Saturday, 09 July 2016 10:29

ደራሲያን ማህበር ያዘጋጀው “የንባብ ቀን” በኪነ ጥበብ ዝግጅት እየተከበረ ነው

Written by 
Rate this item
(0 votes)

እስከ ፊታችን ማክሰኞ ይዘልቃል

የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር በየዓመቱ ሰኔ 30ን ምክንያት በማድረግ የሚያዘጋጀው አገር አቀፍ የንባብ ቀን ባለፈው ሐሙስ በተለያዩ የኪነ ጥበባት ዝግጅቶችና የመፃህፍት አውደ ርዕይ የተከፈተ ሲሆን ክንውኑ የፊታችን ማክሰኞ ድረስ ይዘልቃል ተብሏል፡፡“ንባብ አስተማማኝ ድህነትን መመከቻ ጋሻ ነው” በሚል መርህ እየተካሄደ ባለው በዚህ የኪነ ጥበብ ዝግጅት ላይ በየቀኑ የመፅሀፍት
አውደ ርዕይ፣ ዲስኩር፣ ወግ፣ ጥናታዊ ፅሁፍና፣ ግጥሞችና እንደሚቀርቡ ደራሲያን ማህበር
ባለፈው ማክሰኞ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቋል፡፡ ዛሬ ከምሽቱ 11 ሰዓት ጀምሮ በተዋናይ ፍቃዱ ከበደ፣ በደራሲ እንዳለጌታ ከበደና በኢየሩሳሌም ነጋ ወጎች የሚቀርቡ ሲሆን ነገ ጠዋት ደግሞ “የመፃህፍት ስርጭት በገጠር ኢትዮጵያ” በሚል ርዕስ የፎክሎር እጩ ዶክትሬት (Phd) የሆነው ገዛኸኝ ፀጋው፣ ጥናታዊ ፅሁፍ የሚያቀርቡ ሲሆን ይታገሱ ጌትነት እንዲሁ “የህፃናት
መፅሀፍት በኢትዮጵያ” የሚል ጥናት ያቀርባሉ ተብሏል፡፡ ገጣሚ ስዩም ተፈራ፣ ተዋናይ
አልአዛር ሳሙኤል፣ አርቲስት ተፈሪ አለሙና ገጣሚ ሰለሞን ሞገስ ደግሞ የግጥም ስራቸውን
ያቀርባሉ፡፡ በዕለተ ሰኞ ጋዜጠኛና ደራሲ አበረ አዳሙ፣ደራሲና ጋዜጠኛ ታደለ ገድሌ፣ መዝገበ
ቃል አየለና መምህርት ኑአሚን ቅኔያቸውን በማቅረብ ታዳሚውን ያስደንቃሉ ተብሏል፡፡
ማክሰኞ ጠዋትም የህፃናት መፅሀፍት ንባብና የሽልማት ስነ-ስርዓት ተካሂዶ የፕሮግራሙ መዝጊያ እንደሚሆን ታውቋል፡፡

Read 1082 times