Saturday, 29 October 2016 12:32

እጹብ ድንቅ ጥበብ! - ብርቱ ጠኔ!

Written by  (የተአምረኛው የሙዚቃ ጠ ቢብ ገድል) ፈለቀ አበበ arthabesha@gmail.com
Rate this item
(0 votes)

  ያገራችን ባለቅኔ ለውዳሴዋ ስንኝ ሲሰድሩ ...
 ‹‹ፈልቀሽ የተገኘሽ ከሹበርት ራስ፤
ከቤቶቨን ናላ፡ ከሞዛርት መንፈስ...››
ብለው ይጀምራሉ፡፡ በመድፊያቸው ላይ ደግሞ ‹‹ደማቅ እንደ ጸሐይ፤ ውብ እንደ ጨረቃ›› ብለው የሚያንቆለባብሷትን ይህችን የሙዚቃ ጥበብ፣ በመንፈሱ የተሸከማት ስመ ህያው የዜማ ጠቢብ ግን፤ ቀብሩ ወጪ ያልጠየቀና ቀባሪ አልባም እንደነበረ ገድሉ ይተርካል፡፡ የህይወት ዘመኑ ታሪክም እጅግ መራራ፡፡
እውነታው ባመዛኙ መመሳሰሉ ግርምት ያጭራል፤ ምንም እንኳ የስፍራና ክፍለ ዘመናት እርቀት በመካከሉ ቢኖርም፡፡ ወይም ደግሞ የታሪኩ ባለቤቶች፡ ምዕራባዊያኑ የማህበራዊ መስተጋብራቸው ኡደት ከሞላ ጎደል ከጠኔ ቁስሉ መገረን አሽሯቸው ቢሆን እንኳ፤ በእኛ ምድር ጠቢባን ዘንድ ክፍተቱ ዛሬም ድረስ፤ በ21ኛው ክፍለ ዘመን፤ በዚያው መሰል አስከፊ የኑሮ አዘቅት ውስጥ መመላለስ የመቀጠሉ ነገር ይበልጥ ያስደምማል፡፡ በየመሀሉ በቅንፎች ውስጥ ለጥቂቶቹ ብቻ በስፋት የሚታወቁ ጥቂት ማስረጃዎች ለመጠቆም ከመሞክር በቀር፤ ብዙ ተጨማሪውን ንፅፅር ለትጉኃን አንባቢያን ያልተገደበ የትዝብት አስተውሎት ትቼ፤ የዋና ባለታሪኩን ገድል፤ የህይወት ታሪኩን በሸከፉት ጉምቱ ብእረኛ አንደበት፤ተራኪ ቱርጁማንነቴን እቀጥላለሁ፡፡ እነሆ...
በርካታ የሙዚቃ ልሂቃንን በመፍጠር ረገድ በዘመናት መካከል ከኖሩት መምህራን ሁሉ ተወዳዳሪ ያልነበረው ሩሲያዊው እውቁ የቫዮሊን መምህር ሊኦፖልድ ኦዩር ባንድ ወቅት ሲያወጋኝ፤ ‹‹ታላቅ ሙዚቀኛ መሆን ካሻህ፡ መናጢ ድሀ ሆነህ መፈጠር አለብህ›› አለኝ፡፡ አነጋገሩ፤ ስለሚናገረው ጉዳይ በቅጡ ያልተረዳው ሆኖም ግን ያለማወላወል የሚስማማበት አንድ እውነታ መኖሩን የሚጠቁም ነገር ነው፡፡ ይህ በእርግጠኝነት ለማስቀመጥ የቸገረው ሀሳብ፤ በአንድ በጠኔ በተደቆሰ ሰው መንፈስ ውስጥ የተቀበረ ልዩ መግነጢሳዊ ኃይል መኖሩን የሚዋጅ ነው፡፡ የሆነ ህቡእ የፈጠራ ስነ ህላዌ፤ አንድ የሆነ የጥበብ ውበት፤አንዳች እዝነ ልቦናን ቦርቡሮ የሚያባባ፡ ርብሽብሽ አድርጎ ሲያበቃ ወዲያውም ስሜትን ሰቅዞ የሚይዝ ግፊት፤ እንደ ነጎድጓድ እያስገመገመ፣ እያደገ እየጎመራ፡እየተብላላ፡ እየተቀጣጠለ ሄዶ ሄዶ፣ እንደ ኃይለኛ መብረቅ የሚፈነዳ!!!
(የመግቢያ ስንኙን የቋጠሩትን ኢትዮጵያዊ ባለቅኔ ያመሻሽ እድሜ ዘመን ልብ ይሏል፡፡)
ሞዛርት ያጣ የነጣ፡ መናጢ ድሀ  ነበር፡፡ ይውል ያድርበት የነበረውን ቁር ያዘለ ቤቱን እሳት አንድዶ ለማሞቅ ማገዶ መግዣ እንኳ ቤሳ ቤስቲን የጠረረበት፡፡ ስለዚህም ሙቀት ለማግኘት እጆቹን በካልሲዎቹ ውስጥ ሸጉጦ፣ጭብጥ ኩርምት ብሎ ይቀመጥ ነበር፡፡ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሆኖም ነው፤ ዛሬ፡ ‹መለኮታዊ እርካብ የረገጡ!› የተሰኙትንና እጅግ ላቅ ያለ አለማቀፋዊ ዝና የተቀዳጀባቸውን ዘመን ተሻጋሪ የረቂቅ ሙዚቃ ፈጠራ ስራዎቹን ያቀናበራቸው፡፡
የእለት ተእለት ኑሮውን በወጉ መግፋት ተስኖት፣ ገና በ35 አመት እድሜው የተቀጠፈበት ምክንያትም፤  ሊቋቋመው በማይችለው ከፍተኛ ቅዝቃዜ ውስጥ በመኖሩና ተመጣጣኝ ምግብ ለማግኘት ባለመቻሉ በክፉ ጠኔ ተደቁሶ ነው፡፡
(ከአመታት በፊት ከአዲስ አበባ ከተማ ቤተ ተውኔቶች በአንዱ አዳራሽ ውስጥ፤ ለአንዲት አንጋፋ ኢትዮጵያዊት ከያኒ የገቢ ማሰባሰቢያ ዝግጅት ላይ፤ ‹‹ተወዳጇ ባለሙያ የምትገፋውን መሪር ህይወት ለማሳየት የቀረበ ዘጋቢ ፊልም›› ተብሎ የታየው ምስል እጅግ ዘግናኝ ከመሆኑ የተነሳ እንባና ሳግ አየሩን ሞላው፡፡ ከታዳሚዎች መሀል በርካታ የሰቆቃ አስተያየቶች ተሰነዘሩ፡፡ አንዲት ተዋናዪት፤ ‹‹እከሌም አሁን ሊሞት እያጣጣረ ነው፡፡ ትናንት ልጠይቀው ስሄድ ‹ከበሽታዬ ይልቅ የጎዳኝ የምበላው ማጣቴ ነው›› ብሎኛል፡፡ እባካችሁ ለእሱም እንድረስለት!›› አለች እያነባች፡፡ ሌላ አንጀት የሚያንሰፈስፍ ለቅሶና ያላቋረጡ መነፋረቆች! ዘጋቢ ፊልሙን ቀድሞ የማያውቀው መድረክ መሪ ደንግጦና ተሳቅቆ፤  ‹እነዚህ ችግሮቻችን የሚፈቱት በነጠላ በሚሰጡ እርዳታዎች አይደለም፡፡ የተለያዩ ተቋማት፡ብዙ ፋውንዴሽኖች ያስፈልጉናል! ጠንካራ ኢንስቲትዩሽኖች! ‹የእኛ ለእኛ› መረዳጃ ማህበር ያስፈልገናል›› እያለ ይጮህ ነበር፡፡)
የሞዛርት ቀብር ወጪ አንድ ፓውንድ ብቻ ሲሆን ቀባሪዎችም አልነበሩትም፡፡ አስከሬኑን አጅበው የተከተሉት ስድስት ሰዎች ብቻ ነበሩ፤ እነርሱም ዝናብ ማካፋት ሲጀምር ትተውት ወደ ቤታቸው ተመልሰዋል፡፡
(ፀሐይ የሞቀውን እናም እያደር ባህልም ያደረግነውን የኪነ ጥበብ ባለሞያዎችን በእርዳታ ህክምና እና በመዋጮ ቀብር፤ በተለይ ደግሞ በቅርቡ በቀብሩ ላይ የተገኘው ሰው ብዛት የኤሌክትሮኒክስ መገናኛ ብዙኃንን አየር ሰአትና የህትመት ውጤቶችን ገጾች አጣብቦ መነጋገሪያ ሆኖ የሰነበተውን ከያኒ ጉዳይ ሳያስታውሰን አይቀርም ይኼ፡፡ እረ  ይበቃናል! ‹‹የኪነ ጥበብ ሞያ የግድ ከችግር ጋ የተሰፋች ይመስል!›› ይላል፤ ወዳጄ አማኑኤል በስጨት ሲል፡፡)
ሞዛርት የስጋ ነጋዴ ልጅ ስለነበር፤ አዋዜ ሲበጠብጥም ሆነ ስጋ ሲከትፍና አጥንት ሲተፈትፍ የሚሰማቸውን ድምጾች ወደ ሙዚቃ ምት ለውጦ እያሰላሰለ ያደምጣቸው፡ በልቡም ያዜማቸው ነበር። ከቤተሰቡ ርቆ መኖር ሲጀምር ግን ኑሮ ከበደበት፡፡ መንገድ ላይ ቫዮሊን ተጫወቶ በሚያገኛት ገንዘብ ቤት ኪራዩን መክፈል ስላቃተውም፤ ሌሎች አምስት ተማሪዎችን በደባልነት አስጠጋ፡፡ ለእርሱ በህይወቱ ትልቁ ዋጋ ያለውና በጽኑ የሚያሳስበው፤ቁልፎቹ የወላለቁትን የአሮጌ ፒያኖ ኪራይ መክፈል የመቻሉ ጉዳይ ነበር፡፡ በዚያ ቁር ባዘለ መቃብር መኖሪያ ቤቱ ውስጥ ሆኖም፤ በሙዚቃ ላይ ተራቀቀባት፡፡ ምን ዋጋ አለው፤ ያቀናበራቸውን ሙዚቃዎች ሁሉ በጽሑፍ ለማስፈር ሳይቻለው ቀረ፡፡ ለምን? የወረቀት መግዣ ገንዘብ ስላልነበረው፡፡ እንዲህ ገንነው በአለሙ ዙሪያ የናኙት ሙዚቃዎቹ በወዳደቁ ወረቀቶች ጀርባ ከጻፋቸው መሀል በየስርቻው የተገኙት ጥቂቶቹ ብቻ ናቸው፡፡
ያም ሆኖ ታዲያ፤ሞዛርት ባሳለፈው የመከራ ዘመን በማዘን በእጅጉ መብሰልሰል አይገባንም። ሁለት ክፍለ ዘመናትን ተሻግረው፣ ዛሬም ድረስ ስሙን በህያውነት የሚያስጠሩለት እጹብ ድንቅ የሙዚቃ ስራዎቹ የተወለዱት ከብርቱ ጠኔው አብራክ ነበረና፡፡
እናም ከዚህ በኋላም፤ የቅኝታቸው ንዝረት አቅልን በሚነሱ ምትሀታዊ የዜማ ሞገዶች፡ ሀዘን፤ ጦርነት፤ ፍዳ፤ ሽብር፤ ፍርሀትን፤ ሰላም፡ ደስታ፡ተስፋ፡ ፍቅርንና ረቂቅ ውበትን ...ወዘተ ምኑ ቅጡ፡ የሚያስተጋቡ ተአምረኛ የረቂቅ ሙዚቃ የፈጠራ ስራዎቹን ባደመጥን ጊዜ ሁሉ፤ ከአንድ በሰቆቃ ህይወቱ የመጨረሻውን የመከራ አዘቅት ጥግ ከነካና በቆፈን ብርድ ተኮራምቶ፡ እሚልስ እሚቀምሰው ምናምኒት አጥቶ በችጋር ተቆራምዶ ካለፈ ምስኪን ሰው ህያው መንፈስ የፈለቁ የጥበብ ውጤቶች መሆናቸውን በማስታወስ ልንጽናና ይቻለናልና፡፡
ምንጭ - (LITTLE-KNOWN FACTS ABOUT WELL-KNOWN PEOPLE..
by - Del Carnegie)

Read 1506 times