Monday, 08 August 2016 06:01

የደቡብ ሱዳን ፕሬዚዳንት 6 ከፍተኛ ሚኒስትሮችን አባረሩ

Written by 
Rate this item
(3 votes)

    የደቡብ ሱዳን ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኬር፣ ባለፈው ሳምንት ከምክትል ፕሬዚዳንትነታቸው ካነሷቸው ተቀናቃኛቸው ሬክ ማቻር ጋር ግንኙነት አላቸው የሚሏቸውን ስድስት ሚኒስትሮች፣ባለፈው ማክሰኞ ከስልጣናቸው ማባረራቸውን ሮይተርስ ዘገበ፡፡በአገሪቱ ተቀናቃኝ ሃይሎች መካከል የተደረሰውን የሰላም ስምምነት በሚጻረር መልኩ ሹም ሽር አድርገዋል በሚል ሲተቹ የሰነበቱት የአገሪቱ ፕሬዚደንት ሳልቫ ኬር፤እነዚህን ሚኒስትሮች ማባረራቸው አገሪቱን ወደ ከፋ ቀጣይነት ያለው ግጭት ሊያስገባት እንደሚችል እየተነገረ ነው ብሏል ዘገባው፡፡ ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኬር ከስልጣናቸው ያባረሯቸው ሚኒስትሮች፡- የአገሪቱ የነዳጅ፣ የከፍተኛ ትምህርት፣ የአገር ውስጥ ጉዳይ፣ የሰራተኞች፣ የውሃ እንዲሁም የመሬትና የቤቶች ልማት ሚኒስትሮች እንደሆኑ የጠቆመው ዘገባው፤ሚኒስትሮቹ እንዲባረሩ ሃሳብ ያቀረቡት ከሰሞኑ በፕሬዚዳንቱ አነጋጋሪ ውሳኔ በምክትል ፕሬዚዳንትነት የተሾሙት ታባን ዴንግ ጋኢ መሆናቸውንም ገልጧል፡፡ባለፉት 2 አመታት በአገሪቱ በተከሰቱ ግጭቶች፣በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ዜጎች መሰደዳቸውን ያስታወሰው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት፤ከሶስት ሳምንታት በፊት በሁለቱ ሃይሎች መካከል ዳግም ግጭት ማገርሸቱን ተከትሎም ተጨማሪ 60 ሺህ ያህል ደቡብ ሱዳናውያን አገር ጥለው ተሰደዋል ማለቱን ዘገባው ገልጧል፡፡

Read 1193 times