Monday, 15 August 2016 08:50

ተቃዋሚ ፓርቲዎች የእርቀ ሰላም ጥሪ አቀረቡ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(16 votes)

መድረክ የሽግግር መንግስት እንዲቋቋም ጠይቋል
መንግስት በዜጎች ላይ የኃይል እርምጃ ከመውሰድ እንዲቆጠብ አሳሰቡ

ሰሞኑን በኦሮሚያና በአማራ ክልል የተደረጉ የህዝብ ተቃውሞዎችን ተከትሎ በተከሰተ ግጭት በርካቶች ህይወታቸውን እንዳጡ የገለፁት ዋና ዋና ተቃዋሚ ፓርቲዎች፤ ሁኔታው በዚህ ከቀጠለ ሀገሪቱ ልትበታተን ትችላለች የሚል ስጋት እንዳላቸው ጠቁመው፣ በአስቸኳይ ሁሉንም ወገን ያካተተ የእርቀ ሰላም ጉባኤ እንዲደረግ ጠይቀዋል፡፡
መኢአድ፤ ኢዴፓና መድረክ ሰሞኑን ባወጡት የአቋም መግለጫ፤ መንግስት ለህዝብ ተቃውሞ የኃይል አፀፋ በመውሰዱ፤ ሰዎች ለህልፈት መዳረጋቸው በእጅጉ እንዳሳዘናቸው የገለፁ ሲሆን መንግስት በዜጎች ላይ የኃይል እርምጃ ከመውሰድ እንዲቆጠብ አሳስበዋል፡፡
በአንዳንድ የሀገሪቱ ክፍሎች የሚካሄዱት የተቃውሞ እንቅስቃሴዎች አቅጣጫቸውን እየሳቱ፣ በህዝቡ አብሮ የመኖርና የመቻቻል እሴቶች ላይ እንቅፋት እየሆኑ ነው ያለው ኢዴፓ፤ ሁኔታው በሀገሪቱ ህልውና ላይ የተጋረጠ አደጋ በመሆኑ በእጅጉ ያሳስበኛል ብሏል፡፡
ፓርቲው አክሎም፤ ከነዚህ ተቃውሞዎችና ግጭቶች ጋር በተያያዘ ለእስር የተዳረጉ ዜጎች፤ ሰብአዊ መብታቸው እንዲጠበቅ፤ አላግባብ የታሰሩም በአስቸኳይ እንዲፈቱ ጠይቋል፡፡ መኢአድና መድረክም ተመሳሳይ አቋም ያንፀባረቁ ሲሆን መንግስት የሚወስዳቸውን የኃይል እርምጃዎች አቁሞ፣ ለተጎጂ ቤተሰቦች ካሳ እንዲከፍልና በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ፣ የሀገሪቱ ጉዳይ ያሳስበኛል ከሚሉ አካላት ጋር ለእርቀ ጉባኤ እንዲቀመጥ አሳስበዋል። ለእርቀሰላም ጉባኤው ገለልተኛ የሆነ አካል ሊቋቋም እንደሚገባ ያሳሰበው ኢዴፓ፤ መንግስት ግጭቱ ከተጀመረ ወዲህ በፓርቲው የሚወጡ መግለጫዎችንና ማሳሰቢያዎችን በቸልታ ሲመለከት መቆየቱን በመጥቀስ፤ ፓርቲው ከእንግዲህ ከመንግስት ምላሽ ሳይጠብቅ አቅሙ በሚፈቅደው ወደ እርቀ ሰላም ሂደቱ በመግባት፣ የሀገሪቱ ፖለቲካ ይመለከተኛል ከሚሉ አካላት ጋር መነጋገር እንደሚጀምር አስታውቋል፡፡ ለመንግስትም ብሄራዊ መግባባት ላይ ያተኮረ ሰነድ አቅርቦ፤ ምላሽ በመጠባበቅ ላይ መሆኑን ኢዴፓ አስታውቋል፡፡
መድረክ በበኩሉ፤ ትናንት ከሰአት በኋላ በፅ/ቤቱ በሰጠው መግለጫ፤ አሁን ባለው ህገ መንግስት ማዕቀፍ ውስጥ የሽግግር መንግስት እንዲቋቋም የጠየቀ ሲሆን ከሽግግር መንግስቱ ተግባራት አንዱ እርቀ ሰላም ማስፈን ይሆናል ብሏል፡፡

Read 5528 times