Monday, 15 August 2016 08:59

የተስፋ እና የውጥረት ዓመት

Written by  አበበ ተክለሃይማኖት (ሜጀር ጄኔራል)
Rate this item
(8 votes)

ገዢው ፓርቲ ርዕዮተ-ዓለማዊና ፖለቲካዊ ክስረት ገጥሞታል
ዴሞክራሲያዊ ስርዓታችንን የሚታደገው ወጣቱ ትውልድ ነው
ጭፍን ጥላቻና ጭፍን ፍቅር የጥፋት መንገዶች ናቸው

አበበ ተክለሃይማኖት (ሜጀር ጄኔራል)

 (ካለፈው የቀጠለ)
ቀልጣፋ ማህበራዊ ለውጥና አለመረጋጋት
 ሃንቲንግተን (1983:05) እንደሚለው፤ ፈጣን ማሕበራዊ ለውጥና የአዳዲስ ቡድኖች ፖለቲካዊ ንቅናቄ ከፖለቲካ ተቋማት እድገት ዘገምተኛ መሆን ጋር ሲዳበል ሁከትና አለመረጋጋት ለመከሰት ትልቁን ድርሻ ይወስዳል። “የፖለቲካ ተቋማት እድገት፣ ከማሕበራዊና ኢኮኖሚያዊ ለውጡ ጋር መሄድ አለመቻል  ትልቁ የፖለቲካ ችግር ነው” ይላል፡፡
 ሕገ-መንግስታችን በተወሰነ ደረጃ ተግባራዊ መሆን ሲጀምር፣ በአንድ በኩል በከፊልም ቢሆን የብሄር ብሄረሰቦች ጥያቄ በመመለስ በዋናነት ራስን በራስ ማስተዳደርና በሃገሪቱ አጠቃላይ እንቅስቃሴ ውስጥ መሳተፍ በመጀመሩና ለግለሰብ መብቶች ዕውቅና መሰጠቱ፣ በሌላ በኩል ደግሞ እየተመዘገበ ባለው ፈጣን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ዕድገቶች ተጠቃሚ የሆነ ሕብረተሰብ እያደገ መምጣቱ፣ አዳዲስ ቡድኖች እስካሁን ባልታየ መጠን ፖለቲካዊ ንቅናቄ እንዲያደርጉ በር ከፍቶላቸዋል። በግሎባላይዜሽንና ኢንፎርሜሽን፣ በቴክኖሎጂና ኮሙኒኬሽን መስፋፋት ምክንያት ሕብረተሰቡ ከፍተኛ የሆነ የአስተሳሰብ ዕድገት እያስመዘገበ መጥቷል፡፡
የተለያዩ ማህበራዊ ኃይሎች የራሳቸውን ተጨማሪና ቀጣይነት ያለው ፍላጎታቸውን ማደራጀት፣ መጠየቅና መታገልም ጀምረዋል፡፡ የተሻለ ዴሞክራሲያዊ መብቶች ማረጋገጥ፣ የበራስ ማስተዳደር (Self –rule)  እና በጋራ መስተዳደር (Shared rule) እንዲጠናከር መፈለግ ከሚገኘው ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ዕድገት ፍትሐዊ የሆነ ተቋዳሽነት ለማረጋገጥ ህብረተሰቡ በአጠቃላይ በተለይ ወጣቱ በስፋት እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡
በሌላ በኩል ፖለቲካዊ ተቋማት ማለት ፓርቲዎች (ገዥው ይሁን ተቃዋሚዎች) የሲቪል ማህበረሰብ፣ ሕገ-መንግስታዊ ተቋማት፡- እንደ ሕግ አውጭ፣ ሕግ አስፈጻሚና ሕግ ተርጓሚ ያሉ አካላት ከማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ለውጦች ቀድመው ወይም እኩል መራመድ ባለመቻላቸው፣ በህብረተሰቡ እድገትና ፍላጎት በፖለቲካዊ ማህበረሰብ ትልቅ ክፍተት እየፈጠረ ነው። በአጭሩ ፖለቲካዊ ማህበረሰብ የህብረተሰቡ ሁሉን ዓቀፍ ጥያቄ ለመመለስ ባለመቻሉ ምክንያት በ2008 ዓ.ም የታየው አለመረጋጋት ሊከሰት ችሏል፡፡
ፖለቲካዊ ማህበረሰቡ (Community) ወደ ኋላ ቀርቷል ሲባል፣ በዋናነት የአዲሱን ትውልድ ፍላጎቶች በሚገባ መረዳትንና ይህንን ለመመለስ ራስን አለማብቃትና አለመደራጀትን ያሳያል፡፡ በአንድ በኩል የሚታየው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ለውጦችና ግሎባላይዜሽን አዳዲስ ማህበራዊ ሃይሎች ከነአዲስ ፍላጎታቸው እየበቀሉ ባሉበት አገር፣ የፖለቲካዊ ስርዓቱን ብቃት በተለይ ተቋማዊ (institutionalization) ብቃቱን መፈተሽ አስፈላጊ ነው፡፡
ሃንቲንግተን (1983፡05) ተቋማትን እንደሚከተለው ይገልጸዋል:- ተቋማት ማለት የተረጋጋና የሚደጋገም የድርጅት ባህርያትና ስነ ስርዓቶች (አሰራሮች) ሲሆኑ በመጠነ ተቋምነታቸው አንዳቸው ካንዳቸው ሊለያዩ ይችላሉ። ተቋምነት ማለት ድርጅቶች ስነ ስርዓቶች (አሰራሮች) እርጋታና እሴት ሲላበሱ ማለት ነው።
የአንድ ፖለቲካዊ ስርዓት የተቋምነት ደረጃ የሚበየነው በአራት መለኪያዎች ሲሆን እነሱም፥ አንድ:- ከሁኔታዎች ጋር ራስን ማስማማት (Adaptability) ፣ ሁለት:- ውስብስብነት (Complexity)፣ ሶስት:- አንፃራዊ ነፃነት (Autonomy) አራት:- የድርጅቶችና የአሰራሮች ጥምረት (Coherence) ናቸው:: በእነዚህ መለኪያዎች ፖለቲካዊ ስርዓታችን እስከ ምን ድረስ ወደ ኋላ የቀረ መሆኑን መመዘን እንችላለን፡፡
ከሁኔታዎች ጋር ራስን ማስማማት (Adaptablity)
ገዥው ግንባር/ፓርቲ ይሁን አንዳንድ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በየጊዜው ከሚፈጠረው የማህበራዊ ኃይሎች ፍላጎቶች አንጻር ራሳቸውን adapt በማድረግ በኩል እጅግ ከፍተኛ ችግር አለባቸው፡፡ ሕገ-መንግስታችን ያረጋገጠውን ሰብዓዊ መብቶች ለመተግበር የሚያስችል ብቃት የላቸውም፡፡ አንዳንድ ተቃዋሚዎች አሁን ኢትዮጵያ ተያይዛው ያለው የፌዴራል ስርዓት የሚያንጸባርቀውን ሕገ-መንግስት ተቀብለው፣ የብሄር ብሄረሰብና ህዝቦች መብቶችና ፍላጎቶችን ለመመለስ ማዕከል ያደረገ ፕሮግራም የላቸውም፡፡ በተለያዩ ግንባር የተካተቱ ፀረ-ገዥው ፓርቲ ስብስቦች እንጂ ከሁኔታዎች ጋር ራሳቸውን እያስተካከሉ በመሄድ፣ ህብረተሰቡን የሚመሩ አይደሉም፡፡ በተለይም ወጣቱን ትውልድ ከጎናቸው ለማሳለፍ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ደካማ ነው፡፡ አብዛኞቹ አመራሮች የአመጸኛው ትውልድ አካል በመሆናቸው፣ ከሰጥቶ መቀበልና ማቻቻል (Compromise and accomdate) መርህ በእጅጉ የራቁ ናቸው፡፡ በ1997 ዓ.ም ምርጫ ወቅት የታየው ድርቅ (ከኢዴፓ በስተቀር) እንደ ማሳያ ሊቀርብ ይችላል፡፡
 ገዥው ግንባር/ፓርቲ ባስመዘገባቸው ድሎች ሰክሮ የነሱ እስረኛ ከመሆኑ የተነሳ ራሱን ከአዲስ ማህበራዊ ኃይሎች ፍላጎት አንጻር ማስተካከል አልቻለም፡፡ ደርግን በመደምሰስ በነበረው የመሪነት ሚና፣ ከዚያም ብቃት ያለው ዘመናዊ ሕገ-መንግስት አዘጋጅቶ በተወሰነ ደረጃ መተግበር በመጀመሩ በህዝቦች ዘንድ ድጋፍ አስገኝተውለታል፡፡ በተለይ በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፍ በኩል እምርታ ለማስመዝገብ መቻሉ ከድሎቹ ሁሉ ቀዳሚውን ድርሻ የሚይዙ ናቸው፡፡ ነገር ግን ኢህአዴግ እየመራ ያመጣቸውን ዕድገትና ሰላም ራሱ እየሸረሸረ ከዕድገቱ ጋር ማስተካከል ያልቻለበት ሁኔታ ተከስቷል። በአንድ በኩል ሕብረ-ፓርቲ ስርዓትንና  አንድነትን እንዲሁም ብዙኃንነትን ሲያቀነቅን ቢቆይም፣ከዚህ ጋር የሚጣረሱ አመለካከትና አደረጃጀቶችን ማስተካከል አልቻለም፡፡ “ከኢህአዴግ መስመር/አስተሳሰብ ውጭ ሌላው ሁሉ የጥፋት መንገድ ነው” የሚለው ዋነኛ መገለጫው ነው፡፡ ይህን መሰል ኢ-ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብ ተይዞ ዴሞክራሲያዊ ስርአት መምራት አይቻልም፡፡ ሆኖም ከማህበራዊ ኃይሎች ይሁን ከተቃዋሚ ፓርቲዎች የተለዩ ፍላጎቶችና አስተሳሰቦች ሲንጸባረቅ፣ እንደ ጥፋት መንገድ ቆጥሮ ማፈንን ስራዬ ብሎ ተያይዞታል፡፡
ህዝቦችን በማስፈራራት ዴሞክራሲያዊ መብቶችን የማፈኑ አካሄድ፣ በተለይ ከ1997 ወርቃማ የምርጫ ሂደት በኋላ በተደራጀ መንገድ እያስኬደው ይገኛል። ተቃዋሚዎችን እንደ ጸጋ ከማየት ይልቅ እንደ ጠላት በማየት፣ አጠቃላይ የማዳከም ዘመቻ ይዞ፣የተቃውሞ ማዕከሉ ወደ ዳያስፖራና ጽንፈኞች እንዲዛወር ከፍተኛ አስተዋፅኦ አድርጓል፡፡
ከኢህአዴግ አስተሳሰብ ውጭ ሁሉም የጥፋት መንገድ ነው የሚል አስተሳሰብ፣ በዳኞች እንዲሁም በኮሚሽኖች ምልመላና አሰራር ላይ ጎልቶ እየታየ ሲሆን፣ “መከላከያ የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ብሎም የኢህዴግ የመጨረሻው ምሽግ ነው” በሚል ሰራዊታችን የሚገነባበት ሁኔታም ተፈጥሯል፡፡
ሃንቲንግተን (1969:14) እንደሚለው፤“ሁለተኛው ከሁኔታዎች ጋር ራስን የማስማማት መለኪያ የትውልዶች ለውጥ (Generational Change) ነው። አንድ ድርጅት መስራች ጀማሪ አመራሮቹን ይዞ አሁንም አሰራሩ የሚከወነው በነዚህ ሰዎች ከሆነ፣ራሱን ከሁኔታዎች ጋር የማስማማት አቅሙን አጠራጣሪ ያደርገዋል” ይላል።
የትውልድ መተካካት ሲባል በግለሰቦች መተካካት ሳይሆን በዕድሜም ጭምር ነው፡፡ በሶቭየት ሕብረት ስታሊን፤ ሌኒንን መተካቱ በአንድ ትውልድ ውስጥ ያለ መተካካት ሲሆን የኩርስቼፍ ስልጣን ላይ መውጣት ግን የትውልዶች መተካካት ነው ይለዋል፤ ሃንቲንግተን፡፡ በተመሳሳይ መንገድ በህወሐት ውስጥ አቶ አባይ ወልዱ፣ አቶ መለስ ዜናዊን መተካታቸው በአንድ ትውልድ ውስጥ ያለ መተካካት ነው፡፡ ሕወሓትን ካነሳን፣ ከ40 ዓመት በፊት ወጣት ታጋዮች፣ ደርግን በመደምሰስና አሁን ለተገኙት ለውጦች ምክንያት በመሆን የሰሩ ቢሆንም በ Formative Age በነበሩበት ወቅት ወታደራዊ የትጥቅ ትግል በፈጠረው ችግሮችን በሃይል የመፍታት ባህሪ፣ አመለካከቱ በቀላሉ (እንደ ቡድን ሲታይ) ሊፋቅ የሚችል አይደለም፡፡ ይህ ሚሊታራይዝድ (Militarized) የሆነ አስተሳሰብ ከዴሞክራቲክ አስተሳሰብ ጋር እየተደባለቀ አስቸጋሪ ሁኔታ ይፈጥራል፡፡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዶክተር ቴዎድሮስ አድሃኖም በፌስቡክ ተሳትፎ በማድረጋቸው፤“ምን ሥራ እንዳጣ ሰው፣እዛ ውስጥ ይርመሰመሳል” የሚል አስተያየት ከኢህአዴግ አባላት መሰንዘሩን ሰምተናል፡፡ ይህ የadaptability ችግርን ወለል አድርጎ ያሳያል፡፡ በስብሰባ፣ በውጊያና በግምገማ ውስጥ ተፈጥሮ ያደገ ትውልድ፣መገናኛ ብዙኃንና ማህበራዊ ሚዲያን ተጠቅሞ ወጣቱን ማሳተፍ እንደ ጊዜ ማጥፋት ቢቆጥረው አይገርምም።
በአንድ ድርጅት ራስን ከሁኔታዎች ጋር የማስማማት ጉዳይ በሚደረገው እንቅስቃሴ ሊመዘን ይችላል፤ ይላል ሃንቲንግተን (1968: 15)። “እንደተለመደው አንድ ድርጅት የሚፈጠረው አንድ የተለየ ተግባር እንዲከውን ነው። ያ የተለየ ተግባር አስፈላጊ በማይሆንበት ሰዓት ድርጅቱ ከፍተኛ ቀውስ ውስጥ ይገባል። በዚህ ሁኔታ ያለው አማራጭ ድርጅቱ አዲስ ተግባር ይፈልጋል ወይም ከተራዘመ ግን ከማይቀረው ሞት ጋር ራሱን ያስታርቃል።”
በ1993 ዓ.ም ኢህአዴግ በእርግጥም ተሃድሶ ያስፈልገው ነበር፡፡ ሕገ-መንግስቱን ለማክበር የሚያስችል ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብ እንዲኖረው መታደስ ነበረበት። የተደረገው “ተሃድሶ” ግን እውነተኛውን ተሃድሶ ያጨናገፈ እንቅስቃሴ ነው። ሌላኛው ቡድን ቢያሸንፍ በትክክል ይታደስ ነበር ለማለት አይደለም፡፡
ዴሞክራሲያዊ ማእከላዊነት የላብአደር አምባገነንነት (Proletarian dictatorship) ለማረጋገጥ ሃሳብን የመግለፅ ነፃነት ከድርጊት አንድነት ጋር (freedom of expression unity of action) የሚለው ሌኒናዊ አስተሳሰብ፤ በትጥቅ ትግሉ ወቅት የጦርነት ግዜ በመሆኑ አይነተኛ መሳሪያ የነበረ መሆኑ ባይካድም፣ አሁንም በዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ በባሰና በተጨማለቀ መንገድ ተግባራዊ ለማድረግ  የሞት ሽረት ጥረት  ሲደረግ እያየን ነው፡፡ ዛሬ ሁኔታው ተቀያይሯል፡፡  በኢህአዴግ ውስጥ “freedom of expression” እየጠፋ፣ ጠቅላይነት (Centralism) እየከረረ፣ የጥቂት መሪዎች አምባገነንነት፣ አድርባይነትና ሙስና የነገሰበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ በፓርቲ ደረጃ ዴሞክራሲያዊ ህይወት የሌለው አገርን የሚመራ ፓርቲ፣ ዴሞክራቲክ አመራር ሊያሰፍን አይችልም። ኢህአዴግ  በአስተሳሰብ፣ በትውልድ መተካካትና በተጨባጭ ክንውን በአጠቃላይ ከሁኔታው ጋር ራሱን ማስተካከል ያልቻለ ድርጅት ነው የሆነው፡፡
ዉስብስብነት (Complexity)
ሃንቲንግተን (1968:19) እንደሚለው፤የአሜሪካን ስርዓት ከተመለከትን ፕሬዝዳንቱ፣ ሴኔቱ፣ ጠቅላይ ፍርድ ቤቱና የክልል መንግስታት በተለያዩ ጊዜያት የተለያየ ሚና ተጫውተዋል። አዳዲስ ችግሮች ሲከሰቱ ችግሮቹን ለመፍታት አንዱ ተቋም ተነሳሽነት ይወስድና ሌላው ደግሞ ይከተላል፡፡”
በግሎባይዜሽን ዘመን፣ እንደ ኢትዮጵያ በሽግግር ወቅት ላይ ባለ ትልቅ ሃገር አንድ ቀላል (Simple, not complex)  ከላይ ወደ ታች የሚፈስ የአመራር ዘይቤ ቀጣይነት ያለው ዕድገት፣ ሰላምና ዴሞክራቲክ ግንባታ ሊያረጋግጥ አይችልም፡፡ አገራችን የሚያጋጥሟት ዘርፈ ብዙ ተግዳሮቶች፣የሁሉም ህዝቦችዋን በተለይም ተቋማት ተሳትፎና አዲስ ፈጠራ (innovation and creativity) የግድ ይላል፡፡ ይህ እንዲሆን ደግሞ ዘርፈ ብዙ የተወሳሰቡ (Complex) አደረጃጀት ወደ ጎንም ወደ ላይም (Horizontally and Hierarchical) እና ብዙ ተነጻጻሪ ነጻነት ያላቸው አደረጃጀት በፓርቲዎችም ሆነ በመንግስት እንዲኖር ይጠይቃል፡፡ የሁሉም ተነሳሽነትና ዕውቀት እንዲሁም ልምድ ለአገሪቱ ግንባታ ለመጠቀም ያስችላል፡፡
 አሁን ባለው የጠቅላይነት (Centralization) አካሄድ አገሪቱ በተወሰኑ ሰዎች ፍላጎት፣ተሞክሮና ዕውቀት ብቻ እንድትሽከረከር ማድረግ ውጤቱ አደገኛ ነው፡፡ ፓርላማ/ፍርድ ቤት፣ ኮሚሽኖች ወ.ዘ.ተ በአስፈጻሚው አካል መመሪያ የሚንቀሳቀሱ ሲሆኑ ክልሎች ነጻነታቸውን ያጡበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ በየደረጃው ያለው የፓርቲ መዋቅር ደግሞ ከላይ የሚመጣለትን መመሪያ የሚጠባበቅ ሆኗል፡፡ ኢትዮጵያን የሚያክል ትልቅ ሃገርና ህዝብ በእንዲህ ዓይነት ቀላል አስተሳሰብና አወቃቀር ለመምራት መሞከር ውጤቱ አደገኛ ሊሆን ይችላል ብቻ ሳይሆን መፈጠር የሚገባው የተወሳሰበና የነጠረ ዝርዝር መዋቅራዊ እርከኖች እንዳይፈጠሩ ስለሚያደርግ መመለስ የሚገባቸው ጥያቄዎች ሳይመለሱ ይቀራሉ።
 አንፃራዊ ነፃነት (Authonomy)
በፖለቲካዊ ስርዓቱ ስር ያሉት ድርጅቶች የራሳቸውን ነጻነት ጠብቀው የማይሄዱበት ሁኔታ እናያለን፡፡ ነጻነት ሲባል ለቆሙለት ዓላማ እና ዓላማ ብቻ የሚንቀሳቀሱ በማናቸውም ስልጣን፣ ገንዘብ ተፅዕኖ ሥር የማይወድቅ ህልውና መኖር ማለት ነው፡፡
አንዳንድ ተቃዋሚዎች በአንድ በኩል ባለው ዴሞክራሲያዊ ምህዳር መጥበብና በመንግስት ጣልቃ ገብነት ነጻነታቸውን በሚፈታተን አደረጃጀት፣ የፋይናንስ አቅም፣ ወ.ዘ.ተ አጣብቂኝ ውስጥ የገቡበት ሁኔታ ይታያል። አንዳንዶቹ በመንግስት ጥገኝነት፣ በገዥው ፓርቲ የሚሽከረከሩ “ተቃዋሚዎች” ነን ባዮች ሆነዋል፡፡ ሌሎች ደግሞ በራሳቸው ድክመት ማለት ግልጽ የሆነ ዓላማ፣ ለነሱ የሚመጥን አደረጃጀትና ቁመና ስለሌላቸውና በአብዛኛው ለምርጫ ብቅ የሚሉ በመሆናቸው እንዲሁም ወጣቱን ትውልድ በስፋት ባለማሳተፍና ወደ አመራር ባለማምጣት በዲያስፖራው ገንዘብና ድምጽ ጥገኝነት ስር የሚኖሩ ናቸው፡፡ አብዛኛዎቹ ሲቪል ማህበራት በተለይ የወጣቶች፣ የሴቶች ወ.ዘ.ተ. የራሳቸው ነጻነት የሌላቸው የገዢው ፓርቲ ተቀጥያዎች ናቸው፡፡ ፕሮፌሽናል ማህበራት ገና በእንቅልፍ ላይ ነው ያሉት፡፡ አስቀድሞ እንደተገለጸው፤ ምክር ቤቶችና ኮሚሽኖች በገዥው ፓርቲ እስትንፋስ የሚንቀሳቀሱ፣ ሕገ-መንግስቱ ያጎናጸፋቸውን ነጻነት አሳልፈው የሰጡ ናቸው፡፡ መከላከያም የኢህአዴግ የመጨረሻ ምሽግ ተብሏል፡፡ የተገላቢጦሽ እንዳይሆን ግን ያሰጋል፡፡
ገዢው ፓርቲ አይዲዮሎጂካልና ፖለቲካዊ ክስረት (Bankruptcy) ገጥሞታል፡፡ በወረቀት ላይ የሰፈረው አይዲዮሎጂና በተግባር የሚውለው ለየቅል ነው፡፡ የሕገ-መንግስቱ አቀንቃኝ ነኝ ቢልም ሕገ-መንግስቱን የሚንድ ዋናው ሃይል ሆኗል፡፡ ይህ ክስረት ፓርቲው ከመንግስት ጋር የተጣበቀ መዥገር (parasitic) እንዲሆን አድርጎታል። ጥንካሬው በአይዲዮሎጂካል ጥራቱና የህዝቡን ፍላጎት በማሟላት የሚለካ አልሆነም። በመንግስት ስልጣን፣ ገንዘብ፣ ሚድያ፣ አለም አቀፍ ግንኙነት ረገድ በራሱ ህልውና የሌለው ገዢው ፓርቲ፣ በርዕዮተ-ዓለማዊ ውዥንብር የተዋጠ ስለሚሆን፣ዋና ስራው በመንግስት የዕለት ተዕለት ስራዎች ላይ የተጠመደ ይሆናል፡፡ ይሄ ደግሞ መንግስትን ማድከም ብቻ ሳይሆን እንደ ፓርቲ የራሱን ህልውና እያሽመደመደ የሚገኝ፣ ከመሞት ለመሰንበት በመጣጣር ላይ ያለ ያደርገዋል። ከስልጣን ውጭም ህልውናን ለመጠበቅ ይቸግረዋል፡፡
ገዢው ግንባር በትጥቅ ትግል ግዜ ጠንካራ የአንድነት መንፈስ፣ ጓዳዊነት ሞራልና ዲሲፕሊን የነበረው ድርጅት ቢሆንም በአሁኑ ግዜ በግንባሩ ጥምረት (Coalition) ይሁን በእያንዳንዱ የብሄር ድርጅት ከፍተኛ ችግሮች እየታዩ መሆኑን ማስተዋል ይቻላል፡፡
ድርጅቶች በትምክህት ጠባብነት የሚወነጃጀሉበት፣ የአንዱ ድክመት የራስ ድክመት፣የአንዱ ጥንካሬ የራስ ጥንካሬ እንደሆነ ያለመቀበል ችግር ጎልቶ ይታያል፡፡ የመፎካከር (በህወሓት 40ኛ ዓመትና በብአዴን 35ኛ ዓመት እንደታየው) ችግሮቻቸውን በጋራ የመፍታት አካሄድ እየቀነሰ የሄደበት ሁኔታ ይታያል፡፡ የወልቃይትን ጉዳይ እንደ ምሳሌ መውሰድ ይቻላል፡፡ ሁለቱን ክልሎች የሚመሩት ፓርቲዎች፣ ተስማምተው ጉዳዩን ሕገ-መንግስታዊ በሆነ መንገድ በሰላም ከመፍታት ይልቅ አንዱ በግልፅ ወይም በድብቅ ሌላኛውን በመወንጀል እርስ በእርስ ይካሰሳሉ፡፡ ጉዳዩ የወልቃይት ፀገዴ ህዝብ መብት መሆኑ ቀርቶ እነሱ ቁማር የሚጫወቱበት ሜዳ ሆኗል፡፡
በእያንዳንዱ ድርጅት አመራሩ በተለያየ ደረጃ የሚታይ ቢሆንም እርስ በእርሱ የሚጠራጠርበት፣ ሽኩቻ የሚታይበት፣ networking እና መጠላለፍ የበዛበት ሆኗል፡፡ የግንባሩ አባሎችም ለአንድ ዓላማ የተሰለፉ ሳይሆን ለግል ጥቅም ወይም ደግሞ ዓላማው በውል ሳይገባቸው የተቀላቀሉ በመሆናቸው (የማስፋት ስራውን ህዝብን ከመፍራትና ህዝብን ለመቆጣጠር መነሻ ስለነበረው) የኢህአዴግን ቆብ ከማጥለቅና ከመዘመር አልፈው አለ ለሚባለው ዓላማ የሚዋደቁለት አልሆኑም፡፡
ማጠቃለያ
አንድ ድርጅት ይወለዳል፣ ያድጋል፣ ይበስላል፣ ያረጃል፣ ይሞታል፡፡ በሌላ በኩል አንዱ ትውልድ እያረጀ ሲሄድ፣ በጊዜው አዲስ ትውልድ ድርጅቱን ከተቀባበለው፣ የድርጅቱ እድሜ ከመስራቾቹ ዕድሜ እጅግ የላቀና እየተሻሻለ የሚሄድበት ሁኔታ ይፈጠራል። በዚህ የትውልድ ቅብብሎሽ ድርጅቱ ቀጣይነት ያለው ይሆናል፡፡ ይሄ የፖለቲካ ሳይንቲስቶች የፈጠሩት ሳይሆን በሁሉም ሕብረተሰብ ያለ ክስተት ነው፡፡ ቅብብሎሽ ሲደክም የመውደቅ አዝማምያ ያሳያሉ፡፡ ቅብብሎሽ ሲቀጥል ጥንካሬን ይወልዳሉ፡፡
በአገራችን በሁሉም ብሄረ-ሰብ ያለ ቢሆንም በተለይ የኦሮሞ ገዳ ስርዓትና የኮንሶ መተካካት/ቅብብሎሽ በውል ቢጠና ለአገራችን ትልቅ ጠቀሜታ አለው፡፡ በኮንሶ አንድ ጓደኛዬ ያጠናውን ላካፍላችሁ፡- በኮንሶ ካራ የሚባል ስርዓት አለ፤ በዚህ ስርዓት ስልጣን ከአንድ ትውልድ ወደ ሌላ ትውልድ የሚሸጋገርበት ሂደትና ሰላማዊነቱ ብቻ አይደለም የሚገርመው፡፡ በአስራ አንድ ዓመቱ አንድ ትውልድ ተጠራርጎ፣ በሌላ የአመራር ትውልድ መተካቱ ነው። ስልጣን የሚያስረክበው ትውልድ የአማካሪነት ቦታ ይዞ ይቀጥላል። ሂደቱ እንዲህ እያለ እያንዳንዱ ትውልድ የዘመኑን ፍላጎት በሚረዱ መሪዎች እየተመራ፣ የትውልድ የአመራር ቅብብሎሽና የመማማር ሂደት ስርዓቱን ጠብቆ ይሄዳል። የገዳ ስርዓትንም በተመሳሳይ ማንሳት ይቻላል። ይህ ህዝብ የሚገርሙ እሴቶች ባለቤት ሆኖ ሳለ፣ ፖለቲካዊ ስርዓቱ ግን ከህዝቡ ለመማር ፍላጎት በሌላቸው ሰዎች ስለሚንቀሳቀስ፣ አገራዊ እሴቶቻችን ተገቢ ቦታቸውን ያገኙ አይመስለኝም።
የእኛ ባለስልጣናት በስልጣን ለመቆየት ሲሉ መተካካት በዕድሜ አይደለም ይሉናል፡፡ ኢህአዴግ ኢትዮጵያን እንደፈጠረ ወላጅ በሚመስል አኳሃን፤“አብዮታዊ ዴሞክራሲ ከሌለ ኢትዮጵያ የምትባል ሃገር የለችም” ይለናል፡፡ እየተከሰተ ያለው አለመረጋጋት ሕብረተሰባዊ ኃይሎች/ብሄር-ብሄረሰቦችና በተለይም ወጣት ማሕበራዊ ኃይሎችና ፖለቲካዊ ማህበሩ (community) ያለው የፍላጎት፣የብቃት፣ ልዩነት የፈጠሩት ነው፤ባጭሩ የመብታችን ይከበር እንቅስቃሴና የፖለቲካዊ ተቋማት አለማደግ ያስከተለው ችግር ነው፡፡
ሕዝቡ ተጨማሪና ቀጣይነት ያለው ሲቪል ፖለቲካዊ፣ማህበራዊ፣ኢኮኖሚያዊ፣ የጋራና የልማት መብቶቹ እንዲረጋገጥለት ይፈልጋል፡፡ ፖለቲካዊ ስርዓቱ ግን “ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጥያቄያችሁን እቀበላለሁ፤ ሌላውን በተመለከተ ግን ከ 25 ዓመት በፊት የሰጠናችሁ ይበቃል” ዓይነት መልስ እየሰጠ ነው ያለው፡፡ የሰው ልጅ ከእንስሳ የሚለየው ለሆዱ ብቻ የሚኖር አለመሆኑ ላይ ነው፡፡ ሌሎች እሴቶች የማንነቱ መገለጫዎች ናቸው፡፡ በቀጣይነት የሚጎለብትና እንዲኖርባቸው የሚፈልጋቸው እሴቶች አሉ፡፡ ለአለመረጋጋት ምክንያት የሆነውም እየሞተ ባለው ፖለቲካዊ ስርዓትና በእነዚህ የሕብረተሰብ ፍላጎቶች መካከል አለመጣጣም በመፈጠሩ  ነው፡፡
በፖለቲካዊ ስርዓቱ ያሉት አመራሮች በገዢውም ይሁን በተቃዋሚ (እንደ ኢዴፓ ከመሳሰሉት ውጭ) ድርቅና የሚያጠቃው፣መቻቻል ተሸናፊነት የሚመስለውና አጥፊ ተጋፋጭነት (destructive confrontation) ያለው የአመፀኛ ትውልድ አባሎች ወይም ቅሪቶች ናቸው፡፡ እኒህ የዴሞክራሲ ግንባታ ስርዓት አመራር ሊሆኑ አይችሉም፡፡ ምክንያቱም እላይ ለማሳየት እንደሞከርኩት፤በባህርያቸው ከጊዜ ጋር ሊራመዱ (adapt ሊያደርጉ) የሚችሉ አይደሉም፡፡ በዚህም የተነሳ ነፃነታቸውን አጥተዋል፡፡ አሁን ያለውን ውስብስብ ሁኔታ መምራት ያዳግታቸዋል። ግልፅ የሆነ የተቀደሰ ዓላማ ስለሌላቸው እርስ በርስ መወነጃጀል ያበዛሉ፡፡ የዓላማ አንድነትን የሚፈጥረው ስርዓትና ዲሲፕሊን የላቸውም፡፡
ዴሞክራሲያዊ ስርዓታችንን የሚታደገው ወጣቱ ነው፡፡ ገና በልጅነቱ በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ማጣጣም የጀመረ፣ በትምህርት ቤቶች ሕገ-መንግስት የሚማር፣ የተፈለገውን ያህል ባይሆንም በተለያዩ ፓርቲዎችና ሚድያ፣ ከተለያዩ አስተሳሰቦችና አደረጃጀት ጋር ፖለቲካዊ ልምምድ እያደረገ የመጣ፣ ግሎባላይዜሽንን በትምህርትም በተግባርም በሚድያም የሚገነዘብ፣ ዓለም አቀፍ ትስስር ያለው፣ በምርምር ዕውቀቱን ያዳበረ ወጣት ምሁር ያለበት ነው፡፡ ሕዝብን ማሳመን/መምራት ሲባል በዋናነት ከሃምሳ በመቶ በላይ የሆነውን ወጣት ማሳመን ማለት ነው፡፡ ወጣትን የሚረዳው ደግሞ ወጣት ነው፡፡ በባህሪው ወጣት ነገሮችን ቶሎ ይቀበላል - adapt ያደርጋል፡፡ ወጣት ምሁር ውስብስብ የሆኑ ሁኔታዎችን የመረዳት ዓቅም ስላለው ነፃነቱንም ሊጠበቅ ይችላል፡፡ አንድነቱም ከዚህ የሚመነጭ ነው፡፡ ለዚህ ነው ወጣቱ ምሁር አመራር ይረከብ የምለው፡፡
ኢትዮጵያችን ቀጣይነት ባለው ለውጥ (Change and Contuinity) ውስጥ ትገኛለች። የመጠፋፋት ባህል መቅረት አለበት እላለሁ። የአንድ ትውልድን ጥንካሬን አድንቀን፣ ድክመቶቹን መታገል አለብን፡፡ የአፄ ኃይለስላሴ ስርዓት እንደ ስርዓት የመሳፍንቶች ቢሆንም የሰራቸውን በጎ ስራዎች መቀበል አለብን። ደርግ አረመኔ መንግስት ቢሆንም የሰራቸውን በጎ ተግባራት ለይተን፣ ለምሳሌ እንደ መሬት ላራሹ ያለውን አዋጅ ወዘተ --- ማድነቅ ይገባናል።
ኢህአዴግ ባስመዘገባቸው ማሕበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዕድገቶች አመስግነን፤ሕገ መንግስቱን እየሸረሸረ ዴሞክራሲያዊ ምሕዳሩን ሲያጠብና አገሪቱን ለአደጋ ሲዳርግ ደግሞ መውቀስ ይኖርብናል፡፡ በሁሉም ስርዓቶች የተፈፀሙት ስህተቶች እንዳይደገሙ መትጋት ይጠበቅብናል። ጭፍን ጥላቻና ጭፍን ፍቅር የጥፋት መንገዶች ናቸው። ምክንያታዊነትና መረጃን ማእከል ባደረገ ስልጡን መንገድ የተለያዩ ሃሳቦችን ብናስተናግድ ሃገራችን ትጠቀማለች፤ አሉባልታና የሴራ ሃልዮት (Conspiracy Theory) እንዲሁም ዘረኛ ፍረጃ ግን ለማንም አይበጅም።         



Read 3918 times