Saturday, 30 July 2016 11:59

ቱርክ ከ130 በላይ የመገናኛ ብዙኃንን ዘግታለች

Written by  አንተነህ ይግዛው
Rate this item
(4 votes)

ከመፈንቅለ መንግስቱ ጋር በተያያዘ ከ60 ሺህ በላይ ዜጎች ታስረዋል
     በቅርቡ የተቃጣበት የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ መክሸፉን ተከትሎ መረር ያለ እርምጃ በመውሰድ ላይ የሚገኘው የቱርክ መንግስት፣ ከጉዳዩ ጋር ንክኪ አላቸው ያላቸውን ከ130 በላይ የአገሪቱ የመገናኛ ብዙኃን ለመዝጋት መወሰኑን ስካይ ኒውስ ዘገበ፡፡
የቱርክ መንግስት እንዲዘጉ ከወሰነባቸው የመገናኛ ብዙኃን መካከል 3 የዜና ወኪል ተቋማት፣ 16 የቴሌቪዥን ጣቢያዎች፣ 23 የሬዲዮ ጣቢያዎች፣ 45 ጋዜጦች፣ 15 መጽሔቶችና 29 አሳታሚ ድርጅቶች እንደሚገኙበት ዘገባው አስታውቋል፡፡
ከከሸፈው መፈንቅለ መንግስት ሙከራ ጠንሳሾች ጋር ግንኙነት አላቸው በሚል በ42 ቱርካውያን ጋዜጠኞች ላይ በሳምንቱ መጀመሪያ የእስር ትዕዛዝ ያወጣው የአገሪቱ መንግስት፣ ባለፈው ረቡዕ ዛማን የተባለው የአገሪቱ ጋዜጣ  ባልደረቦች የሆኑ ተጨማሪ 47 ሰዎች እንዲታሰሩ መወሰኑንም ዘገባው ጠቁሟል፡፡
በመፈንቅለ መንግስቱ ሙከራ ከ9 ሺህ በላይ የጦር ሃይል አባላት መሳተፋቸውንና የሴራው ጠንሳሾች 35 አውሮፕላኖችን፣ 37 ሄሊኮፕተሮችን፣ 74 ታንኮችንና 3 መርከቦችን ለአላማቸው መሳካት አሰማርተው እንደነበር የአገሪቱ መንግስት ማስታወቁን የጠቀሰው ዘገባው፤ ከመፈንቅለ መንግስቱ ጋር በተያያዘ ያሰራቸው ዜጎች ቁጥር ከ60 ሺህ በላይ መድረሱንም አመልክቷል፡፡

Read 2481 times