Monday, 25 July 2016 07:25

ስልጣን እና ታዛዥነት

Written by  ሌሊሣ ግርማ
Rate this item
(1 Vote)

…. የህይወታችን አቅጣጫ የሚመራው በስልጣን ስር ነው፡፡
በልጅነታችን ወደድንም ጠላንም ለአስተማሪዎቻችን ወይንም ለወላጆቻችን መታዘዝ ነበረብን፡፡ ከፍ ስንል ደግሞ ለሀገራዊ ህግ ተገዢ መሆን እንገደዳለን፡፡ ስልጣኑ ከፈቀድነው ሀይማኖትም ሆነ ካልፈቀድነው ጉልበተኛ ሊመጣ ይችላል፡፡ ስልጣኑ ከሚያገባውም ከማያገባውም አካል ሊመነጭ ይችላል፡፡  
ህሊናም በአእምሮአችን ላይ ባለስልጣን ይሆናል። ምክኒያታዊነትም እስከፈቀድነው ድረስ ሊያዘን አቅም አለው፡፡ ‹‹አልታዘዝም በይነት›› በሀይማኖት ረገድ ከፍተኛ ሀጢአት ተደርጎ ይወሰዳል፡፡
ጥያቄው ግን ወዲህ ነው፡፡ ስልጣን የያዘ ለምሳሌ አስተማሪ … የበለጠ እውቀት፣ ተሞክሮና ብቃት ስላለው ነው የምንታዘዝለት? ወይስ አስተማሪ ሆኖ መገኘቱ ብቻ ተማሪን ለማዘዝ አቅም ይሰጠዋል? የመጀመሪያው የስልጣን አይነት … ማለትም የበለጠ እውቀት ባለቤት በመሆኑ … ተሞክሮና ልቀት በማስመስከሩ፣አስተማሪ የሚሆንበት “Authority dejure” ልንለው እንችላለን፡፡ “የተማረ ያስተምረን” … ወይንም “የተማረ ይምራኝ” እንደማለት ነው፡፡
ግን በእኛ ሀገራዊ ብሂል ከዚህም ባፈነገጠ እንቆቅልሻዊ አገላለፅ፤“የተማረ የግደለኝ” የሚል የአነጋገር ዘይቤ አለን፡፡ …(በአንድ ወቅት አንዱ ወዳጃችን ከአምስት ኪሎ ሰፈሩ ተነስቶ ጎማ ቁጠባ የሚባል ሌላ ሰፈር ድረስ ሄዶ ተደብድቦ መምጣቱን ሲነግረን … ሌላኛዋ አፈ ጮሌ ቀበል አድርጋ፤ “ለመደብደብ ጎማ ቁጠባ ድረስ መሄድ ለምን አስፈለገህ?” ብላ መጠየቋ ትዝ አለኝ) “የተማረ ይግደለኝ” የሚለውም ከልጅቱ አባባል ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡ “የተማረ ይግደለኝ” ማለት ወታደር ያስተምረኝ እንደ ማለት ነው፡፡ ለመገደል ለመገደል ምሁር ድረስ ምን ወሰደኝ?
“Authority defacto” የሚመጣው እዚህ ላይ ነው፡፡ ሆኖ የተገኘ ሁሉ የስልጣን ባለቤት፣ የማዘዝም ማንዴት አለው እንደ ማለት ነው፡፡ …. እዚህ ላይ ኢዲ አሚን ዳዳ፤ከእነ ህልቆ መሳፍርት የስልጣን ማዕረግ ስሞቹ ትዝ ሊለን ይችላል፡፡ … ‹ፊልድ ማርሻል› እና ‹ዶክተር› የሚሉ በሁለት ጥግ የቆሙ የብቃት ማስረጃ የማዕረግ ስሞችን ለራሱ ሸልሟል። በወንበሩ ላይ ሆኖ ከተገኘ ያስፈለገውን ማድረግ ይችላል እንደ ማለት ነው፡፡ በምን ምክኒያት? ተብሎ ሊጠየቅ አይችልም፡፡
ግን “የተማረ ይግደለኝ” ወደተባባልነው የስልጣን ተገቢነት ስንመጣም ችግር አለ፡፡ ማለትም፤ የተማረ መሆኑ በተከታይ “ያስተምር” ወይንም “ያልተማረውን ይዘዝ” አልያም … “ይግደል” የሚል የቅደም ተከተል ትስስርን አያመለክትም፡፡ … የወንድ ዘር ፍሬ መኖሩ ከሴት እንቁላል ጋር መገናኘት እንዳለበት በተፈጥሮ እንደሚከተለው አይደለም ያንኛው፡፡
የተማረው ሰው ስልጣን ያለው በራሱ የግል ህይወት ላይ ከሆነ----ይሄ አንድ ነገር ነው፡፡ “የተማረ ለሀገር ይጠቅማል” የሚለው አስተሳሰብ “Authority dejure”ን የሚያመለክት ነው፡፡ ግን ለሀገር መጥቀሙ በሀገር ላይ ስልጣን እንዳለው የሚያመለክት አይደለም፡፡ ለሀገር መጥቀሙ፤የሀገር ሸክም ያልሆነ የአንድ ጤናማ ዜጋ ስልጣንና መብት ባለቤት መሆኑን ብቻ ነው የሚያመለክተው፡፡ ለነገሩ ‹እከሌ የሚባል ሰራዊት … እከሌ የሚባለውን መንግስት ገረሰሰው› የሚለው Fact … ወይንም ተጨባጭ ክስተት … እከሌ እከሌን ስለገረሰሰው … በገረሰሰው መንግስት ፋንታ ስልጣን ላይ መቀመጥ እንዳለበት አይጠቁምም፡፡
… ለምሳሌ አንድ ወንጀለኛን አድኖ ይዞ እስር ቤት የከተተ ፖሊስ፤እስር ቤት የገባውን ወንጀለኛ … ሚስት አግብቶ፣ ልጆቹን በተወገደው አባት ፋንታ ማሳደግ እንዳለበት የመጀመሪያው ሁነት (fact) አይጠቁምም፡፡ ፖሊሱ … ወንጀለኛን የመያዝ ብቃት … ተሞክሮና ስልጠና ወይም እውቀት ነው ያለው እንጂ የጉዲፈቻ ብቃት የለውም፡፡ ግን ጉልበተኛ ከሆነ ወንጀለኛን የመያዝና ወንጀለኛ የመሆንን ብቃት አንድ ላይ አጣምሮ ሊያከናውን ይችላል፡፡
እንግዲህ አበሻ፤‹‹የተማረ ይግደለኝ›› እንዳለው… እነ ፕሌቶ ደግሞ ‹‹ፈላስፋ ንጉስ ስልጣን ይገባዋል›› ይላሉ፡፡ ፕሌቶ የሚላቸው የንጉስና ፈላስፋ ዘረ-መል ያላቸው አይነት ሰዎች፤ በምጡቅ ምክኒያታዊነት የታደሉ፣ከልጅነት ልዩ ስልጠና እና ክህሎት ሲቀስሙ ቆይተው…. ለአቅመ ስልጣን ሲደርሱ የሚሾሙ አይነት ናቸው፡፡ ፕሌቶን ለመረዳት አቅም ያላቸው ራሳቸው ፈላስፎች ናቸው፡፡ እንግዲህ በፕሌቶ ‹‹Republic›› ውስጥ የሚካተቱ ህዝቦች ምክኒያታዊና ፈላስፋነት ካልታየባቸው እንደ ዜጋ ሊቆጠሩ ሁሉ አይችሉም ማለት ነው፡፡
የአሪስጣጣሊስም አቋም ከፕሌቶ ብዙም አይርቅም፡፡ የአሪስጣጣሊስ የህዝብ እንደራሴዎችም እንዲሁ የተለየ እውቀትና ምክኒያታዊነት ያላቸው ፈላስፋ (Statesmen)  ናቸው፡፡ የመሪና የተመሪ ዝርያ ይኖራል ነው ሁለቱም ፈላስፎች በአጭሩ እያሉን ያሉት፡፡ መሪዎቹ ፈላስፎቹ ናቸው፡፡ በጥንታዊ ግሪክ ዘመን የነበሩ ምሁራን እንደ ማለት ነው፡፡
የንጉስን ወይንም የፈላስፋን የስልጣን ማንዴት ለማስረዳት ግን አስቸጋሪ ነው፡፡ ንጉስ የመሆን ብቃት በደሙ ምክኒያት የሚመጣ ነው፤ልትሉኝ ትችላላችሁ፡፡ ደሙ ደግሞ ከጥንታዊ … ንጉሳን ወይንም ፃድቃን ቀጥታ የተቀዳ መሆኑን ዘርዝራችሁ ልታረጋግጡልኝ ትችላላችሁ፡፡… ግን ይኼ ሁሉ፤ ምርጥ ዘሩ (በጥንቃቄ የተዳቀለ) ስለመሆኑ ወይንም  የዘር ሀረግ አመዛዘዝና አረዛዘሙን እንጂ… በህዝብ ላይ የስልጣን ባለቤት መሆኑን አይጠቁምም፤ ስለዚህ በደንብ እንዲጠቁምለት ወደ ጉልበት ማሳየት መግባት ይኖርበታል፡፡ በሀይል ከበለጠ… በግድም ይሁን በውድ፣ታሪክንም ይሁን አፈ-ታሪክን አዛውሮ፣ራሱን ንጉስ ማስባል ይችላል፡፡
አንደኛው የጉልበት አማራጭ ከቤተ ሃይማኖት ጋር ራሱን ማጣበቅ ነው፡፡ ስዩመ እግዚአብሔር የተባለ ንጉስ----በጦር ሜዳ ጉልበቱን ካስመሰከረ ጉልበተኛ ሁለት እጥፍ የላቀ ሀይል አለው፡፡ ምክኒያቱም ከሰማዩ ንጉስ ተወክሎ የመጣ ንጉስ፣ ውክልና ከሌለው የበለጠ የዙፋን ማንዴቱን የማሳመን ስልጣን ስላለው ብቻ ነው፡፡
የባለስልጣኑን የስልጣን ብቃት ለማመን ህዝብ ማስረጃ ይሻል፡፡… በምን ክህሎት.. በምን  እውቀቱ… በምን  አርቆ አስተዋይነቱ---ንጉስ ለመሆን በቃ? ብሎ ይጠይቃል፡፡ ህዝብ ፤‹እነዚህን ሁሉ ብቃቶች የሚሰጥና የሚነፍገው ሰማይ ያለው ንጉስ ነው›› ብሎ ቀድሞውንም ስለሚያምን፣ ውክልናው በቤተ-ሀይማኖት በኩል ሲመጣ አሜን ብሎ ይቀበላል። ህዝብን በተመለከተ፤ ‹‹ከአሜን ባሻገር›› ብሎ ማስተዋል የለም፡፡ ህዝብ ወይ ‹‹አሜን›› ይላል፣ ወይ ‹‹እንቢ›› ይላል፤ይኸው ነው፡፡ በምክንያታዊነት መመዘን የግለሰብ ምትሀት እንጂ የህዝብ አይደለም።
የስልጣን ባለቤት ሆኖ በመገኘት (Possession of authority de facto) የስልጣን ተገቢነትን መመዘኛዎች በአቋራጭ ወይንም ወደ ኋላ መመለስ ይቻላል፡፡
የስልጣን ተገቢነት መመዘኛዎች (ማለትም….ብቃትን፣ ክህሎትን፣ ልቀትን አርቆ አስተዋይነትን) አሟልቶ በመገኘት ግን ስልጣን ማግኘት ብዙ ጊዜ አይቻልም፡፡
በምክንያታዊነትና በኢ-ምክንያታዊነት መሀል ያለ ግጭት ቢሆንም፣ ድል የሚነሳው ግን ኢ- ምክንያታዊነት ነው፡፡ ለዚህ ነው ከሳይንስ ስልጣን የበለጠ የሀይማኖትና የእምነት ስልጣን ዘወትር የሰውን ተገዥነት ፈቃድ የሚዘውረው፡፡ ሳይንስ፤ ሀይማኖትን በምክንያታዊነት በማጣጣል፣ በሰው ልጆች አእምሮ ላይ የአመክንዮ ስልጣንን ለማስፈን ካደረገው ጥረትና ካሰረፀው እውቀት አንፃር ያገኘው ውጤት፣ የሀይማኖትና እምነትን ስልጣን መጨመር ብቻ ነው፡፡ በሳይንስ በተፈጠሩ መሳሪያዎች የእምነት ሰበካዎች እንዲሰራጩ አስተዋፅኦ ከማድረግ የዘለለ ስልጣን አላገኘም፡፡፡                        
ምክኒያቱም ሰው ምክንያታዊም ሆነ ኢ-ምክንያታዊ የመሆን አቅም ያለው ፍጡር ነው፡፡ የመምረጥ ተፈጥሮ ያለው ፍጥረት ነው፡፡ ምርጫውን ተጠቅሞ የስልጣን ባለቤት አድርጎ የመረጠው ብቸኛ ነገር ምንድነው? ካላችሁኝ … ‹‹ኢ-ምክኒያታዊነትን›› የሚል ነው፤ መልሴ። … የምክኒያታዊነትን መስመር የሚከተሉ ስልጣኖች በምድር ላይ ካሉ በጣም ጥቂት ናቸው፡፡ የዓለም ህዝብ የሚመራው በስሜት ነው፡፡ ይህ ብቻ ነው እውነቱ። የማይወደደውን የመውደድ … መወደድ የነበረበትን የመናቅ ስሜታዊ ምርጫ አለው፡፡
ይህንን የኢ-ምክንያታዊነት አቅሙን .. በምክንያታዊ ፈላስፋዎች ለመለወጥ ተፈላሰፈ፡፡ ፕሌቶ .. ምናልባት ለራሱ ሀገር ዜጎችና ራሱ ፕሌቶ ለነበረበት ዘመን ሊሰራ ይችላል፡፡ ግን ደግሞ፤ የራሱ ሀገር ዜጎች ናቸው አስተማሪውን ሶቅራጥስን ምክንያታዊ በሚመስል መድረክ ላይ  ኢ-ምክንያታዊ ግን ‹‹ዴሞክራሲያዊ›› ፍርድ የፈረዱበት፡፡ ስለዚህ ምናልባት ለጥቂትም ህዝብ የፕሌቶም ሆነ የኦሪስጣጣሊስ የምክንያታዊነት ስልጣን፣ህዝብን በተመለከተ ላይሰራ ይችላል፡፡ ደግሞ…የሶቅራጥስ የሚገርመው የሞት ፍርድ ከተፈረደበት በኋላ ጓደኞቹ ሊያስመልጡት ቢሞክሩ አሻፈረኝ ብሎ እንቢ ማለቱ ነው፡፡ ኢ-ምክንያታዊ ህዝብ ለፈረደበት ፍርድ ተገዢ መሆን እኮ … ኢ- ምክንያታዊነትን እንደሚያከብር ከመመስከር አይተናነስም፡፡ … ወይንስ ህዝብ የስልጣን ባለቤት መሆኑን ለማሳየት ሲል ይሆን ኢ-ፍትሀዊውን ፍርድ አሜን ብሎ የተቀበለው?… ህዝብ የስልጣን ባለቤት መሆን የሚችለው ግን በ defacto authority …. ነው? ወይንስ በ dejure authority?
ህዝብ የስልጣን ባለቤት እንዲሆን…. የህዝቡን አናት በበቂ ክህሎት … እውቀት … ተሞክሮ … ወይንም አርቆ አስተዋይነት መመስረት አለበት ካላችሁ፣ dejure authority ደጋፊ ናችሁ ማለት ነው፡፡ ‹‹እውቀት የህዝብ ጉልበት ነው›› እንደ ማለት፡፡ ለ ‹‹dejure authority›› ብቁ እስኪሆነ ግን ---- ‹‹defacto authority›› ይጫወትበታል፡፡ ምክንያታዊ ያልሆነ ባለስልጣን በሀይማኖት፣ በባህል፣ በታሪክ ወይንም በመሰል ስሜታዊ የዞረ ድምር ስም እየረገጠ ይገዛዋል፤… እያልኩ ለራሴ አሰብኩኝ፡፡

Read 2911 times