Saturday, 09 July 2016 10:40

“ፍትህ ለሴቶች” የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም ይካሄዳል

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(1 Vote)

1.5 ሚ ብር ይሰበሰባል ተብሎ ይጠበቃል
    የሴቶችን ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና የህግ መብቶችን በማሳደግ ላይ ትኩረት አድርጎ የሚሰራው የኢትዮጵያ የህግ ባለሙያ ሴቶች ማህበር፤  ከምሽቱ 1፡00 የፊታችን ሀሙስ “ፍትህ ለሴቶች” የተሰኘ የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም በደሳለኝ ሆቴል ያካሂዳል፡፡ ማህበሩ ባለፉት 21 ዓመታት ለ125 ሺህ ደሀ ሴቶች ነፃ የህግ አገልግሎት ድጋፍ ሲሰጥ መቆየቱን አስታውሶ፤ አሁንም የህግ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸውንና ፍትህ ያጡ ሴቶችን የበለጠ ለማገዝ ለሚያስፈልገው ወጪ የገቢ ማሰባሰቢያ የእራት ምሽቱን ማዘጋጀቱ ተገልጿል፡፡
ማህበሩ ከትላንት በስቲያ በኢትዮጵያ ሆቴል በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ፤ ለስራ እንቅፋት ከሆኑበት ነገሮች አንዱና ዋነኛው የገንዘብ አቅም ውስንነት እንደሆነ የተገለፀ ሲሆን በዚህም ምክንያት መስራት የሚገባቸውን ያህል እንዳልሰሩ ተናግረዋል፡፡
 በመላው አገሪቱ 60 ያህል የማህበሩ ቅርንጫፎች እንደሚገኙ የገለፁት ዳይሬክተሯ ወ/ሮ ዜናዬ ታደሰ፤ ከ300 በላይ በጎ ፈቃደኛ የህግ ባለሙያዎችን ድጋፍ በማድረግ ደሀ ሴቶች ከሚደርስባቸው የቤት ውስጥ ጥቃት፣ ከቀለብ መከልከል፣ ከድብደባና ከተለያዩ አካላዊ ጉዳቶች እንዴት መከላከል እንዳለባቸው ግንዛቤ ከመስጠት ባለፈ ችግሩ የገጠማቸው 125ሺህ ያህል ሴቶች ነፃ የህግ ድጋፍ አገልግሎት ማግኘታቸውን አስታውሰዋል፡፡ የፊታችን ሀሙስ በሚካሄደው የገቢ ማሰባሰቢያ የእራት ምሽት ከ1.5 ሚ. ብር በላይ እንደሚጠበቅ የገለፁት ወ/ሮ ዜናዬ፤ የመግቢያ ዋጋ አንድ ሺህ ብር መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡ በሚገኘው ገንዘብም በሴቶች ጥቃት ዙሪያ የቅድመ መከላከል፣ የአድቮኬሲና ችግርና ጥቃት ለደረሰባቸው ሴቶች የበለጠ ድጋፍ የማድረግ ስራ እንደሚያከናውኑበት ጠቁመው፤ በምሽቱ በመገኘት ሁሉም የበኩሉን ድጋፍ እንዲያደርግ ዳይሬክተሯ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

Read 1212 times