Saturday, 02 July 2016 11:53

ለምን እንፈራለን? ለምንስ አንፈራም?

Written by  ዓለማየሁ ገላጋይ
Rate this item
(4 votes)

“የዓለም ፈርቶ - አደሮች ተባበሩ!”

“ሰነፍ ሲኮራ ማጭድ ይታጠቃል” ይባላል፡፡ የዛሬ ርዕሰ ጉዳያችን ፍርሃት ነውና ፈሪስ? ብለን እንጠይቅ፡፡ ፈሪ ሲኮራ ምን ያደርጋል? ግልፅ ነው፡፡ “ፈሪ ሲኮራማ የጦር ሜዳ ልብስ ፒጃማ ያደርጋል፡፡” ምን ያደርግ? (ፈሪን ማለቴ ነው) ጦር ሜዳ ውሎው የአልጋ ላይ “አዳር” ሆኖበት በህልሙ ሲጨነቅ፤ የብረት ኮፍያ አድርጎ አለመተኛቱም መለስተኛ ፈሪ ቢሆን ነው፡፡ ልፋ ያለው በህልሙ ዳውላ ሲሸከም፤ ፍራ ያለው ደግሞ በህልሙ ሲሸሽ ያድራል፡፡ ይሁንና በ“ፈርቶ አደሮች” ዘንድሮ “ዛሬ በህልሜ ስሸሽ አደርኩ” አይባልም፡፡ እንደውም “ሳሳድድ አደርኩ” ሲሉ “ቅዠት ነው” ብንላቸው እንኳ ክፉኛ ይቀየሙናል፡፡ “ሸሽቶ አደርነት” እንኳን ለሌላ ለራስም የሚያምኑት ጉዳይ አይደለማ! ከልቡናው አልፎ አደባባይን “እኔ ፈሪ ነኝ!” በሚል የደፈረ አንድ ሰው ብቻ አውቃለሁ፡፡ የእኛው ደራሲ ስብሐት ገብረእግዚአብሔር፡፡ ቆይ-ቆይ አንድ ሌላ ሰው አለ፤ እንግሊዛዊው የቋንቋ ሊቅና ደራሲ ዶ/ር ሳሙኤል ጆንሰን፡፡ ሁለቱም ፍርሃትን የሰው ልጅ ሁሉ እጣ ፈንታ ያደርጉታል፡፡ ባንናገረውም ፍርሃት የነፍስ ፅንስ ነው ባዮች ናቸው፡፡  
ስብሐት ሞትን በነፍስ ሳይሆን በሥጋ የሚሸሹ ግራ አጋቢ ገፀ ባህርይ አሉት፡፡ አጋፋሪ እንደሻው፡፡ ሞትን እንደ ብዙዎቻችን በሐሳብ ሳይሆን በበቅሎ ሲሸሹ እርጅና አፋፍ ደርሰዋል፡፡ ታዲያ ጋዜጠኛ  ጌጡ ተመስገን ስብሐትን ሲያነጋግረው፤ አጋፋሪ እንደሻው የራስህ ቅጂ ናቸው ሊል የሚያስችለውን መንደርደሪያ ጥያቄ ያቀርብለታል፡፡
“ጋሽ ስብሐት”
“አቤት”
“ሞትን ትፈራለህ?”
“አንተስ?”
“ፈሪ አይደለሁም የሚል የመጀመሪያዋን “ፈሪ” የምትል ቃል እኔ ላይ ይወርውር” እንደማለት ነው፡፡ ማን? የትኛው የሰው ልጅ ሞትን አልፈራም ይላል? … የህሊና ፍርድ ነው፡፡ “ሞት ላይቀር ፍርሃት፣ አመል ላይተው ቅጣት” ይባላል፡፡ ይሄ ተረት እንግሊዛዊውን ደራሲ ዶ/ር ጆንሰንን ይመለከታል፡፡ ስለ ሞት ከተነሳ በፍርሃት ይንዘፈዘፋል አሉ፡፡ “ምነው?” ቢሉት፣
“ሞት ሁልጊዜም፣ ምንጊዜም አስጨናቂና አስፈሪ ነገር ነው” ይላል፡፡ ሞትን ደስታም አልነው ሰላማዊ እንቅልፍ ለእኔ ጨርሶ ካለመኖር፤ ከስቃይ ጋር በህይወት መገኘት ይበልጥብኛል” አጋፋሪ እንደሻው ከፈጣሪያቸው ከስብሐት ይልቅ ዶ/ር ሳሙኤል ጆንሰንን መሳይ ናቸው ማለት ይቻላል፡፡ እህል ተዘርቶ እንደሚሰበሰብ ሁሉ ሞትም ወደ “ጎታ” መከተት እንደሆነ ሲነገራቸው አጋፋሪ “እኔን እንደ ቃርሚያ ቆጥራችሁ ተውኝ” ይላሉ፡፡
የብዙዎቻችን ምኞት ይመስላል…፡፡
… ፍርሃትና ሞትን አያይዘን ለማየት “ችክታ” ውስት የገባነው የፍርሃት ሁሉ ምንጭ ሞት ስለሆነ ነው፡፡ ኤልሳቤት ኪዩብለር ሮዝ የተሰኘች ተመራማሪ፤ “ON Death and Dying” መፅሐፏ ላይ እንዲህ ትላለች፡-
“… Man has not basically changed. Death is still a fearful, frightening, happening and the year of death is a universal year even if we think we have mastered it on many levels”
(የሰው ልጅ በመሰረቱ አልተለወጠም፡፡ ሞት አሁንም የጭንቀቱ እና የፍርሃቱ ምንጭ ነው፡፡ በተለያየ ደረጃ ለመቆጣጠር የሞከረ ይምሰለው እንጂ ከሞት ጋር የተያያዘው ፍርሃት አሁንም የሰው ልጆች ሁሉ አለማቀፋዊ ሁኔታ ነው እንደማለት ነው)
“የፍርሃት ዓለማቀፋዊነት ይለምልም!” የማለት ዕድሉን ግን ተነፍገናል፡፡ ለመፍራት ሳይሆን ፍርሃትን መሸፋፈን ላለመቻል ማኅበራዊ መዋቅሩ ሥፍራ የለውም፡፡ ፍርሃትህ ‹ጎዳና ተዳዳሪ› ሆኖ ካሳጣህ ይተረትብሃል፣ ይዘፈንብሃል፣ ይፎከርብሃል፡፡ ከቤትህና ከልጆችህ በላይ ፍርሃትን ቀጥ ሰጥ አድርገህ ማስተዳደር ግድ ነው፡፡ ያለበለዚያ፡-
ነጋሪቱ ሁሉ አብዢር ቀብዢር ሲል
በፈረሶች ኮቴ መሬቱ ሲግል
ፈሪ በሞላ መሸሻ ሲያጣ
ቡኩኑ ሁሉ አፉ ሲነጣ
ከጎበዝም ጎበዝ ጎበዝ ይበልጣል
እኒያ ሲመጡ ያንፈራጥጣል፡፡
ከፈሪም ፈሪ ፈሪ ይበልጣል፣
እኒያ ሲመጡ ሸሽቶ ያመልጣል፡፡
ግን ለምን እንፈራለን? የሚል ጣያቄ ቢቀርብ መልሱ ለምንስ አንፈራም? ይመስላል፡፡ ሞት ወስዶ የመለሰው ማን አለ? እንኳን ሞትና የማያውቁት አገርስ ይናፍቃል?
የሥነ ልቡናው ሊቅ Viktor Frankl ለፍርሃት መድኃኒቱ “ፍቺ” (meaning) መስጠት እንደሆነ ለፍፏል፡፡ ፍርሃት የሰው ልጅ ዘንድ ዘላለም እንደሚኖር የሚያብራራበት አንድ ጥቅስ አለው፡፡ ጥቅሱ የFranz Werfel መሆኑን አልሸሸገም፡፡ “መጠማት የውኃን መኖር ለማረጋገጥ የሚያስችል ዋናው መንገድ ነው” (“Thirst is the surest proof for the existence of water”) ፍርሃትም ህይወት ስለመኖሩ የምናረጋግጥበት ብቸኛው መንገድ ነው፡፡ ፍርሃት ጥማት ሲሆን ህይወት ደግሞ ያንን ጥማት የምንቆርጥበት (መጠጥ) ናት እንደማለት፡፡ “እየፈራን እንኖራለን፣ እየኖርን እንፈራለን፤ ይሁንና ፍቺ እናበጃለን” እያለን ይመስላል፡፡ እንደውም ቃል በቃል እንዲህ ይላል፡- “The greatest human achievement is not success, but facing an unchangeable fate”
(የሰው ልጅ ታላቁ ስኬት የሚፈልገውን ግብ መትቶ መገኘቱ ሳይሆን የማይቀየረውን ዕጣ-ፈንታ ፊት ለፊት መጋፈጥ መቻሉ ነው፡፡) ሞት የማይለወጥ ዕጣ-ፈንታችን ነው፡፡ ስለዚህ መጋፈጥ እንጂ መልመጥመጥ ምን አመጣው? Frank ያስተማረው ከህይወት ስንክሳር ያጠለለውን እውነት ነው፡፡ ከናዚ ጀርመን ማጐሪያ፤ የሞት ወፍጮ ከሚያጓራበት ሥፍራ ህይወቱ ተንጠልጥላ የነበረው እዚች ሰላላ  ቆራጥነት ላይ ነበርና፡፡ ለዚች ሃሳብ ከኛ ዘንድ አቻ ተረት አናጣም፡፡
“ሞት ርስት ነው፣ መፈራቱ ለምንድነው?”
“ሞት ሲገድል፣ መቃብር ሲቀበል፣ በቃኝ ጠገብኩ አይል፡፡”
ነፍስ እንደሁ መቋጠሪያ የላት፤ ሾላኪ - ተንሸራታች ናት፡፡ እንደውም አንዳንዴ መቋጠሪያ ያልነው ፍርሃት ሞት ጠሪ ንግርት ሆኖ ያርፋል፡፡ ሔሮዱተስ “በጥንት ታሪክ” መፅሐፉ ውስጥ ስለዚህ ሞት ጠሪ መቅሰፍት ይነግረናል፡፡ በዳርዮስ ዘመን ነው፡፡ ኦባዙስ የሚባል የፋርስ ሰው ልጆቹ በጦርነት እንዳያልቁበት ስጋት ያዘው፡፡ ወደ ወዳጁ ዳሪዮስ በመሄድ አንዱ ልጁ ከቤት እንዲቀርለትና ከውትድርና ነፃ እንዲወጣ ጠየቀው፡፡ ዳርዮስ ኦባዙስ ካሰበው በላይ ሁሉም ልጆች እንዲቀሩለት ፈቀደ፡፡ ሽማግሌው ተደስቶ ሳያበቃ ግን የንጉሱ ሌላ ትእዛዝ ለወታደሮች ደረሰ፡፡ ”ሦስቱም ልጆች ይገደሉ” የሚል፡፡
እግዚኦ! ሞትና ውሻ የፈራለትን ያሳድዳል ማለት ነው፡፡ ኦባዙስ ለልጆቹ ባይፈራ ልጆቹን ባላጣ ነበር፡፡ ፍርሃት፣ ፍርሃት፣ ፍርሃት… የትኛውም ማህበራዊ ህይወት የማያበረታታው ሰዋዊ ተፈጥሮ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ከፈራህ ባህላዊ ከበሬታን ታጣለህ፤ እድራዊ ቦታን ትነፈጋለህ፤ በአደባባይ ትወረፋለህ፤ ሌላው እንዳይፈራ ማስተማሪያ ትሆናለህ… ያም ሆኖ ከጀግንነት ጋር ከመሞት ይልቅ ከፍርሃት ጋር መኖርን የሚመርጡ አይጠፉም፡፡ በመሆኑም ከአቅማቸው በላይ የሆነን መጋፈጥ ቀርቶ እንደ ኢምንት ለሚታየውም መንፈሳቸው ሲሸበር ይታያል፡፡ ይቺ ግጥም ዋቢ አድርጉልኝማ፡-
ዶሮ ጮኸ ብለሽ አትክፈቺው ደጁን
ዶሮ ጠላቴ ነው በልቼበት ልጁን
“ሰው ከንቱ!” ማለት ይኼኔ ነው፡፡ ብለን - ብለን ዶሮ ፈራን? ምን ነካን? ሰው መሆናችንንስ ምን ነጠቀን!


Read 3103 times