Saturday, 09 July 2016 10:42

ያቺን እናት አልረሳትም!

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ
Rate this item
(0 votes)

      በደብረብርሀን ሪፈራል ሆስፒታል፣ በኤችአይቪ ኤይድስና በጨቅላ ሕጻናት ጤንነት ዙሪያ የሚሰጣቸው አገልግሎቶች ምን እንደሚመስሉ አስነብበና። ዛሬ፣ ለመሆኑ ሆስፒታሉ፣ ከየት ተነስቶ የት ደረሰ? የሚል ጥያቄ በማንሳት፣ አሁን ያለበትን ደረጃ እንቃኛለን።
“...የደብረብርሀን ሆስፒታል የተመሰረተው በኢጣልያ ወታደሮች ነው። ይህ እኔ አሁን ቢሮዬ ያደረግሁት ክፍል በጊዜው የጣሊያኖቹ የኦፕራሲዮን ክፍል ነበር። እኔም  የ6/አመት ልጅ ሆኜ ኦፕራሲዮን ሆኜበታለሁ። የጠቅላላ ሐኪም ስሆንም ታካሚዎችን  ኦፕራሲዮን አድርጌበታለሁ።” ዶ/ር ፍሰሐ ታደሰ  
ዶ/ር ፍሰሀ ታደሰ የዚህ እትም እንግዳ ናቸው። ሆስፒታሉ፣ ከ85 ዓመታት በፊት ሲመሰረት፣ ሀበሻና ጣልያን የሚታከሙበት የተለያየ ብሎክ ነበረ ይላሉ - ዶ/ር ፍሰሐ። ዛሬ ስላሴ ማእከል መደብር ያለበት ቦታ የሀበሻ መታከሚያ ነበር። አሁን ሪፈራል ሆስፒታል ያለበት ቦታ ደግሞ፣ 2 ብሎኮች ለፈረንጆች መታከሚያ አገልግሎት የሚሰጥ ነበር። ሆስፒታሉ የተገነባበት ምክንያት በወቅቱ የኢጣልያን ጦርነት ስለነበር ለወታደሮች ማገገሚያና መታከሚያ ሲባል ነበር።
ከጊዜ በኋላ ሆስፒታሉ ከነበረበት ደረጃ እንዲያድግና ዘመናዊ መልክ እንዲኖረው፣ በቀድሞው አጠራር የተጉለትና ቡልጋ አውራጃ ህዝብ መዋጮ አድርጎ፣ ተጨማሪ የህሙማን መኝታ ክፍሎች ተሰሩ። ከዚህም በተጨማሪ በየጊዜው ከተለያዩ ድጋፍ ሰጪ አካላት በሚገኝ እገዛ፣ ሆስፒታሉ እየተሻሻለ መጥቷል።
የማዋለጃ ክፍል፣ የኦፕራሲዮን ክፍል እና የኤክስሬይ አገልግሎት መስጫ ክፍል የመሳሰሉት ሁሉ በድጋፍ ሰጪ አካላት ተሰርተዋል። የላቦራቶሪ መሳሪያዎችን ጨምሮ፣ በርካታ የህክምና መስጫ ቁሳቁሶች፣ ምር ጄኔሬተር፣ አንቡላንስና ሌሎች እገዛዎች በድጋፍ ተገኝተዋል። ይህም በጥንካሬ ኃላፊነትን የመወጣት ዝንባሌ፣ ሊመሰገን ይገባም። የግቢው አስፋልትና የኮብል ስቶን ንጣፍም፣ በድጋፍ የተሰራ ነው።
የደብረብርሀን ሆስፒታል እንዲሁም ከተማዋ፣ ብዙ ተለውጠዋል። የዛሬ ሀያ አመት ገደማ፣ከተማዋንና ሆስፒታሉን ያየ ሰው፤ ዛሬ ተመልሶ ቢመለከት፣ ግር መሰኘቱ የማይቀር ነው። ረዥም እድሜ ያስቆጠሩ አነስተኛ ቤቶችና ጋሪዎች የሚመላለሱበት የከተማዋ ጠባብ መንገድ፣ ዛሬ ተለቀይረዋል። አዳዲስ ፎቅ ህንፃዎች ግራና ቀኝ እየተበራከቱ ነው። በከተማዋ መንገዶች፣ በርካታ ታክሲዎችና ባጃጆች በሰፊው ያስተናግዳሉ።
ሆስፒታሉም እንደከተማዋ፣ መልኩ ተለውጧል። የሆስፒታሉ ግቢ፣ እንደዛሬ በዛፍና በአበባ የተሞላና ውበትን የተላበሰ አልነበረም። ክፍሎቹ ሰፍተዋል፤ አዳዲስ ግንባታዎችም ይታያሉ። ዘመናዊ የላቦራቶሪ ክፍል ተገንብቶ፣ በዘመናዊ የላቦራቶሪ መሳሪያዎች ተሞልቷል። ብዙ ነገር ተሻሽሏል። ሆስፒታሉ በአገር አቀፍ ደረጃ በተደረጉት ውድድሮች፣ በተደጋጋሚ ተሸላሚ ለመሆን የቻለውም፤ የባለሙያዎች የስራ ጥረት፣ የአገልግሎት ጥራት እና የሆስፒታሉ እድገት ጋር የሚያያዝ ነው ብለዋል ዶ/ር ፍሰሐ ታደሰ።
“በተለይም ደግሞ...” አሉ ዶ/ር ፍሰሐ ፤ “የሆስፒታሎች ሪፎርም፣ በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ከተጀመረ በኋላ፣ ከቀድሞው አሰራር በተለየ መልኩ አገልግሎት እየሰጠን ነው ማለት ይቻላል። ሪፎርሙ አማካኝነት፣ እያንዳንዱ የሆስፒታል ስራ የሚገመገምበትና የሚሻሻልበት ዘመናዊ አሰራር ስለተፈጠረ፤ በሆስፒታሉ ውስጥ ለውጦች እንዲኖሩ አስችሏ። ሆስፒታሉ በሜዲካል ዳይሬክተር ነበር የሚመራው። አሁን ግን፣ ስራ አስኪያጅ እንዲኖረው ተደርጓል። ይህ አሰራር፣ በጣም ምቹ ዘዴ  ነው። ምክንያቱም፣ ሜዲካል ዳይሬክተር ማለት፣ በህክምናው አገልግሎት ላይ በቀጥታ የሚሳተፍ ሐኪም ነው። የስራ አስኪያጅ ስራ ለሌላ ባለሙያ መስጠት፣ ከፍተኛ የስራ ጫናን  ይቀንሳል። ሆስፒታሉ የአመራር ቦርድ እንዲኖረውም ተወስኗል። ይህም፣ ከህብረተሰቡ ጋር በቅርበት  ለመስራት፣ መረጃ ለመለዋወጥና ሁሉንም ነገር ለማወቅ፣ እንዲሁም ቅድመ ጥንቃቄ ለማድረግ ይረዳል። የገንዘብ አጠቃቀምም ተቀይሯል። ሆስፒታሎች፣ ከአገልግሎት የሰበሰቡት ገንዘብ ለመንግስት ፋይናንስ ፈሰስ ይደረግ ነበር። አሁን ግን፣ ያ ተለውጦ መንግስት ከሚመድበው በጀት በተጨማሪ፣ ሆስፒታሎች የውስጥ ገቢያቸውን፣  የአገልግሎት ጥራት ለማሳደግ እንዲያውሉት በመፈቀዱ፣ ብዙ ነገሮችን ለማሻሻል ረድቶአል። ከአሁን ቀደም፣ የሆስፒታሉ በጀት በመቶ ሺ ብሮች የሚቆጠር ነበር። ዛሬ ግን፣ ከ40 ሚሊዮን ብር  በላይ ሆኖአል። መድሀኒት ገበያ ላይ ካልጠፋ በስተቀር፣ በበጀት ችግር  ምክንያት የማይጠፋበት ደረጃ ላይ ተደርሷል።” ብለዋል።
የደብረብርሀን ሆስፒታል በተከታታይ በየሁለት አመቱ ለተሸላሚነት በቅቶአል። ተሸላሚ የሆነውም ብቻውን ሳይሆን በዙሪያው ያሉ ሆስፒታሎችን ጭምር እንዲሸለሙ የሚያስችላቸውን መንገድ እያሳየና አርአያ ጭምር እየሆነ ነው ይላሉ ዶ/ር ፍሰሐ።
“...የጤና ጥበቃ ሚኒስር በ2004 ዓ.ም የመጀመሪያውን ውድድር ሲያከናውን፣ 15 ተመራጭ ሆስፒታሎች ዝርዝር ውስጥ በመግባት፣ የደብረብርሀን ሪፈራል ሆስፒታል ተሸላሚ እንዲሆን ተመርጧል። በዚህም፣ አንድ ሚሊዮን ብር ተሸልማል። ብልጫ በማሳየት የተመረጡት 15 ሆስፒታሎች፣ በየአካባቢያቸው ለሚገኙ ሆስፒታሎች ልምድ እንዲያካፍሉ ተደርጓል። የደብረብርሀን ሪፈራል ሆስፒታልም ተሸላሚ በመሆኑ፣ የልምድ ልውውጥ እንዲያካሂድ፣ በዙሪያው ስምንት ሆስፒታሎች በክላስተር ተደራጅተዋል - ደብረማርቆስ፣ አሶሳ፣ አለም ከተማ፣ መሐል ሜዳ፣ ደሴ፣ ወልድያ፣ ቦሩ ሜዳ፣ አቀስታ። ሆስፒታሎቹ በተወሰነ ጊዜ እየተሰበሰቡ የልምድ ልውውጥ ያደርጋሉ። ስለሰሩት ስራ ሪፖርት ያደርጋሉ። ያጋጠመ ችግርና በጎ ነገር ላይ፣ መረጃ ይቀባበላሉ። በአጠቃላይ፣ ህዝቡን ለማገልግል በጋራ እየተደጋገፉ እንደመስራት ይቆጠራል።”
“እንደገና፣ በ2006 ዓ.ም ውድድሩ ሲካሄድ፣ ከክላስተር ቡድን አንጻርም በአፈጻጸሙ የተሻለ ሆስፒታል ነው ተብሎ፣ በአገር ደረጃ ከ15 ሆስፒታሎች 6ቱ ሲመረጡ፣ የደብረብርሀን ሪፈራል ሆስፒታል አንዱ ሆኗል። ብልጫ ካሳዩ 6 መሪ ሆስፒታሎች መካከል አንዱ በመሆኑም፣ 2 ሚሊዮን ብር ሽልማት አግኝቶአል። በአገር ደረጃ ከተመረጡ 11 ሆስፒታሎች ሲመረጡም፣ 5ቱ ሆስፒታሎች በደብረብርሀን ሪፈራል ሆስፒታል ክላስተር ውስጥ የሚገኙ ሆስፒታሎች ለተሸላሚነት በቅተዋል። በዚህም ምክንያት ክልሉ ተሸላሚ ሆኖአል”
“ለሶስተኛ ጊዜ፣ በ2008 ዓም በተደረገው ውድድር፣ ፊክክሩ እጅግ ጠንካራ ነበር። የውድድሩ ዋነኛ መነሻ፣ የጤና አገልግሎት ብቃት፣ የእናቶችና ሕጻናት አገልግሎት፣ ንጽህና እና ሌሎች የአገልግሎት ጥራቶች ታይተዋል። ከዚህም በተጨማሪ፣ በዙሪያ ላሉ ሆስፒታሎች፣ ልምድ በማካፈል፣ በተጨባጭ የተገኙ ውጤቶችም ተመዝነዋል። በዚሁ ውድድር፣ በአገር ደረጃ፣ አምስት ሆስፒታሎች ሲመረጡ፣ ከተሸላሚዎቹ አንዱ የደብረብርሀን ሪፈራል ሆስፒታል ነው። አምስት ሚሊዮን ብር ተሸልሟል። በዙሪያችንም፣ ቦሩ ሜዳና አከስታ የአምስት ሚሊዮን ብር ተሸላሚ ሆነዋል። በክላስተር ደረጃም እነ አለም ከተማ እነ ወልዲያ አሸናፊ በመሆን የሶስት ሚሊዮን ብር ተሸልመዋል። በዚህም ምክንያት፣ ደብረብርሃን ሪፈራል ሆስፒታል፤ ተጨማሪ 1 ሚሊዮን ብር ሽልማት አግኝቷል። ይህ ውድድር ከገንዘቡ ባሻገር፣ የሆስፒታል አገልግሎት ለማሻሻል ሌላ ጥሩ አስተዋጽኦ አለው። ባለሙያዎችን ለስራ ይበረታታሉ። ጥሩ አገልግሎት ለመስጠት ይነሳሳሉ። ሽታ አልባ የሆነ ንፁህ ሆስፒታል ለመፍጠር፣ ሕመምተኞች ከአልጋ ውጪ በግቢ ውስጥ ሲንቀሳቀሱ ንጹህ አየር እንዲያገኙ ለማስቸል፣ ውድድሩ ያግዛል። የጤና ባለሙያ፣ ለህብረተሰቡ ንጽህናን ማስተማር አለበት። ነገር ግን፣ ሆስፒታሎች የሚቆሽሹ ከሆነ ግን፣ ንፅህናን በቃል ብቻ ማስተማር ዋጋ የለውም። ህብረተሰቡ በተግባር የሚታይ ጥሩ ነገር ያጣል። ጤናንም ለመጠበቅ ያስቸግራል።” ... ደብረብርሀን ሪፈራል ሆስፒታል መጽሔት
ዶ/ር ፍሰሃ፣ የጽንስና ማህጸን ሕክምና እስፔሻሊስት ሙያቸው ሆስፒታሉ ሜዲካል ዳይሬክተርነታቸው፣ በስራ ላይ የተከሰቱ አይረሴ አጋጣሚዎችን  ያስታውሳሉ።
“...የማህጸንና ጽንስ ህክምና፣ ከባድ ሙያ ነው። ምክንያቱም በበርካታ ተግዳሮት የተከበበ ሙያ ነው። በዚያ ላይ፣ ቀንና ሌሊት፣ ሁልጊዜ መገኘኘትን ይጠይቃል። በስራ ጥሩ ውጤት ሲመጣ ያስደስታል። ችግር ሲገጥም ደግሞ፣ በጣም አስጨናቂና አስከፊ ነው። አንድ ጊዜ አስታውሳለሁ። ወደ ኦፕሬሽን ክፍል እየገባሁ ነበር። የታካሚዋ ባለቤት፣ ከአጠገቡ የ3 አመት ልጅ ይዟል። እኔን እያየ፣ ‘አደራ... የዚህ ህጻን ልጅ እናት ናት፣ ...አደራ” አለኝ። እስቲ በዚያ ቦታ ላለ ባለሙያ ምን ሊሰማ እንደሚችል ገምቱ። ደግነቱ፣ ያቺ እናት በኦፕራሲዮን ህክምና ድናለች። ያቺን እናት አልረሳትም።”
ዶ/ር ፍሰሀ ሌላም ገጠመኝ አላቸው።
“...ከሰላ ድንጋይ ለህክምና የመጣች ናት። በማህጸንዋ 36 ኪሎ ግራም እጢ ነበረባት። በጊዜው ወደሆስፒታሉ መጥታ መታከም አልቻለችም። ምክንያቱም እናትዋን ስትጦር ስለነበር፣ ሁለት አመት ሙሉ ስትታመም ቆይታለች። እየባሰበሰባት ሲሄድም፣ ወደሆ ስፒታል የመምጣት አቅም ስላልነበራት፣ የአካባቢው ሕዝብ ገንዘብ አዋጥቶ ነው የመ ጣችው። ያኔ፣የአልትራሳውንድና የተሟላ የላቦራቶሪ አገልግሎት በሆስፒታሉ ውስጥ አልነበረም። ወደ አዲስ አበባ እንድትሄድ ነበር የተፈለገው። ቤተሰቦችዋ ግን፣ አዲስ አበባ የመሔድ አቅም የለንም። እዚህ ካልሆነልን፣ የምንመለሰው ወደቤታችን ነው” አሉ። ባለሙያዎቹ ተመካከርን። እና፣ ኦፕራሲዮን ለማድረግ ወሰንን። ሐኪሞቹ እንደየሙያችን ተባብረን ሰራን። በኦፕራሲዮን 36 ኪሎግራም እጢ ከማህጸንዋ ወጣላት። ትልቅ ስራ ነው። ሲሳካ ደስ ይላል። ከዚህ የበለጠ የህሊና እርካታ የት ይገኛል!”።

Read 1741 times