን ቢጠቀሙበትም እንኳ  የፍልስፍናን የሂስና ክርክር ዘይቤና ዘዴ ለፅሁፋቸው ነፍገውታል፡፡
እስቲ በመጀመሪያ የፀሀፊውን ነባራዊ ስህተቶች (factual errors) እንመልከት፡፡ ይህን ለማየት ይረዳን ዘንድ  ከጸሀፊው የባለፈ ሳምንት መጣጥፍ ቃል በቃል እጠቅሳለሁ፡-“ኂስ አቅራቢው ቤኒናዊውን ፈላስፋ ፓውሎ ሆንቶንዥን አፍሪካዊ አርበኝነት የተጠናወተውን ፍልስፍና በሚያራምዱ ልሂቃን መሃከል ያለ ምክንያት መደንጎራቸው ደንቆኛል። ሆንቶንዥ፣ ከንፍር ውሃ እንዳመለጠች ቅንጣት ባቄላ፣ ከጫጫታው መሃል ዘለግ ብሎ ስለፍልስፍና ዓለምአቀፋዊነት የሚሞግት ልሂቅ ነው፡፡ ይህንን ልሂቅ ከሌሎች አፍሪካዊ ፈላሰፋዎች ጋር በአንድነት መቀየጥ ተገቢ አይደለም።” ይህ ክሳቸው ግን ከእወነት የራቀ ነው፡፡ ጸሀፊው እንደሚሉት፤ ፖውሊን ሆንቶንዥን  አርበኝነት የተጠናወተውን ፍልስፍና በሚያራምዱ ልሂቃን መሃከል አልጨመርኩም፡፡ ለአብነት ያህልም ፖውሊን ሆንቶንዥ ስለ ፍልስፍና ሁለንተናዊነት የሚከራከረው የፕሮፌሽናል ፊሎሶፊና አቀንቃኝ መሆናቸውን አና “አቢዮላ አየርል እና ፓውሊን ሆንቶንዥ የተባሉ እውቅ የምዕራብ አፍሪካ ፈላስፎች ሁለንተናዊ ፍልስፍናን ያራምዳሉ፤ የባህል ብሔርተኝነትን ይተቻሉ፣ ባህልን ብቻ ማወደስ የአፍሪካን ችግር አይፈታም ብለው ይሞግታሉ፣ አፍሪካን ባለችበት አዘቅት ሊያቆያት ይችላል ብለው ይከራከራሉ፡” የሚል በባለፈው ፅሁፌ ውስጥ ይገኛል፡፡
ይህም  በመጀመሪያ  የፀሀፊውን ችኩልነትና አለማገናዘብ ያመለክታል፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ፖውሊን ሆንቶንዥን “ከንፍር ውሃ እንዳመለጠች ባቄላ” ስለ ፍልስፍና ዓለም አቀፋዊነት የሚሞግት ብቸኛ አፍሪካዊ ልሂቅ አድርገው መቁጠራቸው በቅጡ አለማንበባቸውን ያመለክታል፡፡ ምክንያቱም  ብዙ ስለ ፍልስፍና ሁለንተናዊነት  የሚሞግቱ አሉ፡፡ በሌላ በኩል ስለ ፍልስፍና ሁለንተናዊነት የሚሞግተው  ፖውሊን ሆንቶንዥ፤ እንዴት የአፍሪካን ፍልስፍና ዋግ ይመታዋል?  ወይስ እኝህ  ፈላስፋ Decolonization of the Mind  በተሰኘው መፅሀፋቸው፣ አፍሪካን ነፃ ስለማዉጣት መሞገታቸውን  ፀሀፊው አልሰሙም ይሆን ? ፀሀፊው ይህን ሰምተው ከሆነ  ሆንቶንዥ “ከንፍር ውሃ ያመለጠች ባቄላ” አይሆንም፤ ምክንያቱም ስለ አፍሪካ ነፃነትና ማንነት የሰበከ አፍሪካዊ ፈላስፋ በጸሀፊው እይታ ዘረኛ ነው፡፡
ሁለተኛው ነባራዊ ስህተታቸው ደግሞ “የዘረ ያቆብን ጥልቅ እሳቤ፣ በባህልና ትውፊት ላይ ምሕዋሩን ባሳረፈው የፍልስፍና ዘውግ ኢትዮኖፊሎሶፊ /Ethionophilosohy/ መነጽር ነው፡፡” የሚለው ክሳቸው ነው፡፡ ይህ ስህተታቸውም የማጣመም ህፀፅ ጨምረውበታል እንጂ ችኩልነትና አለማገናዘብ ይታይበታል፡፡ “ቀደምት የኢትዮጵያ የስልጣኔና የፍልስፍና ዘይቤዎች በአፍሪካ ፍልስፍና ውስጥ ተገቢ ቦታ አልተሰጣቸውም” ለሚለው የሀሰት ትችታቸው  መልስ ለመስጠት  ክሎውድ ሰምነርና ሄነሪ ኦዴራኦሩካ፤ ስለቀደምት የኢትዮጵያ የፍልስፍና ዘይቤ ትኩረት መስጠታቸውን ለአብነት ያህል ጠቀስኩ እንጅ ስለዘረያቆብ የፍልስፍና ምንነት አልሞገትኩም፡፡
ወደ  ፀሀፊው ጽንሰ-ሀሳባዊና አመክኗዊ ግድፈታቸው ስንመለስ “በአራቱም የአህጉሪቱ ማዕዘናት በቅለው የነበሩ ጥንታዊ ሥልጣኔዎች በደንብ መፈተሽ ተቀዳሚ ሥራ መሆን ይኖርበታል፡፡” የሚል አስተያየት ሰጥተዋል፡፡ ይህም ብዥታ ይፈጥራል፡፡ የዚህን  አስተያየት አንድምታ  መየት ተገቢ ነው፡፡ ፀሀፊው በአንድ በኩል የአፍሪካን ማንነት እንወቅ እንመርምር የሚለውን የአፍሪካ ፍልስፍና  ዘረኛና ዋግ የመታው ይሉታል፤ በሌላ በኩል ቀደምት የአፍሪካ ስልጣኔዎች ተመርምረው ይውጡ  ይላሉ፡፡ አንዳንድ የአፍሪካ ፈላስፎችም የሚሉት ቀደምት የአፍሪካ ስልጣኔ፣ባህልና ትውፊት ተመርምሮ ይውጣ ነው፡፡ ታዲያ ፀሀፊው ራሳቸው የሰጡት አስተያየት  በሌሎች የአፍሪካ ፈላስፎች ሲደገፍ ነው ወለፈንዲ ወይም ግርምቢጥ የሚሆነው?   እዚህ ጋ መታወቅ ያለበት ነገር ቀደምት የአፍሪካ ስልጣኔዎች አይመርመሩ ሳይሆን  የፀሀፊው  አስተያየትና የአፍሪካን ፍልስፍና የተመለከቱበት እይታ እርስ በእርሳቸው ይጣረሳሉ ለማለት ነው፡፡
“የአፍሪካ ፍልስፍና ያደረገው አዕምሯዊ ተጋድሎ” ያለ ወጋግራ የቆመ ከስህተት የጸዳ አመክንዮ የሌለውና ስሜታዊነትን የተላበሰ ብቻ መሆኑን  ጸሀፊው ነግረውናል፡፡ የሚገርመው ግን  እንደተለመደው በደፈናው መወቀሳቸው ነው፡፡፡ ያለ ወጋግራ የቆመና ከስህተት የጸዳ አመክንዮ የሌለው  “የአፍሪካ ፍልስፍና ያደረገው አዕምሯዊ የአርነት ተጋድሎ” ወይስ  “ዋግ የመታው የአፍሪካ ፍልስፍና” የሚለውን፣ ለአንባቢ ትቼ፣ ስሜትን መግለጽ ሰብአዊነት  መሆኑን ለፀሀፊው  ልነግራቸው እወዳለሁ፡፡ ዋናው ነገር በትክክል መግለጽ መቻል ነው፤ ምክንያቱም ከስሜት ሙሉ በሙሉ የጸዳ ምክንያትና እውቀት የለም፤ ምነው ቢሉ ስሜታዊነት የሰው ልጅ አንዱ መሰረታዊ ባህርይ ነው፡፡ ንፁህ፣ ያልተቀየጠና ስሜት አልባ የሚባል እዉቀትና ፅሁፍ ዘበት ነው፡፡ ስለዚህ ስሜትን በተገቢው መንገድ መግለጽ ሰብአዊነት ነው፡፡ ስለ አርት፣ ሙዚቃና ስነ-ምግባር የምናወራው፣ የምንጽፈውና የምናደርገው ሁሉ ከስሜት ጋር ይያያዛል፡፡ የመፃፍና የማወቅ ፍላጎታችንስ ቢሆን ከስሜት የፀዳ ነውን?
ሌላኛውን የጸሀፊውን ውሀ የማይቋጥር ነቀፌታቸውን  የማሳየው “ዋግ የመታው የአፍሪካ ፍልስፍና”  ከመጀመሪያው መጣጥፋቸው ጥቅስ በመውሰድ ነው፡፡ “በግብና በዓላማ ያልተቀየደ መደመም የፍልስፍናን በራፍ ለመቆርቆር ቀዳሚው መላ እንደሆነ ከጥንታዊያን የግሪክ ፈላስፎች ምልከታ መገንዘብ እንችላለን፡፡”  እኔም ፍልስፍና የሚጀምረው በመደመም ነው፤ ጥበብ- መደመሙ ዓላማ ቢስ አይደለም፤ በእርግጥ የጥበብ መጨረሻ ይሄ ነው ብሎ መናገር አይቻልም። ጥበበኛው አንድ ጥበብ ጨበጥኩ ሲል ሌላ የጥበብ ድምፅ ይጠረዋል፡፡…መጥፎም ደግሞ ሊያስደምመን ይችላል፡፡” የሚል መልስ መስጠቴ ይታወሳል፡፡ ፀሀፊው እንዳሉት ከሆነ፤  የእኔ መልስ ዓ.ነገሩን በሰሙ/በደረቁ ከመረዳት የተነሳ ነው፡፡ ፀሀፊው ያልተረዱትና ያልተረጎሙት  ግብና አላማ ምን እንደሆነ ነው፡፡ ግብ ማለት ምን ማለት ነው? እኔ እስከማውቀው ድረስ  የአንድ ድርጊት ወይም ነገር  የመጨረሻ ፍፃሜ ማለት ነው፡፡ “የመደመም ማሳረጊያ” ማለት ግብ አይደለምን?  ከጥበብስ የበለጠ መግነጢሳዊ  ሌላ ግብ አለ?  ከዚህ አንፃር   የጥንት ግሪክ  ፈላስፎች መደመም  ግቡ  ጥበብን ወይም እውቀትን መያዝ ነው፡፡ ነገር ግን የጥበብ ወይም እውቀት መጨረሻ ስለሌለው ጠበበኛው  አንድን ጥበብ ብቻ እንደጨበጠ  አያቆምምመ፡፡ ነገር ግን ለጊዜያዊ ጥቅም ሲሉ አልተደመሙም፡፡ ግብ ማለት ደግሞ ጊዚያዊ ጥቅም ማለት አይደለም፡፡ ያ ለበለዚያ ግን ምንም  ቅኔ በሌለበት ሰምና ወርቅ  መፈለግ ነው የሚሆነው፡፡  ይህ አይነቱ መምታታት  በጽሁፍ ላይ  የሚመነጨው የጠራ አስተሳሰብ ካለመያዝ ነው፡፡
ፀሀፊው የአርስጣጣሊስን አባባል ማለትም “Philosophy begins in wonder. Wonder is something children do quite well. It comes natural to them” በመጠቀም “መደመምን” ለመፍታት ሞክረዋል፡፡ ነገር ግን የአርስጣጣሊስ ትረጓሜ  ፍልስፍና በመደመም  እንደሚጀምር፣ ህጻናትም  እንደሚደመሙና መደመም ለህፃናት ተለምዷዊ እንደሆነ ብቻ ነው፡፡ የመደመምን ምንነት  አያሳይም፤ ያለ ቦታው የገባ ጥቅስ ነው፡፡ ለእኔ መደመም በሆነ ነገር መመሰጥ፣ መሳብ፣ መገረምና መደነቅ ማለት ነው፡፡ ባለፈው ጽሁፌ እንዳልኩት፤ የሚመስጠን፣የሚስበን፣የሚያስገርመንና የሚያስደንቀን  ተፈጥሯዊ ወይም ሰው ሰራሽ፣ አዎንታዊ ወይም አሉታዊ  እንዲሁም በጎ ወይም እኩይ  ነገር ሊሆን ይችላል፡፡ በቅድመ-ሶቅራጥስ  የነበሩ የግሪክ ፈላስፎች ያስደመማቸው ወይም የመሰጣቸው  በአብዛኛው ተፈጥሯዊ ነገር ነበር፡፡ የአፍሪካ ፈላስፎች  ያስገረማቸው መጥፎ ነገር ነው፤ ወደ ቀይ ባህር ሂደው በወጀቡ ሕብር እንዲደመሙ፣ ወደ ሰማይ አንጋጠው  የከዋክብትን ብዛት መቁጠርና ተወርዋሪ ኮከቦች በምን ያህል ፍጥነት እንደሚወነጨፉና ለምን በቅሎ እንደማትወልድ መተወርና መደመም አይጠበቅባቸውም፡፡ እድሜ  ለአስትሮኖሚ፣ ባዮሎጂ ወይም ኦሽኖግራፊ!  በእርግጥ ከፈለጉ መብታቸው ነው ግን ትክክለኛ አይመስለኝም፤ ምክንያቱም የስራ ክፍፍል መርህ ያግዳቸዋል፡፡ የአፍሪካን ፍልስፍና ሊያሳስባቸው  የሚገባው ነገር የፍትህ እጦት፣ በደል፣ ጭቆና፣ ድህነትና የመሳሰሉት ዘግናኝ ችግሮች ናቸው፡፡ ፀሀፊው አንድ ነገር ሊያስቆጭና ሊያስገርም  እንደሚችል አላወቁም መሰል፣  ከ30 ዓመት በፊት የፈረሰውን  የበርሊን ግንብ፣ ሕይወት ሰጥተውታል ፡፡ ለምሳሌ፡- የኢትዮጵያን ድህነት ስናስብ፣ ሊያስገርምንና ሊያስቆጨን ይችላል፡፡
በመጨረሻ  የፍልስፍና ቅርፅ፣ በአካባቢ ባሉ ሀይሎች ይቃኛል፡፡ ለምሳሌ  ከሶቅራጥስ ትንሽ ቀደም ብለው የነበሩ ሶፊስትስ የተባሉ ፈላስፎች፤ ፍልስፍናን እንደ ገቢ ምንጭ ተጠቅመውባታል፤ ሶቅራጥስ፣ አፍላጦንና አርስጣጣሊስ፤ የጊዜውን የስነ-ምግባርና የፖለቲካ ችግሮች ለመፍታት ተጠቅመውበታል - ለምሳሌ የአፍላጦን Republics  እና የአርስጣጣሊስ “The politics and The Nicomachian Ethics፤ የመካከለኛው ዘመን ፈላስፎችም ቢሆን ሀይማኖታዊ የሆኑ ችግሮችን ለመፍታት፣ ሮማውያንም ቢሆኑ “ሰዎች ሁሉ በህግ ፊት እኩል ናቸው”  የሚለውን ለአለም ያበረከቱት  ከጭቆና ለመላቀቅ ፍልስፍናን ተጠቅመው ነው፡፡ የዜን ቡድሂዝም ፍልስፍናም ቢሆን የመንፈሳዊና ግብረ-ገባዊ ችግሮችን መፍታት ላይ ያተኮረ ነው፡፡ ስለዚህ ፍልስፍና ችግሮችን መፍታት ላይም ያተኩራል፡፡ ከዚህ በላይ  ፍልስፍና  በቆሎ አይዘራም፡፡ “በግብና በአላማ ያልተቀየደ መደመም”  የሚለው የፀሀፊው ብሂል ትርኪምርኪነት ከዚህ አንፃር ነው፡፡ የአፍሪካ ፍልስፍና  የወቅቱን አንገብጋቢ ችግሮች መፍታት ላይ ማተኮር ተገቢነትና ምክንያታዊነትም ከዚህ አንፃር ነው፡፡ ከአፍሪካ አንገብጋቢ ችግሮች ውስጥም የቅኝግዛት የወታደራዊ ጭቆና ጠባሳና የድህረ-ቅኝ-ግዛት መዋቅራዊና ተቋማዊ አፈና ይገኙበታል፡፡ እነዚህ  ከምዕራባዊያን የተወነጨፉና የሚወነጨፉ የጭቆና ባሩዶች ምንጫቸው የዘረኛ ድስኩር ነው፡፡ ከእነዚህ መካከልም ኢማኑየል ካንት Moral Anthropology  በተሰኘው መፅሀፉ፤ አፍሪካውያንን  የሰው ሰው መሆናቸውን ካወጀ በኋላ “አፍሪካውያን በአለንጋ ሳይሆን በቀርቀሀ ስንጥቅ መገረፍ አለባቸው፤ ምክንያቱም ባለንጋ ከተገረፉ የሰውነታቸው ቆዳ ስለሚያመረቅዝ ለጉልበት ስራ አይውሉም” የሚል  ምክር ለባሪያ ፈንጋዮች በድርሳን መልክ አበረከተላቸው፡፡ ዴቪድ ሂውም የተባለው ፈላስፋም፤ “አፍሪካውያን ተፈጥሮ ሰብዓዊነትን የነፈገቻቸው ፍጡሮች ናቸው” እና ጆርጅ ሔግል “አፍሪካውያን እድገታቸውን ያልጨረሱ የጫካ ልጆች ሲሆኑ፤ ታሪክ አልባ፣ ስነ-ምግባር የለሽና ስልጣኔ አልባ ናቸው” ብሏል፡፡
የአፍሪካ ፍልስፍና ድግሞ የራሳችን ማንነት፣ ታሪክ፣ ስነ-ምግባርና ስልጣኔ አለን፤ አውሮፓውያን እንደሚሉት ሳይሆን ሰዎች ነን፡፡ ስለዚህ የአውሮፓ ድስኩር መሰረተቢስ ነው ይላል፡፡ ታዲያ ይህ ዘረኝነት ነው?  ፀሀፊው እንደሚለው፤ ዘረኛ ፍልስፍና  የአፍሪካ ነው ወይስ የአውሮፓ? የአፍሪካ ፍልስፍና በሰዎች መካከል የተፈጠረው የዘር ልዩነት   አውሮፓውያን የፈጠሩት ልብ ወለድ ነው፤ ምክንያቱም መሰረታዊ የሆነ መስፈርትና ምክንያት የለም ነው የሚለው፡፡ ታዲያ ዘረኝነቱ ምኑ ጋር ነው? በዘረኛ ድስኩርና የዘረኛ ድስኩርን ለመተቸትና ውድቅ ለማድረግ ስለ ዘረኝነት መደስኮር መካከል ያለው ልዩነት የቱፋም (apple) እና ብርቱካን ልዩነት ያህል ነው፡፡ ፀሀፊው በህገ-ወጥ አመክኗዊ በማጠጋጋት፣ ቱፋምና ብርቱካን አንድ ናቸው ይላል፡፡ ስለ ዘረኝነት ምንም  ነገር ሳይወራ፤  ዘረኝነት ማስወገድ ይቻል እንደሆነ ግን ፀሀፊው  አልነገሩንም፡፡ ወንጀለኛ መሆንና ስለወንጀል መደስኮር  አንድ አይደሉም፡፡ በህገወጥ ማጠጋጋትና ሰዋሰውን በመጨቆን  ብቻ ግን  ግን አንድ ይሆናሉ፡፡
በአጠቃላይ የፍልስፍና ድስኩር በመረጃና በማስረጃ  አንድን ነገር መደገፍና መተቸት ላይ ያተኩራል፡፡ ይህን ለማድረግ ስነ-አመክንዮ ቁልፍ ሚና ይጫወታል፡፡ አንድን ድስኩር ስንነቅፍ ማጣመምና ማዛባት የለብንም፤ አንዱ የአእምሯዊ ልቀትና ብስለት መገለጫ ነው፡፡ ፍልስፍና በንግግር ወይም በጽሁፍ  ረቂቅ የማሳመን ጥበብ አይደልም፡፡ የቃላት  ጨዋታ ዋጋ የለውም፤ የፍልስፍናን ጽሁፍ  ግድ የሚሰጠው  የክርክሩ ሂደት፤ይዘት፤ግልጸኝነትና የሚያቀርበው እውነት ነው፡፡ፍልስፍና የተወለደበትንና የሚያድግበትን  አካባቢ ይመስላል፤ ያ ማለት ግን በአካባቢ ብቻ ተወስኖ ይቀራል ማለት አይደለም፤ ምክንያቱም የጀርመኑ ፈላስፋ የርገን ሀበርማስ ተግባቦታዊ ምክንያታዊነት ብሎ የጠራው ግንኙነት ስላለ ነው፡፡ የአፍሪካ ፍልስፍናም በአፍሪካ  ጉዳዮች ላይ  ማተኮር አለበት፡፡ ግብ አልባ መደመምን ግሪኮች ጀምረው ግሪኮች ሽረውታል፤ ምክንያቱም ፍልስፍና ምንም እንኳ በቆሎ ባይዘራም ፖለቲካዊና ግብረ-ገባዊ ችግሮችን መፍታት አለበት ብለው ስላመኑ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር የአፍሪካ ፍልስፍናን በግብና በአላማ  ያልተቀየደ መደመም  ላይ  ያተኩር ብሎ መከራከር የማያስኬድና አክሳሪ ነው፡፡

 

Read 2063 times