Sunday, 30 October 2016 00:00

የኢትዮጵያ የኮንስትራክሽን ስራ ተቋራጮች ማህበር 25ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን ያከብራል

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(0 votes)

 የኢትዮጵያ የኮንስትራክሽን ስራ ተቋራጮች ማህበር፣ ጥቅምት 20 የተመሰረተበትን 25ኛ ዓመት በተለያዩ ዝግጅቶች እንደሚያከብር አስታወቀ፡፡ ማህበሩ በ25 ዓመት ጉዞው ኢንዱስትሪው፣ በዘርፉ የተሰማሩ ተቋራጮችና መንግስት ከዘርፉ ተጠቃሚ እንዲሆኑ በርካታ ጥረት ሲያደርግ መቆየቱን ለአዲስ አድማስ በላከው መግለጫ አስታውቋል፡፡
ማህበሩ ሀገር በቀል ተቋራጮችን በማህበር በማደራጀትና መብትና ግዴታቸውን እንዲያውቁ በማድረግ፣ የማህበሩን አባላትና መንግስትን በማቀራረብ፣ መንግስት በሚያወጣቸው ግንባታ ነክ አዋጆች፣ ደንቦችና መመሪያዎች በመሳተፍና ሀሳብ በማዋጣት፣ ግንባታ ነክ ጥናትና ምርምሮችን በማሰራት እንዲሁም የተለያዩ አውደ ጥናቶችን፣ የውይይትና እውቀት ማጎልበቻ መድረኮችን ሲያመቻች የቆየ ሲሆን በዚህም ብዙዎቹ የማህበሩ አባላት እውቀትና ልምዳቸውን በማዳበር ተጠቃሚ መሆናቸውን የማህበሩ የቦርድ ሃላፊዎች ተናግረዋል።
ማህበሩ የተመሰረተው ጥቅምት 20 ቀን በመሆኑ ቀኑ ታስቦ ይውላል ያሉት ኃላፊዎቹ፤ 25ኛ ዓመቱ በስፋት የሚከበረው ግን ከሁለት ወር በኋላ ከሚካሄደው የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጎን ለጎን እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡
ከጠቅላላ ጉባኤው ጎን ለጎንም ሲምፖዚየም፣ አውደ ጥናቶችና የተለያዩ ወርክሾፖች በማዘጋጀትና የማህበሩን የ25 ዓመት ጉዞ በመገመገም በስፋት እንደሚከበር ተገልጿል።
የኢትዮጵያ የኮንስትራክሽን ስራ ተቋራጮች ማህበር፤ ከ1 ሺህ በላይ አባል ማህበራትን አቅፎ የያዘ ማህበር መሆኑም ታውቋል።  

Read 1109 times