Saturday, 16 July 2016 12:10

ጥርስን ያለ ድሪልና ያለማደንዘዣ አፅድቶ የሚሞላ መሳሪያ አገራችን ገባ

Written by 
Rate this item
(11 votes)

     የአርጀንቲናው አሊሚኔተር ግሩፕ የቬንዳኖቫ ምርት የሆነውና ላለፉት አራት ዓመታት በአርጀንቲና ጥቅም ላይ የዋለውን ጥርስን ያለ መቦርቦሪያ ድሪልና ያለ ማደንዘዣ አፅድቶ የሚሞላው መሳሪያ ሰሞኑን አገራችን ገባ፡፡ በዓለም ጤና ድርጅት እውቅና የተሰጠውና በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አገር ውስጥ ጥቅም ላይ እንዲውል ፈቃድ የተሰጠው ይሄው መሳሪያ ከተፈጥሮአዊ እፅዋት በሚሰራ ጄል ያለ ማደንዘዣና ያለ ድሪል ጥርስን በማፅዳት የሚሞላ ሲሆን አንድ ሰው በ10 ደቂቃ ውስጥ ጥርሱ ፀድቶና ተሞልቶ ወደቤቱ እንዲሄድ የሚያደርግ ነው ተብሏል፡፡ የአምራች ድርጅቱ ዋና ስራ አስኪያጅ ሚስተር ጆርጅ ሌይንና የኢትዮጵያ ወኪሉ ሚረር ‹ትሬዲንግና ሰርቪስ› ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ተስፋየየ ወንድሙ ባለፈው ሳምንት መጀመሪያ በሂልተን ሆቴል  በሰጡት መግለጫ፤ መጀመሪያ ምርቱ በጥርስ ህመም የሚሰቃዩ ህፃናትን ታሳቢ አድርጎ የተሰራ እንደነበርና በአሁኑ ሰዓት አዋቂዎችም በስፋት እየተጠቀሙበት መሆኑን ተናግረዋል፡፡በሁለቱ ኩባንያዎች መካከል በዕለቱ የ50 ሚ. ዶላር ስምምነት የተደረገ ሲሆን መሳሪያውን በዋና በወኪልነት ሚረር ትሬዲንግና ሰርቪስ እንደሚያከፋፍልና ከአርጀንቲና የሀኪሞች ቡድን እንደሚመጣና ለኢትዮጵያዊያን የጥርስ ሀኪሞች ስለመሳሪያው አጠቃቀም ስልጠና እንደሚሰጥ ታውቋል፡፡ አንዱ መሳሪያ ጫፉ እየተቀየረ ለ10 ሰዎች ያገለግላል የተባለ ሲሆን አንድ ሰው በመሳሪያው ታክሞ ለመዳን አምስት ዶላር ብቻ እንደሚያስፈልገው በስምምነቱ ወቅት ተገልጿል፡፡ የመሳሪያው ተፈላጊነት ከጨመረ ፋብሪካው ኢትዮጵያ ውስጥ እንደሚከፈትና ለሌሎች የአፍሪካ አገራትም እንደሚከፋፈል የገለፁት ሚስተር ጆርጅ፣ እስካሁን ከአርጀንቲናና ከሌሎች የላቲን አሜሪካ አገሮች በተጨማሪ ደቡብ አፍሪካም መሳሪያውን በስፋት እየተጠቀመችበት  እንደምትገኝ በዕለቱ ተገልጿል፡፡


Read 2052 times