Sunday, 30 October 2016 00:00

6ኛው ዙር የንግድ ባንክ የውጭ ምንዛሬ ማበረታቻ ሽልማት ይፋ ተደረገ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(2 votes)

  የ1ኛ ዕጣ ባለዕድል የ1ሚ. ብር አውቶሞቢል አሸናፊ ሆኗል
                               

      የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ 6ኛው ዙር የውጭ ምንዛሬ ማበረታቻ ሽልማት እጣዎችን ባለፈው ማክሰኞ በብሄራዊ ሎተሪ አስተዳደር አዳራሽ ይፋ ያደረገ ሲሆን የአንደኛ እጣ ባለዕድል የ1 ሚ. ብር ኒሳን አልሚራ አውቶሞቢል አሸናፊ ሆኗል፡፡ ባለ ዕድሉ በድሬደዋ ዲስትሪክት ጅጅጋ ቅርንጫፍ ገንዘብ መንዝረው በተሰጣቸው ኩፖን፣ አሸናፊ ለመሆን እንደቻሉ በዕጣ አወጣጡ ላይ የተገኙት የባንኩ የኮሚዩኒኬሽን ስራ አስኪያጅ አቶ ኤፍሬም መኩሪያ ገልፀዋል፡፡
ሁለተኛው እጣ አምስት እጣዎች ያሏቸው ሲሆን እያንዳንዱ ባለ ዕድል 65 ሺህ ብር የሚያወጡና ደረጃቸውን የጠበቁ ሙሉ የቤት ሶፋዎች አሸናፊ ሲሆኑ አምስቱ ሶፋዎች ከ300 ሺህ ብር በላይ ዋጋ እንዳላቸው ተገልጿል፡፡ በ3ኛ ዕጣ 50 ባለ እድሎች እያንዳንዳቸው 320 ሊትር የመያዝ አቅም ያላቸው ዘመናዊ ፍሪጆች አሸናፊ ሆነዋል፡፡
ንግድ ባንክ የውጭ ገንዘብ ማግኛ ዘዴን ለማበረታታት ከአንድ ዓመት በፊት በጀመረው የሽልማት ፕሮግራም ከዚህ ቀደም በአምስቱ ዕድለኞች ላፕቶፕ፣ ስቶቭ፣ ፍሪጅና መሰል እቃዎችን ሲሸልም እንደነበር የገለፁት አቶ ኤፍሬም፤ሽልማቱ ከተጀመረ በኋላ በባንኩ የሚመጣው የውጭ ገንዘብ እየጨመረ መምጣቱን አስታውሰው የውጭ ገንዘብ ግኝት ፍሰቱ እንዲጨምር ሽልማቱን የበለጠ አጓጊ ለማድረግ መታሰቡን ገልፀዋል፡፡
ከነሐሴ 15 እስከ መስከረም 30 ቀን 2009 ዓ.ም በባንኩ የውጭ ገንዘብ የመነዘሩ፣ በውጭ ገንዘብ አስተላላፊዎች የተላከላቸውን ገንዘብ ከባንኩ የወሰዱና “ስዊፍት” በሚባለው የገንዘብ ማስተላለፊያ ዘዴ የተጠቀሙ ዕድለኞች በተሰጣቸው ኩፖን ማሸነፋቸውን የገለፁት የኮሙኒኬሽን ስራ አስኪያጁ፤ ኩፖኑ ኮምፒዩተር ሲስተም ውስጥ ገብቶ ከ1ኛ-3ኛ ዕጣ የወጣላቸው ዕድለኞች ማሸነፋቸውን ተናግረዋል፡፡ ለ6ኛው ዙር የውጭ ምንዛሬ ማበረታቻ ሽልማት ባንኩ ከ2 ሚ. ብር በላይ ማውጣቱንም ገልፀዋል፡፡
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሚታወቅበት የ “ይቆጥቡ ይሸለሙ” የሽልማት ፕሮራም በዓመት አንድ ጊዜ የሚካሄድ ሲሆን የውጭ ምንዛሬ ማበረታቻ ሽልማት የአገራችንን ትልልቅ በዓላት ተከትሎ የሚካሄድ ሲሆን ስድስተኛው ዙር የአዲስ ዓመት በዓልን ተከትሎ በባንኩ የተገለገሉ እድለኞች የተሸለሙበት ነው ብለዋል፡፡ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቀዳሚ እንደመሆኑ ለሌሎች የግል ባንኮች መነቃቃትን ይፈጥራል ያሉት አቶ ኤፍሬም፤ ሌሎች ባንኮችም በራሳቸው መንገድ ሽልማቶችን እያካሄዱ እንደሚገኙ ጠቅሰው፣ለገና በዓል በሚዘጋጀው ሽልማት ደንበኞች በባንኩ በመገልገል ተሸላሚ እንዲሆኑ ጋብዘዋል፡፡  
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በመላ አገሪቱ ከ1151 በላይ ቅርንጫቾች ያሉት ሲሆን ዘንድሮ 70 ተጨማሪ ቅርንጫፎችን ለመክፈት መታቀዱ ተነግሯል፡፡ ባንኩ በአሁኑ ወቅት 13 ሚሊዮን አዳዲስ አካውንት የከፈቱና በኤቲኤምና በፖስ ካር የሚጠቀሙ 3 ሚ. ደንበኞች ያሉት ሲሆን ተቀማጭ ካፒታሉም 280 ቢሊዮን ብር እንደደረሰ አቶ ኤፍሬም መኩሪያ ገልፀዋል፡፡   

Read 2394 times