Sunday, 16 October 2016 00:00

አሜሪካዊው አቀንቃኝ የሥነ ፅሁፍ የኖቤል ሽልማት አሸነፈ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ሽልማቱን ያሸነፈ የመጀመሪያው የዘፈን ግጥም ደራሲ ነው

የ75 ዓመቱ የሮክ ሙዚቃ አቀንቃኝ አሜሪካዊው ቦብ ዳይላን በዘፈን ግጥሞች ደራሲነቱ የ2016 የሥነ ፅሁፍ የኖቤል ሽልማት አሸናፊ ሆነ፡፡ “በታላቁ የአሜሪካውያን የዘፈን ባህል ውስጥ አዲስ ቅኔያዊ አገላለፅ በመፍጠሩ ነው” ለሽልማቱ የበቃው ተብሏል።
እ.ኤ.አ በ1993 ዓ.ም የረዥም ልብ ወለድ ደራሲው ቶኒ ሞሪሰን የሥነ ፅሁፍ የኖቤል ሽልማት ከወሰደ በኋላ ይሄን ሽልማት ያሸነፈ የመጀመሪያው አሜሪካዊ ሆኗል፤ ቦብ ዳይላን፡፡ ይሄን እጅግ የተከበረ ሽልማት ያሸነፈ የመጀመሪያው የዘፈን ግጥም ደራሲም ነው ተብሏል፡፡
ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ሽልማቱን በተመለከተ በሰጡት አስተያየት፤ “በጣም ይገባዋል›› ብለዋል። “ከምወዳቸው ገጣሚያን አንዱ የሆንከው ገጣሚ፣ እንኳን ደስ ያለህ” ሲሉ በትዊተራቸው ላይ አስፍረዋል - ኦባማ፡፡ የስዊዲሽ አካዳሚ ዋና ፀሐፊ ሳራ ዳኒዩስ፤ ቦብ ዳይላን ለሽልማቱ የተመረጠው “በእንግሊዝኛ ተናጋሪው ማህበረሰብ ዘንድ ታላቅ ገጣሚ ስለነበር ነው” ብለዋል፡፡
“ለ54 ዓመት ያህል በሙያው ውስጥ ራሱን ሲፈጥር ኖሯል፤ ያለማቋረጥ አዲስ ማንነት በመፍጠር” ሲሉ ሳራ ዳኒዩስ፤ ለሪፖርተሮች ተናግረዋል፡፡

Read 727 times