Saturday, 10 September 2016 14:03

አመፀኛ ግጥሞች!

Written by 
Rate this item
(5 votes)

 የኛ ሀገር እረኞች
የኛ ሀገር እረኞች፣ ማማ የረገጡ.
ከወንጭፋቸው ጋር፣ ቆጥ ላይ እየወጡ፣
ከማሽላው መሃል፤
አሁንም አሁንም፤
ወፍ አረፈ ብለው፤ ወንጭፍ እያነሱ፤
የድንጋይ ውርጅብኝ፣ ከማሳው መሃከል እየነሰነሱ፤
በወፍ አመካኝተው፣
የስንቱን ማሽላ አንገት ቀነጠሱ፡፡
(በጃኖ መንግስቱ)
አትንኩታ
ድሃን አትንኩታ!
የምን ገፋ … የምንገፋ - ገፋ
ደሳሳ ጎጆውን … ያፈረሰ እንደሆን
የግራ በሬውን … የሸጠው እንደሆን
ዝናር ምንሽሩን … የታጠቀ እንደሆን
ኧረ ምድር ቀውጢ!
ምድር ቁና እንዳትሆን፡፡
አትንኩታ!
አታጨልሙታ!
የምን ገፋ ገፋ ገፋ …
ለምን ደፋ … ደፋ
እርፉን ከማረሻ … ሲወስደው ለያይቶ
አንካሴ ቀጥቅጦ … ሽመል አበጅቶ፣
አፈር እርም ብሎ …. ከወረደ ቆላ፤
ማጠፊያው እንዳያጥር … መመለሻው መላ፡፡
(ከወንድዬ አሊ)
የተጀመረ አንጀት
በደል ያሰለሰው
ጥቃት የበዛበት፣
የተገዘገዘ፤
የተጀመረ አንጀት፣ …
ባልጎደፈ ቃል፣
ባልገረጀፈ ጣት፣
በስሱ ካልነኩት፣
በፍቅር ካልዳሰሱት
በስስት ካልያዙት፣
በዕውቀት ካላከሙት …
በበደል፤ በጥቃት፣
ዳግም ከደፈቁት፣
ደፍቀው ከጎጡት፣
የተብሰከሰከ፤ የተጀመረ አንጀት፣
እንኳንስ ሊቀጥል፣
ጥቂት ይበቃዋል፤ ቆርጦ ለመለየት፡፡
(ከጌትነት እንየው “እውቀትን ፍለጋ”)
አዲስ ዓመት ብቻ!!
አበባየሁ ለምለም፣ አበባየሁ ለምለም
ኢትዮጵያዊ ከሆንክ …
አዲስ ዓመት እንጂ፣ አዲስ ነገር የለም!!
“አድገሃል” ይሉሃል፣ ታድጋለህ ባታድግም
ከዜና አበባ ላይ፣ ፍሬ አትፈልግም፡፡
(ከበላይ በቀለ ወያ)
ከንቱ ፍረጃ
“… አየሽ እዚህ ሀገር፣ ከንቱ ፍረጃ አለ፣
አማኝ ሁሉ አክራሪ፣
ሙስሊሙ አሸባሪ፣
ጉራጌ ቋጣሪ፣
ትግሬ ሁሉ ወያኔ፣
ወጣቱ ወመኔ፣
አማራው ነፍጠኛ፣
ደርግ ሁሉ ግፈኛ፣
ናቸው እያስባለ፣
ቁልቁል የሚነዳን፣ ጭፍን ጥላቻ አለ፡፡…”
(ከዮናስ አንገሶም ኪዳኔ)

Read 2061 times