Sunday, 16 October 2016 00:00

7ኛው አዲስ ዓለም አቀፍ የኮንስትራክሽን ኤግዚቢሽን ይካሄዳል

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(1 Vote)

    በአገሪቷ በዘርፉ ትልቅ የሆነው 7ኛው አዲስ ዓለም አቀፍ የኮንስትራክሽን የግንባታ መሳሪያዎችና ቴክኖሎጂዎች ኤግዚቢሽን በሚሊንየም አዳራሽ ከጥቅምት 4-7፣2009 ዓ.ም በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ ኢቴል አድቨርታይዚንግ ኤንድ ኮሙኒኬሽን አስታወቀ፡፡
ኢቴል አድቨርታይዚንግና ኮሙኒኬሽን ባለፈው ማክሰኞ ለአገር ውስጥ ጋዜጠኞች በሰጠው መግለጫ፤ በኤግዚቢሽኑ ላይ ከቱርክ፣ ከጀርመን፣ ከቻይና፣ ከቡልጋሪያ፣ ከደቡብ ኮሪያ፣ ከሕንድ፣ ከሳዑዲ አረቢያ፣ ከተባበሩት አረብ ኢምሬት የተውጣጡ 120 ኩባንያዎች ይሳተፋሉ ብሏል፡፡
የኤግዚቢሽኑ ዓላማ በአገር ውስጥ ወደ ኮንስትራክሽን ዘርፍ መግባት የሚፈልጉ ድርጅቶች፣ የዓለም አቀፍ እውቅና ካላቸው የኮንስትራክሽን ኩባንያዎች ዕቃ እንዲገዙ ለማገናኘት ነው ያለችው የኢቴል አድቨርታይዚንግና ኮሙኒኬሽን ማኔጂንግ ዳይሬክተር ወ/ሪት ሃይማኖት ተስፋዬ፤ ከ120 አገሮች ሁለት ሰው እንኳ ቢመጣ፣ የአየር ቲኬት፣ የምግብ፣ የማረፊያቸው፣ …. ወጪ በውጭ ምንዛሬ ለአገር ውስጥ ሆቴሎች የሚያስገኘው ጥቅም ከፍተኛ እንደሆነ ገልጻለች፡፡
የቱርክ መንግስት የኮንስትራክሽን ኩባንያዎች አፍሪካ ላይ በተለይ በምስራቅ አፍሪካ ኢትዮጵያ ውስጥ አተኩረው እንዲሰሩ 70 በመቶ ውጪያቸውን ሸፍኖ በኤግዚቢሽኑ እንዲሳተፉ አድርጓል ያለችው ሃይማኖት፤ የውጭ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ኢንቨስት ለማድረግ ከፈለጉ ጥሩ አጋጣሚ ይሆንላቸዋል ብላለች፡፡ ስለዚህ በኮንስትራክሽን ዘርፍ የተሰማሩ ድርጅቶች ኤግዚቢሽኑን ቢጎበኙና አዳዲስ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ቢመለከቱ ጥሩ ጥቅም ያገኛሉ ስትል ጋብዛለች፡፡
በኤግዚቢሽኑ ላይ የአየር ማቀዝቀዣ፣ የመታጠቢያ ቤት ዕቃዎች፣ የግንባታ ዕቃዎችና ሲስተሞች፣ የኤሌክትሪክ ገመዶች፣ የኮንስትራክሽን ዕቃዎች፣ የኤሌክትሪክ ዕቃዎች፣ የወለል፣ የጋዝ ግጣሞች፣ ጀኔሬተሮች፣ ግራናይትና ሴራሚኮች፣ ከባድ የኮንስትራክሽን ዕቃዎች፣ የውስጥ ማስጌጫዎች፣ የኢንዱስትሪ ማሽነሪዎች፣ የጡብ መሳሪያዎች፣ የጂቪሲ መሳሪያዎች. የፀሐይ ኃይል ሲስተሞች፣ የመብራት ዕቃዎች፣ ዕብነበረድ፣ የፓኔል በሮችና ፕሮፋይሎች የደህንነትና የሴኩሪቲ መሳሪያዎች፣ … እንደሚቀርቡ ታውቋል፡፡

Read 1052 times