Monday, 15 August 2016 08:46

የመንገድ ትራንስፖርት ባለስልጣን ያባረራቸው ሰራተኞች ወደ ስራ ሊመለሱ ነው

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(16 votes)

   የአዲስ አበበ መንገድ ትራንስፖርት ባለስልጣን፤ አዲስ በሰራው መዋቅር መስፈርቱን አታሟሉም በሚል ያበረራቸው 600 ሰራተኞች በአንድ ሳምንት ውስጥ ድልድል ሰርቶ ወደ ስራ እንደሚመለሱ ተገለፀ፡፡
ትላንት ከቀትር በፊት ሳር ቤት በሚገኘው የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን የመሰብሰቢያ አዳራሽ በተደረገው ስብሰባ፤ የመንገድ ትራንስፖርት ባለስልጣን ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ያብባል አዲስ፤ የሰራተኛውን አቤቱታ ካደመጡ በኋላ የሰራተኛው ጥያቄ አግባብ መሆኑን አምነው፣ ከ58 ሰራተኞች በስተቀር ሌሎቹ ድልድል ተሰርቶ ወደ ስራቸው ይመለሳሉ ማለታቸውን ምንጮች ገለፁ፡፡
58ቱ ሰራተኞች በስራቸው ላይ በነበሩበት ወቅት ባሳዩት የስነ ምግባር ግድፈትና ተደጋጋሚ ስህተት በህግ እንደሚጠየቁና ከጥፋት ነፃ መሆናቸውን ካረጋገጡ ወደ ስራቸው እንደሚመለሱም ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ አስታውቋል፡፡ ከባለፈው ሰኞ ጀምሮ ንብረት አስረክባችሁ ውጡ የተባሉ ከ600 በላይ የባለስልጣን መ/ቤቱ  ሰራተኞች፤ አፍሪካ ህብረት ጎን የሚገኘውን አዲሱን የባለስልጣኑን መስሪያ ቤት በተቃውሞ አጨናንቀውት ሰንብተዋል፡፡ ሰራተኞቹ ከዋና ስራ አስፈፃሚው ጋር “የመዋቅር አሰራሩ ግልፅነት የጎደለው፣ መስፈርት ያልወጣለት፣ በዘመድ አዝማድ የተሰራና የመስሪያ ቤቱን ሰራተኞች የረጅም ጊዜ ውለታ መና ያስቀረ ነው” በማለት ተቃውሞአቸውን ሲያሰሙ ነበር፡፡ በመስሪያ ቤቱ ውስጥ አዲስ የተመደቡ ሰራተኞች በትምህርት ዝግጅትም ሆነ በስራ ልምድ ለቦታው አይመጥኑም፣ አንዳንዶች ዘመዶቻቸውን ሰብስበው ስራ ላይ አስቀምጠዋል፣ መዋቅሩን ሰርተው ለእንግልት የዳረጉን ግለሰቦች ለህግ ይቅረቡልን” ያሉት “አሁንም መስሪያ ቤቱ ለተጠያቂነት በሩን ክፍት ያደርግ ሲሉ ጠይቀዋል። ኃላፊዎቹም፤ የተነሱ ጥያቄዎች አግባብ መሆናቸውን ገልፀው፤ “ሁሉንም ጉዳይ እናጣራለን፤ እስከሚቀጥለው ሳምንት መጨረሻ ድልድሉን ሰርተን ወደ ስራ እንመልሳችኋለን” ሲሉ ቃል መግባታቸው ታውቋል፡፡
በባለስልጣኑ ውሳኔ ምን እንደተሰማቸው የጠየቅናቸው ሰራተኞቹ፤ ‹‹ሀላፊዎቹ የፖለቲካ ብስለት የጎደላቸው ናቸው ይሄ ሁሉ ቀውስ እስኪፈጠር መጠበቅ አልነበረባቸውም›› ሲሉ ወቅሰዋቸዋል፡፡
አሁንም ቢሆን ኃላፊዎቹ ያሉትን ከመቀበልና ተስፋ ከማድረግ ውጭ ምንም አማራጭ እንደሌላቸው” ሲሉ ወቅሰዋቸዋል፡፡ ያነሳናቸው ጥያቄዎች በአግባቡ እንዲመለሱና መስሪያ ቤቱ ግልፅና ተጠያቂ አሰራር እንዲከተል እንፈልጋለን ያሉት ሰራተኞች፤ ይህ ካልሆነ አሁንም መብታችንን ለማስከበር እስከመጨረሻ እንታገላለን ብለዋል፡፡

Read 3277 times